Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: የሱአሬዝ ነገር ዝውውሩ በአንፊልድ ቅሬታን፤ በኑ ካምፕ ግርታን ትቷል

$
0
0

ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 65 ላይ ታትሞ ወጥቷል።

በችሎታው ‹‹ሊቅ›› ተጨዋች ፈልጉ ታገኛላችሁ፡፡ በምግባሩ ‹‹እብድ›› ብትሹም አታጣም፡፡ አልፎ አልፎ እነዚህን ሁለት ገፅታዎች በአንድ ሰው ላይ ታገኛላችሁ፡፡ ሉዊስ ሱአሬዝ ‹‹ሊቅ›› እና ‹‹እብድ›› ነው፡፡ ኡሯጋያዊው ለየትኛውም ክለብ ውድ ዋጋ የሚከፍልበት ገንዘብ ነው፡፡ እንደ ሣንቲም ብታገላብጡት ሁለት መልኩን መደበቅ የማይችል ኮከብ፡፡
suarze barcelona
ሱአሬዝ ለሚጠሉት አይመችም፡፡ የሚተቹትን በሊቅነቱ ዝም ያሰኛቸዋል፡፡ ልጁ ለሚወድዱትም አይሆንም፡፡ የቀደመ ሀጢያቱን ላለመቁጠር ሲታገሉ ሌላ ይጨምራል፡፡ የሊቨርፑል ደጋፊዎች አጥቂውን እንደ አጥፊ ህፃን ችለውታል፡፡ ሲያሳፍራቸው ደጋግመው ምረውታል፡፡ ከፉልሃም ሲጫወቱ የመሀል ጣቱን አውጥቶ መሳደቡ የሀገሪቱን ጋዜጦች እና ድረገፆች በማስረጃ ፎቶግራፍ ሲያዳርስ እንዳላዩ አልፈዋል፡፡ ሳይነካ እያስመሰለ ሲወድቅ ተከራክረውለታል፡፡ ፓትሪክ ኤቭራን በዘረኝነት ተነኮሰ ተብሎ ሲቀጣም አፅናንተውታል፡፡ በካሜራዎች ፊት የቼልሲውን ብራስላቭ ኢቫኖቪች ሲነክስም አልፈረዱበትም፡፡ በመጨረሻ በዓለም ዋንጫው ጂዮርጂዮ ኪዬሊኒን ሲነክስ ዝምታን መርጠዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን ደጋፊዎቹ በውስጣቸው አዝነዋል፡፡

አሁን ሱአሬዝ የለም፡፡ በክህሎቱ እያስደሰተ በጥፋቶቹ ያሸማቀቃቸው ኮከብ ወደ ባርሴሎና ሄዷል፡፡ በእርግጥ ኡራጓዊው ይዘገይ እንደሆነ እንጂ መሰናበቱ አይቀሬ መሆኑ ይታወቅ ነበርር፡ ባለፈው ክረምት በመጀመሪያ ሪያል ማድሪድ በኋላም አርሰናል የአንፊልድን በር አንኳኩተው ሲመለሱ የአጥቂው መሰንበት ቢረጋገጥም ሊቨርፑል ውዝግብ የማያጣውን ድንቅ ተጨዋች ይዞ መቆየት እንደሚቸገር ግልፅ ነበር::

