Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: የጉበት በሽተኛ ነኝ፣ በምን መልኩ በዕድሜ መቆየት እችላለሁ?

$
0
0

የጉበት በሽተኛ መሆኔ ታውቆ ህክምና መከታተል ከጀመርኩ ወራቶች አለፉኝ፡፡ ሆኖም ስለ በሽታው ያለኝ ግንዛቤ ዘወትር የሚከሰትብኝን ድንገተኛ አካላዊ ለውጥ እና የህመም ስሜት እየረበሸኝ ይገኛል፡፡ አሁን እንደሰማሁት ከሆነ ደግሞ ብዙ አይነት የጉበት ቫይረሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አይነቶች ምን እንደሆኑ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ሐኪሞቼ ከሰጡኝ የጥንቃቄ ምክር ውጭስ እንዴት የህመም ስሜት ሊፈጠርብኝስ ቻለ? በእርግጥ ግን ይህ በሽታ ይድን ይሆን? እባካችሁ ስጋቴን አቅልሉልኝ፡፡
እዮብ ነኝ

hepatitis-s1-liver-hepatitis-virus
ውድ አንባቢያችን ስጋትህ ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ያንተ የጉበት ቫይረስ ችግር የትኛው አይነት እንደሆነ ለማወቅ ዝርዝር ጉዳዮችን አልፃፍክልንም፡፡ ሆኖም በሽታው በአጠቃላይ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ቫይረስ በተመለከተ ግንዛቤ ከማስጨበጥ የዘለለ እርዳታ ልናደርግልህ ባንችልም እነሆ ስለ ጉበትና የጉበት ቫይረሶች እንደሚከተለው ጠቅለል አድርገን ልናጫውትህ ወደድን፡፡
ጉበት የተባለው የሰውነት አካል ከሆድ ዕቃዎች ውስጥ ትልቁና ውስብስብ ስራ ከሚሰሩት ዋና ዋና የሰውነት ክፍላችን ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ጉበት የሚገኘው በቀኝ በኩል ከጎድን አጥንታችን ዝቅ ብሎ ሲሆን የሚሰራቸውን ስራዎች በጥቅሉ ስንመለከት፡-

- የምንመገበውንና የምንጠጣውን ወይም በሰውነታችን ውስጥ የሚመረተውን ጎጂ የሆነ ነገር በማስወገድና ጎጂ ወደ አልሆነ ሁኔታ በመቀየር በደም አማካኝነት በኩላሊት አድርጎ ከሽንት ጋር ወይም በአንጀት በኩል ከአይነ ምድር ጋር እንዲወገድ ለማድረግ ይረዳል፡፡
- ምግብ ከተፈጨ በኋላ በውስጡ ያለውን ንጥረ ነገር ወደ ፕሮቲን፣ ካርቦሃይድሬትና ፋት ከመቀየርም በላይ ሰውነታችን ያልተጠቀመውን የኃይል መጠን በጉበት ውስጥ በሚቀመጥ መልኩ ይዞ የሰውነት ስኳር ዝቅ በሚልበት ወቅት የኃይል ሰጪ ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡
- 50 በመቶ የሚሆነው ሰውነት የሚያስፈልገው የኮሌስትሮል መጠን በጉበት አማካኝነት ሲመረት የተቀየረው 50 ፐርሰንት ደግሞ ከምንመገበው ምግብ የምናገኘው ይሆናል፡፡ በጉበት ከሚመረተው ኮሌስትሮል ውስጥ 80 ፐርሰንት የሚሆነው ሀሞት ለመስራት ሲያገለግል የተቀረው ደግሞ የተለያዩ በሰውነታችን ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ሆርሞኖች ለመስራት ይጠቅማል፡፡ በተጨማሪም በማንኛውም ሴል ውስጥ መገኘት ያለበት እንደመሆኑ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል ማለት ነው፡፡

- በተጨማሪም የተለያዩ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችና ፕሮቲኖች በተለይም ደግሞ ደም እንዲረጋ የሚያግዙ በርካታ ንጥረ ነገሮችን በማምረት መሰረታዊ የሆነ ጥቅም ይሰጣል፡፡

