Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ያለ መድሃኒት! የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የሚረዱ 10 መንገዶች

$
0
0

እነዚህን 10 የአኗኗር ዘዬዎች በመከተል የደም ግፊትዎን እና በልብ ህመም የመጠቃት ዕድልዎን ይቀንሱ

ከዚህ ቀደም በደም ግፊት ሕመም ተጋልጠው (ከ140/90 ወይም ከዛ በላይ) ሆኖ አስጨንቆዎት ነበር? ይህን ቁጥርም ለመቀነስ በተደጋጋሚ የህክምና ተቋም ደጅ ረግጠውም ይሆናል፡፡
ጤናማ የአኗኗር ዘዬዎች ይህን ከፍ ያለ የደም ግፊት ለመቀነስ ይህ ነው የማይባል ሚና ይጫወታሉ፡፡ በእነዚህ አስር የአኗኗር ዘዬዎች የደም ግፊትዎን ይቆጣጠሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሐኪም ቤት የሚመላለሱበትን ጊዜም ሊቀንሱ ብሎም ፈፅሞ ሊያስቀሩ ይችላሉ፡፡
‹‹እንዴት ተደርጎ?›› አሉ?
እስቲ እነዚህን 10 የህይወት ዘዬዎችን ይሞክሯቸው፡፡
highbloodpressure
1. ክብደትዎን ይቀንሱ
አብዛኛውን ጊዜ የደም ግፊት የክብደት መጨመርን ተከትሎ ሽቅብ ይምዘገዘጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ 4.5ኪሎ ብቻ መቀነስ እንኳን የደም ግፊትን ይቀንሳል፡፡ ብቻ ምን አለፋዎ ክብደትዎን በቀነሱ መጠን በተጓዳኛ የደም ግፊትዎንም እየቀነሱ ነው፡፡ ሐኪምዎ ጋርም ጎራ ካሉ በምን ያህል ጊዜ ምን ያህል መቀነስ እንደሚኖርብዎት ስለሚያማክርዎ ውጤቱ የተሻለ አመርቂ ይሆንለዎታል፡፡
ክብደት የመቀነሱ ነገር ላይ ተፍ ተፍ ሲሉ ታዲያ በወገብዎ ዙሪያ ያለውንም ቦርጭ ችላ አይበሉት፡፡ እሱ ነገር ለከፍተኛ የደም ግፊት የማጋለጥ ዕድሉ ሰፋ ያለ ነው፡፡ ለመሆኑ የወገብዎ ስፋት ምን ያህል ሴንቲ ሜትር ይሆናል? የማይጠየቅ ጠየቅን ይሆን? እስቲ ይለኩት፡፡
ወንድ ከሆኑ የወገብዎ ስፋት 102 ሴንቲ ሜትር፣ ሴት ከሆኑ ደግሞ 89 ሴንቲ ሜትርን ከዘለለ የደም ግፊት በዙሪያዎ እያንዣበበ ነውና ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ የተቻለዎትን ያህል የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ ይውሰዱ፡፡

2. መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ
ቢያንስ ከ30-60 ደቂቃ ከሳምንቱ ቀናት አብዛኛውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ ከ4-9 ያህል Millimeters of Mercury የደም ግፊትዎን ይቀንሳል፡፡ ልዩነቱንም በአጭር ጊዜ ያስተውሉታል፡፡ ፈጣን ባይሆኑ እንኳን የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎን አያቋርጡ፣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የደም ግፊትዎ መቀነስ ይችላሉ፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት ካለብዎት የላይኛው ከ120-139 የታችኛው ደግሞ ከ80-89 ከተመዘገበ ጉዳት እንዳያደርስብዎ እና ወደ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳይሻገር መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ታዲያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴውም ቢሆን በእቅድ እና በሐኪምዎ ጋር በመመካከር ቢያደርጉት የተሻለ ይሆናል፡፡ ምናልባትም ሊደፍሩት የማይገባ እንቅስቃሴን በዘፈቀደ አድርገው ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆን፡፡ ምን አይነቱን እንቅስቃሴ ለምን ያህል ሰዓት ማድረግ እንዳለብዎት መመካከሩ አይከፋም፡፡ እርስዎ ጂም ገብተው ኤሮቢክሱን ከአቅምዎ በላይ ሲያጣድፉት ምናልባትም የ20 ደቂቃ የእግር ጉዞ ይበቃዎት ይሆናል፡፡
የእረፍት ቀናትን ተከትሎ ከሚመጣ የበዛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ያስወግዱ፡፡ የሳምንቱን ሁሉ በአንድ ቀን እወጣዋለሁ በሚል ስልት አንድ ቀን የሚደረግ የእንቅስቃሴ ጋጋታ አያዋጣም፡፡ እንዲያውም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

