Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የጎረና ጉርና –ነዳላ (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ልብ አምላክ ዳዊት „ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ“ አለ።
ሱባኤውም ተጠናቀቀ – መልስ ይሰጥበት።

ከሥርጉተ ሥላሴ 25.08.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

ሥርጉተ ሥላሴ

ሥርጉተ ሥላሴ

ይድርስ ለጸሐፊ ጌታቸው ረዳ ካሉበት። እንደምን አሉ? ደህናነዎት ወይ። ደስ ሊለዎት የሚገባ ሊያሰተላልፉት የሚፈልጉትን መልዕክት በማስተላለፈዎት ሳይሆን እራሰዎትን ፈልገው ከመሸ በማግኘተዎት ነው። እንኳን ለዚህ አበቃዎት! አሻቅቦ መናገር ከመንፈሴ ዕድገት ውጪ ቢሆንም ልክን ማወቅ ከልክ የሚያድርስ ስለመሆኑ ተምሬ ስላደኩ አቻውን ዬፍላጎተዎትን እንሆ – ይረከቡኝ!

„ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል“ ወይ ዘመን ምኑን ጉድ ነው እዬዘለዘለ ያለው? እግዚአብሄር ይይልህ አይዋ ዘመን ምን አለበት ጉግልን ባትጋፋው?

የኔዎቹ እንዴት አላችሁልኝ። ጥያቄ ተጠዬቁ እስቲ። ደግሞ ብለው ብለው ላልጠፋው እህል እውሃ በነጭ ሀገር ብዕርና ብራና ስንቃቸው አብሾ ሆነ እንዴ?

አልኳችሁ ወዳጆቼ አጣደፉኝ። ስሄድ ካላሆነ ቦታ ገባሁ። ከዛንላችሁ ቀጥ ብዬ እርእሱን ይዤ ኤዲተር ካላው ወዳጄና ረጃጅም ትንተናዊ ጹሑፍ በማወጣት ወደ ዬሚታወቀው ኢትዮ ሚዲያ ጎራ ስል ተዛም ዝክንትሉ ብራና የለም። ያው እንደፈረደብኝ ተመልሼ እንደ ነገሩ ከብትክትኩ ጋር በባዕቱ መተያዬት አይቀር – ተያዬን። እርእሱና ፎቶው በቂ ነበር „የናዚ ኔት ወርክ“ ዘመናይ ነዎት —  ዖዬ!

ከዛ ደግሞ አነበብሽው? ምንስ ተሰማሽ መጣ? ስለ ወጣቶች „ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ“ በመሆኑ ሰቀጠጠኝ። እኔ ለወጣት የነፃነት ትግሉ ቤተሰቦች ስስታም ነኝ። እንዲሁም ቀጥ ያለ አቋም ብቻ ላላቸው የመወያያ መድረኮችና ሙሁራንም እጅግ ቀናተኛ ነኝ።

በተረፈ እኔን በሚመለከት አደራ አበደች እንዳትሉኝ። ደስ አለኝ። እዬሳቅኩኝ ነበር የተያዬነው። በቃ የጠላት ጎራ መንፈስ እንዲህ በአንድ ጹሑፍ ትቅማጥ ሲይዘው ማዬት የምር ምኞቴ ነበር። ሆድ ዕቃው ወስፋቱ የተንጫጫ ሲገኝ አጋጠመ ነው። ለዚህ ነበር እኮ እኔ የጻፍኩት። በቃ!  ሁልጊዜ ፋሲካ የለምና እንደ ወትሮው መንፈስን ከአንድነት ኃይሉ ማፈናቀል ያልቸል ደካማ መሆኑ ደግሞ ተከታታይ መረጃ ወገኖቼ ሲሰጠኙ የበለጠ ሐሴት አገኘሁበት። አዎና! እኔ እኮ ስጽፍ በውስጤ ሁኜ ነው። የፓርቲ አባል ዬማልሆነውም ለዚህ ነው። በዲስፕሊን መታሰር አልሻም። ፓርቲዬንም ማስነቀስ አልፈልግም። እንዲህ በልቅ ዓለም መኖር፤ በምንም ነገር ያላታሰረ ነፃነት እሻለሁ። ባሩዱ ተነጣጠረ ዓላማውን ሳይስት ጦሮዎ በጠላት ሰፈር ልኮ እንዲህ ቆርቆሮውን ቢና ጢናውን አወጣው። ዓይነተኛ የውስጥ ተቆርቋሪ ይሄው እንዲህ  ከእንቅልፍ ጋር ተጣልቶ ጎልቶ አውሎ ያሳድራል ጌታውን ሲያስጨር። ተመስገን – አነቃነቀ – ናጠም።

በግራ ቀኝ ስውርና ረቂቅ ሴራ በጠላት እጅ ለወደቀ – ስለ ራሱ ቆሞ ሊናገር ለማይችል፤ በጠላት እጅ በመንፈስ ማደንዘዣ የበቀል መርዝ ሙከራ የሚሠራበት ታላቅ ወገኔ በሌለበት ቦታ ስለ እሱ ተናግሬ ወንጀለኛ መሆን ክብር ነው – ለሥርጉትዬ። ይልቅ ያልተገባኝን ክብር ባልተገባኝ ወቅት ሰጡኝና ከነፃነት አባት ጋር አንጠለጠሉኝ። ከአንድ የነፃነት ሙሴ – ሰማዕት ጋር ደረጃዬ አይፈቅድም። ይህ ባይሆን ጥሩ ነበር። ይሄ ወቅትን ጊዜን ያልጠበቀ ከፍ ማለት አልወደወም። አጉል መንጠራራትን ፈጥሮ እሸት ቅመሱ ሳይባል ዘጭ ያደርጋልና። ለዚህም ነው በብዕር ሥሜ እምጽፈው። እንጂ እኔ እህታችሁ በተፈጥሮዬ ደስታ ላይ አልገኝም። ከተሸነፈ ወይንም ከተጠቃ ጋር ግን ማን ይዞኝ። ባለፈው ዓመት የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እዚህ መጥተው አባላቱን ካነጋገሩ በኋላ እንዲሁም በተለዬ ሁኔታ ለሚያግዙ የነፃነት ትግሉን ግንባር ቀደም „አክቲቢስቶች“ ነው የሚባለው ከእነሱ ጋር እንደተወያዩም አዳምጬ ነበር። አሁን ደግሞ ፎቶም አይቻለሁ። ለእኔ ይህ ጉዳዬ አይደለም። ድንበር አለው ኑሮዬም – ተፈጥሮዬም።

አንድ ነገር – እንዲህ ሆነላችሁ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ታስራ በነበረች ወቅት በዬሳምነቱ እደውል ነበር ለቤተሰብ። እምችለውን የመንፈስ ደጋፍ አድርጌያለሁ ብዬ አስባለሁ። ስትፈታ ግን አልደወልኩም። ኢሜሏም አድራሻውም አላስፈለገኝም። አላገኘኋትም።

ለእኔ ቁም ነገሩ ጠላት እንዲህ ጥቃት ሲፈጽም፤ ሰብዕዊነትን ሲዳፈር፤ የዜግነት መንፈስ ሲጨፈለቅ፤ ህግ በጠራራ ፀሐይ በጉልበተኛው ወያኔ ሲረሸን የእኔ ብዬ መቀበል – በግንባር በባለቤትን በዕውነታዊ ውስጥ መገኘት ነው። እንዲያውም ጀግናዬ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የግል ህይወታቸውን ከተከበሩ ወንድማቸው ከሰማሁ በኋላ የበለጠ ነው እኔን ዬመረመረኝ። እንዲህ በአደገ ሀገር በአንዲት ክፍል ቤት ሁሉንም ዓይነት አማራጭ ደፍሮ ለመሞከር እራስን ረስቶ ታጥቆ መጠበቅ ልዩ ጸጋ ነው። መታደል – የእውነት። እና  መከራን ለፈቀደ ወገን መሰከራችሁ ነው „ናዚነቱ ሆነ ጉዲትነቱ“። ወቅትንና ጊዜን ማድመጥ በሚመለከት ለሽበት መንገር ወንዝን አሻቅበህ ተጓዝ እንደማለት ከቶ ይሆንብኝን? ግድፈቱ ዘመን ይቅር አይለውም – ጌታው። ግራጫ አለቀሰ – እዬተቀነሰ – እዬተበጠሰ …. ከቶ ይህቺ ስንኝ ተመቼዎትን?!

