Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ‹‹አርትራይተስ››:- ዛሬም ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚሁ በሽታ ይሰቃያሉ

$
0
0


የአርትራይተስ በሽታ የሰው ልጆችን ማሰቃየት ከጀመረ ብዙ መቶ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በሽታው ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደነበረ በግብፅ እንዳይፈርሱ ተደርገው ከቆዩ አስከሬኖች ማስረጃ ተገኝቷል፡፡ አገር አሳሹ ክርስቶፈር ኮሎምበስ በዚህ በሽታ ይሰቃይ እንደነበር ሊታወቅ ችሏል፡፡ ዛሬም ቢሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚሁ በሽታ ይሰቃያሉ፡፡ በሀገራችንም እንዲሁ የዚህ በሽታ ሰለባ የሆኑ ግን ምንነቱን የማያውቁ ሰዎች ስቃዩን ተሸክመው ለመኖር ተገደዋል፡፡ ለመሆኑ ይህ ሰውነት የማያሽመደምድ በሽታ ምንድን ነው? ከዚህ በመቀጠል ስለዚህ በሽታ ምንነት፣ መንስኤና መፍትሄ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
‹‹አርትራይተስ››
አርትራይተስ ከ100 ከሚበልጡ የተለያዩ የቁርጥማት በሽታ አይነቶች ጋር ተዛማጅነት ያለው ነው ሲል ዌስተርን ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን ይገልፃል፡፡ ከእነዚህ መካከል ኦስትዮአርትራይተስ፣ ሩማቶይድ አርትራይተስ፣ ሲስተሚክ ሉፐስ ኤራይቲማቶሰስ፣ ጁሽ ናይል ሩማቶይድ አርትራይተስ፣ ጋውት፣ በርሳይተስ፣ ሩማቲክ ፊቨር፣ ላይም በሽታ፣ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
እነዚህ በሽታዎች አንጓዎችን ብቻ ሳይሆን አንጓዎቹ ደግፈው የሚይዙትን ጡንቻዎች፣ አጥንቶች እንዲሁም አጥንትን ከጡንቻና አጥንትን ከአጥንት የሚያገናኙ ጅማቶችን ጭምር ያጠቃሉ፡፡ አንዳንድ የአርትራይተስ አይነቶች ቆዳን፣ የውስጥ አካል ክፍሎችንና፣ አይንን ሳይቀር ሊያጠቁ ይችላሉ፡፡
መንስኤና ምልክት
አብዛኛውን ጊዜ ሩማቶይድ አርትራይተስ የሚያጠቃው የግራውንና የቀኙን የሰውነት ክፍል በአንድ ላይ ሲሆን፣ ቁርጭምጭሚቶችን፣ ጉልበቶችንና እግሮችን ይጎዳል፡፡ ሩማቶድ አርትራይተስ እንደያዛቸው በምርመራ ከታወቀላችው ሰዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከቆዳቸው ስር ትናንሽ እባጭ ወይም ዕጢ መሳይ ነገር ይፈጠርባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ የደም ማነስ፣ የዓይን መድረቅና መቆጥቆጥ እንዲሁም የጉሮሮ ህመም ይኖራቸዋል፡፡ ድካም እንዲሁም እንደ ትኩሳትና የጡንቻዎች ህመም የመሳሰሉ የኢንፍሉዌንዛ አይነት የህመም ስሜት ይሰማቸዋል ሲል ዚ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን ይጠቁማል፡፡
ዶ/ር ማይክል ሺፍ ‹‹በመካከለኛው ዕድሜ ላይ በሚገኙ ሴቶች ላይ ሩማቶይድ አርታይተስ በብዛት ይታያል›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሺፍ ‹‹ህፃናትንና ወንዶችን ጨምሮ በማንኛውም ዕድሜ የሚገኝን ሰው ሊያጠቃ ይችላል›› በማለት አክለው ተናግረዋል፡፡ ሩማቶይድ አርትራይተስ ያለባቸው ዘመዶች ያሏቸው ሰዎች በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ማጨስ፣ ከልክ በላይ የሆነ ውፍረትና ደም መውሰድ ለበሽታው የሚያጋልጡ ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑ በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡ በአርትራይተስ በሽታ የተያዙ ሰዎች የቅርጽ መበላሸት፣ መሽመድመድና የህመም ስቃይን ለማስተናገድ ይገደዳሉ፡፡
