በዋሽንግተን ዲስና አካባቢዋ ከሚታተመው ከዘኢትዮጵያ ጋዜጣ የተገኘ
ታሪክ የሚታወቀው ሲጻፍ ወይ ሲነገር ነው። መታመን አለመታመኑም የሚያከራክረው ተጽፎ ወይም በሌላ ቅርጹ ተመዝግቦ ሲገኝ ብቻ ነው። የታሪክ ታሪክነቱ ስነ ጽሑፉነቱ ሳይሆን ሁነቱ ክስተቱ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ መደረግ መፈጸሙ ነው። ካልሆነ ግን ልብወለድ ድርሰት መሆኑ አይቀርም። ሆነም ቀረ ግን ተፈጽሟል እንዲህ ሆኗል እንዲያ ነበር እያሉ ከነማረጋገጫው የሚነግሩን ታሪክ ዘጋቢዎች አሉ። ለተአማኒነቱ ሲባል ከስሜታዊ ወገንተኝነቱ እንዲጸዳ ታሪክ በታሪክ ሠሪዎች ባይጻፍም፣ እነሱ የሚተዉት ማስታወሻ ግን ለታሪክ ፀሐፊዎች ግሩም ስጦታ መሆኑ የታመነ ነው። አቶ ገብሩ አስራት በዚህ ረገድ ለታሪክ ፀሐፊዎች አንድ ማስታወሻ ትተዋል። መጽሐፉ ሰፕቴምበር 1/2014 በዋሽግንተን ዲሲ በተደረገ አንድ ሥነ ሥርዓት ተመርቋል። ዶ/ር ካሳ አያሌው በመሩት በዚህ የመጽሀፍ ምርቃት ፕሮግራም ላይ ተገኝተው መጽሐፉን የቃኙት አቶ ፈቃደ ሸዋቀናም መጽሐፉ ለሌሎች ፀሐፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ፓለቲከኞችና አንባቢዎች እርሾ ሊሆን የሚችል ፈር ቀዳጅና አከራካሪ መጽሐፍ ሆኖ አግኝቸዋለሁ” ብለዋል።
እንደተባለውም ማከራከሩ አይቀርምና ታሪክ ፀሐፊዎች ወደፊት ፍሬውን ከገለባ ለይተው እውነቱን ከሐሰት አበራይተው ይህን ያለንበትን ዘመን ይገልጹታል። የታሪክ ማስታወሻ መተው እየተበራከተ ባለበት በዚህ ዘመን ዘመኑን አሳምሮና ወክሎ የሚገልጸው ታሪክ የትኛው እንደሆነ ማወቁ ይቸግረን ይሆናል።
ቢሆንም ነገሮች በፍጥነት መደበላለቅ በያዙበት በዚህ ዘመን የተደበላለቀ ስሜት የሚፈጥረው የአቶ ገብሩ መጽሐፍ ለታሪክ የሚተወው ማስታወሻ ምን ሊሆን እንደሚችል መቃኘቱ አይከፋም። ዘመኑን ያልተረጋጋ፣ የአፈና፣ የስደት፣ የመከፋፈል፣ የመከራ፣ የእስርና የጭቆና በማድረግ ግንባር ቀደም ተዋናይ ከሆኑት ሰዎች መካከል እግዜር አንዳንዱን እየመዘዘ ቶሎ ሳይዘነጉት፣ እያደረጉ ያሉትን ነገር ቆም ብለው አስተውለው እንዲጽፉት ሲያደርግ ደስ ያሰኛል። አቶ ገብሩም በመጽሀፋቸው ደጋግመው የሚጠቀሙባት “ አሁን ቆም ብዬ ሳዬው፣ አሁን መለስ ብዬ ሳየው፣ አሁን ሳጤነው” የምትል አገላለጽ አለች። ይክፋም ይልማም ቆም ብለው የሚቆጩበት ነገር አለ ማለት ነው። ለምሳሌ በመጽሀፋቸው ገጽ 249 ላይ “አሁን ሳጤነው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነታችን ምክንያት የመረጃ ፍሰትን ገድበን የአገራችንን የአስተሳሰብ እድገት በመጎተታችንና በማጫጨታችን እጸጸታለሁ።” ብለዋል።
ይህን ያጫጩትን የአስተሳሰብ እድገት ለማምጣት ከህሊናቸው ጋር ተማምለው ፋይዳ ያለው መጽሀፍ ለማዘጋጀት መነሳታቸውን በመግቢያቸው ጽፈዋል። “ ስለሆነም ለኀሊናዬ ትክክል የመሰለኝን ሁሉ ለማስፈር ሞክሬም፣ ሰማዕታቱ የተሰውለትን ዓላማ ለማክበር ሞክሬያለሁ” (ገጽ4) በማለት ከደጋፊዎቻቸውና ተቃዋሚዎቻቸው የሚመጣባቸውን ነቀፌታ የገመቱ መስለዋል። ሚዛናዊ ነኝና ልብ አድርጉልኝ ነው ነገሩ። ቢሆንም ነቀፌታውና ውርጅብኙን ያቆሙት ዘንድ ግን አይችሉም። የሚችሉትና ችለው ያሳዩት ነገር ለታሪክ የሚሆን ማስታወሻ መተው ነው። እሱን ትተውልናል! ጥያቄው የተውልን ነገር ምንድነው? የሚለው ነው። በዚህ ዘገባ “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” ከሚለው ባለ 516 ገጽ መጽሐፋቸው የተውልንን ማስታወሻ ከመጠነኛ አስተያየት ጋር መቃኘት ሞክረናል። መቸም የዘንድሮ መጽሐፍ ከድንጋይ ዳቦ ዘመን ካልጀመረ፣ ታሪክ ካላስተማረ አይሆንለትም። መጀመሪያ ረጀሙና ገናናው ታሪካችንን አንስተን እንጸልይበት ካለለ ወደ ፍሬ ነገሩ መምጣት ያስቀስፋል። ስለዚህ አንዴ ሺ ዘመን አንዴ መቶ ዓመት እየሆነ እንደ ስቶክ ማርኬት ገበያ የሚወጣ የሚወርደውን ዘመን እንለፈውና ወደ አቶ ገብሩ ዘመን ቀረብ ብሎ ያለውን የመጽሐፋቸውን ገጽ ገለጥ ገለጥ እናድርገው። መጽሐፉ በስድስት ም ዕራፎች በበርካታ ን ዑስ ም ዕራፎች የተከፋፈለ በቁመቱም ዘለግ ያለ ባለ 516 ገጽ ነው። አክሱምን የድርጅታቸውን የትጥቅ ትግል ዘመን ህወሓት ለሥልጣን የበቃበትንና ከኤርትራ ጋር በመንግሥት አብሮ የኖረበትን እንዲሁም ጦርነቱንን ከጦርነቱ በኋላ ያለውን ሁኔታ ሁሉ በዝርዝር ይዳ ስ ሳል። ሰለኢትዮጵያ የዴሞክራሲና ሰብ አዊ መብቶች አያያዝ ስለምርጫን የፖለቲካ ምህዳር መስፋት መጥበብ ያነሳል። መፍትሔ ሀሳቦች ናቸው የሚላቸውንም ሰንዝሯል። እጅግ የተደከመበት መጽሐፍ መሆኑ ያስታውቃል። ከመጽሐፉ ፍሬ ነገሮች ጥቂቶቹን ለመጋራት ያህል የሚከተለው ቅኝት ተደርጋል።
ፖለቲካ ፓርቲ ተጀመረ!
