Save Waldiba እንደዘገበው
· ማይለበጣ ቤተ-እግዚአብሔር በታጣቂዎች ተዘረፈ
· ዶንዶሮቃ ላይ የሚገኘው የዋልድባ ገዳም ወፍጮ ቤትም በተመሳሳይ ታጣቂዎች ተዘርፏል
· አባ ፍቅረማርያም የተባሉ አባት በደረሰባቸው ከባድ ድብደባ በህክምና ላይ ናቸው
· መናኝ ገብረመድኅን የተባሉ ስመ እግዚአብሔር ጠርተው ለምነው ከድብደባ ድነዋል
· መናኝ ኅይለመለኮት የተባሉ አባት “ታጣቂዎች ዘረፉን፣ ደበደቡን፥ ታጣቂዎችም ሊዳኙን መጡ” ብለዋል በሚል ወደ እስር ቤት ተጥለዋል
እለቱ አርብ ሚያዚያ ፲፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ማታ ከምሽቱ 4:00 ሰዓት ሲሆን ጭልም ድቅድቅ በሆነበት ሰዓት ላይ ማይለበጣ በሚገኘው ቤተ እግዚአብሔር ላይ በከባድ የሚሊተሪ ልብስ እና ትጥቅ የታጠቁ በግምት ስድስት የሚሆኑ ታጣቂዎች በውጪ በረንዳ ላይ ተኝተው የነበሩትን መነኮሳት እና መናንያን ደብድበው እና ብዙ እንግልት አድርሰውባቸው ገንዘብ ያለው የት ነው ተናገሩ በሚል ብዙ እንግልት እና ድብደባ እንዳደረሱባቸው ከቦታው በደረሰን መረጃ መመልከት ችለናል። በመጨረሻም ታጣቂዎቹ ከመሄዳቸው በፊት ጽ/ቤቱን በሰደፍ ሰብረው ሲያበቁ በጽ/ቤት ውስጥ ያለውን ንብረት በመወርወር ሲያምሱ ቆይተው ምንም ባለማግኘታቸው ተበሳጭተው መነኮሳቱን ደብደበው እና አንገላተው ጥለው ወጥተው ለመሄድ ችለዋል።
በዚሁ አርብ ምሽት በማይለበጣ ምንም ያላገኙት ታጣቂዎች ከእኩለ ሌሊት በኃላ ማለትም ከሌሊቱ 1:00 ሰዓት ሲሆን በዳንዶሮቃ በሚገኘው የገዳሙ እህል ወፍጮ ቤት ለነፍሳቸው በረከት ለማግኘት የሚጣደፉ ምዕመናን እገዛ ከገዳሙ ውጪ የአካባቢው ምዕመናን እህል በማስፈጨት የሚገኘውን ገቢ ለገዳሙ መጠቀሚያ እንዲሆን በተዘጋጀው መሰረት እነዚህ ታጣቂዎች በዶንዶሮቃ በሚገኘው የገዳሙ ወፍጮ ቦታ በመሄድ፥ በወፍጮ ቤቱ ውስጥ በጥበቃ እና በግልጋሎት ላይ ያሉትን ሁለት ማናንያን ፩ኛ. አባ ፍቅረ ማርያም የሚባሉትን ክፉኛ ደብድበው በሞት እና በሕይወት መካከል እስኪሆኑ ድረስ ድብደባ ደርሶባቸዋል፣ ሌላው መናኝ ገብረመድኅን የተባሉት በመስኮት ዘለው ለማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ ከታጣቂዎቹ አንዱ ደርሶባቸው ነበር ነገር ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው በመለመናቸው ምንም ሳይሆኑ ተርፈዋል። ታጣቂዎቹም በዘረፋቸው ወቅት ግምቱ ከ$6000.00 ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ከወፍጮ እና የተለያየ ገቢ እጃቸው ላይ የነበረውን በሙሉ ዘርፈው አባ ፍቅረማርያምን በሞትና በሕይወት መካከል ትተው ጥለው ለመሄድ እንደሄዱ ለመረዳት ችለናል።
በሚቀጥለው ቀን የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት በታጣቂዎች ታጅበው ነገሮቹን ለማጣራት ነው በሚል መጥተው ተጠቂዎቹን ሲያዋክቡ፣ ምን እያደረክ ነበር? የት ነበርክ ዘረፋው ሲፈጸም፣ ለምን አንተስ አልተደበደብክም? