Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የጋዜጠኛውን ዓይን በቦክስ መትቷል ተብሎ የታሰረው አርቲስት በዋስ ተፈታ

$
0
0

• ‹‹ያደረግኩት ነገር ኖሮ ሳይሆን ሆን ተብሎ ስሜን ለማጥፋት ነው››

አርቲስት ዳንኤል ተገኝ

በታምሩ ጽጌ

የኢትዮፒካሊንክ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱን ግራ ዓይን በቦክስ በመምታት ጉዳት አድርሶበታል በሚል ተጠርጥሮ የታሰረው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በ3,000 ብር ዋስ ተለቀቀ፡፡

f87ded5e4d4df018eb2f8408a972a0ab_Lበገመና ድራማ ላይ ‹‹ዶ/ር ምስክር››ን ሆኖ በመተወን የሚታወቀው አርቲስት ዳንኤል፣ የተጠረጠረበትን ወንጀል በጋዜጠኛ ግዛቸው ላይ ፈጽሟል የተባለው፣ ነሐሴ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት አካባቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጋዜጠኛው ቦሌ መድኃኔዓለም ሐርመኒ ሆቴል አካባቢ ገልፍ አዚዝ ሕንፃ ካለው የኢትዮፒካሊንክ ቢሮ ወጥቶ ደረጃ በመውረድ ላይ እያለ፣ ተጠርጣሪው ከኋላው ነክቶት ዞር ሲል በሰነዘረው ቦክስ ግራ ዓይኑን መመታቱን ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪው አርቲስት ዳንኤል ለጊዜው ለማምለጥ ቢሞክር፣ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ አስሮ ካሳደረው በኋላ ነሐሴ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ጊዜ ቀጠሮ መስጫ ፍርድ ቤት (የነገው ሰው ትምህርት ቤት አካባቢ) አቅርቦ ስለተጠርጣሪው ሲያስረዳ፣ ተጠርጣሪው ጋዜጠኛውን ባላሰበው ሁኔታ ከፍተኛ ጉዳት በሥራ ቦታው ሄዶ በመደብደብ ያደረሰበት መሆኑንና ከፍተኛ ምርመራ እንደሚያስፈልገው በማስረዳት፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ተጠርጣሪው ካደረሰው የድብደባ ወንጀል አንፃር የ3,000 ብር ዋስ ጠርቶ እንዲለቀቅ በማዘዙ ተጠርጣሪው ከእስር ተለቋል፡፡

ጋዜጠኛው በግራ ዓይኑ ላይ የደረሰበትን ጉዳት ለመታከምና የጉዳቱን መጠን ለማወቅ መጀመሪያ ወደ ቦሌ ጤና ጣቢያ የሄደ ቢሆንም፣ ጤና ጣቢያው ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሪፈር እንደተደረገ ገልጿል፡፡ የየካቲት 12 ሆስፒታል ባደረገው ምርመራ በደረሰበት ምት የዓይኑ ሥሮች የተጐዱ መሆናቸውን በመረዳቱ፣ ለተጨማሪ ምርመራና ሕክምና ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈር አድርጐት በሕክምና ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከአርቲስት ዳንኤል ጋር ለግጭት የዳረጋቸው የተለየ ምክንያት ካለው በሚል የተጠየቀው ግዛቸው በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ከዳንኤል ጋር በግልም ሆነ በሌላ መንገድ ምንም ዓይነት ግጭት የለንም፡፡ አርቲስቱ በሬዲዮ ጣቢያው ሠራተኞች ላይ ሲዝትና ለማጥቃት ሲንቀሳቀስ እንደነበር በሥራ ጓደኞቼ ላይ ካደረገው ሙከራ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በምናቀርበው የሬዲዮ ፕሮግራም፣ በታኅሣሥ ወር 2006 ዓ.ም. አንዲት ባለሀብት ከአርቲስቱ ጋር ፊልም ለመሥራት ተስማምተው ገንዘብ ከከፈሉት በኋላ ፊልሙን እንደማይሠራ ሲነግራቸው፣ የሰጡትን ገንዘብ እንዲመልስላቸው መጠየቃቸውንና ሊከፍላቸው አለመቻሉን የሚመለከት ሪፖርት ሠርተናል፡፡ በዚያን ወቅት ለምን ሠራችሁ? በሚል ቢሮ ድረስ በመምጣት ለመደባደብ መሞከሩን ብቻ ነው የማስታውሰው፤›› ብሏል፡፡