3. ጤናማ አመጋገብ ይኑርዎት
በጥራጥሬ እና ፍራፍሬ እንዲሁም አትክልት የበለፀጉ እና አነስተኛ የቅባት መጠን ያላቸውን የወተት ተዋፅኦ መመገብ፣ ቅባት የበዛባቸውን እና ኮሌስትሮል ነክ ምግቦችን መቀነስ የደም ግፊትን እስከ 14 Millimeters of mercury ያህል ይቀንሳል፡፡ ይህ የአመጋገብ አይነትም “Dietary Approaches to stop Hypertension (DASH)” ወይም ‹‹የደም ግፊትን ለማቆም የሚረዳ የአመጋገብ ዘዴ›› በመባል ይታወቃል፡፡ እርግጥ ነው የአመጋገብ ልማድን መቀየር ቀላል አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን በሚከተሉት ሐሳቦች በመታገዝ ጤናማ አመጋገብን መለማመድ ይቻላል፡፡
– የምግብ መዝገብ ይኑርዎት፡- የሚመገቡትን ይፃፉ፡፡ ቢያንስ ለሳምንት ይህንን ያድርጉ፡፡ ያኔ በእርግጥ የአመጋገብ ልማድዎ ምን እንደሚመስል በመገረም ይገነዘባሉ፡፡ ምን እንደሚመገቡ፣ ምን ያህል እንደሚመገቡ፣ መቼ እና እንዴት እንደሚመገቡም መቆጣጠር ይችላሉ፡፡
– ፖታሺየም ያብዙ፡- ፖታሺየም ሶዲየም በደም ግፊት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ይቀንሳል፡፡ ፖታሺየምን ፍራፍሬ እና አትክልት ከመሳሰሉ ምግቦች ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ለእርስዎ ተመጣጣን የሆነ ፖታሺየም ምን ያህል መሆኑን ለማወቅ ታዲያ ሐኪምዎን ማማከርዎን እንዳይረሱ፡፡
– ብልህ ገበያተኛ ይሁኑ፡- ‹‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት›› ተብሎ እንዳይተረትብዎ ወደ ገበያ ሲወጡ ለመግዛት የሚፈልጉትን መዝግበው ይያዙ፡፡ ይህን ማድረግዎ ፊት ለፊትዎ ያገኙት ሁሉ የቦርሳዎ ወይም የኪስዎ አቅም እስከፈቀደ ከማጋበስ ይድናሉ፡፡ በተጨማሪም የታሸጉ ምግብ ነክ ነገሮችን ሲገዙ እላያቸው ላይ የተፃፈውን ማስረጃ አገላብጠው ያንብቡና ከእርስዎ ጤናማ አመጋገብ ጋር የማይጣረስ መሆኑን ያረጋግጡ፡፡ ይህን የሚያደርጉ ‹‹ብልህ ገበያተኛ›› ይባላሉ፡፡
– አንዳንዴም ላላ ያድርጉት፡- ‹‹ምኑን?›› አሉ፤ ይህ የደም ግፊትን ለማቆም የሚረዳ አመጋገብ ዘዬ ‹‹Dietary approaches to stop hypertension›› ለዕድሜ ልክ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን እጅግ ከሚወዷቸው ምግቦች ጨርሶ ይቆራረጡ ማለት አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ ለአምሮት ያህል ከዚህ የአመጋገብ ስርዓት ውጪ የሆነ ከረሜላም ሆነ የተፈጨ ድንች ያለበት መረቅ ቀመስ ቀመስ ቢያደርጉ ክፋት የለውም፡፡

