1. የኢቦላ በሽታ ምንድ ነው?
የኢቦላ በሽታ በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ፣ በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ የኢቦላ በሽታ በምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች በተደጋጋሚ በመከሰት ከፍተኛ ህመምና ሞት እያደረሰ የሚገኝ በሽታ ነዉ፡፡ በሽታው በማንኛውም ወቅት በአገራችንም በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት የሚችል በመሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የኢቦላ በሽታ ለከፍተኛ ህመምና ለሞት የሚዳርግ ቢሆንም መከላከል ግን ይቻላል፡፡
2. የኢቦላ በሽታ መተላለፊያ መንገዶች፡-
•በኢቦላ ከታመመ ሰው ቁስል፣ ደም፣ ምራቅ፣ ትውከት፣ አይነምድርና ሽንት ጋር በቀጥታ በመነካካት ወይም እነዚህ ፈሳሾች ወደ ጤነኛ ሰው አይን ከተረጩና ከገቡ፣
•ንጽህናቸው ባልተረጋገጠ ወይም ሌሎች ህሙማን የተጠቀሙበትን መርፌ ሳይቀቅሉ በመጠቀም፣
•የኢቦላ በሽታ ታማሚ የተጠቀመባቸዉን ስለታማ መሳሪያዎች በመጠቀም፣
•በኢቦላ በሽታ የሞተ ሰውን አስከሬን በቀጥታ በመነካካት፣
•በኢቦላ በሽታ የሞተውን እንሰሳ ስጋ በመመገብ ናቸው፡፡
3. በኢቦላ በሽታ የተያዘ ሰው የበሽታዉን ምልክቶች የሚያሳያው መቼ ነው?
በኢቦላ በሽታ ከተጠቃ ሰው ጋር ንኪኪ የፈጠረ ሰው ከ 2 እስከ 21 ቀናት ባለዉ ጊዜ ውስጥ የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት ይጀምራል፡፡
4. በኢቦላ በሽታ የተያዘው ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶችና ስሜቶች፡-
•ድንገተኛና ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት ይይዘዋል፡፡ በተጨማሪም ማስመለስ/ትውከት/፣ ተቅማጥ፣ ራስ ምታት፣ የቆዳ ሽፍታ እና የአይን ቅላት ምልክቶች ይታዩበታል፡፡
•በሰውነታችን ክፍት ቦታዎች ማለትም አይን፣ አፍንጫ፣ ድድ፣ ጆሮ፣ ፊንጢጣና በብልት በኩል የመድማት ምልክት ሊታይም ላይታይም ይችላል፡፡
5. በኢቦላ በሽታ መያዙ የተጠረጠረ ወይም የተያዘ ሰው ከገጠመን ምን ማድረግ አለብን?
•ታማሚውን በምንረዳበት ጊዜ ሰውነታችንን ከበሽታው መከላከል የሚያስችለንን የእጅ ጓንት፣ የአይን መከላከያ መሳሪያ (ጎግል) እና የአፍንጫና የአፍ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም፤
•የታመመውን ሰው ወድያውኑ ለአስፈላጊ ህክምናና እርዳታ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጤና ተቋም መወሰድ፤
•በኢቦላ በሽታ የተጠረጠረ ሰው በሚገኝበት ወቅት ወድያውኑ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጤና ተቋም ወይም ጤና ጽ/ቤት ሪፖርት ማድረግ፣
•በበሽታው መያዙ የተጠረጠረ ወይም የታመመ ሰው የተጠቀመባቸዉን አልባሳትና መኝታውን በበረኪና ማጠብ ይኖርብናል፡፡
6. ለኢቦላ በሽታ ተጋላጭ የሆኑት ማናቸው?
•በሽታዉ ከታመመ ሰው የሚወጣውን ደምና ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች በቀጥታ በመነካካት የሚተላለፍ በመሆኑ ከታመመው ሰው ጋር የሚኖር ማንኛውም ሰው በበሽታዉ ሊያዝ ይችላል፡፡
•በሽተኛውን በሚመግቡበትና በሚንከባከቡበት ወቅት የእጅ ጓንትና ሌሎች መከላከያ መሰሪያዎች ሳያደርጉ ከሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ የሚፈፅሙ ሰዎች በቀላሉ በበሽታው ሊያዙ ይችላሉ፡፡
•በኢቦላ በሽታ የሞተውን ሰው አስከሬን ያለ እጅ ጓንትና ሌሎች የመከላከያ መሳሪያዎች የምንነካካ ከሆነ በቀላሉ በበሽታ ልንጠቃ እንችላለን፡፡
7. የኢቦላ በሽታን እንዴት ልንከላከል እንችላለን?
