Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: “ምትሃተኛው!!”–በክርስቲያኖ ሮናልዶ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ የተዘጋጀ ልዩ የጽሁፍ ዶክመንተሪ

$
0
0

የውድድር ዘመኑ የጎል ሪከርድ ያስመዘገበበት፣ የዓለም ኮከብ የሚያስብለውን ‹‹የባሎን ዶር››ን ክብር የተጎናፀፈበት፣ ሀገሩ ፖርቹጋልን በዓለም ዋንጫ ላይ በአምበልነት የመራበት እና ክለቡ ሪያል ማድሪድ በቻምፒዮንስ ሊጉ ለ10ኛ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን እንዲሆን ያስቻለበት ዘመን ነበር፡፡ በዚያች የፀደይ ዕለት ግን በማድሪድ ከተማ አንዳች ነገር አስከፍቶታል፡፡

በልምምድ ማዕከሉ ከሚገኘው ህንፃ ፎቅ ላይ ሆነው እንኳን ፊቱን ተመልክቶ ቅሬታውን ማስተዋል አያቅትም፡፡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተከፍቷል፡፡ አንዳንድ የቡድን ጓደኞቹ ‹‹ኤልአንሲያ›› (ጭንቀታሙ) በሚል ቅጽል ያውቁታል፡፡ በዚያች ዕለት ንዴትና ጭንቀት ይታዩበታል፡፡ አንድ ያልተመቸው ነገር አለ፡፡ በፈጣን እግሮቹ ጭን ላይ ያሉት የጡንቻ ጅማቶች ጤነኛ አይደሉም፡፡ ህመም ይሰማዋል፡፡ እንደልብ የማያንቀሳቅስ እክል ቀስፎ ይዞታል…፡፡
cristiano-ronaldo-09
የሪያል ማድሪድ የልምምድ ማዕከል ከእንቅልፉ ነቅቷል፡፡ የሜዳውን ሳር ውሃ የሚያጠጡት ቧንቧዎች ገና መዘጋታቸው ነው፡፡ ባዶ የነበረው የማዕከሉ የመኪና ማቆሚያ በቅንጡ ስፖርት አውቶሞቢሎች ተጨናንቋል፡፡ ቱጃሮቹ ተጫዋቾች ለዕለታዊው ልምምዳቸው በማዕከሉ ተሰባስበዋል፡፡ የሮናልዶ የቡድን ጓደኞች 260 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ አላቸው፡፡ ጋሬት ቤል፣ አንሄል ዲ ማሪያ፣ ሰርጂዮ ራሞስ እና ማርሴሎ በልዩ እንክብካቤ በተያዘው አረንጓዴ ሜዳ ላይ ፈሰሱ፡፡ የውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ ነው፡፡ ሪያል ማድሪድ የላ ሊጋው የመጨረሻ ጨዋታን መጫወት ይቀረዋል፡፡

ጥርት ባለው ሰማይ አዕዋፍ እንደ ሮኬት ከወዲያ ወዲህ ይተኮሳሉ፡፡ የማድሪድ የሰማይ አድማስ በግንባታ ክሬኖችና ባለመስተዋት ህንፃዎች ታጅቦ ይታያል፡፡ ልምምዱ ግን ለሁሉም ክፍት አይደለም፡፡ በኤሌክትሮኒክ ፍተሻ መሳሪያ ስር ያለፉ ጥቂቶች ብቻ የታደሙበት ዝግ ልምምድ ነው፡፡ ከተፈቀደለት ጋዜጠና ሌላ በልዩ ስምምነት በሪያል ማድሪድ አካዳሚ እንዲሰለጥኑ ከሩቅ ምስራቅ የመጡ ቻይናዊያን ወጣቶች በማዕከሉ ደርሰዋል፡፡ ሮናልዶ በሮጠ ቁጥር ጎረምሶቹ ስሙን ይጠራሉ፡፡ ኳስ ሲመታም ‹‹ሮናልዶን ተመልከተው›› እያሉ ያወራሉ፡፡ በመላው ዓለም እንደሚገኙት ታዳጊዎች ሁሉ እነዚህም ልጆች ሮናልዶ የሚያደርገውን ሁሉ በራሳቸው ለመስራት ይሞክራሉ፡፡ የፖርቹጋላዊው መለያ የሆኑትን አብዶዎች ይኮርጃሉ፡፡ የቅጣት ምት ዓመታት ልማዱን ይደጋግማሉ፡፡ ታዳጊዎቹ ስሜታቸውን ቢቆጣጠሩም ወጣቱን ኤልቪስ ፕሪስሌይ እንዳዩ ኮረዶች በደስታ መቁነጥነጣቸው አልቀረም፡፡

ሮናልዶ ለግማሽ ሰዓት ያህል ከቡድኑ ጋር ልምምዱን ሰራ፡፡ ግን ያለ እንከን መቀጠል አልቻለም፡፡ በድንገት በአንዱ ንስር አይን አሰልጣኝ እይታ ውስጥ ወደቀ፡፡ ወደ ሜዳው ጠርዝ ለይቶት በግራ እግር ጡንቻዎቹ ላይ የጤና ማረጋገጫ ሙከራዎች አደረገለት፡፡ በልምምድ የሚሰራ የጤና ምርመራ እንደማለት ነው፡፡ ለ15 ደቂቃዎች በዚሁ ሂደት ውስጥ አለፈ፡፡ ውጤቱ ግን አስደሳች አልነበረም፡፡ ሮኒ የግድ ልምምዱን ማቋረጥ አለበት፡፡

ካርሎ አንቾሎቲ በውዱ ልጃቸው ላይ ሪስክ መውሰድ አልፈለጉም፡፡ ለተባባሰ ጉዳት ከሚዳረግ ልምምዱን አቁሞ በህክምና ክትትል እንዲቆይ ይሻላቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ የማዴይራውን ልጅ የሚያስደስት አይደለም፡፡ ከቡድኑ ገለል ብሎና ለምቦጩን ጥሎ ተቀመጠ፡፡ ሲያናግሩት እጁን በማወዛወዝ ይመልሳል፡፡ መጫወት ቢፈልግም ወደ መልበሻ ቤት ማምራት ዕጣው ሆነ፡፡ በሜዳ ላይ ሳይሆን በወጌሻ ወንበር ላይ ጊዜውን ለማሳለፍ ተገደደ፡፡