4. ሶድየምን ከምግብዎ ይቀንሱ
ሌላው ቀርቶ መጠኑ ትንሽ የሆነ ሶዲየም ከምግብዎ ሲቀነስ የደም ግፊትን ከ2-8 Millimeters of mercury ያህል ይቀንሳል፡፡
– በቀን ከ2300 ሚሊ ግራም በታች ሶዲየም ብቻ ይውሰዱ፡፡
– በተለይ ዕድሜያቸው ከ51 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች፣ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ አፍሪካ- አሜሪካውያን፣ ከፍተኛ ደም ግፊት ላለባቸው እንዲሁም ደግሞ ስኳር እና ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ላለባቸው ሰዎች በቀን 1500 ሚሊ ግራም በላይ ሶዲየም እንዲመገቡ አይመከርም፡፡
ሶዲየም ለመቀነስ…
በምግብዎ ውስጥ ምን ያህል የጨው መጠን እንዳለ ይድረሱበት፡- የምግብ መዝገቡ በየዕለቱ ምግባችን እና መጠጣችን ውስጥ ምን ያህል ሶዲየም እንደተጠቀምን ለማወቅ ያግዛል፡፡
የታሸጉ ምግቦች የተለጠፈባቸውን ማስረጃ ያንብቡ፡- ከቻሉም የሶዲየም መጠናቸው አናሳ የሆነ ምግቦችን እና መጠጦችን መርጠው ይግዙ፡፡
ብዙም በምግብነት ሂደት ውስጥ ያሳለፉ ምግቦችን ይመገቡ፡- የድንች ጥብስ እጅግ የቀዘቀዙ ምግቦች፣ በእንፋሎት የደረቁ ስጋዎች እና የመሳሰሉት… በምግብነት ሂደት ባለፉበት መንገድ ከፍተኛ ሶዲየም ይይዛሉ፡፡
ጨውን ያስወግዱ፡- 1 የሻይ ማንኪያ ጨው 2300 ሚሊ ግራም ሶዲየም አለው፡፡ ለምግብዎ ጣዕም ለመስጠት ከጨው ይልቅ ቅጠላ ቅጠል እና ቅመማ ቅመሞችን ይጠቀሙ፡፡
ይመችዎት፡- በምንም ተአምር ሶዲየምን በአንድ ጊዜ ከምግብዎ ማስወገድ ካልቻሉ አይጨነቁ፣ በጊዜ ሂደት ሊጠፋ ይችላል፡፡ ጉሮሮዎትም ቢሆን ቀስ በቀስ ጣዕሙን ይለምደዋል፡፡