•የእጅ ጓንት፣ የአይን ጎግል እና ሌሎች የሰውነት መከላከያ መሳሪያዎችን በመጠቀም በበሽታው ከተጠቃ ሰው ውስጥ ከሚወጣው ማንኛውም ፈሳሽ ጋር በቀጥታ ባለመነካካት፤
•ያለ እጅ ጓንት በበሽታው የተጠቃውን ሰው ቁስል አለመንካት፤
•በኢቦላ በሽታ የተያዘው ሰው የተጠቀመውን መርፌና ሌሎች ስለት ያለቸውን መሳሪያዎች አለመጠቀም፤
•በኢቦላ በሽታ መያዙ የተጠረጠረና የሞተ እንስሳን ሥጋ አለመመገብ፤
•በኢቦላ በሽታ የሞተን ሰው አስከሬን ያለጓንትና ሌሎች የመከላከያ መሰሪያዎች ያለመንካት፣ የቀብር ሥነ ሥርኣቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈፀም ማድረግ ፤ እንዲሁም ከቀብር በኋላ ያለውን ስነስርዓት ማሳጠር፤
•የታመመውን ሰው ከረዳን ወይም በበሽታዉ ምክንያት የሞተውን ሰው አስከሬን ከነካን በኋላ እጃችንን በውሃና በሳሙና በደንብ መታጠብ፣
8. በቤት ውስጥ መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ ፡-
•በኢቦላ በሽታ የተጠቃ ወይም የተጠረጠረ ሰውን በተቻለ መጠን ለብቻው በተዘጋጀ ቦታ መለየት፣
•በበሽታው የተጠቃ ወይም የተጠረጠረን ሰው ወደ ጤና ተቋማት በምንወሰወድበት ወቅት ከታማሚው ጋር አላስፈላጊ ንክኪ አለማድረግ፣
•በበሽታው ከተጠቃ ወይም ከተጠረጠረ ሰው ወይም የሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ ከተፈጠረ ወዲያውኑ እጃችንን በውሃና በሳሙና መታጠብ፣
•በኢቦላ በሽታ የተጠቃውን ሰው በምንረዳበት ወይም በምንንከባከብበት ወቅት የእጅ ጓንት፣ የአይን ጎግል፣ የፊት መሸፈኛ እና ሌሎች የሰውነት መከላከያ መሳሪያዎችን መጠቀም፣
•በበሽታው የተጠቃ ወይም የተጠረጠረ ሰው የሰውነት ፈሳሽ መሬት ከበከለ በረኪና ይጨምሩበት፤ ከ15 ደቂቃ በኋላም ይፀዳ፤ በቆሻሻ የተነካኩ ቁሳቁሶችና አልባሳት መቃጠል ይኖርባቸዋል፣
•በኢቦላ በሽታ ታሞ የሞተ ሰው የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም ከአስከሬን ጋር ንክኪ አለማድረግ፣ የጋራ እጅ መታጠቢያም አለመጠቀም፣
•የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም አስከሬኑ በፕላስቲክ ከረጢት መጠቅለል፣ የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም በሰለጠነ የጤና ባለሙያ ምክር መታገዝ፣
9. በሽታው ወደ ሀገራችን ሊገባ የሚችልባቸዉ ሁኔታዎች፡-
በሽታው እስከ አሁን በሀገራችን ያልታየ ቢሆንም በምዕራብ አፍሪካ ሀገሮችና በሀገራችን መካከል ባለው የህዝብ እንቅስቃሴ ምክንያት በማንኛውም ጊዜ ወደ አገራችን ሊገባ ይችላል፡፡ በተለይም በኤርፖርቶችና በድንበር አከባቢ ባሉ መውጫና መግቢያ በሮች በኩል ሊገባ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ስለሚችል አስፈላገው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡
10. እየተወሰዱ ያሉ እምጃዎች
በሽታው እስከ አሁን ወደ ሀገራችን ባይገባም ከወዲሁ ለመከላከልና ከተከሰተም አፋጠኝ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በቂ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በአየር መንገዱ የሚጓዙ መንገደኞችን ጤንነት ሁኔታ መለየት፣ የታመመ ሰው ከተገኘም ወዲያውኑ ህክምና የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ እንዲሁም የህክምና ግብዓቶችና ለባለሙያዎች የሚሆን የመከላከያ መሳሪያዎች ተለይተው በመሟላት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ጤና ተቋማት ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ መስጠት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ፡-
ዶ/ር ዳዲ ጅማ -በስልክ፡ +251911247092
አቶ አህመድ ኢማኖ – በስልክ፡ +251912673924 ማነጋገር ይቻላል
ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ።