በቅርቡ መንግስት በፋክት፣ አዲስ ጉዳይ፣ ሎሚ፣ እንቁ፣ ጃኖ መጽሄቶችና አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ፍትህ ሚኒስትር ክስ መመስረቱን ተከትሎ ሚዲያዎቹ ከህትመት በመውጣታቸው ምክንያት ስራ ሊያቆሙ መሆኑን የጋዜጣ አዙዋሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡
በአራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ መርካቶ፣ ሳሪስ፣ ቦሌና ካሳንቺስ የሚገኙ የጋዜጣ አዙዋሪዎች በርካታ አንባቢ የነበራቸው መጽሄቶችና ጋዜጦች ከገበያ በመውጣታቸው፣ ሌሎቹን ጋዜጦችና መጽሄቶች በማዞር ህይወታቸውን መምራት ስለማይችሉ የጋዜጣ ማዞር ስራቸውን አቁመው ሌላ ስራ ለመፈለግ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ በስርጭት ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው የነበሩት ፋክት፣ አዲስ ጉዳይና ሎሚን በመሸጥም ሆነ በማከራየት አብዛኛውን ገቢያቸውን ያገኙ እንደነበር የገለጹት የጋዜጣ አዙዋሪዎች አሁን ያሉትን ጋዜጦችና መጽሄቶች በህዝቡ ዘንድ እምብዛም ተነባቢ ባለመሆናቸው በዚህ ስራ ህይወታቸውን መምራት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ የፍትህ ሚኒስትር ሚዲያዎቹን ከከሰሰ በኋላ ማተሚያ ቤቶች ቀሪዎቹን ጋዜጦችና መጽሄቶች አናትምም በማለታቸው በርካታ ሚዲያዎች ከገበያ መውጣታቸው ጋዜጣ አዙዋሪዎቹ ስራ እንዲያጡ ምክንያት መሆኑ ተገልጾአል፡፡
አዙዋሪዎቹ በእነዚህ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊትም ቢሆን ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመሆናችሁ የእነሱን አቋም የሚያንጸባርቁ ጋዜጣና መጽሄቶች ለህዝብ እንዲደርስ እያደረጋችሁ ነው፣ ከአጥፊ ኃይሎች ጋር እየተባበራችሁ ነው›› በሚል እርምጃ ይወሰድባቸው እንደነበርና አሁን በመጽሄትና ጋዜጦች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሰርተው መኖር እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ የእነዚህ ሚዲያዎች በመዘጋታቸው የገቢ ምንጫቸውን ከማጣታቸው በተጨማሪም በሚዲያው ላይ የተወሰደው እርምጃ በእነሱም ላይ የማይወሰድበት ምክንያት እንደሌለ ባለፉት ጊዜያት የደረሰባቸው በደል ማሳያ መሆኑን በመግለጽ ስራውን ሊያቆሙ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ከወራት በፊት ገዥው ፓርቲ የሚቀጥለው ምርጫ ተከትሎ ሚዲያዎች ወደ ክፍለ ሀገር እንዳይደርሱ አከፋፋዮችንና አዙዋሪዎችን በማደራጀት ሚዲያዎችን ከስራ ለማስወጣት እንዳቀደ መገለጹ ይታወቃል፡፡