5. የሚወስዱትን የአልኮል መጠን ይቀንሱ
እርግጥ ነው አልኮል በጤና ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በጥቂቱ ከተወሰደ በተወሰነ መልኩ የደም ግፊትን የመቀነስ አቅም አለው፡፡ ከመጠን በላይ መውሰዱ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና አይመከርም፡፡ ሴቶች እና ዕድሜያቸው 65ን የተሻገሩ ወንዶች በቀን 1 ብርጭቆ በቂ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ65 በታች ለሆኑ ወንዶች 2 ብርጭቆ እንዳይዘሉ ይመከራሉ፡፡ አልኮልን የመጎንጨት ልማድ ፈፅሞ ከሌለዎ ግን ‹‹ደም ግፊቴን አስተካክላለሁ›› በሚል ምክንያት እንዳይሞክሩት፡፡ አደራ፡፡ ያንን ቢያደርጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና ኋላ ማጣፊያው እንዳያጥር፡፡ ከመጠን ካለፉም የደም ግፊትዎ ለመቸመሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱለት መሆኑን አይዘንጉ፡፡ የመድሃኒቶቹንም ፈዋሽነት አዳክሞ ለከፋ ጉዳትም ይዳርጋል፡፡
– የአጠጣጥ ልምድዎን ይቆጣጠሩ፡- (ይሄ ነገር ሜኑ መሰለ ካላሉ) ከምግብ መዝገብዎ ጎን ለጎን የመጠጥ ዝርዝርዎንም ቢያሰፍሩ ጤናማ አጠጣጥን ሊቀይሱ ይችላሉ፡፡ አንድ ጊዜ ሊጠጡ የሚፈልጉት ቢራ ከሆነ 355 ሚሊ ሊትር፤ ወይን ከሆነ ደግሞ 148 ሚሊ ሊትር ሌሎች የአልኮል ይዘት ያላቸውን ከ45 ሚሊ ሊትር በላይ የሚወስዱ ከሆነ ይቀንሱ፡፡
– ቀስ በቀስ ይቀንሱ፡- ከአልኮል በእጅጉ ተቆራኝተው ከነበረ በአንድ ጊዜ እርግፍ አድርጎ መተው ለቀናት የሚዘልቅ የደም ግፊትን ሊያስነሳ ይችላልና አቀናነሱ ብልሃት የተሞላበት እንዲሆን የባለሙያ እርዳታን ይሻል፡፡ ከሐኪምዎ ጋር በመመካከር ከቀን ወደ ቀን ከሳምንት ወደ ሳምንት በሂደት ይቀንሱ፡፡
– መጠንዎን አይለፉ፡- ከ4 ብርጭቆ በላይ አልኮል መጠጣት ለሌሎች የጤና ችግሮች ከማጋለጡ በተጨማሪም የደም ግፊትዎን ባልተጠበቀ እና ከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምረው ይችላልና አይሞክሩት፡፡
አያጭሱ፣ በአጫሾች ዙሪያም አይገኙ
ትንባሆ ሌሎች በርካታ ጉዳቶች እንዳሉት ሆኖ በውስጡ የያዘው ኒኮቲን የተባለ ንጥረ ነገር አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የደም ግፊትዎን ከፍ ያደርጋል፡፡ በተለይ በየቀኑ የሚያጨሱ የለየልዎት ከከፍታው ሳይወርድ ይቆያል፡፡
ብዙዎቻችን አለማጨሳችንን እንጂ ለሲጋራ ጭስ አለመጋለጣችንን ትኩረት አንሰጠውም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሲጋራ በሚጨስባቸው አካባቢዎች መገኘትም ከአጫሹ እኩል የኒኮቲን መጠንን ወደ ሰውነት ማስገባት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የደም ግፊትን እና የልብ ህመምን ጨምሮ ለሌሎች የጤና ችግሮች ሁሉ ያጋልጣል፡፡

7. ካፌይን ይቀንሱ
በቡና እና መሰል መጠጦች ውስጥ የሚገኘው ካፌይን የተባለው ንጥረ ነገር በደም ግፊት ላይ ያለው አስተዋፅኦ እስካሁን ድረስ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ካፌይን ያለባቸውን መጠጦች መጠጣት የደም ግፊትዎን ለጊዜውም ቢሆን በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊጨምረው ይችላል፡፡ አወዛጋቢው ነገር ይህ ተፅኖው ‹‹ለጊዜው ብቻ ነው?›› ወይስ ‹‹ለዕድሜ ልክ?›› የሚለው ነው፡፡
እርስዎ ይህንን ይሞክሩ እስቲ…
ቡና በጠጡ በ30 ደቂቃ ውስጥ የደም ደግፊትዎን ይለኩ፡፡ ቁጥሩ ከወትሮው ከ5-10 ጨምሮ ከተገኘ ካፌን ለደም ግፊትዎ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋልና ባያዘወትሩት ደግ ነው፡፡

