(ዘ-ሐበሻ) የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና በአሁኑ ወቅት ለግብጽ አህሊ ቡድን የሚጫወተው የብሔራዊ ቡድናችን የፊት መስመር ተጫዋች ሳላዲን ሰዒድ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ኢትዮጵያ ከማሊ ጋር ላላት ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ እንደማይሳተፍ የስፖርት ምንጮች ለዘ-ሐበሻ ገለጹ።
አህራም የተባለው የግብጽ ጋዜጣ እንደዘገበው ኢትዮጵያዊው አጥቂ እሁድ ሴፕቴምበር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ለክለቡ በሚጫወትበት ወቅት በደረሰበት ከባድ ጉዳት ለስድስት ሳምንታት ያህል ከሜዳ ይርቃል።
የ25 ዓመቱ ሳልሃዲን በግብጽ ስፖርት ውስጥ “የግብጽን የክለቦች ዋንጫ በማንሳት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ” ተብሎ በታሪክ ተጽፏል።
ዋሊያዎቹ በ2015ቱ የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማሊ ጋር ለሚያደረጉት ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድኑ የተመረጡ ተጫዋቾችች ይፋ ሲሆን የሳላዲን ተመርጦ ነበር። ምንም እንኳ በፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሪቶ የሚመሩት ዋልያዎቹ ከአልጀሪያና ከማላዊ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ተጫውተው ድል ባይቀናቸውም በቀጣይ ከማሊ አቻቸው ለሚኖራቸው ግጥሚያም የተመረጡ ተጫዋቾች አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት ሲሳይ ባንጫና ታሪኩ ጌትነት ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ እንዲሁም ጀማል ጣሰው ከኢትዮጵያ ቡና ክለብ በግብ ጠባቂነት ተመርጠዋል፡፡
አሉላ ግርማ፣ አበባው ቡጣቆ፣ አንዳርጋቸው ይላቅና ሳላዲን በርጌቾ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ፣ ብርሃኑ ቦጋለና አክሊሉ አየነው ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ ፣ ቶክ ጃምስ ከኢትዮጵያ ቡና ክለብ፣ዋሊዳ አታ ከሲውድንና አንተነህ ተስፋዬ ከአርባ ምንጭ ከነማ ተከላካዮች ናቸው፡፡
የአማካይ ስፍራ ላይ ወጣቱ ተጫዋች ናትናኤል ዘለቀ፣ አዳነ ግርማ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ምንያህል ተሾመ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ተመርጠዋል፡፡
አስራት መገርሳ ከዳሽን፣ታደለ መንገሻ ከደደቢት፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ፍሬው ሰለሞን ከመከላከያ ክለብ እንዲሁም ሽመልስ በቀለ ከግብጽ ፔትሮ ጀት ክለብ የመሃል ተጫዋች ናቸው፡፡ ሳላህዲን ሰይድና ኡመድ እኩሪ ከግብጽ፣ ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካ፣ አፍሬም አሻሞ ከኢትዮጵያ ቡና፣ አሚን አስካር ከኖርዌይ ዳዋ ሆትሴ ክለብ የብሔራዊ ቡድኑ የአጥቂ ክፍል ተጫዋቾች ሆነው መመረጣቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።