እንደ አቶ ገብሩ መጽሐፍ – ከ1930ዎቹ ቀደም ብሎ በኤርትራና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ትጥቅ አንግበው ከሥርዓት ጋር መፋለም የጀመሩ ግንባሮች ነበር። እነዚህ ከማዕከሉ ርቀው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ቢሆንም ወደኋላው ላይ በአዲስ አበባ ጭምር እየተጧጧፉ ለመጡት አገር አቀፍና ብሔር ተኮር ድርጅቶች እንዲሁም የተማሪ ቤት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ሆነዋል። በመሆኑም ከኤርትራና ከሶማልያ ድርጅቶች ቀጥሎ በ1960 በጀርመን ሃምቡርግ ከተማ በእነ ኃይሌ ፊዳ የተመሠረተው “የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ” /መኢሶን/ አንጋፋው ፓርቲ ነው። ይሁን እንጂ አቶ ገብሩ ይህን ያገኙት ተስፋዬ መኮንን በ1985 ይድረስ ለባለ ታሪኩ በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ ገጽ 119 ላይ መሆኑን ጠቅሰው “አንዳንዶች መኢሶን በ1960 መመስረቱን እንደሚጠራጠሩ” ገልጸዋል። ለታሪክ በተውት መጽሐፋቸው የዘገቡት ግን “መረጃው ትክክል ነው ብለን ከተቀበልነው” (ገጽ35) በሚል ጥርጣሬ ነው። የ66 አብዮቱ ከመፈንዳቱ 10 ዓመት በፊት መሆኑ ነው።
በ1964 በጀርመን በርሊን በእነ አቶ ብረሃነ መስቀል ረዳ፣ ኢያሱ ዓለማየሁ ዘርኡ ክሸን ተስፋይ ደበሳይ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አርነት ድርጅት / ኢሕአድ/ ኋላም አገር ቤት ከነበሩት እንደ አብዮት የመሳሰሉ ቅድመ ፓርቲ ድርጅቶች ጋር አብሮ ሲሰራ ቆይቶ መዋሃዱንና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ/ ኢሕአፓ ተብሎ መሰየሙን ተመሳሳይ ምንጭ ጠቅሰው ጽፈዋል። ከእነዚህ የህብረ ብሔር ከሆኑት የመኢሶንና የኢሕአፓ ፓርቲዎች ቀጥሎ ምናልባትም ቀደም ብለው ሌሎች የብሔር ድርጅቶች እየተቋቋሙ መምጣታቸውን ጽፈዋል። ቀደም ሲል በሜጫና ቱለማ የመረዳጃ እድር እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ በ1966 በይፋ መቋቋሙን ዘግበዋል። ከእነዚህ ሁሉ የቀደመውና እንደ ሌሎቹ በኤርትራ ተጠልሎ ይንቀሳቀስ የነበረው የብሔር ድርጅት በ1962 በትግራይ ተወላጆች የተቋቋመውና በመምህር ዮሐንስ ተክለ ኃይማኖት “ማህበር ፖለቲካ” ተብሎ የሚጠራው ነው። የትጥቅ ትግል በማንሳት ከኤርትራ ድርጅቶች ቀጥሎ በሰሜን ኢትዮያ የተቋቋመው ግምባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ /ግገሓት/ የትግራይ ትግሪኝ ወይም ኤር-ትግራይ በሚል ኤርትራና ትግራይን አቀናጅቶ አንድ አገር ለመፍጠር የተነሳ መሆኑ በመጽሐፉ ተጽፏል። ለማንኛውም እነዚህኞቹን ጀብሃ ኢሕአደንን ደግሞ ሻዕቢያ እየደገፉት ለትጥቅ ትግል ዝጅግት ሲያደርጉ እስከ 1967 በኤርትራ ቆይተዋል። የትጥቅ ትግል ለማድረግ በኤርትራ እየተደገፉ ከተቋቋሙ የትግራይ ብሔር ድርጅቶች መካከል ሌላኛው መጀመሪያ ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ ቀጥሎም ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ /ተሓህት/ እያደርም ህወሓት ሆኖ የወጣው ድርጅት መሆኑን ከገብሩ መጽሐፍ መረዳት ይቻላል። የትግራይ ተማሪዎች ገና ዩኒቨስቲ መግባት ሳይደርሱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ይቀሰቀሱ እንደነበር ገብሩ የራሳቸውን ታሪክ እያመሳከሩ እንዲህ ጽፈዋል፟-
“ገና ዘጠነኛ ክፍል እያለሁ አንዳንድ ከቀዳማዊ ኃለሥላሴ ዩኒቨርስቲ የመጡ ስለአገሪቱ ፖለቲካ ችግሮች እያነሱ ይቀሰቅሱ ነበር..በ1960ዎቹ መጀመሪያ የክልሉ ተወላጆች የሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ክረምት ለዕረፍት እየመጡ ፖለቲካዊ ቅስቀሳዎችን ያካሂዱ ነበር።” (ገጽ 40) “የትግራይ ተወላጅ የሆኑት
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለእረፍት ሲመጡ የክረምት አካዴሚያዊ ትምህርት እንሰጣለን በሚል ሽፋን የፖለቲካ ትምህርት መስጠት ጀምረው ነበር። እነዚህ አስተማሪዎች የሚሰጡን ትምህርት አብዛኛውን ጊዜ የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ይሰጡን ነበር” (ገጽ 41” ብለዋል። የትግራይ ብሔርተኞች የተለያየ ስያሜና የፖለቲካ አስተሳሰብ ቢኖራቸውም ዞሮ መግቢያ መደምደሚያቸው ያቺው ትግራይነታቸው መሆኑን ለማስተዋል የአቶ ገብሩ መጽሐፍ ጥሩ የማመሳከሪያ ሰነድ ነው። ከትግራይም ደግሞ እንዲሁ ወደ ጎጥ እየወረዱ ይሄዳሉ። እነሆ የገብሩ ቃል!“በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች
ተሓትን ጨምሮ እጅግ ወግ አጥባቂ ባህል የተጠናወታቸው ነበሩ። የድርጅቶቹ አመራሮቹም ቢሆኑ ከዚህ የጸዱ አልነበሩም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ሥር የሰደደ ኋላ ቀርነትና ጎጠኝነት የተጠናወታቸው ነበሩ።(ገጽ 82)ከፍ ሲል ያየነውና አቶ ገብሩ በመጽሀፋቸው በአንጋፋነታቸው ከጠቀሷቸው ህብረ ብሄር የፖለቲካ ድርጅቶች መኢሶን አንዱ ነበር። የዚሁ ድርጅት አመራር የነበሩት ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ሰሞኑን “ይድረስ ከየካቲት ለግንቦት” ብለው በወቅቱ ይዋደቁ የነበሩት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዓላማና አደረጃጀት ምን እንደነበር ባወሱበት በዚህ መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል “ በዛሬው ግርግርና የብሄር /ብሄረሰብ ድርጅቶች ማየል የተነሳ ብዙ ሰው ልብ የማይለው ቁም ነገርና እኛ መኢሶኖች የቀሰምነው ትምህርት አለ፡፡ መሬት ለአራሹ ብለን ያኔ ስንዋደቅ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ደህንነት በአንድ ላይ ታግለን ነው፡፡ የደርግ መንግስት የመኢሶን መሪዎች በማለት በአንድ ቀን አምስት ታጋዮችንን ማለትም፤ ሀይሌ ፊዳን፤ ዶክተር ንግስት አዳነን፤ ቆንጂት ከበደን፤ ደስታ ታደሰንና ሃይሉ ገርባባን ወስዶ ሲረሽን እነዚህ መሪዎቻችን ከኦሮሞ፤ ከትግራይ፤ ከአማራና ከጉራጌ ብሄሮች የተውጣጡ ዜጎች ነበሩ፡፡ ለዚህ ወይም ለዚያ ብሄር ሳንል በአንድ መንፈስ በአንድ አላማ በወንድማማችነት መንፈስ ታግለናል፡፡”እነ አቶ ገብሩ የሞቱለት ድርጅት በራሳቸው መጽሐፍ ገጽ 43 ላይ እንደምናስተውለው ገና ከማለዳው በትግራዮቹ ታጋዮች ዘንድ “የታላቋ የኢትዮጵያ አስተሳሰብ አራማጅ” ተብለው መወጀንልና መፈራረጅ የነበረ መሆኑን ነው። የካቲት 11 ቀን 1967 ደደቢት ላይ ትጥቅ ትግል የጀመረው ተሓህት ጠመንጃ ማጮህ ጀመረው ወዴት እንደሚሄድ ምን እንደሚፈልግ አጥርቶ ሳያውቅ፣ በገብሩ አነጋገር “በሰነድ የሰፈረ የፖለቲካ ፕግራም” ሳይኖረው ነው። “ተሓህት ውስጥ እስከ 1968 ዓም ድረስ የዚህ ዓይነቱ ክፍተት ስለነበር አባላቱ የተሓህትን ዓላማ በመሰላቸው መንገድ ይገልጹት ነበር። አንዳንዶቹ የተሓህት ዓላማ የትግራይን ሕዝብ ነጻ ማውጣት ነው ሲሉ” ሌሎች ደግሞ የመደብ ትግል በማካሂያድ ጭቁኖችን ነጻ ለማውጥት ነው ይሉ ነበር። የብሔር ጥያቄና የመደብ ትልግ የተዘባረቁበትና አቅጣጫም ያጡበት ሁኔታ ነበር።”45
ከመጽሐፉ የተወሰዱ
gebru asrat
1ኛ. ህወሃት በ17ቱ የትግል ዓመታቱ 54ሺ ሰዎች መሞታቸውንና ከነዚህ 90 ከመቶ የሚሆኑት የገጠር ወጣቶች ናቸው። በገጽ 165 ።
2ኛ. “የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ እያፈሰሱ ህዝቡ ትግላቸውን እንደገድለ ሰማዕታት እንዲቀበለው አድርገው በሥልጣን ለመቆየትና ከሞቱም በኋላ ዘለዓላማዊ ክብርና ዝና ለማግኘት መሞክሩን ተያዘውታል። ይህን የህዝብና የሰማዕታት የተጋድሎ ታሪክ ጠቅልለው ለአንድ ሰው ለማሸከም ይሞክራሉ። ሰውየው ከሰውነት አልፎ እንዲመለክ ለማድረግ ይሞክራሉ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉትም በአሁኑና በወደፊቱ ተግባሮቻቸው ከመኖር ይልቅ ባለፈው ታሪክ መኖሩ ለሥልጣናቸው ህልውና ጠቃሚ ሆኖ ስላገኙት ነው።(ገጽ 4)
3ኛ. እጅግ የሚያናድደኝ ይህ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው የዘመነ ምኒልክ የጎፌሬዎች ቀረቶና ሸለላ ነው።- ስብሀት ነጋ ገጽ 303