ሱአሬዝ ሲጫወት እና ትኩረቱን ሁሉ ለውጤት ሲያደርግ ከፕላኔታችን ድነቅ ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡ ቅፅበታዊ ሩጫው፣ ልዩ የኳስ ቁጥጥር ችሎታው እና በማንኛውም ጊዜ አደጋ የሚፈጥርበት የኳስ ንክኪ ክህሎቱ ያስገርማል፡፡ ሱአሬዝ ሲፈልግ የሁለት ቡድኖችን ጨዋታ የራሱ ማድረግ የሚችል አይነት ተጨዋች ነው፡፡ ራሱ በራሱ የሚጨርሳቸው ጨዋታዎች የመኖራቸውን ያህል ለጓደኞቹ አሳምሮ የሚያቀብላቸው ኳሶችም ቡድኑን አሸናፊ ያደርጋሉ፡፡ ኳስ በእግሩ ስር ሳትሆን እንኳን በቦታ አያያዙ እና እንቅስቃሴው ባላጋራን ያሸብራል፡፡ ለጓደኞቹም የመጫወቻ ቀዳዳ ይፈጥራል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት ከግማሽ ጊዜያት በእንግሊዝ የሱአሬዝን አስገራሚ አቅም ብዙዎች አስተውለዋል፡፡ በግራ፣ ቀኝ እግሮቹ እና በተለያዩ አካላቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች እንዲሁም ሀትትሪኮች ተመልክተዋል፡፡ ከማይታመን ጠባብ ማዕዘን ከመረብ ያሳረፋቸውን ኳሶች አድንቀው ቪዲዮዎቹን ደጋግመው ማየት ተመኝተዋል፡፡ በአምስት ተከላካዮች መካከል የተደረደሩ ግዑዝ ፍጥረቶች አስመስሏቸው ሲያልፍ ማየት እንግዳ አይደለም፡፡ ከመሀል ሜዳ ብዙም ልዩነት ከሌለው ርቀት የመታው ኳስ እንደ ፍፁም ቅጣት ምት በረኛን አቅመ ቢስ አድርጎ ጎል ሲሆን መመልከትም አዲስ አይደለም፡፡ ሱአሬዝ እግርኳስን ብቻ ሲጫወት ደረጃው ከእነ ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጎራ ነው፡፡

ባለፈው ክረምት ሊቨርፑል በቅጣት በርካታ ጨዋታዎችን የሚያደርገውን አጥቂውን በከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ እንኳን ሊገላግለው አልፈቀደም፡፡ ክለቡ ላሳየው ቆራጥነት ያገኘው ክፍያ አስገራሚ ነበር፡፡ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ አምስት ጨዋታዎች ያልተሰለፈው ሱአሬዝ በመጨረሻ በሊጉ 31 ጎሎች አገባ፡፡

እነዚህን ጎሎች ሲያስቆጥር የተጫዋቹ ውጤታማነት ከፍ ማለት በግልፅ ቢታይም ኡራጓዊው ከድራማዎች ነፃ አልነበረም፡፡ በተሌም በትልልቅ ግጥሚያዎች ሳነካ አስመስሎ መውደቅ ማብዛት ከባላጋራ ቡድን አልፎ የጨዋታ ዳኞችን ሁሉ ለብስጭት ይዳርግ ነበር፡፡ ይህ ድርጊቱ ብዙ ጊዜ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ በሀሰት ሲወድቅ ደጋግመው ያስተዋሉት ዳኞች እውነተኛ ጥፋት ሲሰራበትም ችላ ይሉት ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጨዋታው የመጨረሻ ጊዜያት በወሳኝ ቦታ የሚፈፀሙበት ጥፋቶች ተገቢውን ውሳኔ አለማግኘታቸው ሊቨርፑልን ደጋግሞ ጎድቶታል፡፡
ሊቨርፑል ለፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነትም ምን ያህል ተቃርቦ እንደነበር የሚያስታውስ ሰው ኖሮ ምናልባትም የተሻለ ውጤታማ ሊሆን እና ቡድኑንም ለድል ሊያበቃ ይችል እንደነበር ይገምታል፡፡ የሱአሬዝ ጉዳት በዚህ አይገታም፡፡ ውዝግቦቹ፣ ዘረኝነት ትንኮሳው፣ ንክሻዎቹ እና ሌሎችም ድርጊቶቹ ሊርል በቅጣት የሜዳ ላይ አገልግሎትን እንዲያጣው እና የተጨዋችነት ዋጋውም ይበልጥ እንዳይጨምር ገትቶታል፡፡ በዓለም ዋንጫው ኪዬሊኒን መንከሱ ከተረጋገጠ እና ቅጣት ከተጣለበት በኋላ ጥያቄው ሱአሬዝን ማን ይፈልገዋል? የሚለውን የሚለው ነበር፡፡ በእርግጥ በአንድ የውድድር ዘመን ቢያንስ አንድ ከባድ ውዝግብ ሳይፈጥር የማይቀረውን ተጨዋች ለዚውም የተጋነነ ሂሳብ ከፍሎ የሚወስደው ይኖር ይሆን? የሚለው ጥያቄ ምክንያታዊ ነበር፡፡ የሱአሬዝን ችግር ተቋቁሞ ከችሎታው ሊጠቀም የቆረጠ የሚመስለው ባርሴሎና አጥቂውን የራሱ አድርጓል፡፡