ለአንድ ሰዓት ያህል ያስጠበቀውን ጋዜጠኛ ያገኘው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ላቡን ለመታጠብ ሻወር ወስዶ ድብርታም ገጽታ ካላቸው አጃቢዎቹ ጋር በማዕከሉ አንደኛው የፕሬስ ክፍል ብቅ አለ፡፡ በዳይመንድ ሎቲው አጊጧል፡፡ እጅግ ተውቦ ለመታየት ፀጉሩን በቄንጥ አበጥሮ በጄል ሸብቦታል፡፡ በጆሮ ግንዱ አካባቢ ብቅ ያለው ፀጉሩ እንደ ጩቤ ጫፍ ስል መስሏል፡፡ ጃኮብ ኤንድ ኮ የተባለው እጅግ ውድ ብራንድ ሰዓቱ በእጁ አንጓ ላይ ያብረቀርቃል፡፡ ጀነን ብሎ ጥቂት ከተራመደ በኋላ ተቀመጠ፡፡

ሮናልዶ ራሱን በማስጌጥና ተውቦ ለመታየት ጊዜ የሚያጠፋ ሰው ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡ ኮራ ያለው ጉብል ግን በቀላሉ የሚሰበር ደካማ ጎን አለው፡፡ ነገሮች ባልፈለገው መንገድ ሲጓዙበት በብስጭት የሚሸነቁጥር ውስጣዊ ስሜት አለው፡፡ በዚያ ዕለት የተረጋገጠበት ጉዳት ከቀሪው የሪያል ማድሪድ ጨዋታዎችና ከብራዚሉ የዓለም ዋንጫዎች ውጭ ሊያደርገው እንደሚችል በመታወቁ ብስጭት ሁሉ ጓዙን ጠቅልሎ ሰፍሮበታል፡፡ ይህ ለመሆኑ ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልግም፡፡ በ2009 ወደ ሪያል ማድሪድ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ሮናልዶ ለስፔኑ ዋና ከተማ ክለብ 240 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ የማድሪድ ዓመታት በእግርኳሱ ዓለም ያሉ ውድድሮችንና ዋንጫዎችን ከሞላ ጎደል አሸንፏል፡፡ በ2014 ብቻ ለሪያል ማድሪድ 51 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኝቷል፡፡ እንዲህም ሆኖ ሮኒ ገና አልረካም፡፡ ወደ ፊትም የሚረካ አይደለም፡፡

ሮናልዶን በቅጡ የሚያውቁ ሰዎች ገና በመጎልበት ላይ ያለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ራሱን ወደ ፍፁማዊ የብቃት ጠርዝ ለማድረስ የመትጋት ልክፍት ተጠናውቶታል፡፡ የስኬት ረሃቡም ፈፅሞ የሚጠግብ አይደለም፡፡ በዚህ አስተያየት ክርስቲያኖ ይስማማል፡፡ ‹‹ዘወትር ራሴን ለማሻሻል እሰራለሁ›› የሪያል ማድሪዱ ሰባት ቁጥር ይናገራል፡፡ ‹‹ከዛሬ ይልቅ ነገ የተሻልኩ ተጨዋች እሆናለሁ፡፡ ከዘንድሮ ይበልጥ ለከርሞ ተሽዬ እቀርባለሁ፡፡ ሰዎች በሜዳ ላይ ሲበዛ ኮስታራ እንደሆንኩና ፈገግታ እንደማይታይብኝ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቴ መቶ በመቶ በስራዬ ላይ ትኩረት ማድረጌ ነው፡፡ ሁልጊዜ በቃኝ አላውቅም››
ሮናልዶን መሆን ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የብቃት ጽንፍ ላይ ለመድረስ ያለው ትጋትና የክብሮችን ሁሉ ክብር የመጎናፀፍ ልክፍቱ ይደንቃል፡፡ ራስን የመውደድና ራስን የመተቸት ተቃራኒና ኃይለኛ ስሜቶች ተጣምረው ይታዩበታል፡፡ ‹‹ልዩ ውስጣዊ ጉልበት›› ብሎ በሚጠራው ስሜት ተገፋፍቶ ይሮጣል፡፡ በመላ የእግርኳስ ህይወቱ ለወጣበት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ብቁ ምላሽ መስጠቱን ከማሳየት ከባድ ትግል ጋር ግብግብ ሲፈጥር ኖሯል፡፡ ይህም በቀላሉ ስሜቱ የሚጎዳ፣ ድንጉጥና በስኬት ጊዜም ከልክ ባለፈ የሚደሰት ሰው አድርጎታል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ሮናልዶ ምጡቅ ችሎታን እንዲያሳይ በሚወተውት የገዛ ስሜቱ የሚገፋ ይመስላል፡፡ ሁልጊዜም በተቻለው ሁሉ የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ መድረሻውን ያስቀምጣል፡፡ ከዚያም ካሰበው ጣሪያ የላቀ ስሜት ያስመዘግባል፡፡ ብሪታኒያዊው የእግርኳስ ጋዜጠኛ ባርኒ ሮናይ እንደገለፀው ‹‹ሮናልዶ ሲጫወት በባለጋራ ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን በስታዲየሙ ታዳሚ ሁሉ ሳይቀር የሚሳደድ ይመስላል››
Ronaldo Christiano
ስለ ሮናልዶ ተሰጥኦ ታላቅነት ጥርጣሬ የለም፡፡ ከቀንደኛ ተፎካካሪው ሊዮኔል ሜሲ ጋር የዓለም ምርጡ ተጨዋች መሆኑ ማስረጃ የማይፈልግ እውነት ነው፡፡ ከእነ ፔሌ እና ማራዶና ጋር ከስፖርቱ ታሪካዊ ተጨዋቾች ተርታ ሊሰለፍም ይችላል፡፡ ሁሉን ብቃት ያሟላ ተጨዋች ነው፡፡ በሁለቱም እግሮቹ ተጋጣሚን ይገድላል፡፡ ጥበብ የተሞላበት ድሪብሊንጉ ይለያል፡፡ መረብ በጣሽ የጎል ሙከራዎቹ ኃይልና ጮሌነትን ደባልቀዋል፡፡ እንቅስቃሴው የተከላካዮችን ትኩረት ይበታትናል፡፡ ቅጣት ምቶቹ በግርምት አፍ ያስይዛሉ፡፡ ክፍተት ከሰጡት ፍጥነቱ ለንፅፅር አይቀርብም፡፡
‹‹የዘመኑ እግርኳስ በአካላዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጥንካሬ፣ እና ኢንዱራንስ የላቀ ቦታ አላቸው›› ይላል የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ማይክል ብራድሌይ- በዓለም ዋንጫው ላይ ከፖርቹጋል ጋር ከመጫወታቸው ቀደም ብሎ፡፡ ‹‹ሮናልዶ ደግሞ እነዚህን ሁሉ ያሟላ ተጨዋች ነው፡፡ ስለ ቴክኒካዊ ተሰጥኦው ስታነሳ ደግሞ -የአየር ላይ በቃቱ- በማንኛውም ሰዓት ልዩነቱን መፍጠር የሚችል መሆኑን ትገነዘባለህ››