4ኛ. የደርግ ሠራዊት አባላት በግለሰብ ደረጃ እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በጥቅም ላይ የሚያውሉበትና አዲስ በተደራጀው ሠራዊት ውስጥ በአባልነት የሚቀጥሉበት ሁኔታ ቢመቻች ኖሮ ከፖለቲካው አንጻር ይፈለግ የነበረውን የብሔር ብሄረሰብ ስብጥር ከማሟላትም ሌላ የረጅም ጊዜ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን አገራዊ ሠራዊት ለመገንባት ባዋሉት ነበር።222
5ኛ. አሁን ሳጤነው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነታችን ምክንያት የመረጃ ፍሰትን ገድበን የአገራችንን የአስተሳሰብ እድገት በመጎተታችንና በማጫጨታችን እጸጸታለሁ። ገጽ 249
6ኛ .. ኢህ አዴግ ተቃዋሚዎችን ለመድፈቅና ለማጥፋት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች የአመራር አባላቱንና ከፍተኛ ኃላፊዎችን መቆጣጠር። በጥቅም መግዛትና መደለለል ነው። በክፍያ መዝገብ ስማቸው የሠፈረ አሁን ድረስ ተቃዋሚዎች ነን እያሉ የሚንቀሳቀሱ የማውቃቸው አሉ። የነዚህ ሰዎች ተቀጣሪነት ያወቅኹት በኢሕአዴግ አመራር አባልነቴ ሳይሆን ቅርበት ከነበረኝ የደሐኀንነት አባላት ነውና አሁንም የነዚህን የማውቃቸውን ሰዎች ስም ላለመጥቀስ መርጫለሁ። 251
7ኛ. ኢሕአዴግ አማራው ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀስ ጠባቦች መጥተው ሊውጡህ ስለሆነ ከ እነርሱ የሚያድንህ ከኢህ አዴግ ጎን ተሰለፍ ብሎ ይቀሰቅሳል። በኦሮሚያ በትግራይና በሌሎች ክልሎች ደግሞ ትምክህተኞች ዳግም አንሰራርተው ሊውጡህ ነው ኢሕ አዴግን ካልተቀበልክና ካልደገፍክ መቀመቅ ትገባለህ እያለ በማስፈራራት ይቀሰቅሳል። ገጽ 199
8ኛ. የሓየሎም ሞት ገዳዩ ኤርትራዊ መሆኑን እያወሱ ከኤርትራ ከነበረው አለመግባባት ጋር ያያዙታል። ይህ ፍጹም ሊሆን አይችልም ብሎ ለማለትም ያዳግታል። 265
9ኛ. (ስለተባረሩ ኤርትራውያን) ጉቦ እየተሰጣቸው መባረር ያለባቸውን እያስቀሩና መባረር የሌለባቸውን ያባርሩ እንደነበር የሚባረሩት ንብረታቸውን ሲሸጡ ተደራጅተው ንብረቱን በርካሽ ይገዙ እንደነበር ኋላ ላይ ተጋልጧል።…እኛን ፀረ- ኤርትራውያንና ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ናቸው እያሉ ሲከሱን የነበሩ ቱባ ባለሥልጣኖች ሳይቀሩ ኤርትራውያን ሲባረሩ ቪላዎቻቸውንና የንግድ ድርጅቶቻቸውን ገዝተው እንደነበር ተራው ዜጋ ሳይቀር ያውቀዋል። ሆኖም የህወሃት/ኢህአዴግ አመራር በአንዱ ወይም በሌላው ከኤርትራውያን ጋር በተያያዘ ወንጀል ተዘፍቀው ስለነበር “በመስተዋት በተሠራ ቤት የሚኖር ሰው በድንጋይ አይጫወትም” እንዲሉ ምንም ማድረግ አልቻሉም። 281
እዚህ ላይ ይህን የአቶ ገብሩን አባባል ለመፈተሽ ያህል፣ የመደብ ትግልና ጭቆናን ለመቃወም ማልደው የተነሱ እንደ ኢሕአፓና መኢሶን የመሳሰሉት ሌሎች ድርጅቶች ቀድመው በተቋቋሙበት፣ በመላው ኢትዮጵያ ተማሪዎች ለለውጥ በተነሳሱበት ሁኔታ፣ የትግራይ ልጆች ለብቻቸው ተነጥለው በረሃ ግባታቸው፣
የመደብ ትግል ሳይሆን የብሔር ፖለቲካን ማራመዳቸውን ያመለክታል። ሁለቱን ማጣመር የሚቻል እንኳ ቢሆን ሁለቱንም ያጣመረ ፕሮግራም መቅረጽ አያቅታቸውም ነበር። ግን ጨወታው ወዲህ ይመስላል። ለማንኛውም ገብሩ ራሳቸው ድርጅቱ ከተቋቋመ አንድ ዓመት በኋላ የካቲት 1968 በአመራሩ ተረቆ የጸደቀውን ማኒፊስቶ ወይም መርሐ ግብር ሲጠቅሱት እንዲህ ብለዋል “ …የአብዮታዊው ትግል ዓላማ ከባላባታዊው ሥርዓትና ከኤምፔሪያሊዝም ነጻ የሆነ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ማቋቋም ይሆናል” (ገጽ 51) እዚህ ጋር ምንም እንኳ ይህ ትግራይን ለመገንጠል ያቀደ ማኒፌስቶ በአባላቱ ዘንድ ውዝግብ ፈጥሮ ከ6 ወራት በኋላ ቢለወጥም ይህን በአረቀቁት የአመራር አባላት ውስጥ የተቋጠረውን ችግር መገንዘብና መታዘብ ይቻላል። ይህን እንኳን ሌላው ሰው ገብሩ ራሳቸው በገጽ 98 እንደሚከተለው ታዝበውታል።“በዚሁ አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ድርጅቱን ይመራ የነበረው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባሰራጨው የፖለቲካ ፕሮግራም ያካተተውን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የማቋቋም ዓላማ አንስቶ አልተቸም።…ማን በፕሮግራሙ እንደካተተው የመለየትና ኃላፊነት የመውሰድ ድፍረቱም አልነበራቸውም….ሁሉም እኔ አልነበርኩበትም የሚል መግለጫ ሲሰጡ ይደመጣሉ።” ረቂቅ ፕሮግራሙን እንዲያዘጋጁ ድርጅቱ በወቅቱ መድቧቸው የነበሩት ሁለት ሰዎች ግን መለስ ዜናዊና አባይ ፀሐዬ መሆናቸውን ገብሩ ጽፈዋል። ይህን የማስተዋል ጥቅሙ፣ ነገር መደበቅ፣ መቅጠ ሽምጥጥ አድርጎ በግልም ሆነ በቡድን መካድ ገና ከማለዳው አብሯቸው ተወልዶ ያደገ ልማድ መሆኑን ነው። እንጂማ በፕሮግራም የተጻፈን ነገር ማን እንደጻፈው ማን እንዳዘጋጀው ሳያታወቅ ቀርቶ አይደለም። ከዚህ መጽሐፍና ከሌሎችም መረጃዎች በመነሳት ሕወሓት ማለት አመራሩ ዐይኑን በጨው አጥቦ የሚቀጥፍበት፣ አባላቱም ያዩትን እንዳላዩ ሆነው ማለፉን የተካኑበት ብሔርተኝነት ብቻ አቆራኝቷቸው ተቻችለው የሚኖሩበት
ድርጅት ነው ማለትም የሚቻልበት ሁኔታ ይታያል።
ትግራይ ባንዲራ ነበራት እንዴ?
አቶ ገብሩ ብዙ የተዋደቁለትን ድርጅት አመራሩንና ጓደኞቻቸውን ሲተቹ አንዳንዱን ማፍረጥ እንደፈሩት ቁስል ቀስ ብለው የሚነካኩት መሆኑ ቢያስታውቅም አንዳንዱን ግን ያለምህረት ይሉታል። ለምሳሌ ይህንን በመጽሐፋቸው ገጽ 100 ላይ የታዘቡትን የድርጅታቸውን ጉድና ትዝብት እንመልከት፣ “መጀመሪያ ባንዲራው ከመቀየሩ በፊት የህወሓት ባንዲራ ጥቁርና ቀይ ነበር። “ቀይ መስዋአትነት ቢጫ ተስፋ ኮከብ ዓለም አቀፋዊነት በመጀመሪያ ባንዲራው ለምን ጥቁር ቀለም ተካተተ የሚል ጥያቄ ሲቀርብም በደፈናው የድሮው ትግራይ ባንዲራ ያን ይመስል ስለነበር ነው። የሚል መልስ ይሰጥ ነበር። ኖም ተሓህት/ህወሓት ይል ከነበረው ውጭ በታሪክ ትግራይ የራሷ ባንዲራ ነበራት የሚል ማረጋገጫ አላገኘሁም።” ብለዋል። መቸም አቶ ገብሩ ያላገኙትን አንባቢዎችስ ብንሆን ከየት እናመጣዋለን!ሉዓላዊነት በሶማልያም በኩል ነበር! አቶ ገብሩ ትሑት መሆናቸው ንግግራቸውንም ትችታቸውንም በወጉ ማድረጋቸው ያስመሰግናቸዋል። አንዳንዴ አፍታተው ወይም ጠበቅ አድርገው ሀሰቱን ሀሰት እውነቱን እውነት ቢሉ ከዚያም ርቀው ምነው አንዳንድ ነገሮች ማለት በቻሉ ያሰኛል ። ብዙ ማስረጃ እየደረደሩ የሞገቱትን ሐቅ እንኳ ደፍረው እንዲህ ነው ብለው አይቋጩትም። እያደር ህብረ ብሄራዊና ለሉዓላዊነቱ የሚቆረቆር ድርጅት እየመሰለ መምጣቱን መግለጽ የሚፈለገው ድርጅታቸው በሶማልያ ወረራ ጊዜ እንደሌሎቹ ወረራውን ማውገዝ ብቻ ይሆን ከደርግ መንግሥት ጋር ተሰልፎ ለእናት አገሩ ለመዋጋት ሀሳብ የነበረው መሆኑ እንዲመዘገብለትና የክህደት ታሪኩ እንዲፋቅለት ሲጥር መኖሩ ይታወቃል። ይህን በጨርፍታ አንስተው የተቹት አቶ ገብሩ የአቶ ስብሐት ነጋን አንዲት አብነት አንስተው እንደሚከለተው ጽፈዋል፦
“የድርጅቱ ሊቀመንበር ስብሐት ነጋ ሶማልያ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ስትሰነዝር ከደርግ ጋር በመሆን ጥቃቱን ለመመከት ሓሳብ አድርገን ነበር ቢልም በድርጅቱ ታቅፎ የነበረው አባል ሁሉ ይህን ዓይነት ጥሪ እንደተደረገ ፍጹም አያስታውስም። አባባሉም በሰነድ ሊደገፍ የሚችል አይደለም። ያ ቢሆን ኖሮ የተቃወሙትንና የመስፋፋት ፖሊሲውን ያደናቅፋሉ ያላቸውን የኦሮሞ ተወላጆች ያሰረውና የገደለው ዚያድ ባሬ ተሓህት/ህወሓት በሞቃዲሾ ተወካይ ኖሮት እንዲንቀሳቀስ ባልፈቀደ ነበር። የሶማልያ የይለፍ ፓስፖርት ለተሓህት/ህወሃት ባለሥልጣናት አባላት ባልሰጠ ነበር። ለተሓህት/ህወሃትን በጦር መሣሪያ ባላስታጠቀ ነበር። 93 እንዲያውም ገብሩ ይህኑ የሚያጠናክር መረጃ በሌላኛው ገጽ 117 ላይ ሰጥተዋል። “ የህወሃት ፖለቲ ቢሮው እኔና አው አውሎም ወደ ኤርትራ ሳህል ሄደን ..የሶማልያ መንግሥት የሰጠንንና በሻዕቢያ በኩል ተጓጉዞ እንዲደርሰን የተስማማንበትን ከ3ሺ በላይ ክላሺንኮቭና ሲሞኖቭ ጠመንጃዎች ከነመሰል ጥይቶቻቸው የመረከብ…ተልእኮም ሰጥቶን ነበር” እያሉ ጽፈዋል። ስለዚህ ድርጅታቸው የአገር ሉዓላዊነት ሊያሳስበው ቀርቶ ከወራሪው ኃይል ጋር ተስማምቶ መሣሪያ እስከመታጠቅ መድረሱን አጋልጠዋል። ይሁን እንጂ ሉዓላዊነትን በኤርትራ ብቻ ሳይሆን በሶማልያም በኩል አያይዘው ቢያነሱትና ቢያሰፉት መልካም ነበር። ለወረራውም ቢሆንኮ ኤርትራ እናት አገሯን ከእናት አገሯም ትግራይን ነው የወረረችው ሶማሌን ግን ጎረቤቷን ነው የወረረችው ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ወይንም አለን።
ኤርትራን እናስተኛት!?