8. ጭንቀትዎን ይቀንሱ
ጭንቀት ለጊዜውም ቢሆን የደም ግፊትን ይጨምራል፡፡ ምን ይሆን የሚያስጨንቅዎት? ስራ? ቤተሰብ? የንዘብ እጥረት? ወይስ ጤና ማጣት? እስቲ ጊዜ ወስደው ያስቡበት፡፡ አንዴ የጭንቀትዎ መንስኤ ምን እንደሆነ ካወቁት እንዴት መቀነስ ወይም ማስወገድ እንዳለብዎት ይረዳሉ፡፡ ያንን ማድረግ ካልቻሉ ግን ቢያንስ ችግሮቹን መቀበል እና በጤናማ መንገድ እንዴት አብሮ መቀጠል እንደሚቻል መላ ማበጀቱ አያቅትዎም፡፡ የጥልቅ አተነፋፈስ ልምምድ በማድረግ ፋታ ይውሰዱ፡፡ ማሳጅ ይደረጉ ወይም ዮጋ እና ተመስጥኦ ለዚህ ጥሩ መፍትሄ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ በዚህ መንገድ ራስን የመርዳቱ ሙከራ ካልተሳካ በሙያው የሰለጠኑ አማካሪዎችን መጎብኘት ያሻል፡፡

9. የደም ግፊትዎን ከቻሉ በቤትዎ ይቆጣጠሩ፤ በመደበኛነትም የሐኪም ክትትል ይኑርዎት
ከፍተኛ የደም ደግፊት ካለብዎት የደም ግፊትዎን በቤትዎ መቆጣጠር ሳያስፈልግዎ አይቀርም፡፡ በላይኛው የክንድ ክፍል የሚታሰረው መቆጣጠሪያም ጥቂት ቢማሩት የራስዎን ደም ግፊት ራስዎ ለመቆጣጠር የማያስቸግር ነው፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ሐኪምዎን ያናግሩና ይጀምሩት፡፡ ምናልባት በቋሚነት ሐኪምዎን መጎብኘትዎ መደበኛ ክንውንዎ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ጉብኝትም የደም ግፊትዎ ያለበትን ደረጃ በግልፅ ለማወቅ እና ለመረዳት ይረዳዎታል፡፡
– በቋሚነት የሚከታተልዎት ሐኪም ይኑርዎት
እንዲህ ያለ ሐኪም የሌላቸው ሰዎች የደም ደግፊታቸውን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኖ ያገኙታል፡፡ ቢቻል በቋሚነት አንድ የህክምና ተቋምና ሐኪም ለአስፈላጊው የጤንነት እንክብካቤ ቢጎበኙ ይመረጣል፡፡
– ሐኪምዎን በቋሚነት ይጎብኙ፡- የደም ግፊትዎ በአግባቡ በቁጥጥር ስር ካልዋለ፤ ተጓዳኝ ህመሞች ካሉብዎ በቋሚነት በየወሩ ሐኪምዎን ማግኘት ያስፈልግዎታል፡፡ የደም ግፊትዎን በአግባቡ መቆጣጠር ከቻሉ ደግሞ ከ6-12 ወራት ባሉት ጊዜ ውስጥ ቢጎበኙ በቂ ይሆናል፡፡ ይህ ታዲያ ባሉበት ሁኔታዎች ላይ የተወሰነ ይሆናል፡፡

10. ከቤተሰብ እና ከጓደኞች እርዳታ ይቀበሉ
በዙሪያዎ ያሉ ጓደኞች እና ቤተሰበቾች ለጤናዎ መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉና ችላ አይበሏቸው፡፡ ራስዎን እንዲንከባከቡ ሊያበረታትዎት፣ ሐኪም ዘንድ ሲሄዱና ሌሎች የደም ግፊትዎን ለመቀነስ በሚረዱ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ አብሮዎት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለ ህመሙ አስከፊነት መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መንገዶችን መወያየትም ቀላል ነገር አይደለም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>