ብራድሌይ አልተሳሳተም፡፡ በጨዋታው 95ኛው ደቂቃ ላይ ሮናልዶ በሚሊ ሜትር መጥኖ ያሻገራት ኳስ ለፖርቹጋል ማሸነፊያ ጎል መገኘት ምክንያት ሆናለች፡፡ ‹‹ሮናልዶ ኳስ ይዞ ወደ ክንፍ ሲጠጋ ማየት ለተጋጣሚ ተከላካዮች የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡ የትኛውም ተከላካይ ሊያየው የሚወድ አጋጣሚ አይደለም›› ይላ የኢኤስፔኤኑ ኮሜንታተር እና የቀድሞው የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ አሌክሲስ ላላስ፡፡ ‹‹ይህ ሲሆን እኔም ትንፋሼን ዋጥ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድ ምትሃታዊ አጋጣሚ ይፈጠር ዘንድ የሚጀምረው ከዚያ ነውና››
አሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪንሆ ለሮናልዶ አድናቆት ለማግኘት ከዚህ ዓለም ወጥተዋል፡፡ ‹‹እነርሱ ከሌላ ፕላኔት ነው፡፡ እኔ ካሰለጠንኳቸው ተጨዋቾች ሁሉ እንደ ክርስቲያኖ በተሰጥኦ የታደሰ አላየሁም›› ብለውታል፡፡ የማንችስተር ዩናይትዱ የቀድሞው አሰልጣኝ ደግሞ ‹‹ምትሃተኛው›› ሲሉ ይገልፁታል፡፡ ‹‹እርሱ ሲጫወት መመልከት ፕሌይስቴሽን ጌምን እንደመጫወት ይቆጠራል›› ያለው ደግሞ የቶተንሃሙ አጥቂ አማኑኤል አዴባየር ነው፡፡

የሮናልዶን የእግርኳስ ህይወት በማናጀርነት የመራው የተጨዋቾች ወኪል ጆርጌ ሜንዴዝ የኮከቡን ህይወት ሲገልፅ ከአንድ ኢንጂነሪንግ ፕሮጀክት ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ‹‹ለመጪዎቹ 500 ዓመታት ክርስቲያኖ ሮናልዶ መሳይን ለመገንባት ፈፅሞ የማይቻል ነው›› ሲል ይተነብያል፡፡
የሮናልዶ ብቃት ባለፈው ኖቬምበር ወር በስቶክሆልም ከተማ በይለብጥ ተገልጧል፡፡ ለዓም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ማጣሪያ ጨዋታ ፖርቹጋል ስዊድንን ገጠመች፡፡ የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች ‹‹ሜሲ! ሜሲ!›› እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡ ሮናልዶን ለማበሳጨት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እርሱ ግን አልተሸበረም፡፡ በሶስት ድንቅ ጎሎቹ ተበቀላቸው፡፡ ሁለተኛው ጎል ሲያስቆጥር ወደ መሬት እየጠቆመ ‹‹እነሆኝ!›› አላቸው፡፡ የስዊድን የዓለም ዋንጫ ህልምም ቅዠት ሆኖ ቀረ፡፡

‹‹ምርጥ እንድትሆን በስራህ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብህ›› ይላል ሮናልዶ፡፡ ‹‹አዕምሮህን ማሰልጠን በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሽንፈት ሽንፈት መስሎ አይሰማህም፡፡ በራስህ የምትተማመን ከሆነ መረጋጋትህን የሚያውክ ነገር አይኖርም፡፡ ጠንክረህ በሰራህና ራስህን ለስራህ ባስገባህ ቁጥር ይበልጥ በራስህ ትተማመናለህ››

ከስፖርታዊ ክህሎቱ በተጨማሪ ሮናልዶ በመሮ የተቀረፀ የሚመስል ሰውነት ባለቤት ነው፡፡ አካላዊ ቅርፁና ውበቱ ስፖንሰሮችን ምራቅ ያስውጣል፡፡ በሞዴልነቱ መስክም ክርስቲያኖ ሌላው ዴቪድ ቤካም ነው፡፡ ሮናልዶ ታላቅ ስፖርተኛ ብቻ አይደለም፡፡ ታላቅ ስፖርተኛ ሊኖረው የሚገባ አካል ተምሳሌትም ጭምር እንጂ፡፡ በእግርኳሱ ዓለም እጅግ ታዋቂውና ተወዳጁ ተጨዋች ሲሆን ናይኪ፣ ሳምሰንግ፣ ሄርባልላይፍን ከመሳሰሉት ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የስፖንሰርሺፕ ኮንትራት አለው፡፡ ዓመታዊ ገቢውን 73 ሚሊዮን ዶላር ያደረሱትም እነዚሁ ስምምነቶቹ ናቸው፡፡ ‹‹በህዝብ መካከል ከብዙ ተጨዋቾች ጋር ዞሬያለሁ፡፡ የሮናልዶ ያህል ድጋፍ ጩኸት የሰማሁበት ግን የለም›› ይላል የቢኢን ስፖርት የእግርኳስ ኮሜንታተር ሬይ ሃድሰን፡፡ ‹‹መነኩሴዎችን ሳይቀር ሊያስጮህ የሚችል ሰው ነው›› ሲል የኮከቡን ተወዳጅነት ይገልፀዋል፡፡ በእንስቶች የመወደዱን ያህል ህይወቱ በልቅ ግንኙነት የተሞላ አይደለም፡፡ ከእውቋ ራሺያዊት ሱፐር ሞዴል ኢሪና ሻይክ ጋር በፍቅር ተጣምሯል፡፡