ሌላው ከትክት ብዬ በፈንጠርጣራ ጥርሶቼ የሳቅኩት ደግሞ በነፃነት ሀገር ፈቃድ ጥዬቃ መዝመት ነበረብን ወደ ዘመን ሰጡ ጌታው። ወይ አቅምን አለማወቅ?! „ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል“ ይላል ጎንደሬ ሲተርት።  ሃሳብን በሃሳብ መታገል የአባት። ድንበር ዘለል የጎጥ አገዛዝ ለዛውም ነጭ ሀገር ግን እማይቻል ልግጫ ነው። ዝለት – በፍዘት ይሉታል ዕብኑን ህልም። ለነገሩ የጎጥ በሽታ ከዚህ በላይ መሄድ አይችልም … በጣም ረጅም ጊዜ እኮ ነው፤ 23 ዓመት መስሎ – ተመሳስሎ መኖር መርግ ነው አቅልን የሚፈትል።

መኖር ማለት መኖር የለገሰውን ተፈጥሯዊ ጸጋና ክህሎት በጊዜ አውቆ ተጠቃሚ መሆን መቻል ነው። መቻል ደግሞ እራስን ሆኖ እንደ ራስ ሆኖ በመጤ እንደራሴ ሳይጠቀለሉ እንዲህ አደባባይ ላይ ወጥቶ ውስጥን ማስጎብኘት ነው። ይህ መሸቢያ መንገድ ነው። ስለምን? ድርጀቶችን ተጠልሎ ጥቃት መፈጸም ሆነ ወቅትን አስታኮ ማመስ ከምድር በታች ይቀበራሉና። ብዙ ድርጅቶች ታሪካዊ ስህተት የሚፈጽሙት በእንዲህ ዓይነት ዝበትና ግብዝነት በጎበኛቸው መንፈሶች የዋህ ወገኖች በቅንነትና በአዎንታዊ ተመልክተው ይጥቅማል በማለት ሃሳብን ስለሚያስተናግዱ ነው። ስንሰበሰብ ሲበተን፤ አፍሰን ስንለቅም ወይንም ለቅመን ስናፈስ የኖርነው … በዚህ ጆሮ አልቦሽ መንገድ ነበር።

ከእንግዲህ ያ ይናፈቅ የነበረ ዬናሙናዊነት መለዮ ልዑቅ ክብር፤ ተወዶና ተፈቅዶ የተለገሰው ንጡር ፍቅር፤ በብዙኃኑ የተጫነለወት ልዩ ዘውድ ተምልሶ ዳግም አይገኝም። ቁርጠዎትን ይወቁ – ጌታው። ዬትኛው ጌታቸው ረዳ? የኛው ወይንስ የወያኔው? ….. መለያወት ላቂያ ፍቅር ነበረው። ጌጥማ አቅርቦትና ልዩ ዜማዊ አክብሮት – ቅርበትም በነኑ – ስለፈቀዱላቸው። የአብነት ት/ቤት – ነትወትንም ለዘለዓለም ከረቸሙት – ምነው እንዲህ – የጤና?! ከብዙኃኑ ቤተኝነት መውጣትስ ይመች ይሆን? ይህ ግንፍል ግንፍል ማለቱስ — ?

ማንም ሰው እንደ ሰው በምድር ላይ ብዙ ነገር ሊኖረው ይችላል። ከሁሉ የሚልቀው ግን የህዝብ ፍቅር ሃብት ነው። ፍቅር የተጠረገ ልብና ብቁ አስተዳዳሪን ይሻል። ፍቅር አድማጭና ተናጋሪም ነው። ስለፍቅር መሸነፍም ውስጥን እንደ ተፈጥሮው እንዲኖር መፍቀድ ነው። ይህን ሁሉ ዘመን በነፃነት የኖረ አባወራ በመዳፉ ላይ ያለውን የህዝብን ፍቅርን በአግባቡ ለማስተዳደር አቅቶት ወይንም ግራጫዊ ዘመን ዘለቅ ተመከሮው መተርጎም ተስኖት እንዲህ እናት ሀገር ማቅ ለብሳ በማህጸኗ የደም ዕንባ በምታለቅስበት እጅግ በጠቆረ ዘመኗ፤ በከፋት ዘመኗ፤ ሾልኮ መቅረት ….. ብልሃት የሌለው ቅላት ነው ለእኔ።

እኔ ሰው ነኝ። ከዚህ በላይ ስለ እኔ የሚተረጉም ምንም አልፈልግም። እርስዎ ግን አስፈለገዎት። በአደገው ሀገር ተቀመጠው ዘመን የሰጠውን፤ የፈቀደውን ፍትህና ነፃነት አግኝተው እዬኖሩ በጣም ታች ወረዱ። ጎሳ ላይ -

ዘመነዎትና ተመክሮዎት ውስጥዎትን ለማሸነፍ አቅልም  - አቅም አነሰው። ምነው ቸኮሉ?! ኩታረነቱን* ለልጅ መስጠት ይገባ ነበር። ምን ቆጠቆጠዎት? ምን እንዲህ አንተከተከዎት? ምን አበሳጨዎት? ምን አቅለዎትን ነስቶ በነፈሰበት መረጃ አካልዎትን የገዛ ቤተሰቦወትን ለመወንጀል ምን አስነሳዎት? የምን ጥድፊያ ነው ትቅማጥ እንደያዘው ሰው?

እኔ ልመልሰው። እስከ ዛሬ ድርስ እራስዎትን አሸንፈው አልኖሩም ነበር። ፍላጎቶዎትና እርስዎ አብራችሁ አልነበራችሁም። ወይንም ውስጥወትን አያውቁትም ነበር። ከዚህ የከፋ ነገርም እኮ ሊመጣ ይችላል። በደለኛ እስካለ ድረስ። ሰው እራሱን ሳያውቅ ወይንም እራሱን ሳያዳምጥ ሲኖር አንድ ቀን እንዲህ እራሱን ፈልጎ ያገኛዋል። እሱን ያገኘው ዕለት እንዲህ ይቧርቃል። ሜዳውም ሸንተረሩም አይበቁትም። ይጠበዋል። ታፍኖ እንደ ኖረ ስለሚቆጥረውም ይተነፍሰውና እንዲህ ይወጣለታል። እንኳን ለዚህ አበቃዎት – ጌታው። እንጡሩብ አዘለለዎት …. ነዘረዎት – ሰረሰረዎት።

መመካት ቢኖር አብነት ላለው – ትንሽ ብጣቂ የመንፈስ ማረፊያ ዬብትን አፈር ተቆርቋሪነት ቢኖር ነበር። አንድ የመንደር ወመኔ ስብስብ የፈጸመው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚል ጣዕም ቢኖረው፤ ወይንም ሰውኛ ያለው ጠረኑ ቋት የሚሞላ ተግባር ላይ የሚታይ ተጨባጭ ነገር ቢኖር በነበር። ዕድሉን ቢጠቀምበት በነበረ። ጭብጦ አኮ የለም።  የፈለሰ = የመከነ – የተፋቀ፤ የፈሰሰበት ዘመን ጥልማሞተ ነው የወያኔ ያረገዘው ዘመኑ። ምን ተነስቶ ምንስ ተጥሎ? …. በወያኔ ያልተበከለ ወይንም ያልተጠቃ – ያልተቃጠለ ተቋም ምን አለና? መርዝ!

