Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሹሞች በመንግሥት ላይ ከ5.2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ታሰሩ

$
0
0

- ዋስትና ተከልክለው ወደ ማረሚያ ቤት ወርደዋል

የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት፣ በመንግሥት ላይ ከ5.2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ 11 ሹሞችና ሦስት ነጋዴዎች፣ ክስ ተመሥርቶባቸውና ዋስትና ሳይፈቀድላቸው ማረሚያ ቤት ወረዱ፡፡

የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመመራት የሙስና ወንጀል ክስ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት የተመሠረተባቸው ሹሞች የክፍለ ከተማው የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት የገበያ ጥናት ባለሙያው አቶ ሞላ ሙጨ፣ የገበያ ልማት ትስስርና መረጃ ከፍተኛ ኦፊሰር አቶ መልካሙ ዘሪሁን፣ የግዥ ንብረት አስተዳደር የሥራ አስተባባሪ አቶ ጌትነት መረሳ፣ የፋይናንስ ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ሲኒየር የፋይናንስ ኦፊሰር አቶ ዳንኤል ታዬ፣ የግዥ ንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ደጋፊ የሥራ ሒደት ወ/ሮ አስናቀች ዓለማየሁ፣ የግዥ ንብረት አስተዳደር የሒሳብ ሰነድ ያዥ አቶ ዮሐንስ አሰፋ፣ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት የክፍያና ሒሳብ ደጋፊ የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ፍቃዱ አንጫሞ፣ የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት የግዥ የሥራ ሒደት ኃላፊ አቶ ግርማ ቶሎሳ፣ የአቅም ግንባታ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ማሞ፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተገኝ ጦፋና የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ ታደሰ ናቸው፡፡

ክሱን የመሠረተው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ውስጥ የሚገኘው የኢዜድ አጠቃላይ ንግድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዮብ ዘነበ፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ውስጥ የሚገኘው የሱሳ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ወንድሙና በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ውስጥ የሚገኘው የአጋዘወርቅ ጠቅላላ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ወርቁ የተባሉ ግለሰቦችንም በክሱ አካቷቸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ክስ የተመሠረተባቸው ክፍለ ከተማው ለአቅም ግንባታ፣ ለዋና ሥራ አስፈጻሚና መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት አገልግሎት የሚውሉ የቢሮ ዕቃዎች ለመግዛት የካቲት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በጋዜጣ ከወጣ የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ ጋር በተያያዘ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪ ሹሞቹ የቴክኒክ ኮሚቴና የጨረታ ኮሚቴ ሆነው ሲሠሩ፣ በአንድነት መንግሥትን ጐድተው ከላይ የተጠቀሱትን ሦስቱን ድርጅቶች ለመጥቀም በማሰብና በመተባበር፣ የክፍለ ከተማውን የግዥ መመርያ 3/2002 ሳይከተሉ፣ የዝርዝር ፍላጐት መግለጫ (Specification) ባልወጣላቸው የቢሮ ዕቃዎች ላይ ውድድር ማካሄዳቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ በጨረታ ሰነዱ ላይ ከተቀመጠው ዝቅተኛ ዝርዝር መሥፈርት በታች (Minimum Standard Specification) መምረጣቸውን፣ በጨረታ ሰነዱ ላይ የተቀመጠውን ዝርዝር የፍላጐት መግለጫ አሻሽለው መረጣ ማካሄዳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በጨረታ ሰነዱ ውስጥ ግዥ እንዲፈጸም ከተዘረዘሩ ዕቃዎች መካከል እያንዳንዱ ተጫራች ያቀረባቸው የቢሮ ዕቃዎች በምን ቴክኒካዊ ውጤትና የጥራት ደረጃ እንደወደቁ እንደማይታወቅ፣ በቅድመ ሁኔታ መቀመጥ የነበረበትን ዝርዝር የጥራት መሥፈርት ሲያስቀምጡ ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድር በአቅራቢዎቹ መካከል ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ አቅራቢው ከገበያ ዋጋ በላይ ወስኖ ያቀረበላቸውን የቢሮ ዕቃዎች የቴክኒክ ኮሚቴው የዕቃ ጥራት ብቻ እንዳወዳደረ አስመስሎ፣ የጨረታ ኮሚቴው በአንድ ዋጋ ላይ ብቻ እንዲወስንና በጨረታ ኮሚቴው ግዥ እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡

በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ የግዥ መመርያ 3/2002 መሠረት የማወዳደሪያ መሥፈርት አዘጋጅተው ማወዳደር ሲገባቸው፣ አቅራቢዎቹ በምን መሥፈርት እንደተመረጡ ግልጽ ባልሆነበትና የቴክኒክ ውድድር በሌለበት ሁኔታ ሕጋዊ አሠራሩን ወደ ጐን በመተው፣ በራሳቸው መንገድ የቴክኒክ ውድድር ማካሄዳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴው ያለምንም የዝርዝር ፍላጎት መግለጫ የጨረታ ኮሚቴው ደግሞ ያለምንም የገበያ ጥናት በፈጸሙት ግዥ፣ በመንግሥት ላይ የ5,209,964 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው በክሱ ላይ ሰፍሯል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ክሱን አይተውና ተገንዝበው ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ተነጋግረው ለመቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ተሰጥቷል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

bigwhy


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>