ከገብሩ መጽሀፍ የሉዓላዊነት ፍሬነገሮች ሁለቱን ዋና ዋና ነገሮች አውጥተን ብንመለከት አንደኛው ቁጭታቸው ሌላኛው ስጋታቸው ነው። ስለተቆጩበት እንዲህ ይላሉ-፤ “ከሁሉም በላይ የሚከነክነው በወቅቱ ኢትዮጵያ በዓሰብ ላይ የነበራትን የባለቤትነት መብት ያመለምንም ድርድር ለሻዕቢያ አሳልፋ መስጠቷና በታሪክ ትልቅ ጥቁር ነጥብ መጣሉ ነው። ከ30 ዓመት በላይ የህዝቦችን ደም ያፋሳሰሰው ጦርነት በሰላም መፈታቱ ተገቢ ቢሆንም የኢትዮጵያ ጥቅሞች ሳይከበሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአንድ ኮንፈረንስ ለኤርትራ ነጻነት ሕጋዊ እውቅና መስጠቱ ግን ከፍተኛ ስህተት ነበር። የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች
ከዚህ ስህተት ተጠያቂነት ሊያመልጡ ባይችሉም ዋናው ተጠያቂ ግን ውሳኔውን የቀየሰውና ተቀብይነት እንዲያገኝ ቁልፍ ሚና የተጫወተው የህወሓት/ኢሕአዴግ አመራር ነው። (ገጽ 184)ስጋታቸው ደግሞ የኤርትራ መንግሥት መቸም አይተኛልንም የሚል ነው። “ ..እንደኔ አመለካከት በኢሳያስ የሚመራው
የሻዕቢያ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመውረር ያነሳሳውን በአካባቢው የኢኮኖሚ፣ የወታደራዊና የዲፕሎማስያዊ የበላይነት የመጎናጸፍ ፍላጎት እስካሁና አልጠፋም።..ኢትዮጵያን በማዳከምና በመበታተን በአካባቢው የበላይ የሚሆንበትን ስትራቴጂ ቀይሶ በመንቀሳቀስ ከትግራይ ጀምሮ እስከ ኦጋዴን ትግል እያካሄድን ነው ብለው ለሚያምኑ….መጠጊያ ሆኖ ሥልጠናና ትጥቅ በመስጠት ኢትዮጵያን ለማተራመስ እየሠራ ነው፡፡ (ገጽ 427)
እነዚህን የአቶ ገብሩ ሁለት ቁጭትና ስጋት ፈጣሪ ነገሮችን ብንመለከት። አንደኛ የፈሰሰ የቀይ ባህር ውሃ አይታፈስም። ጥፋተኞችን ለፍርድ ማቅረብም ቢሆን አገርና ዘመን ላይ አይፈረድም። በታሪክ ተጠያቂ የሚባለውም ነገር ታሪክ ማንን ጠይቆ እንዳፋጠጠ ስላማናውቅ ብዙ አንራቀቅበትም። እንኳን ሊያፋጥጣቸው ይኸው ታሪክ ሰሪዎቹ በቁማቸው መጽሀፍ እየጻፉ በቁማችን ያስነበቡናል። ኤርትራ ትወረናለች አትተኛልንም ማለቱም ጥሩ ስጋት ነው። ታዲያ እንድትተኛልን ምን ማድረግ ይበጃል? ኤርትራ ኢትዮጵያን መጥላት ትታ ራሷን ብቻ ብትወድ ኖሮ ይኼኔ የት በደረሰች ብሎ መምከር ይቻል ይሆናል። ግን ትግሬ ለአማራው፣ አማራው ለትግሬ፣ ኦሮሞው ለአማራ፣ አማራው ለኦሮሞው፣ እስካልተኙ ድረስ እኛም ለኤርትራ ኤርትራም ለኛ ትተኛለች ብሎ መጠበቅ አይሆንልንም። መቸም በዚሁ ገመድ ሲጠላለፉና ሲገዳደሉ የኖሩት ምሁራኑ ፖለቲከኞቻችን ይህን አፍታተው የሚያውቁት ጉዳይ ሊሆን
ይችላል። ይልቁንስ መበላላት የትም ካልቀረ ኤርትራውያን ተመልሰው መጥተው እዚሁ ከኛው ጋር እየተበላሉ ቢኖሩ ይሻላቸዋል ብሎ ከመቀለድ ጋር ቁጭት የሚፈውሰውን ስጋት የሚያስቀረውን ዘለቄታዊ መፍትሔ ማሰቡና ስለሱ መጻፉ ይበጃል።
የአቶ ገብሩ መጽሀፍ ጉልበቱ አንባቢን እስከዚህ ድረስ በሀሳብ መንዳቱ ነው። የሚያሳስበው ትልቁ ነገር የኤርትራ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ ሆኖ ይዝለቅ ወይስ እዚያው እየተገፋ ከባህር ይጥለቅ የሚለው ጥያቄ ነው። ቀኝ እጁ ኢትዮጵያዊ ግራ እጁ ኤርትራዊ እየሆነበት ግራ የተጋባ ትውልድ፣ አንዴ እንጣበቅ አንዴ እንላቀቅ፣ ከሚል ማለቂያ አልባ ፍልሚያ የሚገላገልበት መካሪ መጽሀፍ ማስፈለጉን የገብሩ መጽሐፍ ሹክ ይላል። ካለበለዚያ መሬት ወንበር የሆነ ይመስል እስኪ እሱን የተቀመጥክበትን መሬት አቀበልኝ አይባልም። ስለዚህ ይህን ችግር አሰብ፣ ወደብ፣ ባድመ፣ ሉዓላዊነት፣ የሚል ጥያቄ ብቻውን አይፈታውም። ከወንድማማቾች ጋር ዘላቂ ሰላም የሚመጣው፣ መሬት በመተሳሰብ ሳይሆን፣ እርስ በርስ በመተሳሰብ ነው። እሱን ደግሞ ስላቃተን ነው ወንድም ወንድሙን ወግቶ ድል ሊነሳ በረሃ የሚወርደው። በእነ አቶ ገብሩ መጽሐፍ የሚታየውም ይኸው ነው። ማንኛቸው ኢትዮጵያዊ ማንኛቸው ኤርትራዊ መሆናቸውን መለየት እስኪያቅታቸው ድረስ እንደቆቅ ሲጠባበቁና ሲተናነቁ ኖረው መጨረሻቸውና መጨረሻችን እንዲህ ሆኖ ቀርቷል። አቶ ገብሩ እንደሚነግሩን በድርጅታቸው ህወሃት የትግል ዘመን የሞቱት የትግራይ ልጆች ብዛት ወደ 54ሺ ይጠጋል። ይሄ ቁጥር ባንድ ሰሞኑ የባድመ ጦርነት ብቻ ካለቁት 70 እና 80ሺ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲተያይ በራሱ የሚናገረው ነገር ይኖረዋል። የሚሰማው ከተገኘ! ለማንኛውም አቶ ገበሩ የድንበር ማካለልንና የአልጀርስ ስምምነትን አለመቀበልንና ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን የምታረጋግጥበትን መንገድ የመሻት አስፈላጊነትን በመፍትሔነት ከዘረዘሯቸው ሀሳቦች ውስጥ ይካተታሉ። ይህ ሁሉ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በዚሁ ይቀራል ኤርትራም እንደወጣች ትቀራለች፣ ወይም እንደ አንዳንዶቹም የታባቷንስና በዚያው መቅረት አለባት ከሚል ስጋትና ፍላጎት የመነጨ ይመስላል። ያም ሆኖ ግን ገብሩ ምንም እንኳ ትልቁ ተስፋ ሰጪ ነገር አድርገው ባያጎሉትም በገጽ 478 ላይ በመፍትሄነት ከዘረዘሯቸውና በመጨረሻውና በ4ኛ ደረጃ ባሰፈሩት ላይ፣ “ሁለቱ አገሮች የላቀ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትስስር ለማድረግ ከተስማሙ፣ ህዝቡን በስፋት ያሳተፈና የቆየውን ባላንጣነት የሚያስወግድ ግንኙነት እንዲመሠርቱ ህዝቦቻቸው በነጻ የሚገናኙበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት” ብለዋል። የህዝብ ለህዝቡ ግኑኝነት መሻሻል (ኖርማይላዜሽን) በሰከነ መርሃ ግብር ተደግፎ ወደላቀ ትስስር ለማምራት በር ከፋች መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። በአቶ መለስ ወገኖችና በእነ አቶ ገብሩ ወገኖች በኩል የነበረው አንዱ ፈተና ይሄን የህዝብ ለህዝብ ሚዛን የመጠበቅ ችግር መሆኑንም ከጠቅላላው የአቶ ገብሩ መጽሀፍ ይዘት መረዳት ይቻላል። ሻዕቢያና ወያኔ ተብለው ትግራይ ትግሪኝ ሆነው አብረው ለአንድ ዓላማ ለሞቱት ሰዎች ቀላል ያልሆነው ኖርማላይዜሽን ለሌላው ሊከብድ መቻሉንም ከመመርመር ጋር፣ ይህን ሀሳብ ከመደገፍ የተሻለ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስልም። በመጽሐፍ የተዘረዘሩት ሌሉቹ የአቶ ገበሩ አማራጮችም ከዚህኛው ጋር ባይሻሙ ይሻላቸው ነበር።
ወያኔን አትናገሩ ህወሓትን ግን እንደፈለጋችሁ!