ጸሐፊ ጌታቸው እረዳ እንደ እርስዎ ያለ ታላቅ የዕድሜም ባለጸጋ፤ በፖለቲካ ልምድ የበለጸገ አባወራ፤ በቀለም ትምህርትም ሙሑርነቱ ታክሎበት „ከትግራይ የወጣ፤ ከትግራይ የተፈለፈለ እጭ’፤ ትግራይን ነፃ እናወጣለን ብለው የተነሱ ጎጠኞች፤ ሀገርና ትውልድን የገደሉ፤ ትውፊትና ማንነትን የቀበሩ፤ የሀገራችን አካል የጎረዱ፤ ዜግነታችን የጠቀጠቁ፤ በዘር እዬነጠሉ ያጠቁ፤ እረቂቅ ዛሬ የማናያቸው ነገ ግን እዬፈነዱ ሀገር አልባ የሚያደርጉን ደባ የፈጸሙ፤ ሰንድቅዓላማን የተዳፈሩ – የተጸዬፉም፤ ባህልን ካለርህራሄ የጠቀጠቁ፤ ግብረ ሰዶምን ያበረታቱ፤ የዕምነት ምኩራቦችን በትዕቢት የረገጡ፤ በወገኖቻችን ላይ አራዊታዊ ተግባር የሚፈጽሙ፤ ሀገራቸውን በጠላትነት ፈርጀው ተቋማቷን ሁሉ ያከሰሉ፤ ጥርጣሬን ያነገሡ፤ ምቀኝነትን ያፋፉ፤ አብሮነትን በተባይ ያስወረሩ….“ ምኑ ያልቃል እንዲህ አውሎ ጎልቶ በሚያሳደር የብዕር እልልታ ጎሽ ያሰኝ ነበርን? ህሊና ቢኖርስ አንገት ያስደፋል። ያሳፍራል?

ብዕረኛው ቢያውቁትና ቢገነዘቡት ዛሬ ወያኔ በሚፈጽመው በደል የተፈጠረበት መሬት ያለው ንክኪ ሁሉ ቁስል ነው። መግልን ፈቅዶ ያዘለ። አጋጣሚው ቢሾልክ እንዴት እልቂትን በቀለን ታግሶ ምህረት ማውረድ እንደሚቻል በዚህ መስመር ነበር ምርምር ሊያደርጉበት የሚገባ። እኛ አንቅልፍ የነሳን ይህ ነው። …. ጀግና አንዳርጋቸው ጽጌን የማድንቅበት ትልቁ መስፈርቴ ይህን የተፈራ አምክንዮ ሁሉን ችለው – ዘለፋውን ሁሉ ተሸክመው፤ ወጨፈውን ሁሉ ተቋቁመው ደፈረው መግባታቸው ነው። ጤናማ የመተንፈሻ ቧንቧ ለመዘርጋት አብነቱ ነበሩ – ቀንዲል

እንደ እርስዎ ያለ በልምድና በተመክሮ ከለማ ወገን እምንጠብቀው የነበረ የበቀል ተጠቂ ተቋማትና ወገን ለማዳን የትግራይን ዬኢትዮጵያዊነት ጉልተኝነት ለማስከበር ፊተኛው ረድፍ ላይ ቆመው እሳቱን ቋያውን እንዲቀበሉ ነበር። ተዉ! በቃ! በዛ! እንዲሉ ነበር። እንጂ እንዲህ አይጥ የበላው ጨርቅ የመሰለ ብትክትክ ያለ፤ በዬቦታው የተቦጫጨቀ፤ ዘሎ ፈርጦ ዪሚወራጭ የነገር ጅምናስቲክ አስተሳሰብ ይዘው ብዕርና ብራናን ሲያገናኙ አንገትን ቀና አድርጎ ለመሄድ  ከእንግዲህ ጋዳ ነው የሚሆነው። ፍሰኃና ሰናይ ከሆነወት —— ስ

እውነቱን ብነግረዎት ለትግራይና ለትግራይ ህዝብም የእርስዎ መስመር መዳህኒቱ አይሆንም። በፍጹም። …. ደግሞስ ወጪውንስ ጉዞውንስ እንዴት ቻሉት? – የቀረዎት ሀገር፤ የቀረዎት ሰው፤ የቀረዎት የነፃነት መንፈስ የለም። አዳረሱት። ግን ብዕሮዎት እንዲህ ዟሪ ናት? … ኧረ እንዲህ ስድ አደግማ አያድረጓት!…. የጠብ ተጠማኝም አያድርጓት። እ! መንጠራራቷም ልክ ቢኖረው መልካም ነው። ምን አልባት እርስዎን እረስታ በራሷ ኢጎ መጪ ብላ ይሆን? ኧረ በፈጠረዎ ልጓም ቢጤ ይፈልጉላት …. እዘጭ ያደረገችው እኮ ትልቁን ዳቦ …. እም! አቤት ያንት ያለህ! ከስንቱ ረገጠች? ደግሞ ጠላት ማብዛት ግጥሟ ሆኖ አረፈ — አፈርም ላይ ፈርፈር አለች …. ተጋግጣ – ህም!

አሁን ባለው ሁኔታ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ጎሽ እንኳንም የኛ ሆናችሁ የሚያስብልበት ጊዜ አይደለም። የትግራይን ክብርና ዝና የፈገፈገ የጎጥ ስብስብ ከረፋህን ብሎ ትግራይን ማዳን ማለት ለእኔ ኢትዮጵያን ማዳን ስለሆነ፤ በዚህ በጣም የተጋ ተግባር በተከታታይነት በተከወነበት ነበር። መሬት ያያዘ፤ ጭብጥን የተንተራሰ፤ ሥልጡን – እርጋታ የከበከበው የምርምር ድርጊት ያስፈልግ ነበር። የማዳን ዘመቻ እራስን አቅልጦ …..

የብዕረዎት ጠብታ ግን ጦርነት ነው ያወጀች ….. ይገባልን? በመገዳደል፤ በመጨፋጨፍ፤ በጥላቻ በተከዘነ ጎጣዊ ጉዞ ሀገርና ህዝብ ይድናሉን? ለመሆኑ ሽበተዎት በውስጥ ወይንስ ውጪ ላይ ነው ያለው ይሆን? ለሰው አይደለም ለታሪክ – ለትውፊት – ለሀገር – ለሰንድቅአላማ – ለአደራ -ሽምግልና በሚያስፈልጉበት ጊዜ እንዲህ ያለ መላቅጡ የጠፋ የጎረና ጉርና ነዳላ አስተሳሰብ ይዞ መቅረብ ከቶ ወደ ዬትኛው ዕድሜዎት ላይ ተመልሰው ይሆን?

አሁንም አልጠገቡም ይጽፋሉ። ስህተቶችን አነባብረው እዬካቡ ነው። ቃላቶቹ አምጸው – ተንደው ቢደርምሰዎትስ? ሞትንም እርሰዎም ብዕረዎት እረሱ መሰል። ሰው ያዘነበትም ሰው ….. የበቀል አምላክ አለና ይበቀላል። „ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ“ አድርገው ጭንግፍ ያደረጓችን የነገ ወጣቶች እኛ ህይወቱ ባይኖረን ወላጆቻቸው ያነባሉ — ሀገርም ….. ታነባላች። ጊዜያቸውን – ጉልበታቸውን – ገንዘባቸውን – እያፈሰሱ፤ ደፍረው ቅራኔ ውስጥ እዬገቡ፤ ሌትና ቀን በሚተጉ የነፃነት አርበኞች፤ ወጣትነታቸው ሳያውቁት አልፎ ሲሄድ እያዬዩት ኑሮን ንቀው ነገን በተግባር በሚያደምቁት ላይ …. እነዚህ ፎቷቸውን በማናለብኝነት የለጠፏቸው ወጣቶች አንድ ነገር በህይወታቸው ቢደርስ – ተጠያቂ መሆነዎትን ግን ልብ ብለውታልን? …. ከልበዎት ሆነው ይስቡት። ጹሑፎዎትንም ደግሞው ያንብቡት። ተኝተውም ይሰቡ። ግን ግን እርሰዎ ነው የጻፉት ወይንስ ኮበሌው ጌታቸው ይሆን የጻፈለዎት …..? አምላኬ! ተሳህለነ!