የአንፊልድ አሻራው

በአንፊልድ ሱአሬዝን አስታውሶ ጎሎቹን መርሳት አይቻልም፡፡ ለሊቨርፑል ከ133 በላይ ነጥብ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 82 ጎሎች ሲያገባ በጨዋታው አማካይ የጎል ሪከርድ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ይህ በአውሮፓ ደረጃ በጥቅል ሲታይ ብዙ ላይባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ሱአሬዝ በንፅፅር ከፕሪሚየር ሊግ ይልቅ ጎል ለማስቆጠር ፈተናው ዝተኛ በሆነባቸው የሆላንድ ወይም የስፔን አይነት ሊጎች ምን አይነት አስደናቂ ሪከርድ እንደሚኖረው መገመት ይቻላል፡፡
suarez
በሊቨርፑል ማሊያ ለጎል አመቻችቶ ያቀበላቸው ኳሶችም 50 ደርሰውለታል፡፡ በዚህ ላይ ተጨዋቹ እንደ አንዳንድ አትቂዎች በአነስተኛ ክለቦች ላይ ብቻ የሚበረታ አይደለም፡፡ በእንግሊዝ ዋነኞቹ የሊቨርፑል ተቀናቃኞች ላይ ደጋግሞ ጎል አስቆጥሯል፡፡ በቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲ እና ቶተንሃም ላይ ጎሎች በማስቆጠር እና ለጎል ምክንያት በመሆን ረብሿቸዋል፡፡ የሊቨርፑል ጎረቤት ከሆነው ኤቨርተን ጋር በተደረጉ ጨዋታዎች ያሳያቸው ብቃት ከአንፊልድ ታዳሚዎች ልብ አያስወጣውም፡፡

ሊቨርልን ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ለመመለስ ያገባቸው 31 ጎሎች እና የፈጠራቸው ዕድሎች በአውሮፓ ለራሱም የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ማዕረግ እንዲጋራ እና በእንግሊዝ የውድድር ዘመኑ ኮከብ እንዲሰኝ አብቅቶታል፡፡ እነዚህ ስኬቶቹም የብሬንዳን ሮጀርስን ቡድን ሲጠቅሙ ለእርሱም በደጋፊዎች ዘንድ ፍቅር አስገኝተውለታል፡፡