የሮናልዶን የታይታ ህይወት የማይወዱለት ወገኖች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ እዩኝ እዩኝ የሚለው ባህሪዩን የሚጠሉለት ብዙ ናቸው፡፡ በሜዳ ላይ በንዴት አኩርፎ መታየቱን፣ ብሎም ማልቀሱ የጥላቻቸው ምክንያት የሆነላቸውም አሉ፡፡ ቅንጡ ጌጣጌጡንና ብርቅርቅ ፎቶግራፎቹን በደስታ ያልተቀበሉም አይጠፉም፡፡ ነገር ግን ከተቺዎቹ መካከል ለራሱ ባለው ከፍ ያለ ግምት ምክንያት የጠሉት ይበዛሉ፡፡

በራሱ ምስል ያጌጡ የቅልጥም መከላከያዎችን ያደርጋል፡፡ 7 ቁጥሩ ማሊያው ምትሃታዊ ኃይል አለው ብሎ ያምናል፡፡ ከዲዛይነር ሪቻርድ ቻይ እና ከዴንማርኩ የቡቲክ ብራድ ጂቢኤስ ጋር በመተባበር በራሱ ስም ያመረተው ሙታንታ አለው፡፡ ላ ፊንቻ በተሰኘው የማድሪድ ከተማ ባለፀጋዎች ሰፈር በሚገኘው ቤቱ ውስጥ ወንበርና ጠረጴዛው ሳይቀር ‹‹ሲአር 7›› የተሰኘው የግል ብራንዱ ያረፈባቸው መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በአንድ ወቅት እርሱን ሲመለከቱ ሰዎች ስለምን እንደሚጮሁ ተጠይቆ ‹‹ቆንጆ፣ ታዋቂና ሃብታም በመሆኔ ስለሚቀኑ ነው›› ሲል የሰጠው መልስ አስተችቶታል፡፡ ባለፈው ዓመት ዲሴምበር ወር ላይ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ 540 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የትውልድ ደሴቱ ማዴይራ ፉንቻል ከተማ የራሱን መታሰቢያ ሙዚየም ከፍቷል፡፡ በማዕከሉም ‹‹በሲአር7›› ብራንድ የተሰሩ ቁሳቁሶች፣ በግል በቡድን ያሸነፋቸው ዋንጫዎች፣ ፊርማው ያረፈባቸው ማሊያዎች እና ኳሶች ሁሉ ተሰብስበው ለእይታ ተቀምጠውበታል፡፡ በስሙ የተቀረፀ የተጫዋቹ ሀውልት ሳይቀር እዚያ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ስፖርቶች ላይ የተሳካላቸው ከዋክብት የዋንጫ መሰብሰቢያ ሙዚየሞችን መስራታቸው የተለመደ ቢሆን ክርስቲያኖ ግን ለየት አድርጎታል፡፡ በራሱ መንገድ እየተጓዘ እንደ አርማታ የጠነከረ በራስ መተማመን ገንብቷል፡፡ ‹‹እናቴ ሁል ጊዜ ራሴን መስዬ እንድኖር እየመከረች አሳድጋኛለች፡፡ ይህን ባህሪዬን ሰዎች ሊወዱትም ሆነ ሊጠሉትም ይችላሉ፡፡ ችግር የለውም፡፡ለእኔ ግን ጠንካራ ሰብዕና እንዲኖረኝ አግዞኛል›› ይላል ሮናልዶ፡፡

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶ ሳንቶስ አቬዬሮ ከእግርኳስ ጋር በፍቅር የወደቀው የእሳተ ገሞራ ኮረብቶች በበዙባት ፉንቻል ከተማ ነው በሜዴይራ ደሴት፡፡ ወላጆቹ የቀድሞው አሜሪካው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን አድናቂ በመሆናቸው ለአብራካቸው ክፋይ ስሙን አውጥተውታል፡፡ ከደሃ ቤተሰብ የተገኘ ሲሆን ታዳጊው ሮናልዶ ያደገው በደሳሳ ጎጆ ከሁለት ልጆች ጋር በጋራ በሚጠቀምባት አንድ ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ዕቃ ለማስቀመጫ በቂ ቦታ ስላልነበር የልብስ ማጠቢያ ማሽናቸውን በቤቱ ጣሪያ ላይ እስከማኖር ደርሰዋል፡፡ እናቱ ዶሎሬስ የጽዳት ሠራተኛ፣ አባቱ ዲኒስ ደግሞ አትክልተኛ ነበሩ፡፡ አባት በመጠጥ ሱሰኝነትና በእግርኳስ አፍቃሪነታቸው ይታወቁ ነበር፡፡

በወላጆቹ አበረታችነት ትንሹ ክርስቲያኖ በመኖሪያ ቤታቸው ዙሪያ በተገኘው ጠባብ ቦታ እግር ኳስን መጫወት ጀመረ፡፡ እግሮቹ የፉትቦልን ጥበብ ማዳበርን የጀመሩት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ለትንሹ ልጅ የኳስ ፍቅር ደንቃራ የሆነ አንድ ሰው ቢኖር ሚስተር አጎስቲኖ ይሰኛል፡፡ ሰውዬው በልጆች ቅሪላ የአትክልት ቦታው እየተበላሸ ቢቸግረው አንድ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ወደ አትክልት ቦታው የገባ ኳስ ሁሉ ለባለቤቱ ከመመለስ ይልቅ ተቀዶ ይጣላል፡፡ የሚስተር አጎስቲኖ ነገር ሮናልዶን አንድ አብይ ትምህርት አስተማረው፡፡ ያለማቋረጥ ኳስን ለመጫወት ሲል ስህተት መፈፀም የለበትም፡፡ ተሳስቶ ኳስ ወደ አትክልት ቦታው ከገባች ያበቃላታልና፡፡