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ሲያዋክቧቸው እንደነበር ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ የምርመራ ሰዓት ታጣቂዎቹ ገዳማውያኑን በሚጠይቁበት ጊዜ አንድ መናኝም በእነዚህ ታጣቂዎች ወደ እስር ቤት ተወስደው እስከ አሁን ድረስም በእስር ቤት እንደሚገኙ ለመረዳት ችለናል። የታሰሩበትን ምክንያት ለማጣራት ስንሞክር እንደተረዳንው፥ የመንግሥት ታጣቂዎቹ መናኝ ኅይለመለኮትን ለእስር ያበቃቸው የተባለው “የሚዘርፉን ታጣቂዎቹ ፥ የሚዳኙንም ታጣቂዎች ምን ይሻለናል” ነገር ግን የታሰሩት መናኝ እንደተናገሩት ምንም የተናገሩት ነገር እንደሌለ በአካባቢው የነበሩት መነኮሳት ወንድሞቻቸው ምስክርነታቸውን ቢሰጡም ለእስር መዳረጋቸው ብዙዎችን አሳዝኗል፥ ሁልጊዜም እንደሚያደርጉት የሚደርስባቸውን ግፍ እና እንግልት ለመድኃኒዓለም በጸሎት እና በምኅላ ገልጸዋል።
ከዚሁ ከዋልድባ አካባቢ ሳንወጣ፥ ባለፈው ጥቂት ሳምንታት እንደዘገብነው በዋልድባ ሸንኮራ ለማልማት ይገደባል የተባለው ግድብ በመድኃኒዓለም ፈቃድ ሳይገነባ (ሳይገደብ) በመቅረቱ መንግሥት ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት በዛሬማ ወንዝ አካባቢ ያሉትን ዛሮች እያስቆረጠ ከሰል አክሳዮችን በማምጣት በከፍተኛ ሁኔታ ደኑን እየመነጠሩ ከሰል በማክሰል ላይ ይገኛሉ የአካባቢው ነዋሪም የመጠየቅ ባይችልም ነገሩን በግርምት እየተመለከተው እንደሚገኝ እና ምን ሊመጣ እንደሚችል ለመተንበይ ባይችልም ነገሩ ግን መጠነኛ የሆነ ስጋት ሊያስድርባቸው ችሏል። እርግጥ ነው እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥትም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናት የፈለጋቸውን ነገር ያደርጋሉ፣ ሲያሻቸው ያርሳሉ፣ ሲያሻቸው ይቆፍራሉ፣ ሲያሻቸው ቤተ እግዚአብሔርን ያፈርሳሉ፣ ሲያሻቸው የቅዱሳን መካናትን ይፈነቅላሉ ይህ ሁሉ ሲደረግ የገዳሙን መነኮሳት ሆነ የቤተክርስቲያን ተወካዮች ተጠይቀው አያውቁም፥ የፈለጋቸውን ነገር በፈለጉበት ሰዓት እና ቦታ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታሰሳል ነገር ግን የቦታው ባለቤት መድኃኒዓለም፥ የርስቱ ጠባቂዎች መነኮሳቱ ስለሆኑ የቦታው ባለቤት በጊዜው ሊጠይቃቸው እንደሚችል እናምናለን ነገር ግን ሁልጊዜ እግዚአብሔር አምላክ እርሱ እሳት ልብሱ እሳት የተባለለት አምላክ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው እርሱ እሳት ልብሱ እሳት ነው፣ ማንም ፍጥረት እፊቱ ሊቆም ቀርቶ ሊቀርብ ባልቻለ ነበር፥ ነገር ግን ምሕረቱ ደግሞ ያንን እሳት አቀዝቅዞት ዛሬ አረማውያን እንደፈለጋቸው ሲሆኑ እና ሲያደርጉ ዝም ብሏቸዋል እድሜ ለንሰሐ ይሰጣቸዋል አልመለስ ቢሉ ግን በሰዶም እና ገሞራ የወረደው እሳት እና መከራ ዛሬም በእነዚህ አረማውያን ላይ እንዳይወርድ ፍራቻችን ነው ያም ከመሆኑ በፊት ወደ ልቦናቸው ተመልሰው የሀገርን ቅርስ፣ ሃይማኖትን ከማጥፋት፣ አረጋውያን መነኮሳትን ከማንገላታት እና ከማሰቃየት፣ ለወገን መኩሪያ እና ለመጪው ትውልድ ኩራት የሚሆኑትን ብርቅዬ ሃብቶቻችንን እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ ልቦናውን ይስጥልን እንላለን።
ይቆየን
ቸር ይግጠመን
IUEOTCFF
Let’s save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!