ማለት የፈለጉትን አይበሉት ወይም ካሉት በላይ አይግለጹት እንጂ አቶ ገብሩ አስራት በተዋቃሚው ጎራ የሚታመሙበት አባባል ያላቸው ይመስላል። የምርጫ 97ን ወቅት እያሰቡ እንዲህ ጽፈዋል “የወቅቱ ተቃዋሚዎች የትግራይን ህዝብና ህወሓትን ያለመየት ችግር የሚጀምረው ከህወሓት ስያሜያቸው ነበር። ምንም እንኳን ህወሃት “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ተብሎ ቢጠራም ተቃዋሚዎች ህወሃትን የሚጠሩት ወያኔ ብለው ነበር። ወያኔና ህወሃት አንድ አይደሉም። ወያኔ በትግራይ ህዝብ ሥነ-ልቦና ከፍተኛ ቦታ ያለው የአልገዛምና የእምቢተኝነት መገለጫ ነው። ህወሓትም ይህን ስያሜ የመረጠው የህዝቡን የቆየ ሥነ-ልቦና ለማጋራት ነው።” ወረድ ብለውም “ኢህአዴግ ራሱ በፈጠረውና አንዳንድ ተቃዋሚዎችም ባስተጋቡት የፍርሃት ድባብ ምክንያት ብዙ የትግራይ ተወላጆች በገዛ አገራቸው በስጋት እንዲኖሩና አማራጭ አጥተው የኢህአዴግን ከለላ እንዲሹ አድርጓቸዋል። ለህወሓት/ኢህአዴግ አንዱ የሥልጣን መሠረት
የሆነውም የእነዚህ በስጋት የተዋጡ ዜጎች ሥነ-ልቦና ነው።” (ገጽ 436)አቶ ገብሩ ይህን ይበሉ እንጂ በድርጅታቸውም በኩል ያለውንም የተጠያቂነት ችግርና ድርሻ አልዘነጉትም። ምክንያቱም ቀደም ሲል በመጽሐፋቸው በገጽ 140 ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል “ የጠባብነት ጥያቄ ከተነሳ መጠየቅ የነበረበት
ከጅምሩ ብሔራዊ (ትግራዊነት?) ስሜትን ከአገራዊ አንድነትና ስሜት በላይ በማስጮኽ ይቀሰቀስ የነበረው አመራሩ ነበር። ድርጅቱ (ህወሃት) ከሌሎች አገር አቀፍና ብሔር ተኮር ድርጅቶችጋ ያደረገው ትስስር ደካማ ነበር። እንዲያውም ከመሸ በኋላ ከኢሕዴን ጋር ከፈጠረው ግንባር ውጪ፣ ለአስራ ሶስት ዓመታት ያህል በብሄር ተደራጅቶ በተናጠል የተጓዘበት ሁኔታ ነበር። የላብ አደሩ ፓርቲ ሲመሰረት እንኳን ብሔር ተኮር መልክ ይዞ (ትግራይ ብቻ ሆኖ?) እንዲደራጅ ተደርጓል፡፤ እነዚህ በአመራሩ የተቀየሱ ዓላማዎች አደረጃጀቶችና የትግል ስልቶች በታጋዩ ሥነ-ልቦናና አስተሳሰብ ላይ ተጽእኖ ነበራቸው። የታጋዩ አስተሳሰብ ቅድሚያ ተሰጥቶት የተገነባበት አቅጣጫ በብሔራዊ ወይም ክልላዊ ማንነቱ እንጂ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ዙሪያ አልነበረም። በአጠቃላይ የተከተልነው የትግል ስልት ዋና ማጠንጠኛም ብሄራዊ እንጂ አገራዊ ወይም መደባዊ አልነበረም” በወዲያና ወዲህኞቻችን ምህረት አልባ ነቀፋ አጣብቂኝ ውስጥ ያሉት ገብሩ ይህን ሲሉ በፍጹም ቅንነት የተናገሩት መሆኑን ያለጥርጥር መገመት ይቻላል። አቶ ገብሩ በዚህ መጽሐፋቸው ያወቁትን ሁሉ ተናግረዋል ማለቱ ጨርሶ የማይታሰብ ቢሆንም ሆን ብለው ያጣመሙት ነገር አለ ብሎ ለማሰብም ይቸግራል። የሚያግባባ ነገር ላይጽፉ ይችላሉ የጻፉት ግን ያመኑበትን ነው ብሎ ማሰቡን መጽሐፋቸው አይከለክልም።
ሉዓላዊነት እና ባለማህተቡ ኢህአፓ
ምንም እንኳ የድርሻቸውን ያህል ስህተትና ተጠያቂነትን የሚጋሩ ቢሆንም፣ ምንም እንኳ አብረዋቸው በእምነት ተሳፍረው እንድ ዓለም ሰፍተው እንደመንደር ጠበው፣ በክህደት የተንጠባጠቡ ቢኖሩባቸውም፣ ምንም እንኳ የእድሜና የርዕዮተ ዓለም ለጋነት እናም የዋህነት ለቅጽበት አሳስቶ የፈጃቸው ቢመስልም፣ በእናት አገር ኢትዮጵያ ፍቅር ግን ስተው ያልተገኙት የኢህአፓ ልጆች ታሪክ እያደር ይፈካል። እንደ ስልባቦት ከላያቸው የሚገፈፈው ስህተታቸው ሲነሳ እንደ ወተት የነጣው የልጅነት ልባቸው ወከክ ብሎ ይታያል። ያን ጊዜ ገድላቸው እንኳን በወዳጆቻቸው የኛ ልጆች አይደላችሁም ብለው በፈጇቸው ጠላቶቻቸው አንደበት ጭምር ይመሰከርላቸዋል። ኢህአፓዎች ሥርዓትን እንጂ አገራቸውን አለመክሰሳቸው ለሌሎች ሁሉ እንጂ ለራሳቸው ወገን ብቻ ያልሞቱ የማንነት ስግብግቦች አለመሆናቸውን እነሆ ታሪክ ይናገርላቸዋል። በገዛ ግዛቱ እንደ ውጭ ጠላት እያሳደደ በወጋቸው፣ በቀድሞው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ድርጅት፣ ፖሊት ቢሮ አባልና አንጋፋ ታጋይ አቶ ገበሩ አስራት ብዕር ሳይቀር እንደሚከተለው ተመስክሮላቸዋል!“ኢህአፓ በአብዛኛው የመኻል አገር ከተሞች በምሁራንና በወጣቶች ከፍተኛ ድጋፍ የነበረው ፓርቲ ቢሆንም በብሔር ድርጅቶች ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። በተለይ ተሓትና ኦነግ የብሔር ብሔረሰብ አቋሞቹን በተመለከት በጥርጣሬ ይመለከቱት ነበር። …..ኢህአፓ በመርህ በደረጃ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እስከመገንጠል ተቀብሎ ከብሔሮች ትግል ይልቅ ለመደባዊ ትግል ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል በማለቱና በኤርትራ ጥያቄ ቁርጥ ያለ አቋም ባለመውሰዱ በአንዳንድ ብሔር ተኮር ድርጅቶች በተለይ ደግሞ በተሓትና በሻዕቢያ የታላቋ ኢትዮጵያ (ግሬተር ኢትዮጵያ) አቀንቃኝ ወይም የንኡስ ከበርቴ ትምክህተኛ ፓርቲ የሚል ስም አሰጥቶታል። (አረጋዊ በርሔም በመጽሐፋቸው ገጽ 119 ያሉትን መጥቀሳቸውን ጠቅሰዋል)ገጽ 53። “ኢህአፓ በፕሮግራሙ ውስጥ የኤርትራ ጥያቄ በሰለማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ከመግለጹም በላይ በዲሞክራሲያ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ከሰላማዊ ድርድር ውጭ ሌላ መፍትሔ ማፈላለግ እልቂት እንጂ ሌላ ውጤት እንደማይኖረው በተደጋጋሚ ይገልጽ ነበር። ይህ የኢህአፓ አቋም የኤርትራን ድርጅቶች የሚያረካ አልነበረም። የኤርትራ ድርጅቶች
ኢሕአፓ በሁለት ጉዳዩች ላይ ጠንከር ያለ አቋም እንዲኖረው ይፈልጉ ነበር። አንደኛው አቋም የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት መሆኑንና ቅኝ ገዢዋም ኢትዮጵያ እንደሆነች መቀበል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጥያቄው በኤርትራ ነጻነት መፈታት እንዳለበት መቀበል ነበር። እነዚህ ሁለት አቋሞች ከኢህአፓ ሊገኙ ባለመቻላቸው የኤርትራ ድርጅቶች በኢሕአፓ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬና ጥላቻ ነበራቸው። የኢህአፓ አቋም ባይዋጥላቸውም ኢህአፓ ደርግን ከማዳከም አንጻር ሊኖረው ከሚችለው አስተዋጽ ኦንጻር ድጋፋቸውን ይሰጡት ነበር። (ገጽ 54)