ድብደባ በመፈጸም የተጠረጠረው ዳንኤል ተገኝ ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹በጋዜጠኛው ላይ ምንም የፈጠርኩት ጉዳት የለም፡፡ ሆን ተብሎ መልካም ስሜን ለማጥፋት የተደረገ ጥረት ነው፤›› ብሏል፡፡

በዕለቱ ነሐሴ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ገልፍ አዚዝ ሕንፃ አካባቢ የሄደው፣ ከአዲስ ዓመት ጀምሮ በመቅዲ ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በተከታታይ የሚተላለፍ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የዶክተር ገፀ ባህሪ ተላብሶ ለሚሠራው ትወና ለመቀረጽ እንደነበር ተናግሯል፡፡

የመቅዲ ፕሮዳክሽን ቢሮ በሚገኝበት ሕንፃ ወደ አምስተኛ ፎቅ በመውጣት ላይ እያለ ከጋዜጠኛው ጋር መገናኘቱን የገለጸው ዳንኤል፣ ‹‹አገኝሀለሁ›› ብሎ ሲዝትበት፣ ‹‹ምን ልትሆን ነው የምትፈልገኝ? አሁን አገኘኸን አይደል?›› እንዳለውና ለመደባደብ ሲያያዙ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች እንደገላገሏቸው አስረድቷል፡፡

ከወራት በፊት በሬዲዮ በሚሠሩት ፕሮግራም ሥነ ምግባሩን ባልጠበቀ ሁኔታ ስሙን በማጥፋታቸው በማዕከላዊ ክስ መሥርቶ ጉዳዩ በሒደት ላይ መሆኑን የገለጸው ዳንኤል፣ ሥራውን የመቃወም መብት ባይኖረውም፣ መብቱን ግን በሕግ ለማስከበር በክስ ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ቦክስ ሲሰነዝርበት እሱም በወቅቱ ምን እንዳደረገ ባያስታውስም፣ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ‹‹አንተ ስለምትታወቅ ስምህን ሊያጠፋ ፈልጐ ነው›› ሲሉት ሁሉንም ነገር ትቶ ወደ ቢሮ የገባ ቢሆንም፣ ቆይቶ ከቢሮ ሲወጣ ግዛቸው ድንጋይ ይዞ እንደጠበቀውና ተንደርድሮ ወደሱ ሲመጣ ባካባቢው የነበሩ ሰዎች በድጋሚ ይዘው እንዳስቆሙት ገልጿል፡፡

ገላጋዮች ግራ ተጋብተው እሱን እያነጋገሩት እያለ፣ ‹‹ተደብድቤያለሁ፤ በሕግ አምላክ፤›› በማለት፣ ፖሊሶች ይዞ መጥቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄዳቸውን የገለጸው ዳንኤል፣ እሱ ሕጉን ስለሚያውቀው ፖሊስ ጣቢያ ሲደርሱ፣ የምስክሮቹን ቃል ካሰጠ በኋላ፣ ‹‹ስለተጐዳሁ መታከም አለበኝ›› ብሎ መሄዱን አስረድቷል፡፡

ታክሞ እስከሚመለስ በፖሊስ ጣቢያ መቆየት እንዳለበት ስለተነገረው እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ ጣቢያ በመቆየቱና ግዛቸውም ባለመምጣቱ እዚያው ሊያድር መገደዱን ተናግሯል፡፡ ነሐሴ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስ መብቱ ተከብሮለት መለቀቁንም አክሏል፡፡

እሱም በተራው ጣቢያ ሄዶ በጋዜጠኛው ላይ ክስ መመሥረቱን፣ ምስክሮችን አቅርቦ ማስመስከሩንና ቀሪ ምስክሮችን ለማሰማት ለነሐሴ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዞ መመለሱን ተናግሯል፡፡

የሬዲዮ ፕሮግራሙን በፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ኤፍኤም ሬዲዮ የጀመረውና ‹‹ውስጥ አዋቂ ምንጮች›› በሚለው ያልተነገሩ ወሬዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ኢቶፒካሊንክ፣ ከፋና ኤፍኤም፣ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ጋር በተያያዘ ባስተላለፈው ፕሮግራም ከጣቢያው ጋር አለመግባባት በመፍጠሩ፣ ወደ ዛሚ ኤፍኤም 90.7 ሬዲዮ ጣቢያ በመዛወር እየሠራ ይገኛል፡፡

በአክሱም ፒክቸርስ ድርጅት ሥራ የሚገኘው ኢትዮፒካሊንክ ከሰኞ እስከ ዓርብ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት እንዲሁም፣ ቅዳሜ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ድረስ ሥርጭቱን ያስተላልፋል፡፡

 Source- ethiopianreporter

Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>