የሱአዘሬዝ ሽያጭ የሮጀርስን ቡድን ምን ያህል እንደሚያጎድል እርግጠና ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡ ይህ ክለብ በተለያዩ ጊዜያት ምርጥ ተጨዋቾቹን እያጣ እና በተቃራኒው እየበረታ ሲሄድ የታየ ነው፡፡ ኬቪን ኪጋን ሲለቅቅ ሊቨርፑል ተሻሽሏል፡፡ ኢያን ረሽ ሲሸጥም ቡድኑ በርቷል፡፡ የፈርናንዶ ቶሬስ ስንብትም ሊቨርፑልን ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አልጎተተውም፡፡ የተጠቀሱት ተጨዋቾች ሁሉ ስለሊቨርፑል ስኬት ቁልፎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ሲሰናበቱ በቦታቸው የተሻሉ ተጨዋቾች መጥተው ቡድኑን ይበልጥ ጠንካራ አድርገውታል፡፡ በአንፃሩ ቀዮቹ ግራይም ሱነስ፣ ዣቪ አሎንሶ እና ስቲቭ ማክማናማንን ሸጦ ተዳክሟል፡፡ ነገር ግን በሂደት እየተካቸው ተጉዞ እነርሱ በነበሩበት ወቅት ከነበረው የተሻለ ጥንካሬ ሲያሳይ ብዙዎች አይተዋል፡፡ በ1987፣ በ2001 እና 2014 የታዩት የሊቨርፑል ቡድኖች በተለየ መለኪያ የተሻሉ እና አስደሳቾች ነበሩ፡፡
በመጪው ጃንዋሪ ሱአሬዝ 28 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ይህም ማለት ከአሁኑ ረጅም ቅጣቱ ከተመለሰ ከጥቂት ወራት በኋላ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ተጨዋቾ በትልቅ ብቃት እንደሚጫወት መገመት ቢቻልም በከፍተኛ ደረጃ እየተጫወተ ለመቀጠል ቢበዛ ከሶስት ወይም አራት ዓመታት የበለጠ ጊዜ እንደማያኖረው እርግጥ ነው፡፡ ክለቦች ምርጥ ብቃቱን ሊያሳይ በሚችልበት ዕድሜው ላይ ተጫዋቾቻቸውን መሸጥ አይፈልጉም፡፡ ሆኖም ኮከቡ በ30 ዓመቱ ሊያወጣ የሚችለው ዋጋ በ28 ዓመቱ ከሚያስገኘው ገንዘብ በእጅጉ ያንሳል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ሊቨርፑል ሱአሬዝን ለመሸጡ ምክንያታዊ ሊባል ይችላል፡፡

ይልቅኑ ጥያቄው ክለቡ ተጨዋቹን ሸጦ ያገኘውን ገንዘብ እንዴት ይጠቀምበታል የሚለው ነው፡፡ ሊቨርፑል እንደ ቶተንሃም ሆትስፐር ስም ያላቸውን ውድ ተጨዋቾች ገዝቶ እንዳይከስር ትንቃቄ ያሻዋል፡፡ የኋይት ሀርት ሌኑ ክለብ ጋሬት ቤልን ሸጦ ባገኘው መጠኑ ከፍ ያለ በጀት በተሰጥኦው ላቅ ያለውን ኤሪክ ላሜላ እንዲሁም ሌሎች ሶስት እና አራት ከዋክብት ቢያመጣም አልተጠቀመባቸውም፡፡

ክለቦች ተጨዋቾቻቸውን በትክክለኛው ጊዜ ወይም በተሳሳተ ወቅት ሊሸጡ እንደሚችሉ ሁሉ በሽያጭ ያገኙትን ገንዘብ በትክክለኛ ወይም በተሳሳተ ሌላ ተጨዋች ግዢ ላይ ሊያፈስሱት ይችላሉ፡፡ ትልቅ ተጨዋች ሸጦ ሌላ ትልቅ ተጨዋች ስኬት ላያረጋግጥ ዕድል አለው፡፡ ይህ ማለት ግን አንዱን ኮከብ በሌሎች ሶስት ወይም አራት መካከለኛ ደረጃ በሚሰጣቸው ተጨዋቾች መለወጥ ይሻል ማለት አይደለም፡፡

በርከት ያሉ መካከለኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ተጨዋቾች የቡድንን ትልቀት በመጨመር በኩል ጠቃሚ እና በአሰልታኞች ተመራጭ ናቸው፡፡ ሆኖም 80 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ አንድ ኮከብ ዋጋቸው በነፍስ ወከፍ 8 ሚሊዮን ፓውንድ ከሚተመኑ 10 ተጨዋቾች ይሻላል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ 8 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገዙትን ተጨዋቾች ማንነት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ፊሊፕ ኩቲንሆ ያሉትንም ይጨምራሉ? ሊቨርፑል ከሱአሬዝ ሽያጭ ያገኘውን 75 ሚሊዮን ፓውንድ በጥሩ ተጨዋቾቹ ግዚ ላይ ካዋለው እና በአዲሶቹ ከዋክብት ውጤታማ ከሆነ የኡራጓዊው ስንብት ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የሱአሬዝ ጉዳይ ጫና ውስጥ የሚያስገባው ሊቨርፑልን ብቻ አይደለም፡፡ ባርሴሎናም በቀጣይ በተያያዥ ብዙ ጥያቄዎች መመለስ ይጠበቅበታል፡፡
suarez
ለባርሴሎና ብልሀት ወይስ እብደት?