በፉንቻል የታዳጊዎች ውድድር ላይ ክሪስቲያኖ ተለይቶ ለመታየት ጊዜ አላስፈለገውም፡፡ አባቱ የቡድኑ ትጥቅ ያዥ ነበሩ፡፡ የመጫወቻ ትጥቆችን ከመያዙም በተጨማሪ ክርስቲያኖን ለክብር ያዘጋጁታል፡፡ ያን ጊዜ በሜዳ ላይ ለሚያሳየው ጉልበተኛ አጨዋወት ሰዎች ‹‹አቤሊንሃ›› ብለው ይጠሩት ነበር፡፡ ‹‹ትንሹ ንብ›› እንደማለት ነው፡፡ ለመሸነፍ ፈጽሞ ዝግጁ አልነበረም፡፡ ቡድኑ ካላሸነፈ ወይም የቡድን ጓደኛው ኳስ ካልሰጠው ያለቅሳል፡፡ 12 ዓመት ሲሞላው ደሴቲቷን ለቅቆ በስፖርቲንግ አካዳሚ ሙከራ ላይ ሊገኝ ወደ ሊዝበን በረረ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፕላን የተጓዘው በዚያች ዕለት ሲሆን ከቤተሰብ ናፍቆትና በጉዞው ላይ በነበረው የበረራ ጩኸት ምክንያት አልቅሷል፡፡

የወደፊቱን ኮከብ እምቅ ብቃት ለማወቅ ግን ደጋግሞ ማየት አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ገና ከጅምሩ በሙከራው ላይ የነበረው አሰልጣኝ ‹‹ኧረ ይሄስ ልጅ ይለያል›› ሲል ለሌላው ባልደረባው በጆሮው ላይ አንሾካሾከ፡፡ ጊዜ ሳይፈጅ ክርስቲያኖ ሜዴይራን ተሰናብቶ ሊዝበን የሙሉ ሰዓት መኖሪያው ሆነች፡፡ በመጀመሪያ ላይ የደሴቲቱ ህዝቦች የሚያወሩበት የንግግር ቅላፄው ለሌሎች ሰልጣኞች ቀልድ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ ‹‹ገና ለመናገር አፌን ከመክፈቴ›› ይላል ሮናልዶ ‹‹ሞመንትስ›› በተሰኘው የግል ማስታወሻ መጽሐፉ ላይ ዘመኑን ሲያስታውስ፡፡ ‹‹ልጆቹ ይስቃሉ፣ ያሾፋሉ፡፡ እኔም ሞኛሞኝ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል››

ህይወት በሊዝበን አልተመቸችውም፡፡ ከቤተሰብ ርቆ መኖር ለክርስቲያኖ ፈተና ሆነ፡፡ ናፍቆት ሁሉን ሊያሳጣው ቀረበ፡፡ ኳሱን ትቶ ጠቅልሎ ወደ ማዴይራ እስከ መመለስ ድረስ አሳሰበው፡፡ በተደጋጋሚ በዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ቢቃረብም ጨክኖ አላደረገውም፡፡ ደጋግሞ ማልቀስ ግን ሥራው ሆነ፡፡ የ14 ዓመት ልጅ ሳለ በመምህሩ ላይ ወንበር ወርውሮ ከትምህርት ቤት በመባረሩ ሙሉ ትኩረቱን በእግር ኳሱ ላይ አደረገ፡፡ ደግሞ ደጋግሞ ልምምዱን ይሰራል፡፡ በክለቡ ውስጥ ዝናው እያደገ ሄደ፡፡ የ17 ዓመት ልጅ ሳለ የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ጨዋታውን ተጫወተ፡፡ ለስፖርቲንግ ሊዝበን የመጀመሪያ ጎሉን ሲያስቆጥር እናቱ ከልክ ባለፈ ከመደሰታቸው የተነሳ የህክምና እርዳታ አስፈልጓቸዋል፡፡

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ አሌክስ ፈርጉሰን ለልጁ ችሎታ ትኩረት ሰጡ፡፡ ካዩዋቸው ወጣት ተጨዋቾች ሁሉ እጅግ የተደነቁበት ሆነ፡፡ ስለዚህ በተጠየቀው ተመን ሊያስፈርሙት ቆረጡ፡፡ ለእኩዮቹ ተከፍሎ በማያውቅ 12 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ኦልድትራፎርድ አመጡት፡፡ ወደ እንግሊዙ ክለብ ሲዛወር ክርስቲያኖ የጥርሱን ብሬስ አልጣለም፣ ፊቱም ከመጥፎ የቆዳ በሽታ ጋር በተያያዘ ከመጣ ብጉር አልፀዳም ነበረ፡፡ ፈርጉሰን ግን በችሎታው ተማመኑ፡፡ በማንቸስተር ዩናይትድ ታሪክ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠውን የክዋክብቱን 7 ቁጥር ማሊያ አለበሱት፡፡ በጆርጅ ቤስት፣ ኤሪክ ካንቶና እና ዴቪድ ቤካም ቦታ ሌለው ባለጊዜ ተተካ፡፡ ‹‹7 ቁጥር ማሊያን መልበስ›› ይላል ሮናልዶ ‹‹ክብርና ታላቅ ኃላፊነት ነው››

ኦገስት 16 ቀን 2003 ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኦልድ ትራፎርድ የመጀመሪያውን ጨዋታ አከናወነ፡፡ ሰር አሌክስ በግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩትም ‹‹ደጋፊዎች አዳኝ እንደመጣላቸው ወዲያውኑ ተረዱ፡፡ ልዩ ተሰጥኦውም ሳይውል ሳያድር ታወቀ››

