Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ይድረስ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ: ሕገ-መንገስቱ ተጣሰ፣ ሻለቃ መላኩ ተፈራ ታገተ

$
0
0

ለክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

ጉዳዩ፡- በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 37(1) መሠረት ፍትሕ ለማግኘት ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበ አቤቱታ፤

1. በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 51(1) ሕገ-መንግሥቱን መጠበቅና መከላከል የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር በመሆኑ፤

2. በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 74(13) ሕገ-መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር በመሆኑ፤ አቤቱታዬን እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ለክቡርነትዎ ለማቅረብ ተገድጃለሁ፡-

ጅቡቲ በስደተኞች ሰፈር በምኖርበት ቤት ውስጥ ታሕሣሥ 26 ቀን 1985 ዓ.ም. ከምሽቱ 3 ሰዓት በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በተፈጸመብኝ የመግደል ሙከራ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኝ፣ በጅቡቲ ሆስፒታል ለ1 ዓመት ከ3 ወራት በሕክምና ስረዳ ቆይቼ በእግዚአብሔር ቸርነት ከሞት ልተርፍ ችያለሁ፡፡ በወቅቱ በጭካኔ ከተደበደብኩባቸው 9 ጥይቶች መካከል አንዱ ጥይት አሁንም በሰውነቴ ውስጥ ስለሚገኝ ከሳምባዬ ጋር በሚያደርግው ንክኪ በየጊዜው ለከባድ የሳል ሕመም የሚዳርገኝ መሆኑን በሐኪም ተረጋግጦ ተነግሮኛል፡፡ ለዚህ የወንጀል ድርጊት ተጠያቂ የሆኑት ሰዎች ግን ዛሬም የመንግሥት ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው ከእሥር እንዳልፈታ የተለመደ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡ አልፎ ተርፎም ከማረሚያ ቤት ብወጣም ሕይወቴ በእነሱ እጅ እንደሆነና የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ዛቻዎቻቸው እየደረሰኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ደምን በደም ቢያጥቡት ተመልሶ ደም ነው፡፡
pen
የሆነው ሆነ ይህንን ማመልከቻ ልጽፍልዎ የተነሳሁበት ዋና ምክንያት፣ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 25 እና በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 4 ‹‹ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው›› የሚለውን ድንጋጌ በሚቃረን መልኩ በዜግነቱ በዕኩልነት የመታየትና የመዳኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብቴ በመጣሱ የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰብኝ፤ ፍትሐዊ ውሳኔ ይሰጡኛል በሚል እምነት ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም አቤቱታዬን በጽሑፍ ለክቡርነትዎ ማቅረቤን ያስታውሱታል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደሚታወቀው በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 202(1) ማንኛውም ተቀጪ ፍርዱ የዕድሜ ልክ እስራት ከሆነና ታሳሪው ሃያ ዓመት ከታሰረ፣ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛው በአመክሮ እንዲፈታ እንደሚወስን ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሰረት እኔም በተከሰስኩበት ጉዳይ እጄ ከተያዘበት ከ22/8/1986 ዓ.ም. አንስቶ የተፈረደብኝን የእድሜ ልክ እሥራት (20 ዓመት) በ22/8/2006 ዓ.ም. ጨርሻለሁ፡፡ ሆኖም ከ23/8/2006 ዓ.ም ጀምሮ በማላውቀው ጉዳይ ሕገ-መንግስታዊ መታግቼ አሁንም በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት /ቃሊቲ/ ዞን አራት ውስጥ በእሥር ላይ እገኛለሁ፡፡ ማረሚያ ቤቱ የአመክሮ መብትን ለማክብር ታራሚው በእስር ቤት ቆይታው ያለውን ባሕሪ መገምገም እንዳለበት አውቃለሁ፤ በዚህ መሰረትም እኔ 20 ዓመት በእሥር በቆየሁበት ጊዜ የነበረኝ ጠባይ ተገምግሞ ያገኘሁት ውጤት እጅግ የሚያስመሰግነውን ዘጠና አምስት ከመቶ (95%) ነው፡፡ ይህም በማረሚያ ቤቱ ኃላፊ በአቶ አብርሃም ወልደአረጋይ ፊርማ ተረጋግጦ፣ ለፍቺ ከሌሎች ታራሚዎች ሠነዶች ጋር በ9/8/2006 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ተልኮ የነበረ ቢሆንም፤ በ17/8/2006 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ከተላኩት ሠነዶች መካከል የእኔን ብቻ ነጥለው መለሰው በማስመጣ ራሳቸው አቶ አብርሃም ወልደአጋይ በእጃቸው እንደያዙት በማረሚያ ቤቱና በፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ተረጋግጦ ተነግሮኛል፡፡ ይህን የሚያስረዳ የፍርድ ቤቱ ማረጋገጫ ሠነድም ከዚህ ጋር ተያይዟል፡፡ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ፣ አቶ አብርሃም ወልደአረጋይን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ሊያነጋግሩን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሳካልን አልቻለም፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 19(3) በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳላቸው የተደነገገ ቢሆንም፤ እኔ ግን የተፈረደብኝን ቅጣት ጨርሼ ያለአንዳች ምክንያት ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ እስከ ዛሬ (ነሐሴ 17 ቀን 2006ዓ.ም) ድረስ 115 ቀናት ወይም 2760 ሰዓታት ታግቼ እገኛለሁ፡፡

ክብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 365/1999 አንቀጽ 39(1) መሠረት በወጣው የፌዴራል ታራሚዎች አያያዝ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/1999 አንቀጽ 44(1) ስለማረሚያ ቤቱ ግዴታ እንደሚከተለው ተደንግጓል፡፡
‹‹ማንኛውም ታራሚ የእሥራት ጊዜውን ሲጨርስ፣ ይቅርታ ወይም ምሕረት ሲያገኝ ወይም ፍርድ ቤት በአመክሮ እንዲፈታ ትእዛዝ ሲሰጥ ማረሚያ ቤቱ ታራሚውን ወዲያው የመፍታት ግዴታ አለበት››፡፡
ነገር ግን እኔን ለመጉዳት ሲባል ብቻ ይህ ደንብ ሊጣስ መቻሉን ክብሩነቶ እንዲያውቁት ነው፡፡

እንዲሁም በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(1) የሕገ-መንግሥቱ የበላይነት እንደሚከተለው ታውጇል፡-
‹‹ሕገ-መንግሥቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም›› ተብሎ የተደነገገ ቢሆንም አሁንም እኔን ለመጉዳት ሲባል ብቻ ይህ የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ተጥሷል፡፡
ስለዚህም እስከ ዛሬ ድረስ ከነቤተሰቤ የደረሰብኝን የረዥም ጊዜ ተደራራቢ ችግር በጥሞና ተረድተውልኝ በሕገ-መንግሥቱ የበላይነት ከእስር እንድፈታ ክቡርነትዎ ለማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ለአቶ አብርሃም ወልደአረጋይ ትእዛዝ እንዲሰጡልኝ በማክበር አመለክታለሁ፡፡
ሻለቃ መላኩ ተፈራ ይመር


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>