የሱአሬዝ ዝውውር የሊቨርፑልን ደጋፊዎችን አላስደሰተም፡፡ በአንፃሩ ከባርሴሎና ደጋፊዎች ፈንጠዝያ አልተጠበቀም፡፡ የካምፕኑ ታዳሚዎች ለ27 ዓመቱ አጥቂ ፊርማ 75 ሚሊዮን ፓውንድ መከፈሉ አላሳመናቸውም፡፡ በችሎታቸው ላይ ጥርጣሬ ሳይኖራቸው የባህሪዩ ተግባር በክለባቸው ገፅ ላይ የሚያመጣው ጣጣ ያሳሰባቸውም ትቂት አይደሉም፡፡

ከደጋፊዎቹ መካከል ትክክለኛው አመለካከት የትኛው ነው? ባርሴሎና ሱአሬዝን በእግርኳሱ ታሪክ ሶስተኛው ውድ ተጨዋች ማድረጉ ስህተት ነው? ተጨዋቹ በባርሴሎና ስለሚኖረው አስተዋፅኦ እና ለአጥቂዎች ለመደላደል አስቸጋሪ ነው በሚባለው ኑ ካምፕ የሚያገኘውን ቦታ እንመልከት፡፡
የብዙ ሰዎች ችግር ዝውውሮች ከገንዘብ አንፃር ብቻ ለመመዘን መሞከራቸው ነው፡፡ አንድ ነገር ግልፅ ነው፡፡ በአነስተኛ የዝውውር ሂሳብ ቢሆን ኖሮ ሊቨርፑልም ተጨዋቾን አይቀለውም ነበር፡፡ ባርሴሎና በየትኛውም መንገድ ቢሞክር ተጨዋቹ ወደ ኑ ካምፕ ለማምጣት ከፍ ያለ ዋጋ መክፈሉ አይቀሬ ነበር፡፡ በእርግጥ የዝውውር ዋጋው እንዲህ ለፖርቹጋላዊው ሮናልዶ የቀረበ መሆን ነበረበት ወይ የሚለው ያከራክር ይሆናል፡፡ ያለፉት ዓመታት ሪከርዶቹ አስደናቂዎች መሆናቸው ግን ጥያቄ አያስነሳም፡፡
የባርሳ ደጋፊዎች በዝውውሩ ላይ የሚያነሱት ሌላ ጥቄ ዕድሜው ጋር ያያያዛል፡፡ ሮናልዶም ሆነ ቤል በከፍተኛ ሂሳብ ወደ ሪያል ማድሪድ ሲያመሩ ዕድሜያቸው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ይህም ማለት ተጨዋቾቹን ሪያል መልሶ መሸጥ ቢፈልግ ተጠቅሞባቸው ለገበያ የሚያቀርብበት ጊዜው ነበረው፡፡ ሱአሬዝ ከዚህ በኋላ ለተጨማሪ የእግርኳስ ህይወት ከባርሴሎና የሚዘዋወርበት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ ቢዘዋወርም እንኳን ባርሴሎና ለዝውውሩ የከፈለውን ሂሳብ የሚጠጋ ክፍያ አያገኝለትም፡፡ የሱአሬዝ የአሁኑ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እንጂ ክለቦች ፈጣን ስኬት የሚያመጡላቸውን ድንቅ ተጨዋቾች በተመሳሳይ ዕድሜ እያሉ ሊያስፈርሟቸው ይችላሉ፡፡