„ኢትዮጵያዊነትን ሃይማኖታቸው“ ስላደረጉ ብቻ ፎቷቸውን የለጠፉት ወጣቶች ወያኔ አፍኖ ወስዶ ምን እንዲያደርጋቸው ይሆን የፈለጉት? ወይንም ሽፍታው ወያኔ የሞት ቅጣት ወይንም ዕድሜ ልክ እስራት ፈርዶባቸው በዛ ተደናግጠው ምን እንዲሆኑ ይሆን ምኞተዎትና ዓላማዎት? ወይንም አንዱ እንዲህ እራሱ የሾለከበት የዘር በሽተኛ  ባገኘው አጋጣሚ  አነጣጥሮ እንዲገድላቸው ይሆን? ለምንስ መሳሪያውን ገዝተው አይሰጡትም ለአንዱ የዘር ብኩን?! ….. ገድለዋቸዋል እኮ እርስዎ። ሞት እኮ ነው የፈረዱባቸው።

እኔ እኮ እበቃዎት ነበር – ጌታው። የጻፍኩት እኔ። ስለምንድነው ሳቢያ ዬሚፈልጉት። „አንዳርጋቸው ስለምን ጀግና ተባለ?“ ነው አይደል። ጸሐፊዋ እኮ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ነኝ። ፎቶዬ ከናፈቀዎት ከፈለጉት ላይ ይለብዱት። በፈሉጉት ዘይቤ ይሰልቁኝ። እንዳሻዎ ይቀጥቅጡኝ። እኔ እመመኘው ነፃነት የማይመቸኘን ሃሳብ ለማስመቸት ነው። ሃሳብን በሃሳብና በፋክት አፋጭቶ በነጠረው ሃሳብ በብዙሃን ድምጽ የሚመራ ነፃነት ነው ናፍቆቴ። ስለሆነም በፈለጉት ዓይነት አቀራረብ ዱላዎት ይደላው ነበር። እችለዋለሁ። ምንም እንኳን ጹሑፎ ብናኝ ጭብጥ ባይኖረውም – እንኩቶ ቢሆንም።

ከእነዚህ ወጣቶች እራስ ግን መውረድ አለበዎት። ፎቷቸውንም ማንሳት። ትእዛዝ አይደለም – አስተያዬት እንጂ። እኔና እርስዎ አንደራረስም እርስዎ ከፍ ያሉ እኔ ደግሞ ትቢያ። በሁሉም ነገር እንደሚበልጡኝ አሳምሬ አውቃለሁ። ለዚህም ነበር በጭምትነት ዝም ብዬ የሰነበትኩት። እርስዎ ግን የከተቡት ሁሉ የተሰባባረ – አቅጣጫው የጠፋበት – የወለላለቀ – ወለምታው የሰቀዘው የቃላት ድርደር ሁሉ ቁጭተዎትን፤ ለወያኔ ያለዎትን መጠነ ሰፊ ተቆርቋሪነተዎትን ሁሉ ሊመክትለውት አልቻለም። መደረት – መደረት በላይ በላይ – ከሽበተዎት ጋር ይምከሩ።

እኔ ልንገርዎት ዓላማው የሥነ – ልቦና ጦርነት በውጪ የነፃነት ታጋይ ቤተሰብ ለመሰንዘር ነው። ችግሩ አንተዋወቅም። ከብረት ቁርጥራጭ ዬተሰራው መንፈሳችን ግን ከቶውንም ለአፍታ አያንቀላፋም። ጠላታችን ወያኔ ፋሽስታዊ ማኒፌስቶው እስኪነቀል ድረስ የነፃነት ትግሉ በበቃን መሪነት ይቀጥላል። ለሰማዕትነት የቆረጠ ጀግና በጠላት እጅ ነው። ውስጡን ጎርጉራችሁ ምን እንዳደረጋችሁት አይተናል። ይህ ደግሞ ሃይልና አቅም እንደ አዲስ እዬፋፋ እንዲሄድ ያደርገዋል። አንፈራም! አንገታታችንም አንደፋም – በፍጹም።

በስሜት ጋልበንም ከህዝብ ፍቅር ማሳ አንወጣም። ይህ ይመረወታል – ይወረወታልም። ይህ ተቆስቁሶ „ትግራይን“ እንደናብጠለጥል ነበር የፈለጉት። ጓደኛ ፍለጋም እዬባዘኑ ነው። በዓይናችን በተከበሩ አቶ ገ/ድህን አርያማ አይምጡ። አዩ ቅናት! እኔ ስነግረዎት –  የተጠለሉበት ጥግ ቀን ዋቢ የለውም። ቀን ወዳጅ የለውም – አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎዎት እንዲህ እብስ -

የፈሩት – እንዲህ ያባከነዎት የተከበሩ የአቶ አንዳርጋቸው ዝክረ ጀግንነት በቋሚነት ጽላታችን ይሆናል – ለአብዛኞቻችን። ተከፍሎን ወይንም ባውንድ ተሸልመን አይደለም። እንዲያውም እንዲህ አቅም ሆነን ማገር እንዳንሆን የራሳችን ቅንቅኖችን እዬተጋፋን – እዬገፈተርን ነው ዕውነትና ሃቅን ለማድመጥ የፈቀድነው። በገንዘብ ተገዝቶ ዕንባና ጥቁር ልብስ ሄሮድስ መለስን ቀበረ። እኛ ግን  ለአርበኞቻችን – ለሰማዕቶቻችን ፈቅደንና ወደን ደስ ብሎን የምናደርገው ድርጊት ነው …. ለህሊና መኖር ማለት ተፈጥሮን የመተርጎም አቅምና ብቃት ማለት ነው።

መላሾ አሞሌ እኔ ሳውቀው ለከብት እንጂ ለሰው ልጅ አይታሰብም።  የወያኔ ሥር ለማረግረግ ጥሎሹ ወይንም እጅ መንሻው እንደልቡሻ ማይጨውና መተማን እንዲሁም ሌሎች ሀገር ወዳድ ወገኖቼን ታሪካቸውን አቃጥለው፤ ሞት ፈርደው ሲባትሉ ሰነበቱ። መጥኔ ለእርስዎና ለአውቆ አበድ ብዕርዎ። እኔ ልንገረዎ እንደ እግር እሳት ያንገበገበዎት ለወያኔ ሽፋን ለመስጠት በሰላማዊ ትግሉ ስም ጠንከር ብለው የሚወጡትን የነፃነት ድርጅቶችን በውስጥ ለውስጥ መንገድ ስትንዱ፤ ስታናክሱ፤ አንጃ ስታስፈጥሩ በዚህ ለሰው በማይታይ ደባ እሳካሁን አረሙ ወያኔ ትንፋሹን እዬሰበሰባ የተፈጠረበትን የጥፋትና የባንዳነት ተልዕኮውን ሲከውን ኖረ።

ከዛም በፊት አልተሳካም እንጂ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በሚያመክኑ ሥውር ሴራ ረቂቅ በሆነ – ሰልጠን ባለ መንገድ ፍርሻ -ህውክት – ሲፈጠር ማገዶዎች ሌሎች ነበሩ። አሁን ጥግ ጠፋ …. በጠራራ ጸሐይ መሸፈኛ አልባ  ገመና መውጣቱ ግድ ሆነ። የወገን የበዛ ሰቃይ የምትፈሩትን አቅም በመንፈስ ጽዑም ለዛ አጋባና ፋሽስቱን ወያኔ ፊት ለፊት ወጥቶ አወገዘ። ይህ ሲቀጠል ደግሞ ተከታዩ ምን ሊሆን እንደሚችል ታውቁታላችሁ …. አጃቢ ጠፋ … አቆላማጭ ጠፋ …. ሸፋኝ ጠፋ …. ቅኖች ዛሬን አነበቡ ….. ሚስጥር ተግልጦ እንዲህ በጉባኤ ሥጋና ደምን አዋህደ፤ የሀገራችን ውርዴት ውርዴታችን ነው አሉ ዬእትብት የቁርጥ ቀን አላማና ራዕይ ያላቸው ልጆቿ እንሆ ፊት ላይ ተገኙ። የወገናችን ስቃዩ ስቃያችን ነው አሉ የትውፊት አንበሶች።  የወገናችን መከራው መከራችን ብለው ሆ! ብለው እንደ ትሩፋታቸው ተነሱ። ሌሎችም በዚህ በመከራ ቀን መታቀብ አለብን ብለው ሰብሰብ ብለው ተቀመጡ። ወቀሳ የለ ነቀሳ የለ። መነገድ በቃ ….. እዬተጣቡ መጣባት ማብቃት አለበት አሉ። ወሰኑ  - ቆረጡ – ተንቀሳቀሱ። ይህ ደግሞ መሽጎ ብቅ እያለ ቤንዚን ለሚያርከፈክፈው አልማጭ አልተመቸም።