ህክምና
የአርትራይተስ ህክምና አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ መድኃኒቶችን መውሰድን፣ አካላዊ እንቅስቃሴና የአኗኗር ለውጥ ማድረግን ያጠቃልላል፡፡ አንድ ፊዚካል ቴራፒስት ጤናን ለማሻሻል የሚረዳ የሰውነት እንቅስቃሴ ያሰራን ይሆናል፡፡ ይህም ጡንቻዎች እንዲሳሳቡና እንዲለጠጡ የሚያደርግ (Isometric)፣ ክብደት እንደማንሳት ያሉትን (Isotonic) እና የኤይሮቢክ እንቅስቃሴዎችን ሊያካትት ይችላል፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች እንደ አንጓ ህመምና እብጠት፣ ድካም፣ መጥፎ ስሜት እንደመሰማትና ጭንቀት ያሉትን የህመም ስሜቶች እንደሚቀንሱ ታውቋል፡፡ የአካላዊ እንቅስቃሴ ጥቅም በጣም ባረጁ ሰዎች ላይ ሳይቀር ታይቷል፡፡ በተጨማሪም አካላዊ እንቅስቃሴ የሚደርሰውን የአጥንት መሳሳት ያስወግዳል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በሙቀትና በቅዝቃዜ በሚሰጡ የተለያዩ ህክምናዎችና በአኩፓንክቸር ከህመማቸው ፋታ እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡
ክብደት መቀነስ የአንጓ ህመሞችን በከፍተኛ መጠን ስለሚቀንስ የአመጋገብ ለውጥ ማድረግ ለአርትራይተስ ከሚደረጉት ጥንቃቄዎች ዋነኛውን ቦታ ሊይዝ ይችላል፡፡ ጠቆር ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸውን በካልስየም የበለፀጉ ቅጠላ ቅጠሎችን፣ ትኩስ ፍራፍሬዎችን፣ ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ የሚባለው ንጥረ ምግብ የሚገኝባቸውን የቀዝቃዛ አካባቢዎች ዓሣ አዘውትሮ መመገብና በፋብሪካዎች በመዘጋጀታቸው ምክንያት የተፈጥሮ ባህርያቸውን ያጡና የቅባት ክምችት ያላቸውን ምግቦች መቀነስ ክብደት ለመቀነስ ከመርዳቱ በተጨማሪ የህመም ስሜትን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡
አርትሮስኮፒ የሚባለውን ቀዶ ህክምና መውሰድ የሚመከርበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ ህክምና በሚሰጥበት ጊዜ መሳሪያው አንጓ ውስጥ እንዲገባ ይደረግና የቀዶ ህክምና ባለሙያው ጉዳት የሚያስከትሉ ኢንዛይሞች የሚያመነጨውን ሲኖቭያለ ህብረህዋስ ያስወግዳል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ አንጓው ተመልሶ ስለሚቆጣ ይህን አይነቱ ቀዶ ህክምና የሚያስገኘው ጥቅም በጣም ውስን ነው፡፡ ከዚህ ይበልጥ ከባድ የሆነው ህክምና አርትሮፕላስቲ ይባላል፡፡ በዚህ ህክምና መላው አንጓ (አብዛኛውን ጊዜ የዳሌ ወይም የጉልበት አንጓ) ይወገድና በቦታው ሰው ሰራሽ አንጓ ይተካል፡፡ ይህ ህክምና ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊያቆይ ሲችል ህመም በማስወገድ ረገድ በጣም ውጤታማ ነው፡፡
አርትራይተስን ጨርሶ የሚያድን መድኃኒት ባይገኝም፣ የህመም ስሜቶችንና የአንጓ ብግነትን የሚያስታግሱ በርካታ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ሐኪምዎን ያማክሩ!