የሱአሬዝ ጉዳይ ለአሰልጣኝ ለዊስ ኤንሪኬም ራስ ምታት መሆኑ አይቀሬ ይመስላል፡፡ ባርሴሎና ጎል የሚያስቆጥርለት 9 ቁትር አጥቂ መፈለጉ ግልፅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ስፔን ብሔራዊ ቡድን ሁሉ የባርሳ አጨዋወትም ለአጥቂ የሚመች አይደለም፡፡ በእርግጥ ይበልጥ የሚቸገሩት አጥቂዎች ብዙ የማይንቀሳቀሱት እና ጎል የማስቆጠር ብቻን ኃላፊነት የሚወስዱት ናቸው፡፡ ሱአሬዝ እረፍት የማያውቅ እና ለቡድን ባላጋራን መጭመቅን መሰረት ያደረገ አጨዋወት የተመቸ ነው፡፡ ጎሎች ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን የጎል ዕድሎችን መፍጠርንም ያውቅበታል፡፡ ይህም ማለት ባርሴሎና በፊት መስመር በተመሳሳይ መልኩ ጎል ማስቆጠር እና የጎል እድል መፍጠር የሚችሉትን ሶስት ተጨዋቾች ኔይማር፣ ሱአሬዝ እና ሜሲ በጋራ ይጠቀማል፡፡ በዚህ አሰላለፍ መሰረት አንድሬስ ኢኒዬሽታ ከተለመደው ቦታው ወደ ኋላ አፈግፍጎ እንዲጫወት የሚገደድ ሲሆን ከፊት ያሉት ሶስት ተጨዋቾች ግን ምናልባትም በመላው አውሮፓ አስፈሪውን የአጥቂ መስመር ይፈጥራሉ፡፡

ጥቂት ጊዜ ይወስድ እንደሆነ እንጂ ሱአሬዝ ቡድኑን ጥሩ አድርጎ እንደሚዋሃድ የሚጠራጠር አይገኝም፡፡ ይልቁን የተጨዋቹን ውዝግብ የመፍጠር ባህርይን ክለቡ እንዴት ይለምደዋል የሚለው ጥያቄ ግን ይነሳል፡፡ ባርሴሎና ረብሻ የማያጣውን ተጨዋች እንዴት ሊተማመንበት ይችላል? በዘረኝነት ትንኮሳ ስሙ የተበላሸው እና የሜዳ ላይ ተጋጣሚዎቹን በመንከስ የተኮነነው ተጨዋች ለባርሴሎና ጥሩ ገፅታ ይሆናል?

የዓለም ዋንጫ ድርጊቱን ተከትሎ የተላለፈበት የፊፋ ቅጣትም ሌላኛው ነጥብ ነው፡፡ ሱአሬዝ በቅጣት ምክንያት ከዘጠኝ እስከ 10 የላ ሊጋ ጨዋታዎችን ብቻ ሳይሆን የቻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎችም ያመልጡታል፡፡ በእርግጥ ሱአሬዝ ወኪሎች እና ጠበቃዎች የእገዳው መጠን እንዲቀንስ ለማድረግ ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር እየተዘጋጁ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ውሳኔውን እንደማይለውጥ ያስታወቀው የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል በቀጣዮቹ ሳምንታት ሃሳቡን መልሶ ያጤነዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ከቡድኑ ጋር አብሮ ልምምድ አለመስራቱ በአዲሱ ክለብ በእንግድነት እንዲቀጥል ያስገድደዋል፡፡ ማንኛውም ተጨዋች ወደ አዲስ ክለብ ሲሄድ ከአጨዋወት ፍልስፍናው፣ ከቡድን ጓደኞቹ እና አጠቃላይ ድባቡ ጋር መላመድ ይጠይቃል፡፡ ሱአሬዝ ይህን ዕድል አያገኝም፡፡ በእርግጥ የእገዳውን ዝርዝር የተመለከተ ሰው በዚህ አይደነቅም፡፡ ሱአሬዝ አብሮ አለመለማመድ ብቻ ሳይሆን በኑካምፕ እና ሌሎች ስታዲየሞች ተገኝቶም ጨዋታዎችን ማየት አይችልም፡፡ ስለዚህ እርሱም እንደሌሎች ሰዎች የባርሴሎናን ተጨዋቾች እና ግጥሚያውን በቴሌቪዥን ይመለከታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሱአሬዝ እንደ ቡድን አባልነቱ የባርሴሎና ስኳድ ጋር በውድድር ዘመኑ የመክፈቻ ፎቶግራፍ ከኔይማር እና ሜሲ ጎን ሆኖ አይታይም፡፡ ሌላው ቀርቶ ክለቡ ከዚህ ቀደም ዝለታን ኢብራሂሞቪች፣ ሴስክ ፋብሪጋዝ፣ ኔይማር እና የመሳሰሉትን ከዋክብት ሲያስፈርም በኑ ካምፕ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን የሚያስተዋወቅበትን ዕድል በሱአሬዝ አላገኘም፡፡ በአጠቃላይ አጥቂው አሁን ከሊቨርፑል እዳነት ወደ ባርሴሎና ችግርነት ተለውጧል፡፡