ጭድ ከማቀበሉ በፊት ሃሳቡና እልሙ ጭድ ሆኖ አረፈ። ራሱን ገልብጦ አቃጠለው። እኔ እንደማስበው ወቅቱን በአግባቡ አድምጦ ማስተዳደር ከተቻለ አሁን የነፃነት ትግሉ ከጠራ መስመር ላይ ይገኛል። በእጣት የምትቆጠሩ ወገኖች በሰላማዊ ትግል ሥም፤ ወይንም በሉዕላዊነት ተቆርቋሪነት ሥም፤ ወይንም ሊዋህዱ ባልቻሉ የአንድነቱ ቤተሰቦች ሥም ወይንም በሃይማኖት ሥም፤ ወይንም በብሄርና ብሄረሰቦች ሥም ስሱን ቦታ እያዩ ካቫውን ደረብ አድርጎ ጠቅ እያደረጉ አጋግሞ ዞር፤ ወይንም እኔም አለሁ እያሉ እዬገቡ ማመስና ማተራመስ አይቻልም። ቀኑ እንደ ክብረዎት ሾለከ …. አዬ ቀን! …. እርግጥ ሲያስቡት ጎሽ መሸቢያ የሚባሉ መስሎዎት ነበር። በጣም ብዙ ሰው ነው ያዘነቦዎት።

እጅግ የምትናፍቁኝ የሀገሬ ልጆች በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ነገር ተከሰተ። ጀግና ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን በሚመለከት በተፈጠሩ ክስተቶች በዬቦታው እጅግ በጣም ብዙ ነገር ነው የተዝረከረከው፤ የነፃነት ትግሉ አካል ተብለው ባለወርቅ ተክሊል ባለቤት የነበሩትን ሁሉ ነው የዛ ጀግና ድል ያንዘረዘረው – ካልጎሽ አይጣራ፤

ከዚህ ቀጥሎ ጀግናዬ አንዳርጋቸው ጽጌን በማፍያ ትብብር ከወያኔ እጅ መግባት በሚመለከት ደማችን የተቆጣ ሃይሎች የሀገራችን ክብር መደፈር ያነገበገበን ወገኖች፤ በገፍ ሰላማዊ ቀንበጥ አርበኞቻችን ወደ እስር እዬተጣሉ በሚወሰድባቸው ፋሽስታዊ ህገ ወጥ እርምጃ ይግርመዎታል ብዕረኛው አቶ ጌታቸው እረዳ ጉዳያችን ነው ብለን አካላችን እንዳይመስለዎት መንፈሳችን በፈቃድ አጋባን። በቃ! ተሰደንም ሰላም እንዴት እናጣለን ብለን ለይ አልን። ….. ለስላሳዊ ተፈጥሯዊ ባህሪያችን ጎርበጥባጣ ሆነ … ልንመች አልቻልነም። እኔ እንዲያውም ቆርጫለሁ የፈለገ ህዝባዊ ስበሰባ ይሁን አቋሙ ባለዬ፤ በተወዛወዘ ቦታ አልገኝም። ብዕሬም ብራናዬም መደከም የለባትም። በሃይማኖት፤ በማህበራዊ ግንኙነት ሁሉ ጥርት ባለ መስመር መድከም – ለትርፍ፤ በስተቀር ለኪሳራ ቆራጣ ነገር አይባክንም ከእንግዲህ።

ኢትዮጵያዊነት ሃይማኖታችን፤ ኢትዮጵያዊነት ቀለበታችን፤ ኢትዮጵያዊነት ድምጻችን፤ ኢትዮጵያዊነት ቀለማችን፤ ኢትዮጵያዊነት ህገ – መንግሥታችን፤  ኢትዮጵያዊነት ቅኔያችን፤ ኢትዮጵያዊነት ውስጣችን ብለን እነሆ ተነሳን። የሃይላችን ምንጩ – የሃይላችን ጭንቅላቱ – የሃይላችን ጉልበቱ – ብንዘገይም እግዚአብሄር ምክንያት ሰጥቶ ከቀስት እናመልጥበት ዘንድ አጥቢያ ኮከብ አበራልን።

ይህ ነው ፋታ ነስቶ – እረፍት ነስቶ አምክንዮው የፈለሰበት፤ ጠረኑ የተበተነ፤ መግቢያና መውጫው የተተበተበ፤ ፍላጎቱ እንጡሩብ የሚዘል፣ አንድም መረጃ ሊቀርብበት ያልቻለ ብትክ – ብትክትክ ያለ የቃላት ድርድር ያሰነበቡን።  …. ድጋሚ እንኳን ደስ አለዎት እራስዎትን ስላገኙ። ከመሼ ቢሆንም። ከቻሉ በመጪው ምርጫ ለጠ/ሚር ውድር ወይንም ለከዘራ ደጋፊነት ይወዳደሩ …. ምን ሻታ ያዞረዎታል? … ከዘራ ስል እርጅና ማለቴ አይደለም። አልወጣኝም እንዲያውም ብዕረዎት በሬ ወለደ ናት እንኳንስ እኔ ብዬ። ለማለት የፈለግኩት ስንት ናቸው የሽፍታው ዬወያኔ ም/ጠ ሚር …. ለነገሩ በመጪው ምርጫ ያው ዘሬን ዘሬን እያለ የሚዳጭረው አቶ ወንበር  ከቦታው ወርቃማውን ካገኘ ከዘራ ላያስፈልገው ይችል ይሆናል …. ከዛ በፊት ግን ነፍሳችን በመቋጠሪያ አልያዝናትም ሁላችንም …. ማን ያውቃል የሁለት ቢላዋ ባላቤቶች …. ሽኝት ቢጤ ይኖር ይሆን? ወፏን ጥያቄ መሄድ ….. አሰኘኝ …. እንደ ማለት —-

ሌላው እንዲያውቁት ዬምፈልገው ነገር ኢትዮጵዊ ተቋማቱ የመወያያ መድረኮች ስለምን እንዲህ „የናዚ ኔት ወርክ“ እስከማለት አደረስዎት ቢባል። ለዘር – ለመንደር በሽተኞች „ኢትዮጵያ“ የምትል ሥም ሁሉ ዛር ታስወርዳላች …. የወያኔ ተልዕኮ ይህቺን ምድር በተፈለገው መልክ ማጥፋት ነው። ይመኟት የነበሩት ባእድ ሀገሮችም እነሱ ስላልቻሉ ከማህጸኗ በፈሉ ተውሳኮች ፍላጎታቸውን በማስፈጸም ላይ ይገኛሉ።….ሽፍታው ወ ያኔ መሰረተ ጥንስሱ በአንድ ዘር የበላይነት ኢትዮጵያዊነትን ለማጠፋት፤ ለመደምሰስ በተከታታይነተትና በትጋት መሥራቱ ፍጥረተ ነገሩ ነው። ሲከስም ግን ከሥሩ ዘር አልባ ሆኖ ይሆናል። እኔ እምሻው እንደዚህ ነው  …  መርዝ መነቀል አለበት።!

ሌላው ቀርቶ ወያኔን የተገባውን ያህል „ለትግራይ“ አላደረገም ወይንም በደሉ መረን ለቀቀ እቃወመዋለሁ ብሎ የሚነሳ አንድም ድርጅት ወይንም አንድም የመወያያ ክፍል „ኢትዮጵያ“ የምትለውን አስቀድሞ አያውቅም። አይደፍሯትም። ቀዳሚው …. ለምን ይህ አልጎረበጠወትም? ይመቸወት ይሆን  - የሸረፋ ሸጎሬ?