ታዲያ ጉበቱ ይሄንን ያህል ጥቅም ካለው የጉበት መጎዳት ምን ያህል ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አያዳግትም፡፡ ለዛሬ በዋነኛነት የምንመለከተው የጉበት መቆጣት ሄፖታይተስ /hepatitis/ ሲሆን ይሄንን ጉዳይ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
Hepatitis የተባለው የጉበት በሽታ በተለያየ ምክንያት ሊፈጠር የሚችል የጉበት የመቆጣት ሁኔታ ነው፡፡ ለዚህ ችግር በዋነኛነት እንደ መንስኤ የሚጠቀሱት የሄፖታይተስ ቫይረስ የሚባሉ አምስት የተለያዩ የቫይረስ አይነቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ቫይረሶች በአንዱ ወይንም ከዛ በላይ በአንድ ጊዜ የመጠቃት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች እንደ የአልኮል መጠጥና መድሃኒት የመሳሰሉ ነገሮች ተመሳሳይ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
እነዚህ አምስት አይነት አሉ ያልናቸው የሄፖታይተስ ቫይረሶችን ስንመለከት፡

- ሄፖታይተስ ኤ ቫይረስ፡- በዋነኛነት የሚተላለፈው በንፅህና ጉድለት ሲሆን ይሄም ከተበከለ ምግብ/መጠጥ ወይንም እጅ ካለመታጠብ ከሰው ሰው በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል ሁኔታ ነው፡፡
- ሄፖታይተስ ቢ ቫይረስ፡- ይህ የቫይረስ አይነት በዋነኛነት የሚተላለፈው በደምና በደም ውጤቶች እንዲሁም ሌሎች የሰውነት ፈሳሽ ንክኪ በሚሆንበት ጊዜ ሲሆን ከእናት ወደ ልጅ፣ ያልተመረመረ ደም በመውሰድ፣ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት እንዲሁም በዲያሊስስ ጊዜ ሊተላለፍ የሚችል ሁኔታ ነው፡፡
- ሄፖታይተስ ሲ ቫይረስ፡- ይህ የቫይረስ አይነት ከሄፖታይተስ ቢ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይ የመተላለፊያ መንገድ ቢኖረውም ከግብረ ስጋ ግንኙነትና ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ በተወሰነ መልኩ ይቀንሳል፡፡
ሄፖታይተስ ዲ ቫይረስ፡- ይህ ቫይረስ ሄፖታይተሲስ ባላቸው ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰት ሲሆን መተላለፊያ መንገዶቹ በመሰረቱ ከሄፖታይተስ ቢ እና ሲ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
- ሄፖታይተስ ኢ ቫይረስ፡- ከሄፖታይተስ ኤ ጋር ተመሳሳይ የመተላለፊያ ባህሪ ያለው ነው፡፡
በመሰረቱ የጉበት መቆጣት፡- ከ6 ወር በታች የሚቆይ የጉበት ችግር
- ረጅም ጊዜ የሚቆይ /chronic hepatitis/፡- 6 ወርና ከዛ በላይ የሚቆይ የጉበት ችግር በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት በቫይረስ አማካኝነት የሚፈጠረውን ‹‹A cute hepatitis››እና በተለያየ ሳቢያ ሊከተል የሚችለውን ‹‹Chronic hepatitis›› ሰፋ አድርገን እንመለከታለን፡፡
Acute viral hepatitis:- ይህ ሁኔታ ከላይ እንደተጠቀሰው በቫይረሶች ሳቢያ የሚመጣ ሁኔታ ሲሆን በአብዛኛው ጊዜ ሲታይ በአፋጣኝ የሚከሰትና ለመጥፋትም ብዙ ጊዜ የማይፈጅበት ሁኔታ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ከሚከተሉ ስሜቶች ውስጥ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ ትኩሳትና፣ የአጥንት መገጣጠሚያ ህመም መሰማት፣ እንዲሁም አጠቃላይ የህመም ስሜት በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በአፋጣኝ ከተከሰተ ከትንሽ ቀናት በኋላ የአይንና የቆዳ ቀለም ቢጫ መሆን፣ የሽንት ቀለም መጥቆርና የአይነ ምድር ቀለም መንጣት ይከተላልና በአብዛኛው ጊዜ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ጠፍተው የጤንነት ስሜት መሰማት ይከተላል፡፡

ነገር ግን የሰውነት/የአይን ቀለም ቢጫ መሆን ይቀጥልና ከ1-2 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ በመድረስ ከ2-4 ባሉት ሳምንታት ውስጥ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ የአይንና የቆዳ ቀለም ወደ ቀድሞው ይመለሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀኝ በኩል ጎድን አጥንት ስር የህመም ስሜት መሰማትና አጠቃላይ ሰውነት ማሳከክ በተደጋጋሚ የሚታዩ ስሜቶች ናቸው፡፡