ሻእቢያዎቹ ይሰጡ ነበር የተባለውም ድጋፍ ወዲያ ተቋርጦ እንዲያውም ህወሃት ኢሕአፓን ወግቶ ሲያጠፋው እንደ ገብሩ አገላለጽ “ ሻዕቢያ አስተያየት ባለመስጠት የዝምታ ድጋፉን ሰጥትቶታል። ኢሕአፓ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ነው አፈታቱም በነጻነት መሆን አለበት፣ ብሎ ቁርጥ ያለ አቋም ባለመውሰዱ እሳት ሲጎርስ በአንጻሩ የሚፈልገውን አቋም ለወሰደው ህወሓት በመሪዎቹ በእነ ሮመዳን መሐመድ ኑርና በኢሳያስ አፈወርቂ አማካይነት ከፍተኛ ምስጋና ችረውታል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከኢሕአፓ ይልቅ ከህወሓት ጋር የተሻለ ግንኙነት ነበራቸው። (ገጽ 105) የኢህአፓ የወቅቱ ተቀናቃኝና የፖለቲካ ባላንጣ እንደነበረ የሚነገረው መኢሶን አመራር የነበሩት ዶ/ር ነገደ ጎበዜም በበኩላቸው በአዲሱ መጽሐፋቸው “ኢህአፓን ጨምሮ የየካቲት ሃይሎች እንደንጉሱ ዘመን አንዱን ወገን ብቻ እያወገዙ ከመቀጠልይልቅ የሁለቱምተጠያቂነትብቻ ሳይሆን የኤርትራ ግንባሮች በጠባብ አጀንዳ ተሰማርተው ከኤርትራም ከኢትዮጵያም ህዝቦች የጋራ ጠላቶች ጎን መሰለፋቸውን” ወደ ማውገዝ ተሸጋግረዋል ሲሉ የወቅቱን ሁኔታ ጽፈዋል። ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም መንግስታቸውንና ሥርዓቱን ለመቃወም ሲሉ የውጭ መንግሥታትን እርዳታ ይሹ ይሆናል። በ ኢትዮጵያዊነታቸው ግን አይደራደሩም። ሉዓላዊነት ማለት
እሱ ማለት ከሆነ በጣልያንም በሶማሌም በሻዕቢያም ዘመን ኢትዮጵያውያን ሲያከብሩትና ሲሞቱለት የኖሩት ጉዳይ ነው።
አሳሩ ገና ነው! መቸም እኛ ከገብሩ አናውቅም
የህወሃት ሰዎችም ደጋፊዎችም በኤርትራ ጥያቄና ወዳጅነት ላይ ሌላውን ሲከሱም ሆነ ሲወቅሱ ሲደመጥ መኖራቸው ይታወቃል። እሱስ ይቅር መቸም ፖለቲካቸው እንደሱ ነው። ወቀሳቸው ግን ኤርትራውያንን በፀረ ኤርትራዊነት እስከመክሰስ ከሄደ ምን ይባላል? ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ የሚለው የአቶ ገብሩ አስራት መጽሐፍ ከገጽ 125 እስከ 126 ያስፈረውን አንዲት አንቀጽ ቀንጭበን እንመልከት! በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኤርትራ ድርጅቶች ከደርግ ጋር ሊደራደሩ ነው የሚል ጭምጭምታ በተሰማበት ወቅት ህወሃቶች እጅግ ተናደን ነበር። በአንድ በኩል ሻዕቢያ ተስፋ ቆርጦ ትግሉን አቋርጦ
እጁን ለደርግ ሊሰጥ ነው የሚል ስጋት ነበር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሻዕቢያ በኤርትራ ነጻነት ጉዳይ ላይ ከደርግ ጋር ሊደራደር ነው የሚል ስጋት ነበር። ሁለተኛው ስጋት አግባብ አልነበረም፡፡ …ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው እንዲሉ ባለቤቶቹ ችግራችንን በአንድነት ማዕቀፍ እንፈታለን ሲሉ፣ እኛ የለም ይህን መሆን የለበትም ብንል፣ የድርጅቶቹን ነጻነት ከመጻረራችን ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ጥቅም እየጎዳን እንደነበር አልተገነዘብነውም ነበር። ከዚህ በመነሳት ሻዕቢያ ከደርግ ጋር ሊደራደር ነው የሚለውን ወሬ ስንሰማ ሻዕቢያን በተምበርካኪነት ፈርጀን መክሰስ ጀመርን። የኤርትራ ነጻነት እርግፍ አድርጎ ትቶ ከደርግ ጋር ሊታረቅ እንደሚችል ገመትን። የደርግና የሻዕቢያ ጌቶችም ሶቭዬቶች ስለሆኑ ሊያስታርቋቸው ይችላሉ የሚል ግምት ስለነበረንም ስለ ኤርትራ የምንጽፋቸው ጽሑፎችና የምናወጣቸው መግለጫዎች ሁሉ የኤርትራ ህዝብ ከነጻነት ባሻገር ሌላ መፍትሔው እንዳይቀበል የሚሰብኩ ነበሩ። እንዲያውም አንዳንድ የምናወጣቸው ጽሑፎች ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከኤርትራ ድርጅት የመነጩ ይመስሉ ነበር።
ህወሓት ኤርትራን በተመለከት ካቀረባቸው ጽሑፎች አንዱ “ብረት ህዝቢ ኤርትራ ቁልቁል አፉ አይድፋእን!” “የኤርትራ ጠመንጃ አፈሙዝ ቁልቁል አይዘቀዘቅም!” በሚል ርዕስ የተጻፈው ነበር። ይህ በመለስ ዜናዊ የተጻፈው ጽሑፍ ምሁሩና አርቆ አሳቢው ኤርትራዊው ተስፋ ጽዮን መድኃኔ ለጻፈው የተሰጠ ምላሽ ነበር፡፡…ባለቤቶቹ ጉዳዩ ሳያሳስባቸው ህወሃት ተቆርቋሪ ሆኖ መቅረቡ ያስገርማል። ኤርትራዊ ስለ አንድነትን ሲጽፍ አንድነትም ለሁለቱም ህዝቦች የሚጠቅም ሆኖ ሳለ፤ መገንጠልን ደግፈን ያን ያህል ርቀን መሄድ ባልንበረብን ጉዳዩም ይበልጥ ለኤርትራውያን መተው ነበረብን። 126 አቶ ገብሩ በመጽሀፋቸው ከቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው ያለ ይቅርታ የሚወቅሷቸውና አውራ ተጠያቂ የሚያደርጓቸው ሟቹን አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ስብሐት ነጋን ነው። በተለይ እጅጉን በተማረሩበትና የመጽሐፋቸውም ርዕስና ማጠንጠኛ ያደረጉት የኤርትራ ጥያቄና የሉዓላዊነት ጉዳይ ዋነኛ ተጠያቂዎቹ እነዚህ ሁለት ሰዎች
ናቸው። አቶ ሥዩም መስፍን፣ ብረሃነ ገ/ክርስቶስ ኤታማዦር ሹሙ ሳሞራ የኑስ፣ ሟቹ የቀድሞ ደህንነት ሹሙ አቶ ክንፈ ገመድህንና የአሁኑ ደህንነት ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ እንዲሁም የአቶ መለስ አማካሪ የነበሩ አቶ ሙልጌታ ዓለምሰገድን በተለያዩ ጊዜያት ኤርትራን አስመልክቶ በወሰዷቸው አቋሞቻቸውና ባሳዩት ተባባሪነት ታሪክ እንዲወቅሳቸው ያጠቆሯቸው ይመስላል። የስብሀትና የአቶ መለስ ግን የተለየ ነው።
ሻዕቢያዎቹ ከህወሓቶች ሁሉ አጥብቀው የሚወዷቸውና የሚያምኗቸው አቶ ስብሐት ነጋን መሆኑን ገብሩ ጽፈዋል። እንዲያውም ባንድ ወቅት ኢሳያስ ሞቅ ብሏቸው “ ስብሐት ነጋ ስልጣኑን ሳይለቅ አጥብቆ ቢሄድ ኖሮ የሻዕቢያና በሕወሃት መካከል አለመግባባት እንደማይፈጠር “መናገራቸውን በገጽ 223 ጽፈዋል። ስብሐት “ ከድርጅቱ የጸጥታ ክፍል /ሐለዋ ወያነ/ ጋር በመሆን ቀውስ ፈጣሪዎች በተባሉት ላይ የምርመራና የማጣራት ሥራ ሲያካሂድና አብዛኛውን ጊዜ የቅጣት ውሳኔ ሲሰጥ የነበረ የአመራር አባል ነበር።101” ያሉት ገብሩ ስብሐት በዚያ ልምዳቸው የተነሳ የራሳቸውን ሥልጣን ሲክቡና ሰዎቻቸውን ቦታ ቦታ ሲያዙ መኖራቸውን ይገልጻሉ። የኤርትራን ጉዳይን በሚመለከትም ስብሐት በገዛ ፍቃዳቸው መሬት አሳልፎ ይሰጡ እንደነበር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል። “በ1990 ዓም ግጭቶች የተኪያዱባቸውን አንዳንድ የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ስብሐት ነጋ በሊቀመንበርነት ሥልጣኑ ከህዝቡ ፍላጎት ውጭ ከ1974 እስከ 1976 ባለው ጊዜ ለሻዕቢያ የሸለማቸው ነበሩ። ስብሓት መንደሮቹን ለሻዕቢያ አሳልፎ ሲሰጥ ከህወሃት የህዝብ አደረጃጀት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም ማዕከላዊ ኮሚቴው ግን ለጉዳዩ እምብዛም ትኩረት አልሰጠውም ነበር።” 