አቶ ጌታቸው ረዳ ጹሑፎዎት በጣም ቁንጥንጥ ያበዛ ቁንጣን ያያዘው ነበር። እጅግ አብዝቶ የዕድሜዎትን ተፈጥሯዊ ጸጋ ሁሉ ድጦታል ልበልን? ጥንቃቄ ፈጽሞ አልጎበኘውም። ማገናዘቢያው ሆነ ማመሳካሪያው የእንቧይ ካብ ነበር። እንዲህ የሚጋልብ ስሜታዊነት ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊነትን አያድንም። የሳሙና አረፋ ያውቃሉ? ወይንም  ፈረሰኛ ውሃ ሙላት የሚባል እንደዛ ነው ልበልን? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የሚያድነው ከበቀል የጸዳ ከቂም የነፃ እራስን በፍጹም ሁኔታ ያሸነፈ፤ ውስጥን በሚገባ መቆጣጠር የቻለ፤ ዬባህላዊ ትውፊታችን ህግጋት በስክነት ያወያዬ መንገድ ብቻ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊነት እንደማንነት መግለጫ ያድነዋል። በዚህ ሃዲድ ብቻ ትውልዱ ከአፍር ለማኝነት ይድናል። በስተቀር ግን ዛሬ ስንዴ ነገ ደግሞ ከበለጸጉ ሀገሮች አፈር ለማኝ መሆናችን አይቀሬ ነው። የአንድነቱ ዋቢ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በወያኔ አቅም ብቻ አይደለም ለዚህ የበቁት። ዬኢትዮጵያ ዬአፍሪካ ቀንድነት፤ የመካከለኛው አፍሪካ እራስነት መናድ በጥረታቸው የማይቻል መሆኑን ሲያውቁ ከውስጧ ባንዳ አመረቱላት። ይህ ዕውን እንዳይሆን ነው የሴራው ድርና ማግ። ለማንኛውም በዚህ ሳይሞቅ እንደ ጉድ በሚፈላ ኮበሌ ብዕርና ብራና የተበዳይን – የመከራን – የግፉዕንን ሰዉ ትእግስቱን ያሸፍታል። አይገባም። እልህና ቁጭት ሌላም እሳት ያቀጣላል። የከረፋ በደል አለ። የሚያንገሸግሽ አድሎ አለ። የሚያንገፈግፍ መገፋት አለ።

በከረፋው በደል ውስጥ ወያኔ እንዲሸፈን ሽፋን ፈልጎ የትግራይን ህዝብ ምሽጉ አድርጓል። ይህን ሚስጥር ተፈልፍሎ እንዲገኝ ማስተዋል ተንበርክኮ ይጠይቃል። ማስተዋል ሱባኤ ላይ ነው። ዕንባም ህማማት ላይ። ስለሆነም መርዛማ እጩን ለይቶ ነቅሎ ዬማውጣት ሥራ ነው መሠራት ያለበት። እርስዎ እያሉን ያሉት ደግሞ ሌላ በበቀል የጨቀዬ – ጨቀጨቅ ከሃሞት ጋር አንድንጎርስ ነው። ቢያዳምጡኝ ምልዕትን አግልሎ ኢትዮጵያን ማዳን ከቶ አይቻልም። ስለዚህ ወቅቱ አብዝቶ  ከእያንዳንዳችን እላፊ አለመሄድን ይጠይቃል። በተጨማሪም እራስን አሸንፎ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። እርስው እኮ እራስዎት አመለጠወት። ሰው መሆን በቂ ነው – ለዛሬም – ለነገም – ለነገ ተወዲያም። በበቀል ብቅል እዬታረሰ ያለውን የምልዕት መንፈስ መፈወስ የሚቻለው እርስው በመረጡት መንገድ አይደደለም። የድህንቱ መንፈስ እንዲህ ሲል ይቃኙታል http://www.zehabesha.com/amharic/archives/33615

ህዝባችን ጎጥ አስተዳደር እጅ እጅ ብሎታል።  እጅ እጅ ያለውን አስተዳደር የበቀል ብቅል ሚዛን ላይ አስቀምጦ ፍትሃትንት ማወጅ …. ቢደለዝ – ቢቀባባ – ቢሸፋፈን አይሆንም። ኢትዮጵያ ከትግራይ በወጡ ፈለፈሎች እዬተደበደበች ነው ያለችውልጆቿ መጠጊያ አልባ በቀን ብርሃን ጨለማ ተውጠው ነው ያሉት። በዜግነታቸው ለመኖር አልተፈቀደላቸውም። አልሰሙም ማለት ነው። የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ታላቅ እህት እኮ በ24 ሰዓት ሀገር ለቀው እንዲወጡ ነው የተበዬነባቸው … ምን ማለት ነው ይሄ …. የቀለም ጥልቅ ዕውቀተዎት ይህንን አምክንዮ እንዴት ይተረጉመዋል? እውነትና ሃቅን አይሸሹት! … ይድፈሩት! ….. ማነው የዜግነት ፈቃድ ሰጪው?! …. ሀገሬ ሰንድቅዓለማዬ ብሎ የማያውቅ የጎጥ አስተዳደር ….? ብዕረዎት ማጅራቷ ላይ ይሆን ዓይኗ ያለው? የጥበብ ሰው እኮ መከራን አብዝቶ መጋራት አለበት። መረመጥ አለበት። አልቻለችም ብዕረዎት …. ወንዝ መሻገር አቃታት …. ቃተተችም። የጥበብ ቋንቋ እኮ ሰውነት ብቻ ነው። የፍቅር መግለጫው ደግሞ ህግን አለመዳፍር ነበረ። ወደቀች አንዘላልጦትም። ወያኔ ማለት በግልጽ ቋንቋ ከባህር የወጣ አሳ ማለት ነው።

የኔዎቹ ወገኖቼ። እንደዚህ ዓይነት ክብሪት ብዕሮችና አንደበቶች አብረው የኖሩ ናቸው። በሰላሙ ጊዜ የተረጋጋ ተግባር ሲከውን ከቀፏቸው ውስጥ ተሰብስበው አድብተው ይቆያሉ። ወያኔ በወሰደው ጨካኝ እርምጃ ቁጣ ሲነሳ ግን አዲስ ተለጣፊ ነገር ፈብርከው ብቅ ይላሉ። መጠለያ አላቸው ድርጅት። ይህንንም መፈተሽ ያስፈልጋል። ማንዘርዘሪያ ማዘጋጀት በእጅጉ ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው አንድ የፖለቲካ ድርጅት አባላቱ የሚተዳደሩበት ደንብ ለአባላቱ የህይወታቸው መተዳደሪያቸው ነው። ከዚህ ማዕቀፍ ከወጡ በድርጅቱ ሥርዓት ቅጣት ይፈጸምባቸዋል። እንደዚህ ዓይነት ሀገር የሚንድ ውጪ ያለነውን ሳይቀር ህግን ጥሶ ነፃነት የሚቀማ፤ ክብርን የሚዳፍር ተግባር አባላት ሲፈጽሙ ድርጅቶች ሃግ ማለት አለባቸው። በስተቀር ግን ተስማምተውበታል ማለት ነው።

