ፍኖተ ነፃነት
የአንድነት ፓርቲ የመቱ ዞን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ታመነ መንገሻ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስከረም 3 ቀን 2007 ዓ.ም በመቱ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ከአካባቢው የደረሰን ዜና ያመለክታል፡፡ አቶ ታመነ መንገሻ የታሰሩት አማራ ይቀውጣ ብለሃል በሚል ሰበብ እንደሆነና ይህን ተናገሩ በተባለበት ወቅት ታመው አልጋ ላይ እንደነበሩ ምንጮቻችን የገለጹ ሲሆን ፖሊስ በሳቸው ላይ እንዲመሰክር ፖሊስ ጣቢያ ለምስክርነት የቀረበው ግለሰብ እሳቸው ሲናገሩ የሰማሁት ዓላማችን መለያየት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት እንዲቀጥል ነው ብለው በማለታቸው መስካሪውም እንዲታሰሩ ተደርገው በዋስ ተለቀዋል፡፡አቶ ታመነ መንገሻ ጳጉሜ 4 ቀን ታስረው እንደነበረና ጳጉሜ 5 ቀን 2006 ዓ.ም በዋስ ቢለቀቁም በአካባቢው ያሉ የመንግስት ካድሬዎች ለምን ተለቀቁ መታሰር አለባቸው በማለታቸው በድጋሚ እንደታሰሩ እስካሁንም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ በተያያዘም በመቱ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያም የታሰሩ 15 እና ከ 15 ዓመት በታች የሚገኙ በርካታ ወጣቶች እንደሚገኙና የታሰሩበት ምክንያትም የተቃዋሚ ፓርቲ አባልና ደጋፊ ናችሁ በሚል እንደሆነ ከአካቢው ምንጮቻችን ያደረሱን ዜና ያመለክታል፡፡