በአብዛኛው ይህ የጉበት በሽታ የሚታወቀው በሚያስከትለው የህመም ስሜቶች ሳቢያ ቢሆንም የተለያየ የደም ምርመራዎችን ማድረግና ሁኔታውን ማጣራት/ማረጋገጥ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ተገቢ ይሆናል…

አጣዳፊ ያልሆነና ረጅም ጊዜ የሚቆይ
ሄፓታይተስ /chronic hepatitis/

ይህ ክሮኒክ ሄፖታይተስ ከአጣዳፊው ሄፖታይተስ ባነሰ ሁኔታ የሚታይ ቢሆንም ለወራትና ለዓመታት ምንም አይነት ስሜትና ችግር ሳያስከትል መቆየት የሚችል ነገር ግን በአንድ አንድ ሁኔታዎች ደግሞ ለከፍተኛ የጉበት መጎዳትና ብሎም ለሞት ሊዳርግ የሚችል ሁኔታ ነው፡፡
በአብዛኛው ለዚህ ሁኔታ የሚዳርገው የሄፖታይተስ ሲ ቫይረስ ሲሆን 75 ፐርሰንት የሚሆነው በዚህ ቫይረስ የሚከሰተው የጉበት ችግር ወደ ክሮኒክ ሄፖተይተስ የመቀየር ባህሪ ያሳያል፡፡ የሄፖታይቲስ ቢ ቫይረስም በተለይ ከሄፖታይተስ ዲ ቫይረስ ጋር በመሆን በተወሰነ መልኩ ይሄንን ሁኔታ ሊያስከትሉ፣ በአንፃሩ የሄፖታይቲስ ኤ እናኢ ቫይረስ ይሄንን ችግር የማስከተል ዕድል የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የተለያዩ የጉበት በሽታዎች፣ መድሃኒትና አልኮል መጠጥ ለዚህ ሁኔታ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡

በአብዛኛው ጊዜ ክሮኒክ ሄፖታይተስ ስሜት አልባ የሆነ የህመም አይነት ቢሆንም ሊያስከትል ከሚችለው ስሜቶች ውስጥ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ድካምና አጠቃላይ የህመም ስሜት መሰማት፣ አነስተኛ ትኩሳት፣ አይንና ቆዳ ቢጫ መሆን እንዲሁም በቀኝ በኩል የህመም ስሜት መሰማት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከጊዜ በኋላ ጉበት መጎዳቱን የሚያመላክቱ እንደ ጣፊያ ማበጥና፣ የሰውነት ውሃ መቋጠርና ማበጥ ተከትሎ ሊታይ ይችላል፡፡ በአብዛኛው ይህንን ሁኔታ ለማወቅና ለማጣራት ከደም ምርመራ ባሻገር ከጉበት ላይ ናሙና በመውሰድ መመርመር ተመራጩ የምርመራ አይነት ናቸው፡፡
ከላይ እንደተመለከትናቸው የተለያዩ አይነት ሁኔታዎች የጉበት ጉዳትን ሊያስከትሉ እንደመቻላቸው መጠን ተገቢውን ጥንቃቄ አስቀድሞ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡
- አጠቃላይ ንፅህናን መጠበቅና ምግብ ከመብላት ወይንም ከማዘጋጀት በፊት እጅን መታጠብ አስፈላጊና መሰረታዊ ነው፡፡
- የደምና የደም ውጤቶች እንዲሁም የሰውነት ፈሳሽ ንክኪ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት እንደየፈርጁ መከላከል፣ ለምሳሌ በሆስፒታል ውስጥ ጓንት መጠቀም፣ ንፁህ/አዲስ መርፌ ብቻ መጠቀም፣ ደም ከመለገስ በፊት ማጣራት፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶም መጠቀም የመሳሰሉት በጥቂቱ ይገለፃሉ፡፡
- በእርግዝና ወቅት የደም ምርመራ ማድረግና ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ፡፡
- ለሄፖታይተስ ኤ እና ቢ ቫይረሶች የተዘጋጀ ክትባት እንደ አስፈላጊ መውሰድ
ማንኛውም ተመሳሳይ የሆነ የህመም ስሜት በሚሰማ ወቅት የህክምና ባለሙያ ጋር በመሄድ አስፈላጊውን ምክርና የህክምና አገልግሎት መቀበል ተገቢ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ በመጠንቀቅ ከጉበት ህመም መራቅ ይቻላል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>