ሮናልዶ ግን ያልተጠረገ አልማዝ ነበር፡፡ በሜዳ ላይ የሚያሳያቸው አንዳንድ የጨዋታ ባህሪያት አሰልጣኙን ሊያስደስቱት አልቻሉም፡፡ ይጮሃል፤ ከኳስ ጋር አላስፈላጊ ጊዜ ያባክናል፡፡ ለታታ የሚሆኑ አብዶዎችን ለመፈፀም ይሞክራል፡፡ ይህ በፈርጉሰን አይን ተገቢ ያልሆነና ውጤታማም አይደለም፡፡ ምን ያህል ጥሩ ተጨዋች መሆኑን ለህዝብ ለማሳየት የሚያደርገው ጥረት የማደጊያው መንገድ አልነበረም፡፡ ሰር አሌክስ ሊገሩት ተነሱ፡፡ ሮናልዶም ደካማ ጎኑን እየጣለና ጠንካራውን ጎኑን እያጎለበተ በመሄዱ ላይ አተኮረ፡፡

የማንቸስተር ዩናይትድ ህይወቱ ተጀምሮ የዝናውን መንገድ እንደጀመረ በግል ህይወቱ ሀዘን ገጠመው፡፡ ለእግርኳስ ስኬቱ ብዙ የለፉት አባቱ በሞት ተለዩት፡፡ ዲኒስ በጉበት በሽታ ለህልፈት ሲበቁ የ20 ዓመቱ ሮኒ ልብ በሀዘን ተሰበረ፡፡ የአባቱ ሞት በህይወቱ የማይሽር ጠባሳ ትቶ አለፈ፡፡ በግለ ማስታወሻ መጽሐፉ ላይም እንዳሰፈረው እስካሁንም ድረስ ያልሻረ ቁስል ፈጥሮበታል፡፡ የአባቱን ጤና ያቀወሰውና በኋላም ለህልፈት ያደረሰ በመሆኑ ሮናልዶ እስካሁንም አልኮል እንደማይጠጣ ይናገራል፡፡ ‹‹አባቴ አሁንም በህይወት ያለና አብሮኝ ያለ ያህል ይመስለኛል፡፡ አስበዋለሁ፡፡ እንዴት እንደሆነ ልገልፀው ባልችልም እስካሁን ድረስ አንዳንድ ጊዜ ምክሩን እሰማለሁ››
ሀዘኑ ጥሎት ያለፈው ቀዳዳ በብዙ መልኩ በሰር አሌክስ ተሞልቷል፡፡ 7 ቁጥሩ በማንቸስተር ዩናይትድ በቆየባቸው ሰባት ዓመታት አጨዋወቱን አጎልብቷል፣ በስሏል፡፡ በርካታ ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ክለቡ ተደራራሚ ዋንጫዎችን እንዲያነሳ አስችሎታል፡፡ በግሉም በ2008 የመጀመሪያውን ባሎን ዶሩን አግኝቷል፡፡ የሮናልዶ ታላቁ ጥንካሬ አዕምሮውና የትኛውንም አይነት ተጋጣሚ ከኳስ ጋር መጋፈጥ መሆኑን ሰር አሌክስ ተገነዘቡ፡፡ ‹‹ጉብዝና በተለያዩ መልኮች ይገለጣል፡፡ (የሮናልዶ አይነቱ የአዕምሮ ጉብዝና) ግን እጅግ ምርጡ ነው፡፡ በግንብ አጥር መሀል የሚሮጡ ሰዎች፣ ከባድ ሸርተቴዎችን ተጋፍጠው የሚጫወቱ፣ ጭንቅላታቸው ተፈንክቶ ትግላቸውን የማያቆሙ ተጨዋቾች አሉ፡፡ ሁል ጊዜ ኳስን ይዞ ለመሄድ የሚያስችል ድፍረት ግን ከሁሉም የላቀው ጉብዝና ነው››

ከፍ ያለ የስኬት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደሚመኝ ማንኛውም ወጣት በመጨረሻ ሮናልዶ የአባት ያህል ከሆኑለት ሰው መለየት ነበረበት፡፡ በ2009 ማንቸስተር ዩናይትድ ከሪያል ማድሪድ የቀረበለትን 133 ሚሊዮን ዶላር ለመቀበልና ኮከቡን ልጁን ወደ ስፔን ለመላክ ተስማማ፡፡ በወቅቱ ለአንድ የእግርኳስ ተጨዋች ዝውውር ያን ያህል ገንዘብ ተከፍሎ አያውቅም፡፡ ከዚያ ዋጋ ጋር ቢመጣም ሮናልዶ የተጠበቀውን ያህል ከመሆን ያገደው ነገር አልነበረም፡፡ ጎሎችን በጎሎች ላይ ማዝነቡን ቀጠለ፡፡ የበለጠው ሮናልዶ በሪያል ማድሪድ ማሊያ ታየ፡፡ ለሪያል የመጀመሪያ የውድድር ዘመን 33 ጎሎችን አገባ፡፡ በቀጣዩ ዓመት 55፣ ከዚያም 55…፡፡

የሮናልዶ የሪያል ማድሪድ ህይወት የስኬት ጣሪያን የነካው ባለፈው ግንቦት በሊዝበን የከተማ ተቀናቃኛቸውን አትሌቲኮ ማድሪድን ድል በማድረግ ቻምፒዮንስ ሊግን ሲያሸንፉ ነበር፡፡ ሮናልዶም ሪል ማድሪድን ለፍፃሜ ለማብቃት 16 ጎሎች አግብቷል፡፡ በውድድሩ ላይ ያሳየው ብቃት አድናቆት የሚያንሰው ነበር፡፡ በፍፃሜውም ጨዋታ ውጤቱ 3-1 ሳለ ወደ መጨረሻ በፍፁም ቅጣት ምት አንድ ጎል አስቆጥሯል፡፡ ጎሉ የተለየ ትርጉም ባይኖረውም ሮናልዶ ማሊያውን በማውለቅ፣ ጡንቸውን በማሳየትና እንደ ሃልክ ሆገን ኃይል የተሞላበትን የደስታ አገላለፅ ከጩኸት ጋር በማሳየት መወያያ ርዕስ ፈጥሯል፡፡ ትዕይንቱ ጥንካሬውንና አንዳንድ ሰዎች የማይወዱለትን የእዩኝ እዩኝ ባህሪውን በአንድ ጊዜ ያሳየበት ትክክለኛው የሮናልዶ መገለጫ ነበር፡፡ ሪያል ማድሪድ የአውሮፓ ሻምፒዮን በሆነበት ምሽት ከእርሱ በቀር ንጉስ በዚያ ስታዲየም ውስጥ አልነበረም፡፡