በሌላ በኩል ድርጅቱን አትንኩ፤ የግል አስተያዬት ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም። የፓርቲ አባል ትንፋሹ ከፓርቲው ማልያ ጋር የተሳሰረ ነው። በፓርቲ ህይወት ውስጥ ዬግል ዕይታ የሚባል ነገር የለም። በቀኝም – በግራም – በፊትም ሆነ በኋላም ቢመዘን – ቢፈተሽ በስተጀርባ ካላው የፓርቲውን አቋም ጋር እንደዚህ መሰል የአባላት ግድፈቶች ነፃ ሊሆኑ ከቶውንም አይችሉም። ነፃ ሊሆን የሚችሉት ፓርቲው በአባሉ ላይ ፈጣን  እርምጃ ሲወስድ ወይንም ግልጽ የሆነ አቋሙን በአደባባይ ሲገልጽ ብቻ ነው። በስተቀር ድርጅቱ አብሮ መድቀቁ የግድ ነው። አኔ ከፓርቲዬ – ፓርቲም ከእኔ ፈጽሞ መለዬት አይችልም። ምክንያቱም አንድ የፓርቲ አባልን ከፓርቲው ነጥሎ ለማዬት ፈጽሞ  አይቻልም። ሰርገኛ ጤፍ ላይ ነጭ ጤፍን ለቅሞ የማውጣት ያህል ከባድ ነው። ስለዚህ የእስካሁኑ ጉዞ በዚህ በተደባለቀ ዝንቅ ጉዙ ጊዜው መቃጠሉ አይደለም በጣም ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ተጎድተዋል። ተመስገን! ሱማሌን መመከት በይቻል ዛሬ እንደ ህዝብና እንደ ሀገር ለመጠራት ባልቻልንም ርፍራፊ ነገር አለችን።

ከዚህ ባለፈ በዚህ መሰል የሀገር ጠላትንት ነቀዝነት ማጋዶዎቹ – ቅኖች – ደጎች – የእውነት አርበኞች – የግንባር ሥጋዎቹ አለፉ፤ ቤት ንብረት ፈረሰ፤ ልጆች ወላጅ አልባ ሆኑ፤ የሰው ልጅ እንደ እንሰሳ በመርዝ መሞከሪያ ሆነ …. በቤንዝንም ተቃጠለ … በጠራራ ጸሀይም በመዲናዋ የባሩድ እራት ሆኑ … በርካቶች ታፈኑ …. ከእንግዲህ ግን ዬሚከፈለው መስዋዕትና የትግሉ የጥራት ጉዙ መመጣጠን አለበት። ይህ የማግለል ዘመቻና ፖሊሲ የወያኔ ብቻ አይደለም አዲስ ነገር በቅሎ ለማዬት አይናቸው የማይችሉትም አቅም ቢሶች መገለጫ ነው። የሆነ ሆኖ የሾለከው ነጥሎ ሌላው ሾላኪውን እዬቀደሙ በጥንቃቄና በማስተዋል መጓዝን ይጠይቃል። ወቅቱ የመቆላማጫ የመላላሻ የጥሎሽ ጊዜ አይደለም።

…. ግን እንዲያው ለነገሩ ለእርሰዎ የተከበሩ ዬአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመያዛቸው እንደዛ ሆነው በጎጥ አራዊቶች ማዬታችን፤ ወጣት ጀግኖቻችን የሃብታሙን፣ የዳንኤልን፤ የሽዋስን፤ የአብርሽን የጣር ድምጽ መሰማት እንዲህ ያስጨፍራል? ለእኔ አቶ አንዳርጋቸውን ጀግናዬም ሽልማቴም ብዬ መጻፌ ይህን ያህል ዛር ያስነሳል? ጎሽ ወያኔ ደግ አደረክ መልካም ሰራህ – የምትፈራውን ሰማዕት በእጅህ ስለገባልህ ሻማ ይብራልህ ልንል ነበር የተፈለገው …. ደግሞስ እኔ እኮ ነፃ ሴት ነኝ። የፈለግኩትን ድርጅት የመቀላቀል፤ የፈለኩትን ድርጅት ዬማድነቅና ዬማክበር፤ ውስጤ የሚያምንበትን አውጥቼ መጻፍ እንድችል እኮ ነው የተሰደድኩት። የእሶዎ አጋዚ ብዕር ተፈርቶ ጭጭ ረጭ እንዲባል ነበር የሚፈልጉት። እንዴት ተቀለደ?!

…. እጅግ የማከብራቸው ሙሴን ነው ወያኔ ያፈነው – የማድመጥ ሊቅም ነበሩ። ይውጣለዎት። ወያኔ ባንዳው ጠላቴ ነው። አሁንም ይደገም እስከ ማንፌስቶው መነቀል አለበት። www.tsegaye.ethio.info በዚህ ገባ ብለው „ተስፋ“ ላይ የድህረ ገጹን ዓላማ ያንብቡት ካስፈለገዎም በድምጽም ያገኙታል። በተጨማሪም እኔ ስላለኝ አቋም በዬ15 ቀኑ በዚህ በድምጽ ያገኙኛል እርግጥ አሁን የበጋ እረፍት ላይ ነን ግን አርኬቡ ላይ ያለውንም Radio Tsegaye Aktuell Sendung ገባ እያሉ ይኮምኩሙ።

ትናንት የተፈጠረች አይደለችም ሥርጉተ። እንዲህ ገባ ተብሎ የሚዘለልባትም አይደለችም። ነዳያንን ስንት ፍሪዳ አርደው ድንኳን ጥለው የልደት ፆምን አደግድግዎ ጉንብስ ቀና ብለው ከሚያስተናግዱ ሊቀ ሊቃውንታት የተፈጠረች ናት።  መንገድና መርህ ራይና ተስፋዋ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። በምንም ንቅዘትና ጸያፍ ተግባራትም ፈጽሞ የማትታሰብ ክውን ናት። እንዴት የምትደነግጣውን ሴት አግኝተዋል? እሷን አፍ ለማዘጋት – አይችሉም! – ህልም ነው! — ለመሆኑ ይህ ግራ በሚባለወስ ታላቁ መርህ „የሴቶች የእኩልነት የአርነት ትግል አልነበረንም? ምነው ግፊያ አሰኘዎት? አንዲት ሴት እንኳን ለማስተናገድ ታዬ አቅመዎት …. ትንሽ እራፊ ቦታ የለዎትም ለሴቶች ተሳትፎ …. እግዚኦ! አዬ አቅል – አዬ አቅል — አይገዛ ነገር ———–

በተረፈ የሀገሬ ጫካ ሆነ እስር ቤቱንም የማውቀው ነው። ለእኔ አዲስ ዬሆነ ነገር የለም። ምነው ወጣት በሆንኩ በነበረ እንዲህ የዘር ዛርን በብዕር ሳይሆን በባሩድ ነበር የማሰተነፍሰው በለመድኩት ጫካ።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ የመወያያ ክፍል መድረክን  በሚመለከት በእኔ ሥም አይወርፉት። እኔ አድሚንም ቦርድም አባል አይደለሁም። በህግ ዕውቅና ያለው የተደራጀ ስለሆነ ዕውቅና የሰጠው አካል ቢጠይቀዎት መልስዎት ምን ይሆን? በቃ ቱግ – ቱጉ ብቻ … ማህከነ!

ከረንትን ያህል ኢትዮጵያዊ ተቋም በቦርድ አባልነት ለመምራት አቅሙ የለኝም። ቢሆን ግን ደስታውን አልችለውም። እርግጥ ነው ከዬካቲት 2009 አስከ የከቲት 8 . 2010 ቋሚ አባል ነበርኩኝ። አሁን አባል ባልሆንም እናት ቤቴነቱ ግን እንደተጠበቀ ሆኖ የድህረ ገጹ ደግሞ ዘበኛው ነኝ። የማይመቸኝ ላይ ሚዛን ለመጠበቅ ብዙ ጊዜ ከሥር እጽፋለሁ። አላምነውም በቀን እስከ ስድስት ጊዜ አዬዋለሁ። ይገርመወታል ሌሊት ሁሉ ክፈት አድርጌ አዬዋለሁ። እንደ ጦር የምትፈሩት የተግባር ቤት ስለሆነ ነው። ከረንት አቅሙን የሚገልጸው በሥራ ነው። አቋሙ ደግሞ ከጊዜ ጋር እንደ ወጀብ እንደነካው ዛፍ አይዘፍንም። ቀጥ ያለ የአደራ ማውጫ ቤት ነው። ኢትዮጵያዊነትን ሰንደቁ ስላደረገ ትቢያ ለበሳችሁ አፈር ቆረጠማችሁ ብትረግሙትም ከተግባሩ አንድ ጋት ፈቅ እንደማይል አስባለሁ። ግልጽና ጽኑ አቋም ነው ያለው። አቋሙ ወያኔ ከነጉቱ ከነ ዘረኛ ማኒፌስቶው መነቀል አለበት ባይ ነው። ይህ ደግሞ የእኔም የህይወቴ መርህ ነው ተግባባን ጌታው?!።

