(ዘ-ሐበሻ) በፓርላማው ውስጥ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ በጥርጣሪ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤው እንደወረደ ይኸው፦
ሐምሌ 11 ቀን 2006
ለክቡር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡ በጥርጣሪ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ መብት አያያዝ ይመለከታል
ክቡር ኮሚሽነር ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ በ “ወንጀል” ተጠርጥረዋል በሚል የፓርቲያችን አንድነት ለፍትህና ዲሞክራሲ (አንድነት) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው እና የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም አቶ አብርሃ ደስታ ከአረና ፓርቲ እና አቶ የሺዋስ አሰፋ ከሰማያዊ ፓርቲ በፖሊስ ቁጥጥር ስር አንደሚገኙ ሰምተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሁን አንጂ ይህን ማመልከቻ እሰከምፅፍበት ሰዓት ድረስ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ታሳሪዎች ከህግ አማካሪ እና ቤተሰብ ጋር በህግ በተፈቀደው ስርዓት መሰረት ሊገናኙ አልቻሉም፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ማንም በሌለበት እና ከህግ አማካሪዎች ጋር ሳይገናኙ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ወደ ማእከላዊ ሄደዋል የሚል ዜና ቢወጣም አሁንም በትክክለኛ ሁኔታ ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸው መረጃ የሚሰጥ አካል አላገኘንም፡፡ አንድ እድ ሰዎች ከምሸቱ በአንድ ሰዓት ፍርድ ቤት ቀርበዋል የሚሉም አሉ፡፡
በዚህ የተነሳም ተሳሪዎች በድብቅ ፍርድ ቤት ቀርበዋል የሚባልበት ሁኔታ እና ይልቁንም ከህግ አማከሪያቸው እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ የተደረገበት ሁኔታ ለከፍተኛ ጥርጣሬ የሚያሳድር ነው፡፡ የእነዚህ ታሳሪዎች በጥርጣሬ የታያዙበትን ወንጅል እንዲያምኑ በኢትዮጵያ ህገ መንግሰትም ሆነ በህገ መንግሰት ተቀባይነት ባገኙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ምንም ዓይነት የሀይል እርምጃ እና ህገወጥ የሆነ ምርመራ ማካሄድ አይቻለም፡፡ ሰለሆነም ክቡር ኮሚሽነር በህግ መንግሰት የተፈቀደ ሰብዓዊ መብታቸውን የተነፈጉ እነዚህ ታሳሪዎች ያሉበትን ሁኔታ መስሪያ ቤቶ ክትትል እንዲያደርግ እና ለቤተሰቦች እንዲያሳውቅ አደራ ጭምር እየጠየቅሁ፡፡ የፖሊስ አካላትም ይህን ህገወጥ ክልከላቸውን እንዲያቆሙና ለህግ ተገዢ እንዲሆን እንዲያሳሰቡልን እንጠይቃለን፡፡ በአፋጣኝ ታሳሪዎችን ሁኔታ ማወቅ በታሳሪዎች ላይ ሊደርስ ከሚችል አካላዊም ሆነ ሌላ ማንኛውም ጉዳት ለመታደግ ስለሚረዳ፣ ሀገርም ከዚህ የምትጠቀመው አንድም ነገር ስለማይኖር ክቡርነትዎ አሰፈላጊውን ትኩረት ስጥተው ኃላፊነቶን እንደሚወጡ ተሰፋ አለኝ፡፡
ከማክበር ከሠላምታ ጋር
ግርማ ሠይፉ ማሩ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል