(ዘ-ሐበሻ) አሁን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በአፋር ክልል በሰሜን ዞን በኮናባ ወረዳ ነዋሪዎች እና በትግራይ ክልል የአፅቢ ወንባርታ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ግጭት የተቀሰቀሰ ሲሆን እስካሁን የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ተዘግቧል።
አኩ ኢቢን ከአፋር ለዘ-ሐበሻ ባደረሰው መረጃ በኮናባ ወረዳ የዋህደስ ቀበለ አፋሮችና በአፅቢ ወረዳ ኦሳት ቁሼት ከ1 አመት በፊት የድምበር ይገባኛል ያለመገግባባት የነበረ መሆኑ በተደጋጋሚ የተዘገበ ሲሆን ዛሬ ከሳዓት በኋላ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 8:30 ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ግጭት ላይ ይገኛሉ።
በድንበር ይገባኛል ግጭት የተነሳ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ከዚህ ቀደም ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን አሁንም በአፋሮች እና በትግራዮች መካከል የተነሳው ግጭት ሥርዓቱ የፈጠረው የዘረኝነት አስተዳደር ውጤት ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
ለዘ-ሐበሻ መረጃውን ያደረሰው አኩ ኢቢን ኮናባ መተው እየተዋጉ ያሉት የወታደር ልብስ የለበሱ የሚሊሻ አባላት ናቸው ሲል እስካሁን በዚህ ግጭት 1 ሰው ሲሞት 2 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብሏል። በሞተው ሰው ጉዳይ ዘ-ሐበሻ ከመንግስት ወገኖች ለማጣራት ያደረገችው ጥረት ባይሳካም የድንበር ግጭቱን ለማብረድ ከመንግስት በኩል እየተደረገ ያለው ዝግመተኛ ሥራ የአካባቢውን ነዋሪዎች እንዳስቆጣ ምንጮች ገልጸውልናል።
በዚህ ግጭት ዙሪያ ተጨማሪ መረጃዎች እንደደረሱን እንመለሳለን።