ማይጨውን ሳዬው ደግሞ …  ዬሽበት ትርጉሙ ሽሽጉኝ ብሎ ጆንያ ውስጥ ሲቀረቀር አዬሁት። ታዬኝ እኮ ማይጮ የግንቦት 7 አባል ሲሆን? በመንፈሱ የጉልማ መሬት ታህል ለትጥቅ ትግል ቦታ እንዳልነበረው ነበር እኔ ሳውቀው። ሰላማዊ ትግል ደጋፊ ሆኖ ነው እኔ የማውቀው። ኢሳትን ሊደግፍ ይችላል – የነፃነት ትግሉ መተንፈሻ ንጹህ ቧንቧ ስለሆነ። ይህ ደግሞ ለወያኔ ስርዎ ስውርም ደጋፊዎች ረመጥ ነው። ቅጥል – ድብን  - ፍርክርክ አድርጎ ብርክ ያስይዛችኋል።  እኔ እንደማስበው ያው እርስዎም ተደብቀው ያጣጥሙታል ብዬ አስባለሁ። ያው ቅናት ናት እንዲህ ፈርፈር የምታደረግዎ እንጂ። በልበዎ ያደንቁታል አይደል ኢሳትን? ማንም የአፍሪካ ሀገር ያልደረሰበት የእድገት ደረጃ ላይ ስደት ላይ ሆኖ ተግባሩ አንቱ ነው።

ሳረሳው ደግሞ አንድ ነገር – አልኮዎት ጌታው አሁን እኔ ሌላ የወመኔውን ድራማ እዬጠበኩ ነው። … ኢሳትን የሚረዱት ጥንታዊ ጠላቶችችን ናቸው የሚል …. ይህ አይቀሬ ነው። ለነገሩ እርሰዎም እኔም ተሰደን የምንኖርባቸው ሐገሮች አንድም ቀን ለአፍሪካ የነፃነት ትግል ቀን ያወጣቸው ዬሀገረ – ኢትዮጵያ ወዳጆች አይደሉም። ማንስ ወዳጅ ኖሯት ሲያውቅ ነውና? ስለዚህ እርስዎም እኔም ጓዛችን ጠቅለላ ነዋ ከእነሱ ዘንድ አይደለን ያለነው? በፈለገው ቅርጽና ይዘት ብቅ ይበል  ዬእንኮሸሽሊቱን* የበቀል ብቅሉ ድራማ እንኩቶ እናዳርገዋለን። አይገርመንም – አይደንቀንም። አሁንስ ተግባባን?! … ያው ያችን አንጠልጥሎ ማቀጣጠያ የባህር ዛፍ ቅጠል ለቀማ ቢወጣ ባዶ እጁን ተመላሽ ይሆናል – ግፋፎው – ወያኔ። ሌላው እርስዎም አንደሚያውቁት  ዘረኛው ወያኔ የሚተነፍስው በልምና ስንዴ ነው እንኳንስ የስደቱ ሚዲያ …. ስለዚህ ገና ወያኔ አፉን ሲከፍት ቆረቆንዳ በልኩ ተሰርቶለት ይደፈናል – እሺ!

ሲገርሙ! ምነው ይህቺ ሚዛኗ ላይ አስኳላዋን ገፋ አላደረጉ ይሆን? ሰው በነፃነት በሚኖርበት ሀገር ካላፈቃድ ፎቶ በወንጀለኛ ሥንኝ … መለጠፍ፤  እንደ ተቋም ሶስቱም ሩሞች ህግ በመተላለፍ ክስ ቢመሰርቱ ዋጋወን ያገኙ ነበር። ታዳሚውን ሁሉ እኮ ነው አብረው ያረሱት። ኦኦ!  በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ፎቶና ከሥሩ የጨነቆሩት ሐረግ በራሱ ገመድ ነበር አዙሮ የሚያንቅዎት። በጣም ተዳፈሩ፤ በጣም እራስዎትን ውድና ዬትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ አደረጉ፤ ቆርጠውና ቀደው የሚያሳድሩን ያህል ነው የተጋፉት፤ ግን ህግ እዬተላለፉ – እዬዘለፉ – እያዋራዱ …. እንዴት እንቅልፍ ወሰዶዎት?

ለመሆኑ „ናዚ“ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ በምንስ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል? አስፈጻሚ ተቋማቱ ምንድን ናቸው? ዬዶክተሪኑ ሥነ ህይወት ገጽታ ሆነ ፍለስፍናው በምን ይገለጻል? በዚህ እድሜ -  በዚህ የዘመናት ተመክሮ በስሜት የተከዘነ ጆንያ ሙሉ የጭድ ትንፋሽ የኢትዮጵያን የነፃነት ራህብ አይታደግም። ዙሪያ ገባው ነዳላ – መወተፊያ ወይንም መጥቀሚያ መርፌ ወይንም ለማያያዝ ሙጫ ነገር የማይደፈረው  የተቆራረጠ ሙጣጭ – ግብና መቋጠሪያ አልቦሽ ኩረት ነው ሲደረደሩ እንቅልፍ አልባ ሆነው የሰነበቱት ….

ጌታው አንሰነባበት – ስንብቱ ለዳርቻ ነው። ከዚህ በኋላ የገደሉትን ገድለው – የወቁትን ወቅተው – ቀረኝ የሚሉት ማሳ ካለዎት ያስኬዱት። የፈራን እንዳይመስለዎት። ከትጋታችን አንዲት ጋት ፈቅ የማንል እንደሆነ እንዲያውቁት ነው የተጣፈለዎት። ቀጣዩ ህይወትዎትን – ዘርዎትን ፍለጋ መማሰን ሽበትዎትን – ዝልቅ ተመክሮዎት አንገቱን ደፍቶ እዬጠበቀዎት ነውና ይታረቁት። የሽንፍላ ጹሑፎወትን የመረጃ ማያያዣ ሊንከዎትን አለጠፍኩትም ተጸዬፍኩት – ገዳይ ገዳይ ወይንም አስገዳይ አስገዳይ ይሸታልይከረፋል። እኔ አብቅቻለሁ። መልካም የምንም ጊዜ …..

ውዶቼ የእኔዎቹ አሻቅቦ በሁሉ ነገር የሚበልጥን ወገን መናገር እንዴት ይከብድ ይመስላችኋል። ያልኖርኩበትና ያላደኩበት ሆኖ ውስጤን አብዝቶ አስጨነኩት። ግን መሆን ነበረበት። የኔዎቹ ደህና ሰንብቱልኝ። መሸቢያ ጊዜ! ውድድድ.

 

  • ጉርና – የቅል ዕድገት ማብቂያ – ቅርጽ የለሽ ዕድገቱ አንገቱን ውጦ ሽንጡን ያሰፋዋል። በባለሙያ ውስጡ በሚገባ ይዘጋጅና ማንገቻ ይሠራለታል። ከባላ መንታ እንጨት ላይ ሆኖ እርጎ ይገፋበታል ወይንም እርጎው ተንጦ ቅቤ እንዲወጣ የሚረዳ ባህላዊ ዕቃ ነው። ትንሽ የምትሉት ብዙ ስለሚይዝ ጉርና ይመስል ሆድ አታብዛ ይባላል። ከተሰጠው ጸጋ ወጥቶ እሳት ላይ ቢጣድ ግን ከማረርም አልፎ ከእርጎ ጋር ጎርንቶ ተነዳድሎ እራሱ ህልፈቱን ያውጃል።
  • ኩታራ - የልጅነት ጊዜ። ምራቁን ለዋጠ የእድገት ደረጃ ገና ጮርቃ የሆነ እንደ ማለት።
  • እንኮሸሸሊት - ቅጠሉም ግንዱም ፍሬውም እሾህ የሆነ በወይና ደጋ የሚበቅል የዕጽዋት ዓይነት

 

 

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል!

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጥር ነው!

ደሜን ሳደምጠው ውስጤን አገኘዋለሁ!

 

 

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>