109አይ መለስ ዜናዊአቶ ገብሩ በጣም ሚወቅሷቸውን አቶ መለስ ዜናዊን ደግሞ እንዲህ ገልጸዋቸዋል “መለስ በወታደራዊና በሕዝብ አደረጃጀት እንቅስቃሴዎች ይህ ነው የሚባል ሚና ባይጫወትም ታጋዮችን በመቀስቀስና በመስበክ ጽሑፎችን ቶሎ በማንበብና በመጻፍ ረገድ ከፍተኛ ችሎታ ነበረው። ዐልፎ ዐልፎም ድንጋይ ዳቦ ነው ብሎ እስከማሳመን ይደርስ ነበር። አብዛኛው ገበሬና ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ የነበረው የድርጅቱ አባል በመለስ የስብከት ችሎታ እጅግ ይገረም ነበር። ይህ በአብዛኛው የድርጅቱ አባላት ተሰሚነት እንዲያገኝ ረድቶታትል፡፤ በ1969 ዓም ከጦርነት አፈግፍጓል ተብሎ በደረሰበት ብርቱ ሂስ ሞራሉ ዝቅ ብሎ የነበረውም መለስ ከሁለተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በኋላ ሲያንሰራራና የሐሳብ መሪነት ለመጨበጥ ሙከራ ሲያደርግ ታይቷል።113ሌሎች አቶ መለስን እንዴት እንደሚያይዋቸው ሲጽፉም “አረጋዊ በርሄና ግደይ ዘርአ ፅዮን መለስን ጽናት እንደሌለው ከመጠን በላይ ተናጋሪና ተግባር ላይ እንደማይገኝ ታጋይ ያዩት ነበር114” ብለዋል። ይሁን እንጂ አቶ መለስ ዜናዊ ገና ከጧቱ በሥራ አጋጣሚ ከተቀራረቧቸው “እነ ተወልደ ወ/ማርያምን ስዬ አብርሃን፣ ክንፈ ገ/መድህን ሳሞራ የኑስ ጋር የጠበቀ ዝምድና መስረታቸውንና ወደ ሥልጣን መፈናጠጣቸውን ጽፈዋል።
በመለስ ተወጥረው በተያዙበት የኢትዮ-ኤርትራ አንድ ስብሰባ ላይ የቀድሞ አቋማቸውን ሽምጥጥ አድርገው ሲክዱ አቶ ስዬ ንዴታቸውን መቆጣጠር ያቅታቸዋል ። በቃለ ጉባኤ የተያዘ ነገር እንዴት ይክዳሉ? መለስ ይቺን አጥተዋት አይደለም። ገብሩ እንዲህ ጽፈውታል- ስዬ “መለስ የቀድሞ ሐሳቡን
ለውጦ ሌላ ሐሳብ እያቀረበ እያጭበረበረ ነው፣ ይህ አኪያሄዱ ትክክል አይደለም፣ የአቋም መንሸራተቱን ለማረጋገጥ በቃለ ጉባኤው የሰፈረው ይታይልኝ ብሎ አለ። ….ቃለ ጉባኤው ቢታይ በአግባቡ ያልተመዘገበ ሆኖ ተገኘ። ምክንያቱም ቃለ ጉባኤ ያዡ በረከት ስለነበር አልመዘገበውም።” (ገጽ 340) መለስ ምናቸው ሞኝ ነው። እነ በረከትን ቃለ ጉባኤ እያስያዙ ካልሆነ እነዚህን ሰዎች የት ይችሏቸዋል። መቸም ተንኮለኛ ናቸው ። ተቃናቃኛቸው ስዬን በልማት ስም ከመከላከያ ሚኒስትርነት አንስተው የኤፍረት ስራ አስኪያጅ ሲያደርጓቸው ማዕከላዊ ኮሚቴ ብዙም ያላስታውለው ጉዳይ ነበር ይላል
የገብሩ መጽሐፍ። ለነገሩ ስመ ገናና የመሰሉት ስዬም ከዚህ ተነስተህ እዚያ ሂድ ከዚያ ወደዚህ ና ሲባሉ ዝምብለው የሚሽከርከሩ ኖረዋል እንዴ ያስብላል።መለስ ግምገማና ስብሰባ የሚወዱትን ጓደኞቻቸውን በስብሰባ እያጠመዱ እሳቸው በጎን ሥራቸውን ይሠሩ ነበር። ይህም ሌላው ጮሌነታቸው ነበር “ የሥራ አስፈጻሚውንና ማዕከላዊ ኮሚቴውን በማያባራ ውይይት ጠምዶ ዋነኛ የሥልጣን ማስጠበቂያ መሣሪያዎች የሆኑትን የጸጥታና የመከላከያ ኃይሎችን እያባባለ ድጋፋቸውን ለማሰባሰብ እየተቀንሳቀሰ እንደነበር መገንዘቡም ከባድ አልነበረም። (ገጽ 340)
መለስ ጮሌ ብቻ ሳይሆኑ ለሥልጣናቸው ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይክዱት ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ ለሥልጣን ያበቃቸውን የትግራይ ህዝብና ጓደኞቻቸውን እንኳ አሳልፈው ከመስጠት አልተመለሱም። አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ከሥልጣናቸው ሊባረሩ በደረሱበት አንድ ወቅት ድርጅታቸውን ህወሃትን ትተው የአማራው ወኪሎች ነን የሚሉ ብአዴኖችን ተቀላቅለው እንዴት ከጎናቸው እንዳሰለፏቸውና ህወሓቶችን ክስ እንደመሰረቱባቸው ይታያል። ነገሩ ሲወራ የቆየ ቢሆንም ገብሩም በዚህ መጽሐፋቸው አረጋግጠውታል። አዲሱ ለገሠ እነዚህ ሰዎች (እኛን) ጠባቦችና የበሰበሱ ናቸው- ብሎ ተናግሮ ነበር። 391 ….በተለይ አዲሱ አፈንጋጮች የበሰበሱና ጠባቦች ነበሩ እያለ የትግራይ ህዝብ በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ ሆኗል የሚለውን የመለስን የፕሮፖጋንዳ ጨዋታ ከመጠን በላይ ያራግበው ነበር። (ገጽ 392) ። በአቶ መለስ እርዳታ ከጀኔራሎችም እነ ባጫ ደበሌ ሳይቀሩ የትግራይ ገበሬዎች
የበለጠ ተጠቃሚ ሆነዋል ሁሉ ነገር ትግራይ ትግራይ ብቻ መሆን የለበትም ብለው እስከመናገር መድረሳቸውና ሥርዓቱን በጠባብ ብሔርተኝነት መክሰሳቸው ታይቷል።
አቶ መለስ የፓርቲ አባሎቻቸው ድጋፍና ድምጽ በጎደላቸው ወቅትም ባለቤታቸውና ማሰማራታቸውን ገብሩ ጽፈዋል። “አዜብ ለመለስ ድጋፍ ለመሰብሰብ በቤተ መንግሥት ቅልጥ ያለ ግብዣ እያዘጋጀች ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ታምበሸብሽ ነበር” ገጽ 351 ብለዋል። ከአቶ ገብሩ አጻጻፍ የዘወትር አቶ
መለስ አቋማቸውን በፍጥነት በመገለባበጥ የሚታወቁ የልባቸውን ካደረጉ በኋላ ፈጥነው ይቅርታ ተሳስቻለሁ ብለው አ ም ታ ተ ው እ ን ደ ሚ ያ ል ፉ የተለያዩ አጋጣሚዎችን እየጠቀሱ ጽፈዋል። ከሁሉም የእግር እሳት ሆኖ የሚያቃጥላቸው ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ዋስትና ሊሰጥ በሚችል መልኩ ሊጠናቀቅ ይችል ነበር ያሉት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ባልፈለጉት መንገድ ድንገት መጨናገፉ ነው። እንደገብሩ ገለጻ ለዚህ ዋነኛ ተጠያቂው አቶ መለስ ናቸው እንዲህ ጽፈዋል፦መለሰ በዚህ ዓይነት የተወሳሰበና ተንኮል የተሞላበት አግባብ ብቻውን ያደረገውን የጦርነቱን ሂደት የማስቆም ውሳኔ ተገቢ እንዳልነበረና ይህን ለመወሰንና ለማወጅ የሚያስችል ሥልጣን እንዳልነበረው ኋላ ላይ ሂስ ሲቀርብለት “አዎን ስህተት ፈጽሜያለሁ ሆኖም ከጦር ግንባር ሳገኘው የነበረው መረጃ ጦርነቱን ለማስቀጠል ያስችላል የሚል ስላልነበረ ከዚህ ተነስቼ ጦርነቱን በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲቆም አውጃለሁ። የሥራ ባልደረቦቼን ማማከር ነበረብኝ ይህን ባለማድረጌ ተሳስቻለሁ።” አብዛኛዎቹ የማዕከላዊ ኮሚቴ ወታደራዊ እዝ አባላትና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አዋጁን የሰማነው እንደተራው ዜጋ በመገናኛ ብዙኃን ስለነበር አዋጁ የተጣደፈው ምናልባት በግንባር የነበሩት አዛዦች ግምገማቸውን አስተላልፈው መቀጠል እንደማይችሉ ስለገለጹ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ነበረን። ነገር ግን የግንባር አዛዦቹ ግምገማ ለማዕከላዊ እዙና ለሥራ አስፈጻሚው አባላት የደረሰው መለስ ጦርነቱ እንዳበቃ ካወጀ ከቀናት በኋላ ነበር። ይህ በመሆኑ የግንባር አዛዦቹ ግምገማ እርሱ ከሚፈለገው ውጭ እንደማይሆን አስቀድሞ በደጋፊዎቹ ተነግሮታል የሚል ግምት አለኝ። ሳሞራና ተከታዮቹ ከነዚህ ህወሓት ውስጥ ቴክኒካል አሬንጅመቱን ተቀብለን እንፈርም ከሚሉ ወገኖች ጋር ጥብቅ ግንኙነት ነበራቸው። 314-315
በተቃዋሚዎች ምሽግ ላይ እልል በል!- አብ ዱፋዖም አልል!
