በ አሸናፊ ደምሴ
ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ውስጥ የተጓዝኩባቸው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገዶች ውጣ ውረድ የበዛባቸው ናቸው የሚለው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ በተለይም የመልካም አስተዳደር ችግሮቼ በማንም ላይ አይላከኩም ሲል ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ለሚማሩ ተማሪዎች በመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሥልጠና ላይ ባሰራጨው ሰነድ ጠቆመ።
በሐምሌ 2006 ዓ.ም ታትሞ ለተማሪዎች በተበተነውና “የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ” በሚል የቀረበው ሰነድ የመልካም አስተዳደር ችግሮቹን ተከትሎ ትምክህትና ጠባብነት፤ የሃይማኖት አክራሪነትና የዚህ ሁሉ መንስኤ የሆነው አለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ የሥርዓቱ አብይ ፈተናዎች መሆናቸውን ገልጿል።
“የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እየወደቅን እየተነሳን ነው” ያለው ፅሑፉ፤ ከደረስንበት የእድገት ደረጃን ከህዝቡም ፍላጎት አንፃር ሲታይ ገና ብዙ እንደሚቀረውም ይጠቁማል። በተለይም በከተሞች አካባቢ ከህዝቡ የሚነሱትን ጥያቄዎች በየደረጃው ባሉ አመራሮች በጊዜና በፍጥነት ውሳኔዎች አለመስጠታቸው፤ በዚህም የልማት እንቅስቃሴዎች መጓተታቸውና በቂና አሳማኝ ምላሽ የመስጠት ችግሮች መኖራቸውን እንደማሳያ ጠቅሷል። አክሎም ዜጎች በመንግስት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ያለአንዳች አድልኦና መጉላላት መጠቀም ሲችሉና ሲገባቸው አላስፈላጊ አድልዎና ውጣ ውረድ ያጋጥማቸዋል ሲል በሰነዱ ላይ ያትታል።
በሰነዱ እንደተጠቀሰው ዜጎች ከመንግሥት ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢ አገልግሎቶች ባለማግኘት እጅ መንሻ ከሚጠየቅባቸውና ችግር አለባቸው ተብለው ከተጠቀሱት ተቋማት መካከል የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም፣ የውሃና የመንገድ አገልግሎቶች በምሳሌነት በሰነዱ ተጠቅሰዋል። በመጨረሻም ሰነዱ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በተመለከተ ህዝቡ በስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው በየጊዜው የሚያማርርባቸውን ችግሮች በየጊዜው በአስተማማኝ ሁኔታ መቅረፍ ይገባል፤ ሲል ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ለተውጣጡ ተማሪዎች በመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ የተሰጠው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ባሳለፍነው ቅዳሜ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በቀጣዩ መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም ደግሞ ሁለተኛ ዙር ሥልጠና እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።