ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጫንቃ፣ ሁርሙ፣ ዶረኒ፣ ኃይና፣ ከሚሴጎንደራ፣ በዴሳና ሄና በተባሉ ወረዳዎች የኦህዴድ ካድሬዎች የአማርኛ እና ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን ሰብልና ንብረት እያወደሙ መሆኑን ምንጮች ነገረ ኢትዮጵያ ዝግጅት ክፍል ድረስ በመምጣት ገልጸዋል፡፡
ካድሬዎቹ ሰብሉን ማውደም የጀመሩት ከሀምሌ ወር መጀመሪያ ጀምረው እንደሆነና ማሽላ፣ በቆሎ፣ ቡና፣ ባህር ዛፍ የመሳሰሉትን ሰብሎችና ንብረቶች ጨለማን ተገን በማድረግ በገጀራና በመሳሰሉት መሳሪያዎች በማውደም ላይ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይህ ድርጊት እየተፈጸመ ያለው በአካባቢው የሚኖሩት ከላይ የተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን ልቀቁ ሲባሉ ለቀው ለመውጣት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሰብላቸውና ንብረታቸው ከወደመ ይለቃሉ ከሚል ስልታዊ ማፈናቀል ዘዴ መሆኑን ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡
ከሶስት አመት በፊት በቾ በተባለ ወረዳ ተመሳሳይ ተግባር እንደተፈጸመ የገለጹት ምንጮቻችን፣ በወቅቱ ይህ ሰብል የማውደም ተግባር የተመራው በሚሊሻ ጽ/ቤቱ ኃላፊ እንደነበር እማኝነታቸውን ገልጸውልናል፡፡ ይህን ተግባር የፈጸመው ግለሰብ መልካም ስራ እንደሰራ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ስልጣን ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ስልታዊ የማፈናቀል ተግባር የኦህዴድ ካቢኔ ለሁለት እንደተከፈለ የገለጹት ምንጮቻችን ንብረት የማውደሙ ተግባር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተጠናክሮ መቀጠሉ የነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ንብረታቸው እየወደመባቸው የሚገኙ ዜጎች ሌሊት ሌሊት ተደራጅተው ሰብላቸውንና ንብረታቸውን ለመጠበቅ በዝግጅት ላይ በመሆናቸው ከካድሬዎቹ ጋር ሊጋጩ እንደሚችሉና ይህንንም ካድሬዎች የህዝብ ግጭት አስመስለው ስለሚያቀርቡት በህዝብ መካከል ግጭት ሊያስነሳ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