ሊጋን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ሮናልዶ ወደ ሪያል ማድሪድ ከመጣ ወዲህ እንደ ተጨዋች ብቻ ሳይሆን እንደሰውም እጅጉን መጎልበቱን ይመሰክራሉ፡፡ በማንቸስተር ዩናይትድ ሳለ አብረውት ከነበሩት መጥፎ ልማዶቹ ብዙዎቹ ተወግደዋል፡፡ የተጫዋቹ የረጅም ጊዜ ፊዚዮቴራፒስት አንቶኒዮ ጋስፐር ‹‹ሮናልዶ የላቀ ስፖርተኛና በሜዳ ላይም እውነተኛ መሪ ሆኗል›› ይላል፡፡ ‹‹መሻሻሉን ሳይ እደሰታለሁ፡፡ አሁንም ጠንካራ እና ፈጣን ነው፡፡ የቴክኒክ ችሎታው አስደናቂ ቢሆንም ከቀድሞ የበለጠ በብልጠት ይጫወታል፡፡ ጠንካራ ጎኖቹን በተሻለ ሁኔታ የመተቀም ብስለትንም አዳብሯል›› በማለት የማዴይራውን ልጅ ይገልፀዋል፡፡ አካላዊ ብቃቱና ተሰጥኦው የብቃት ጣሪያን በነኩበት ሰዓት ላይ ይገኛል፡፡ በኢስፔኤን ቴሌቪዥን በላ ሊጋ ላይ የሚሰራው ግራሃም ሃንተር በበኩሉ ‹‹የላቀ ክህሎት የተፈጥሮ ስጦታ ሳይሆን የጥረት ውጤት መሆኑን ያሳየ ስፖርተኛ ሆኗል›› ባይ ነው፡፡

በእርግጥ ከዚህ በተቃራኒ አንዳንዶች የሮናልዶ በራስ መተማመንና በፍፁምነት ጽንፍ ላይ ለመድረስ ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያስቻለው ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ፍፁም ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት ያቆመ ዕለት ብቃቱ ማሽቆልቆል ይጀምራል›› ይላል የቢኢን ስፖርቱ ሃድሰን፡፡ ‹‹በውስጡ ለሚቀጣጠለው የስሜት እሳት ነዳጁ እብሪቱ ነው፡፡ ለስኬት የሚያተጋውን ውስጣዊ ኃይል ያባብስለታል፡፡ ጫና ታላላቅ ተጨዋቾችን ሳይቀር ያጠፋል፡፡ ሮናልዶ ግን እንደ አልማስ ሃብሉ ለብሶት ተላምዶታል››

በሪያል ማድሪድ የክርስቲያኖ ህይወት በልዩ የተፎካካሪነት ስሜትም የሚገለፅ ነው፡፡ በዚሁ ዘመን እግርኳስ ሌላውን አብሪ ኮከብ አግኝቷል፡፡ ‹‹ቁንጮው›› በሚለው ቅጽል የሚታወቀው ሊዮኔል ሜሲ ከሮናልዶ የተለየ አካላዊ ተፈጥሮ፣ የጨዋታ ዘይቤና ሰብዕና ያለው ተጨዋች ነው፡፡ የባርሴሎናው አጥቂ በክለብ እግርኳስ ላይ ባለ ተፅዕኖ ሲሆን ሮናልዶ በብቃቱ ልቆ እንዳይታይ የራሱን የፉክክር ጥላ አጥልቶበት አራት ጊዜ ባሎን ዶርን በተከታታይ አሸንፏል፡፡ የሜሲን የበላይነት ሰብሮ ልቆ መገኘትም የሮናልዶ አላማ ሆኖ ቆይቷል፡፡

አሁን ሮናልዶ ከሜሲ ጋር መነጻፀሩ ሰልችቶታል፡፡ ስለ ንፅፅሩ ሲጠየቅ ‹‹እኔ የምወዳደረው ከሜሲ ጋር አይደለም፡፡ ከራሴ ጋር እንጂ›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ‹‹ከሌሎች ጋር ከመፎካከር ይልቅ በራሴ ጨዋታ ላይ ማተኮርን እመርጣለሁ››

የሮናልዶ የሜዳ ላይ ብስለት ከሜዳ ውጭም ባለው ህይወቱም ይበልጥ ይደፋል፡፡ ዛሬ ክርስቲያኖ የልጅ አባት ነው፡፡ ጁላይ 3 ቀን 2010 ሮናልዶ በፌስቡክና በትዊተር ገፆቹ ላይ አዲስ ዜና አስነበበ፡፡ የወንድ ልጅ አባት መሆኑ ደስተኛ እንዳደረገው ገለፀ፡፡ የሮናልዶን ዙሪያ ለሚከታተሉ ዜናው ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ሳይታሰብ ይፋ የሆነው መረጃ ግን ጥያቄን ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ዕድለኛዋ ሴት ማን ትሆን? የፍቅር ጓደኛው ኢሪና ሻይክ ነፍሰ ጡር ሆና አልታየችም፡፡ ታዲያ የልጁ እናት ማን ናት? ተባለ፡፡