‹‹በ16 ዓመት የሊቨርፑል ቆይታዬ ሱአሬዝ፣ ማይክል ኦዌን እና ፈረንናዶ ቶሬስ አብረውኝ ከተጫወቱት አጥቂዎች ሁሉ ምርጦቹ ናቸውው፡ እኔ የዋናው ቡድን አባል ስሆን ሮቢ ፎውለር በብቃቱ ጫፍ ላይ አይገኝም ነበር፡፡ ከሁሉም ግን ሱአሬዝ የተሻለው አጥቂ ነው›› የሚለው የቀድሞው የክለቡ ተከላካይ ጃሚ ካራገር ነው፡፡

‹‹ሉዊስ በሜዳ ላይ የሚሰራቸውን ነገሮች አይተህ በአድናቆት ከመዋጥ ሌላ ምንም መናገር አትችልም፡፡ አሁን ግን ጥያቄው ይህ ነው፡፡ በአንፊልድ ያገኘው የነበረውን አድናቆት እና ክብር በኑካምፕ ያገኛል? ወይስ እንደ ኦዌን እና ቶሬስ ፍቅርን እና የመርሲሳይድ የጎል ሪከርዱን አጥቶ ይንከራተታል? ኦዌን እና ቶሬስ በአንፊልድ የሰሩትን ገደል በሌላ ቦታ ለመድገም የመቸገራቸው አንዱ ሰበብ ይህ ነበር፡፡

‹‹እንደ እኔ ግምት ወደ ሪያል ማድሪድ ቢሄድ ኖሮ ነገሮች ይበልጥ ይመቹት ነበር፡፡ በእርግጥ ሮናልዶ ትልቅ ተጨዋች ነው፡፡ ነገር ግን ሉዊስ ከካሪም ቤንዜማ የተሻለ አጥቂ በመሆን ቦታውን የራሱን ማድረግ ይችል ነበር››
ካራገር የተጫዋቹን ወደ ካታሎኒያ መሄድ ያልወደደበት ምክንያት የባርሴሎና ወግ አጥባቂ ደጋፊዎች ከሚያቀርቡት ጋር ባይመሳሰልም የአጥቂው ዝውውር ሁሉንም ወገኖች ቅር ማሰኘቱ ግን ግልፅ ነው፡፡ የባርሳ ባለስልጣናት ሱአሬዝን ማስፈረማቸው ብቻ ሳይሆን ለግዢ አስቀድመው ማሰባቸው በራሱ ያስገረማቸው የሚመስሉ የክለቡ አፍቃሪዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ባርሳ በሱአሬዝ ፊርማ ሜዳ ላይ ራሱን አጠናክሮ ከሜዳ ውጪ ለውርደት መዳረጉን ያብራራሉ፡፡

