Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በብጥብጥ የተቋጨው የጁምዓ ስግደት በአንዋር መስጊድ

$
0
0

ከኤልያስ ገብሩ (አዲስ አበባ)

መጽሐፍ ሳነብ ስለነበር በጣም አምሽቼ የተኛሁት፡፡ ጠዋት አረፍጄ ተነሳሁ፡፡ ቁርሴንም ሳልበላ ወደ አንዋር መስኪድ አመራሁ፡፡ ከፒያሣ ጀምሮ መንገድ የተዘጋጋ ስለነበረ፤ ከሦስት ሙስሊም ወንድሞቼ ጋር አንድ ላዳ ታክሲ ኮንትራት ይዘን አቆራረጥን ታላቁ አንዋር መስኪድ ደረስን፡፡ አካባቢው በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተሞልቷል፡፡ አብዛኛው ምንጣፍ እና ካኪ ወረቀት አንጥፈው ለጁምዓ ጸሎት እና ለስግደት ተቀምጠዋል – አስፋልቱን ጭምር ተጠቅመውበታል፡፡ ለመቀመጫ ቦታ ያላገኙት ቆመው ከመስኪዱ በአረብኛ ቋንቋ የሚነገረውን ምስጋና (ትምህርት) በጥሞና እየተለታተሉ ነው፡፡
በርከት ያሉ ፖሊሶች በመስኪዱ አቅርቢያ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ቆመዋል – ረዥም ሽመል ይዘዋል! እኔም እንደ ጋዜጠኛ የሙስሊሞቹን ሰላማዊ ተቃውሞ ለመከታታል በማሰብ ነው አንዋር መስኪድ የተገኘሁት፡፡ ከመስኪዱ ራቅ ብዬ በመቆም ሁኔታውን መከታተል ጀመርኩ፡፡ ነገሮች ሰላማዊ ነበሩ፡፡ ከሥፍራው ከተገኘሁ ከአሥራ አምስት ደቂቃ በኋላ በመስኪዱ ዋና በር አካባቢ ወረቀቶች ወደ ላይ ይበተኑ ጀመር፡፡ ሦስት፣ አራት ቦታም ተመሳሳይ ወረቆች መበተናቸውን ቀጠሉ፡፡
demtschin yesema 2
ወዲያው፣ ከርቀት ከመስኪዱ በስተቀኝ በኩል ረብሻ ነገር ተመለከትኩ፡፡ ድንጋይ ሲወረውር እና ፖሊሶች ዱላ እንደያዙ ሲሯራጡም ማየት ችያለሁ፡፡

አፍታም ሳይቆይ አካባቢው በሰዎች ሩጫ፣ በረብሻና በፖሊሶች ማሳደድ ትርምስምሱ ወጣ፡፡ ብዙ ሰው በአካባቢው ወደሚገኙ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች እየዘለለ መግባት ጀመረ፡፡ ነገሮች ለአፍታ ጋብ ያሉ ቢመስሉም ሁኔታው በድጋሚ ተቀሰቀሰ፡፡ በርካታ ፖሊሶች ወደ መኖሪያ ሰፈሮች እና ግቢዎች ውስጥ ዱላቸውን ይዘው በመግባት ሰዎች ማባረር፣ ማሳደድና በዱላ መማታት ጀመሩ፡፡

እኔም ከሦስት ፖሊሶች ጋር ከአንድ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ተፋጥቼ ነበር፡፡ አንድ ዱላ ሲሰነዘርብኝ በእጄ ተንቀሳቃሽ ኮምፕዩተር (ላፕቶፕ) ይዤ ስለነበረ እሱ ከፍ በማድረግ ዱላው የላፕቶፕ ቦርሳዬ ላይ አረፈ፡፡ የቀኝ እጄ ጠቋሚ ጣት ግን ከበትሩ ማምለጥ ሳይቻለው ቀረ፡፡
… ከበሩ ፊት ለፊት የነበሩት ፖሊሶች ጥለውን ሄዱ፡፡ ወደ አሜሪካን ግቢ በጉራንጉር ውስጥ አልፌ ብሄድም ድብደባው እና ወከባው በዚህ አለ፡፡ ብዙ ወጣቶች ተደብድበው፣ ጭንቅላታቸው ተበረቃቅሶ ደም በደም ሆነው ተመልክቻለሁ፡፡
በዛሬው ዕለት ምስቅልቅሏ የወጣውን መርካቶ በቻልኩት አቅም ለማየት ችያለሁ፡፡ ሱቆች ተዘጋግተዋል፡፡ አንዋር መስኪድ በፌዴራል ፖሊስ ባልደረቦች እና መኪኖች ተከብቦ ነበር፡፡ አድማ በታኝ ፖሊሶችም በምዕራብ ሆቴል ቁልቁል በሰልፍ ሲያዘግሙ እና ሰፊዋ መርካቶ በፌዴራል ፖሊሶች ተወርራ ነበር፡፡
በጥቅሉ በዛሬው የአንዋር መስኪድ የጁምዓን ጸሎት ተከትሎ የተፈጠረው ሁኔታ አሳዛኝ እና ዘግናኝ ሆኖብኛል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>