ሮናልዶ ‹‹ምስጢሩን ለእኔ ተዉት›› ቢልም ዓለም ዝም ማለትን አልመረጠም፡፡ ታብሎይድ ጋዜጦች የተለያዩ መረጃዎችን እየመዘዙ ዘገቡ፡፡ የህፃኑ ስነ ህይወታዊ እናት ካልሆነች ሴት በማህፀን ኪራይ ብቻ የተወለደ ነው የሚለው መረጃ አንደኛው ነው፡፡ በአንድ ምሽት ድንገተኛ ወሲብ የተረገዘ ነው የሚለው ሌላኛው ጥርጣሬ ነው፡፡ ለዚህ መረጃ እንደ ማጠናከሪያ የሚቀርበው እናት በድጋሚ ልጄ ብላ መብቷን እንዳትጠይቅና ማንነቷን ይፋ እንዳታደርግ በስምምነት አፍ ማስያዣ ከተጨዋቹ 10 ሚሊዮን ፓውንድ ተቀብላለች መባሉ ነው፡፡ በ2007 ባሳተመው መፅሐፉ ለይ በጋብቻ ከመተሳሰሩ በፊት የልጅ አባት የመሆን ምኞት እንዳለው ገልጿል፡፡ ‹‹ወንድ ከሆነ እኔኑ እንዲመስል እመኛለሁ፡፡ ተመሳሳይ የመልክ ቅጂ እንዲሆን ሳይሆን እንደኔ የእግርኳስ ዘረመል በውስጡ ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ መመሳሰሉ በቀላሉ የሚለይ እንዲሆንም እፈልጋለሁ›› ብሏል፡፡

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጁንየር ዛሬ አራት ዓመት ሞልቶታል፡፡ ሪያል ማድሪድ የላሊጋውን የመጨረሻ ጨዋታ ባከናወነበት ዕለት ልጁ በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ የመስታወት ትሪቡን ተቀምጦ በሜዳ ላይ አባቱ ያልተሰለፈበትን ጨዋታ ተመልክቷል፡፡ በዲዛይነሮች በተሰሩ የህፃናት ልብሶች ዘንጦና ፀጉሩንም በዘይቤ ተበጥሮ አስተናጋጆች ጭማቂዎችንና የኢቤሪያን ሳንድዊች በሚያቀርቡበት ትሪቡን ወዲያ ወዲህ ሲል ታይቷል፡፡ በዕለቱ ልጁን የመጠበቁ ኃላፊነት ለሮናልዶ እና ዶሎሬስ የተተወ ጉዳይ ነበር፡፡ ልጁ አባቱን ይመስላል፡፡ ሮናልዶም ለል የተሰጠ ሰው ነው፡፡ ‹‹አባትነት እጅግ ደስ የሚል ነገር ነው›› ይላል፡፡ ቀጥሎም ‹‹ልጄ ዘወትር ደስታን ይሰጠኛል፡፡ ዘወትር ህልምን የመኖር ያህል ነው›› በማለት የትንሹ ሮናልዶ ወደዚህ ዓለም መምጣት በህይወቱ ላይ የጨመረለትን ዋጋ ይገልፃል፡፡

በዙሪክ ስዊዘርላንድ አንድ ብርዳማ ምሽት ብራዚላዊው ፔሌ ከተሰበሰቡ እንግዶች ፊት በመድረክ ላይ ቆመ፡፡ የ2014 ፊፋ ባሎን ዶር ሽልማት ስነ ስርዓት ነበር፡፡ የብራዚል እግርኳስ ፓትሪያክ በመድረኩ ላይ የተገኘው የዓመቱን የዓለም የእግር ኳስ ኮከብ አሸናፊን ሊናገር ነው፡፡ በተጠናቀቀው የካሌንደር ዓመት የላቀ ብቃት ያሳየ ተጨዋች ይሸለማል፡፡ ፔሌ ኤንቬሎፑን ሲከፍት የቴሌቪዥን ካሜራዎች በሶቱ ዕጩዎች ፊት ላይ አረፉ፡፡ ፍራንክ ሪቤሪ፣ ሊዮኔል ሜሲና ክርስቲያኖ ሮናልዶ፡፡ የፖርቹጋሉ ኮከብ ፍቅረኛውን ከጎኑ አድርጎ በልዩ ሙሉ ልብስ ዘንጧል፡፡ የፔሌ ድምፅ ተሰማ፡፡ ‹‹…ክርስቲያኖ ሮናልዶ››
ሮናልዶ ኢሪናን ሳመና ከመቀመጫው ተነስቶ ፔሌን ለማቀፍ ወደ መድረኩ አመራ፡፡ ከዚያ ዘናጭ ልጁ ወደ መድረኩ ተከተለው፡፡ ሮናልዶ ከእንባ ጋር እየታገለ ‹‹ሁላችሁንም አመሰግናለሁ›› አለ፡፡ በአይኑ ላይ እንጥፍጣፊ እብሪት እንኳን አልቀረም፡፡ ትህትና እና ብስለት ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ድምፁ በስሜት እንቅፋት ይቆራረጣል፡፡ ቤተሰቡን አመሰገነ፡፡ እናት በኩራት ፊታቸውን በመረሃረብ ሲጠራርጉ እንኳን አይኖቻቸውን ከልጆቻቸው አልተነቀለም፡፡ ሮናልዶ ሽልማቱን ሁሉም እንዲያየው ከፍ አደረገው፡፡ የወርቅ ኳሱ የኋላ ማረፊያው በፉንቻል በሚገኘው የግል ሙዚየሙ መሆኑ እርግጥ ነበር፡፡ ‹‹እኔን የሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ስንት ሰዎች እንደረዱኝ ያውቃሉ፡፡ የረሳሁት ካለ ይቅርታ እጠይቃለሁ››

የሜሲ ዘመን (ቢያንስ ለዘንድሮ) ፍፃሜ ለማግኘቱ የታወጀ አዋጅ ነበር፡፡ ህይወት ግን በ2013 ብቻ አትገደብም፡፡ ፉክክሩ ይቀጥላል፡፡ በቅርቡም የ2014 15 ላሊጋ ይጀምራል፡፡ ‹‹ጭንቀታሙ›› ሮናልዶም ‹‹ከቁንጫው›› ጋር ባላንጣነቱን ያድሳል፡፡ አሁንም ከሜሲ በላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ የብቃትን ፅንፍ ለመጨበጥ ይተጋል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>