ገረ ኢትዮጵያ
እንደሰማሁት ከሆነ ጥቁር ሳምንት በሚል የተጀመረው ዘመቻ ጥሩ ዘመቻ ነው፡፡ በማህራዊ ሚዲያው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትም ሆነ ጋዜጠኞች በመታሰራቸው እንቅስቃሴው አለመዳከሙ ያስደስታል፡፡ መጭው ዘመን የነጻነት ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያውያን ይህን የመሰሉ እንቅስቃሴዎችን መደገፍ፣ ማበረታታትና መቀላቀል አለባቸው፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን ማህበራዊ ሚዲያው ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡ በግብጽና ቱኒዚያ ማህበራዊ ሚዲያው ቀላል የማይባል ለውጥ አምጥቷል፡፡ ህወሓትና ሌሎችም ታጣቂ ኃይሎች ከቻይና እና ከቬትናም ልምድ ቀስመዋል፡፡ ያ ሌላ ዘመኑ ነበር፡፡ አሁን ዘመኑ ተለውጧል፡፡ ዘመኑ የሰጠንን አጋጣሚ ተጠቅመን ለነጻነታችን በሰላማዊ መንገድ መታገል አለብን፡፡ ጥቁር ሳምንት በሚል የተጀመረውን ዘመቻ በርትታችሁ መቀጠል አለባችሁ፡፡ ወጣቱ፣ ዳያስፖራው፣ ጋዜጠኛው በእንደዚህ አይት ዘመቻዎች፣ በሰላማዊ ሰልፎች፣ ማህበራትን በማቋቋማ፣ በውይይቶች መሳተፍ አለበት፡፡
አንዳንዶች ፌስ ቡክ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ሊገምቱ ይችላሉ፡፡ ከፌስ ቡክ አልፎ በአሁኑ ወቅት ያለው እንቅስቃሴ ለውጥ አያመጣም ብለው የሚገምቱ ይኖራሉ፡፡ ግን ያለ ጥርጥር ለውጥ ያመጣል፡፡ ውሃ በ99ንኛው ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው የሚፈላው፡፡ እስከዛ ድረስ ምንም አይነት ለውጥ አይታይበትም፡፡ ውሃ የሚያፈላ ሰው 99 እስኪደርስ ድረስ ማህል ላይ ተስፋ ቆርጦ ሊተውው ይችላል፡፡ ግን 99 ዲግሪ እስኪደርስ ድረስ የራሱ የሆነ የማይታይ ለውጥ ያደርጋል፡፡ ተስፋ ያልቆረጠ በአንድ ዲግሪ ለውጡን ያየዋል፡፡ በፌስ ቡክ የሚደረጉትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችም ከዚህ አንጻር ነው መታየት ያለባቸው፡፡ ለውጥ የሚመጣው በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ድምር ውጤት ነው፡፡ 99 ዲግሪ እስኪደርስ ለውጡ ላይታይ ይችላል፡፡ ጥቁር ሳምንትን የመሳሰሉት ተደማምረው ነው የሰላማዊ ትግሉን 99 ዲግሪ የሚያደርሱት፡፡ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡
በጥቁር ሳምንት የታሰርነውንና ሌሎች ችግር እየደረሰባቸው የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንን በማስታወሳችሁ በግሌ ማመስገን እወዳለሁ፡፡ ኮርቼባችኋለሁ፡፡ የእኛን መታሰር ብቻ ማንሳቱ አሊያም መጨነቁ በቂ አይደለም፡፡ እንደዚህ በተግባር ንቅናቄ መጀመር አለበት፡፡ ውጤት እናመጣለን፡፡ የሰላማዊ ትግሉ ዲግሪ ሴንቲግሬድ 99 የሚደርስበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡
መልዕክት ለዳያስፖራው
የእኛ አገር ፖለቲካ አንድ ችግር የገንዘብ አቅም ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትን ለማደራጀት፣ ቢሮ ለመክፈት፣ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማካሄድ፣ ውይይቶችን ለማድረግ፣ ልሳንና በራሪ ወረቀት ለማሳተም ገንዘብ ያጥራቸዋል፡፡ የፖለቲካው አንቀሳቃሽ ኃይል ቢሆኑም በገንዘብ ችግር ምክንያት አጀንዳ ማንሳት ይሳናቸዋል፡፡ በቂ አባላት አያገኙም፡፡ ህዝብ ውስጥ ለመግባትም ይቸገራሉ፡፡ ገንዘብ ከሌለ ምንም ሊሰሩ አይችሉም፡፡ ይህ በእኛ አገር ብቻ የሚደረግ አይደለም፡፡ የአሜሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ትግል የገንዘብ ነው፡፡ በምርጫም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች ፓርቲዎቹ ከተለያዩ አካላት በሚያገኙት ገንዘብ ነው ውጤታማ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት ውስጥ የሚኖር እንደመሆኑ የእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአባላቸው አሊያም አገር ውስጥ ከሚገኘው ህዝብ ሰብስበው የተሳካ ስራ ሊሰሩ አይችሉም፡፡ በመሆኑም አማራጭ ሊሆን የሚችለው በዳያስፖራው ነው፡፡ ዳያስፖራው ማህበረሰብ በአገሩ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋል፡፡ በለውጡ ግን ቀጥተኛ ተሳታፊ አይደለም፡፡ ለዚህም አገር ውስጥ ለሚገኙትና በሰላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱትና ለሚደግፋቸው ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው መስዋዕትነት የሚከፍሉትን መደገፍ ካልተቻለ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡
ራዕያችን የማይደረስበት አይደለም
ከ50ና 60 አመታት በፊት ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ ትልቅ እገዛ ያደረገችላቸው አገራት አሁን ዴሞክራሲያዊ ሆነዋል፡፡ ጋና፣ ማላዊና ቤኒንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእነዚህ አገራት ዴሞክራሲ ሲሰፍን እኛ ወደኋላ ተመልሰናል፡፡ ነጻ ፕሬስ አላቸው፡፡ ነጻ ምርጫ ያካሂዳሉ፡፡ ህዝባቸው በነጻነትና በመረጠው መንግስት መተዳደር ጀምሯል፡፡ በተቃራኒው እኛ በአፈና ውስጥ ገብተናል፡፡ እኛ የምንጠይቀው እንደነዚህ አገራት ህዝቦች ነጻ ሆኖ ለመኖር ነው፡፡ የእንግሊዝንና የአሜሪካን ያህል ባይሆንም የእነዚህን አገራት ያህል ዴሞክራሲ ማስፈን ከቻልን ራዕያችን ተሳካ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የጠየቅነው ነገር ትንሽ ነው፡፡ ይህን ያህል የተለጠጠና የማይደረስበት አይደለም፡፡ ነጻ ያወጣናቸውን አገራት ያህል ዴሞክራሲ ለመገንባት መነሳት ትንሽ ነገር ነው፡፡ በመሆኑም በቀላሉ ልናሳካው የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