ምንጭ፡- ዌስተርን ጆርናል ኦቭ ሜዲስ

የጤና
አጫጭር ዜናዎች
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለመንፈስ ጭንቀት
‹‹ለመንፈስ ጭንቀት መድኃኒት ከመጠቀም ይልቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለአንዳንድ ህመምተኞች የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል›› ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ሄልዝ ሌተር ተናግሯል፡፡ በሶስት ቡድን ለተከፈሉ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ለተያዙ 50 ሰዎች ለ4 ወር የሚቆይ የተለያየ ህክምና ተሰጣቸው፡፡ በመጀመሪያው ቡድን ውስጥ ለሚገኙት ጭንቀት የሚያስታግስ መድኃኒት ተሰጣቸው፡፡ በሁለተኛው ቡድን ውስጥ የሚገኙት የአካል በቃት እንቅስቃሴ ብቻ እንዲሰሩ ተደረገ፡፡ በሶስተኛው ቡድን ውስጥ የሚገኙት ደግሞ ሁለቱንም የህክምና ዘዴ እንዲጠቀሙ ተደረገ፡፡ ከአራት ወር በኋላ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት በሶስቱም ቡድን ውስጥ የሚገኙ ህመምተኞች ‹‹የነበረባቸው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ለቅቋቸዋል፡፡›› በማለት ሂልዝ ሌተር ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ለስድስት ወራት በተደረገው ክትትል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሰሩ የተደረጉት ህመምተኞች ‹‹በስሜትም ሆነ በአካል በተሻለ ሁኔታ ላይ የተገኙ ሲሆን በበሽታው እንደገና የመጠቃት እድላቸው ስምንት በመቶ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡›› ከዚህ ጋር ሲነፃፀር መድኃኒት እንዲወስዱ የተደረጉትና መድኃኒት እየወሰዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሰሩ የተደረጉት ህመምተኞች በበሽታው እንደገና የመጠቃት እድላቸው 38 እና 31 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ከልክ ያለፈ ውፍረትና ካንሰር
የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት እንደዘገበው፤ ‹‹በምዕራቡ ዓለም ለማያጨሱ ሰዎች ዋነኛው ሲወገድ የሚችል የካንሰር ምክንያት ውፍረት ነው፡፡›› ለሃምሳ ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች ወፍራም ከሆኑ ክብደት መቀነስን ጨምሮ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ አጫሽ ላልሆኑ ሰዎች በካንሰር የመያዝን ዕድል በግማሽ እንደሚቀንስ አመልክቷል፡፡ ‹‹አጫሽ ካልሆንክ የሚያሳስቡህ ሁለት ነገሮች ውፍረትና የሆድ ዕቃና የማህፀን ካንሰር መንስኤ የሆኑት ቫይረሶች ናቸው›› ይላሉ የብሪታኒያ ካንሰር ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጁልያን ፔቶ፡፡ ‹‹የአመጋገብ ቁጥጥር በተደረገባቸው እንስሳት ላይ የተደረጉ ሙከራዎች ለካንሰር የመጋለጥ ዕድል በእጅጉ ቀንሶ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡›› በህክምና መመዘኛዎች መሰረት አንድ ሰው ወፍራም ነው የሚባለው ለዕድሜው፣ ለይታው፣ ለቁመቱና ለቁመናው ትክክል ነው ተብሎ ከሚታሰበው ሰውነት ክብደት 20 በመቶ በልጦ ሲገኝ ነው፡፡

የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን በዶሮ ሾርባ
‹‹የዶሮ ሥጋ፣ እንደ ብዙዎቹ የፕሮቲን ምግቦች ሲሶቴይን የተባለ ተፈጥሯዊ አሚኖ አሲድ አለው፡፡ ሥጋው በሚቀቀልበት ጊዜ ይህ አሚኖ አሲድ ይወጣል፡፡ ሲሶቴይን ዶክተሮች በብሮንካይትስና በሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ለተያዙት ሰዎች ከሚያዙት አሴትልሲስቴይን ከተባለው መድኃኒት ጋር በጣም ይመሳሰላል፡፡ በመሆኑም የዶሮ ሾርባ እንደ ጉንፋን ላሉት የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ይጠቅማል›› ሲል ፉድ፣ ዩር ሚሩክል ሜዲሲን የተባለው መጽሐፍ አስታወቀ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ከዶሮ ላባና ቆዳ ይዘጋጅ የነበረው ይህ መድኃኒት በአፍንጫ፣ በጉሮሮና በሣንባ ውስጥ የተጠራቀመውን ንፍጥ የማቅጠንና ወደ ውጭ እንዲፈርስ የማድረግ ችሎታ አለው፡፡ ሾርባው የተዘጉ የመተንፈሻ አካላትን የመክፈት ኃይሉ እንዲጨምር ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርትና እንደ ሚጥሚጣ የመሳሰሉትን ተኮስ የሚያደርጉ ቅመሞች መጨመሩ ጥሩ እንደሚሆን ዶ/ር ዚመንት ይመክራሉ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>