በአጠቃላይ የመንግሥት ሥልጣን ከመቆጣጠራችን በፊት ስንጠቀምባቸው የነበሩትን ጠላትና ወዳጅ የሚለዩ ፅንሰ ሐሳቦች መንግሥት ካቋቋምን በኋላም አላስወገድናቸውም ነበር። 186 አብ ዱፋዖም አልል- በምሽጋቸው ላይ እልል በል! በ002 ምርጫ ወቅት ኢህአዴግ ያልተገበረው የአፈና ስልትና ያላካሄደው ከባ አልነበረም። ወቅቱ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ የተካሄደበት ሳሆን በተቃዋሚዎች ላይ ግልጽ ጦርነት የታወጀበት እንበር። ለነገሩ በዚህ የምርጫ ዋዜማ ህወሓት/ኢህ አዴግ አብአብ ዱፋዖም አልል- በምሽጋቸው ላይ እልል በል! የሚለውን የትጥቅ ትግል የድል ዘፈን በተደጋጋሚ ያስዘፍን ነበር። ይህ የዋዛ ቢመስልም መልዕክቱን በጥልቀት ለተመለከተው በተቃዋሚዎች ላይ እንደ ደርግ ጦርነት መታወጁ ግልጽ ነበር።463
ትግራይና ኤርትራ – አንቺው
ታመጪው አንቺው ታሮጪው
አቶ ገብሩ ስለ ህወሓትና ሻዕቢያ ግንኙነት አንድነትና ልዩነት ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል ” እውነቱን ለመናገር ግን ግኙነታችን ሞቅ ሲል ልክ እንደ አንድ ድርጅት በጋራ የምንሠራበት ግንኙነቱ ሲቀዘቅዝ ደግሞ በዓይነ ቁራኛ የምንተያይበት ሁኔታ ነበር እንጂ ግንኙነታችን ስትራቴጂያዊ አይደለም የሚለው አቋማችን ግንኙነትቻን ላይ ስለሚኖረ ተጽ እኖ በግልጽ ተዘርዝሮ አልተቀመጠም ነበር። ስለዚህ ከሻ ዕቢያ ጋር አሉን ያልናቸው የፖለቲካ ልዩነቶቻም የይዘት ሳይሆን የስም ብቻ እንደነበሩ እነዚህ ያደረግናቸው የፖለቲካ ለውጦች ያሳያሉ…በመሆኑም ሁለቱም ድርጅቶች በተጨባጭ ከቃላት ያለፈ የር ዕዮት ዓለምም የስትራቴጂም ልዩነት አልነበራቸውም ማለት ይቻላል። (ገጽ 236)ስለዚህ በሁለቱ መካከል የዓላማም ሆነ የስትራቴጂም ልዩነት ከሌለ ወደ ግጭት የወሰዳቸው ወይም ህመማቸው ታዲያ ምንድነው የሚል ጥያቄ ያጭራል። አቶ ገብሩንና መሰሎቻቸውን ሁሌም የሚያበግናቸው ነገር ከበረሃ ጀምሮ የሻዕቢያ ባለሥልጣናት ለህወሓት ባለሥልጣናት የሚያሳዩት ንቀትና የሚፈጽሙት የትዕቢት ድርጊት ነው። እንደገብሩ መጽሐፍ ያኔ ሁለቱ ሻዕቢያና ህወሓት ወዳጅ መንግሥታት በነበሩ ጊዜ ኢሳያስ ምንም የፕሮቶኮል አግባብ ሳይጠብቁ መኪናቸውን አስነስተው መቀሌ ይገቡ ነበር። ከካርቱም አልበሽርን ከአዲስ አበባ አቶ መለስን ይዘው መቀሌ ላይ ስብሰባ ይቀምጡ ነበር። ሌላው ቢቀር ፕሮቶኮል አለመጠበቁን ያማርሩ የነበሩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶም ስለ ጉዳዩ ቅሬታቸውን መግለጻቸውን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል”
“የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ነጋሶ በሽርና ኢሳያስ አፈወርቂ ያለ እርሱ እውቅና በበርካታ አጋጣሚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡና ….365 ሲያሰኘን እንደ መንግሥት ሲያሰኘን እንደታጋይ ሆነን የፈለግነውን እንግዳ ወደ ኢትዮጵያ ስናስገባና ስናስወጣስ ነጋሶ ከፕሮቶኮልና ከአሠራር አንጻር ላነሳው ጥያቄ ክብደት ልንሰጠው በተገባ ነበር። በሽርና ኢሳያስ አዲስ አበባ ሳይደርሱ በቀጥታ ወደ መቀሌ መጥተው በወቅቱ ርዕሰ ብሔር ካልነበረው ከመለስጋ ሶስቱን አገሮች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ብዙ ጊዜ ይነጋገሩ ነበር። 365ይህ የሚሆነው እንግዲህ አቶ ገብሩ ፕሬዚዳንት ሆነው በሚያስተዳድሯት የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ውስጥ ነው። ይህም ሳይበቃ ለኤርትራ አዋሳኝ በሆነቸው የትግራይ ክልልና ድንበር ውስጥ በሚፈጸሙ አንዳንድ ቅሬታዎች የተቆጡት አቶ ኢሳያስ በአስመራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለነበሩት አቶ አውአሎም ዛሬ ሄጄ ገብሩን ሰድቤ እመጣለሁ ብለው እየነዱ እንደሚመጡ ገብሩ ጽፈዋል።
ዋነኛው ችግርና ለግጭት ያበቃቸው ምክንያት ግን የኢኮኖሚ ግኙነት መሆኑን አቶ ገብሩ በመጽሐፋቸው ለማሳየት ሞክረዋል። ይህም ቢሆን ኤርትራን አምራች ኢትዮጵያን ሸማች ከማድረግ ኤርትራን መሪ ኢትዮጵያን ተከታይ የማድረግ አዝማሚያ መታየቱ ዋነኛው ሰበብ ይመስላል። መጽሐፉ “ ሻዕቢያዎች ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ስለነበራችው ህልምና ነጻነታቸውን ባወጁ ሁለተኛው ወር ላይ ሐምሌ 1983 ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኮንፈረንስ ማዘጋጀታቸውን፣ በኮንፈረንሱም የኢትዮጵያን አየር መንገድ እንደገና አዋቅሮ ከኤርትራውያን ጋር የጋራ አክስዮን ኩባንያ እንዲፈጠር፣ ትግራይ ውስጥ የሚሠራውን የመንገድ ፕሮጀክት ሁሉ ኤርትራውያን እንዲገነቡት፣ ቀይ ባህር የንግድ ድርጅት በሚል አንድ የንግድ ኩባንያ እንዲቋቋም ማንኛውም ኤርትራዊ 500 ብር አውጥቶ አክስዮን እንዲገዛ የመሳሰሉት ውጥኖች መኖራቸው በመጽሀፉ ተመልክቷል፡፡ አስመራና መቀሌ ላይ ብዙ ምክክሮች ቢደረጉም ጨርሶ ሊስማሙ የሚችሉበት ሁኔታ ግን አልነበረም።ከዚያም አልፎ ወደ በጥቃቅን ጉዳዮች ሁሉ ወደ መጨቃጨቅና የንግድ ልውውጥና የገንዘብ ዝውውርን እስከ መገደብ ተደረሰ። ሁኔታው ከባለሥልጣናቱ እጅ ወጥቶ ወደ ህዝብና ሚዲያ ጆሮ መድረስ ጀመረ። ኤርትራን የሚከሱት አቶ ገብሩ አንዱን ምናልባትም የግንኙነት
መበጠሻ የሆነውን የመጨረሻ አጋጣሚ እንደሚከተለው ገልጸውታል፦
በሻዕቢያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከፍተኛ የፀረ- ትግራይ ቅስቀሳ ይደረግ ነበር።“በአንድ ወቅት ከትግራይ ወደ ኤርትራ የሚገባውን ማንኛውንም ሸቀጥ በመከልከል ጉሮሮአችንን ለማነቅ እየተንቀሳቀሱ ነው ነው የሚል የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ይደመጥ ነበር። ይህን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያንና የተወሰኑ የሻ ዕቢያ አባላትት እጅግ ተደናግጠው ምን እየተደረገ እንው? ይህ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻስ ወዴት እያመራ ነው?” የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር። ኢሳያስ የመጨረሻውን ስብሰባ ከኛ ጋር ሲያደርግም “የዚህ ዓይነት ዘመቻ እየተኪያሄደ ያለው ለምንድነው? ብለን ስንጠይቀው ለጥያቄያችን ያህን ያህል ክብደት
ሳይሰጠው “የምታነሱት ነገር በሚዲያ ሲተላለፍ ባልሰማም ሰዎች ሲንጫጩ ሰምቼ እስቲ በቴሌቪዥን የተላለፈውን አሳዩኝ ብዬ ምጽዋ ላይ ተመልክቼው ነበር። የተላለፈው መልዕክት ትንሽ የተጋነነ ቢሆንም መሠረታዊ ስህተት ግን አላየሁበት። አሁንም ትግራይ ጉሮሮአችንን ለማነቅ እየተንቀሳቀች ነው።
ብሎ አረፈው። 256ይህን ካለ በኋላም ኢትዮጵያ ኤርትራ ያቀረበቻቸውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎች ብትመልስ እንድሚሻላት ደጋግሞ አሳሰበን። በኛ በኩል ደግሞ እየቀረበ ያለው ጥያቄ አግባብነት እንደሌለው ደጋግመን መለስንለት። “መልሳችሁ ይህ ከሆነ ከ እንግዲህ በሁለት አገሮች መካከል ግንኙነት ልሊኖር አይችልም አለ። እንዲያውም ድንበራችንን የሚያካልል ኮሚቴ(በአስቸኳይ) ይቋቋም የሚላ አሳብ አቀረበ። 256ወደ አዲስ አበባ ከተመለስን በኋላ አስመራ ላይ የሆነውም ሁሉ ለመግለጽ አስችኳይ የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንዲጠራልን መለስን ጠየቅነው። ሻዕቢያ ወረራ ያካሂዳል ብለን እናምናለን አናምን ተብሎ በተሰጠ የፖሊት ቢሮው ድምጽ መለስ ዜናዊ ስዩም መስፍን ስዬ አብርሃ ስብሐት ነጋ ክንፈ ገ/መድህን ሲሆኑ ወረራ ያካሂዳል ብለን እናምናለን ያሉት ዓባይ ተወልደ ወልደ ማርያም፣ ዓለምሰገድ ገ/አምላክ ዓባይ ፀሐዬ እና ገብሩ አስራት ነበሩ። (ገጽ 258) በፀረ ሻዕቢያ አቋማቸው ይታወቃሉ የተባሉት አቶ ስዬ አብርሃ እስከዚያ ድረስ ታውረው ነበር ማለት ይሆን? እስከ ህወሓት አምስተኛው ጉባኤ ድረስ አልነቁም ነበር።
ከዚያ በኋላ የአቶ ገብሩ መጽሀፍ እንደሚያትተው አይቀሬው ጦርነት ተካሄደ። በጦርነቱ ዙሪያ በተያዘው አቅዋምና እሱን ተከትሎ በተነሳ ክፍፍል አቶ መለስ ተቀናቃኞቻቸውን በሙሉ እንዴት አድርገው ከፓርቲው እንዳባረሩ መጽሀፉ ይተረካል። መለስ የኢህአዴግ ጽ/ቤት እንዲታሸግና እንዲፈተሽ ማድረጋቸውን ለዚህም ደህነቱ አቶ ክንፈ ታዘው መፈጸማቸውን ያትታል። ከዚያ በኋላማ በቃ ከአቶ መለስ በስተቀር ሌላው የአመራር አባል ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ እየተፈተሸ ወደ ስብሰባ አዳራሾች መግባት ጀመረ ብለዋል ከአፈንጋጮች አንዱ የተባሉት አቶ ገብሩ አስራት፡፡ አቶ መለስ በብቸኝነት ወጡ!እሱ በህይወት ኖሮ ይህን መጽሀፍ ባሳተምኩ ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር ያሉት አቶ ገብሩ ይህን መጽሐፍ ለማሳተፍ ያሰብኩት ከመለስ ዜናዊ እልፈት በፊት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳካልኝም ብለዋል። እሱ በሕይወት ኖሮ መልስ ቢሰጥበት ደስ ባለኝ” በማለት ይህ ባለመሆኑ ቅሬታ ንደሚሰማቸው
ገልጸዋል። አቶ መለስን በህይወት ያሉትንም ሰዎች የሚተቹት በቂም በቀል ሳይሆን ሥርዓቱን ለመተችት እንደሆነም ጽፈዋል። መልካም ንባብ! (ዘኢትዮጵያ)