የባርሴሎና ቦርድ ወቅታዊ ትልቅ እቅድ ግልፅ ነው፡፡ ቡድኑ ወደ አሸናፊነቱ መመለስ አለበት፡፡ ይህንን ለማሳካት በምርጥ ተጨዋቾች የተሰራ ምርጥ ቡድን ያስፈልጋል፡፡ የክለቡ ባለስልጣናት እቅዳቸውን ከግብ ለማድረስ ሲሉ ባርሴሎና የኖረለት ባህሉን እና መልኩን እየጠፋ መሆናቸው ይወራባቸዋል፡፡ የአሌክሲስ ሳንቼዝን 9 ቁጥር ማሊያ ለሱአሬዝ ሰጥተው የቡድኑን ጥንካሬ ሲያሻሽሉ የክለቡ ታሪክ እና ዓለም አቀፍ ገጽታ አበላሽተዋል፡፡ ሳንድሮ ሮሴል በኔይማር ውስብስብ የዝውውር ሂደት መሳቂያ ያደረጉት የባርሴሎና ስም አሁን በሱአሬዝ የግል ተጠባቂ ችግሮች ይበልጥ እንዳያድፍ ያሰጋል፡፡
ሱአሬዝን ባለፉት ዓመታት የሚያውቀው ሁሉ ተጨዋቾ ምን ያህል በተደጋጋሚ ችግሮችን የመፍጠር አቅም ያለው ሰው እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ ሜዳ ላይ የጨዋታን ዳኛ ገፍትሮ በቴስታ ሲማታ ገና የ16 ዓመት ልጅ ነበር፡፡ በእግርኳስ ህይወቱ በአውሮፓ ሊጎች በፕሮፌሽናልነት መጫወት ከጀመረ ወዲህ ብቻ ሶስት ሰዎችን ነክሷል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በዘረኝነት ሜዳ ላይ ባላጋራውን መተንኮሱ ሳያንስ እስካሁንም ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም፡፡ አሁን የተጣለበትን ቅጣት ጨምሮ ከ2010 ወዲህ በእገዳ ምክንያት የሚያልፉት ጨዋታዎች ብዛት 48 ደርሷል፡፡ እነዚህን ጨዋታዎች የተቀጣው የቀይ ካርድ ሳይመዘገብበት መሆኑን ልብ በሉ፡፡ እስከመጪው ኦክቶበር የባርሴሎናን ማሊያ ለብሶ ሜዳ ላይ አይታይም፡፡

ይህ ሁሉ የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይመስልም፡፡ ሮሴል፣ ፔፕ ማሪያ ባርቶሜኡ፣ አንዶኒ ዙቢዛሬታ እና ሌሎችም የቦርዱ ሰዎች የቡድኑ ውጤት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ባርሴሎና በሜዳ ላይ ተፎካካሪነቱን ይዞ እንዲቀጥል ቡድኑን ማጠናከሪያ ገንዘብ ለማግኘት በሚሉ ተመሳሳይ ሰበብ የካታር ኢንቨስትመንት የንግድ ምልክትን ከክለቡ መልክ ጋር የቀላቀሉት እነዚሁ ሰዎች ናቸው፡፡ በዓለም ሊግ ምርጥ ተስፈኛ የሚባለው ተጨዋች ለሪያል ማድሪድ እንዳይፈረም በሚል ብቻ በርካታ ህጎችን ለመጣስ የሚደፍሩትም እነርሱ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ 95 ሚሊዮንዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ አውጥተው የወቅቱን የዓለማችን የተጠላ፣ ይቅርታ ያልተደረገለት እና ብዙዎች ጀርባቸውን የሰጡትን ተጨዋች አምጥተዋል፡፡

የክለቡ ቦርድ እና ሱአሬዝ ከተቀሩት የክለቡ ተጨዋቾች ጋር ተባብረው ዋንጫዎችን ማሸነፋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ባርሴሎናም እንደ ፔፕ ጋርዲዮላ ዘመን የሰዎችን ልብ ገዝቶም ባይሆን ማሸነፍ ይቀጥላል፡፡ በተመሳሳይ የማይቀጥል አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ‹‹ባርሴሎና ከክለብም በላይ!›› የሚለው ስም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>