ደምሰው በንቲ
ለፖሊስ እና እርምጃው ጋዜጣ እንደጻፈው
ዕድሜዋ በ3ዐዎቹ ውስጥ እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም፡፡ ይህች ግለሰብ ግን ስለ ጉዳዩ ማብራራት ከመጀመሯ እንባዎቿ በሁለቱ ዓይኖቿ ጫፍና ጫፍ ቦይ እየሰሩ ይወርዱ ጀመር፡፡ ተረጋግታ የመጣችበትን ጉዳይ ታስረዳ ዘንድ ብንማፀናትም በቀላሉ የምትመለስ አልሆነችም፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ አፍንጫዋን በሶፍት እያባበሰች አሁንም ልውረድ አልውረድ እያለ ከሚታገላት እንባ ጋር በሚቆራረጥ ድምፅ “እህቴን —- ” ስትል ጀመረች፡፡ ቦርሣዋን ከፈታተሸች በኋላም የተወሰኑ ፎቶዎችን አውጥታ ከጠረጴዛው ላይ በተነቻቸው፡፡ በዓይናችን ያየነውን ነገር ለማመን ተስኖን ነበር፡፡ “እህቴ—” ስትል የገለፀቻት ግለሰብ ደረቷና ከደረቷ በላይ እስከ ፊት ገጽታዋ ድረስ በእሳት ተለብልቦ የከፋ ጉዳት አስተናግዷል፡፡
አዲስ አበባ እንዲህ የመሰለውን አደጋ ከዚህ በፊት በከፋ ሁናቴ ሁለት ጊዜ ያህል አስተናግዳ የነበረ በመሆኑ መሰል ጥቃት ታስተናግዳለች ብሎ የሚያስብና የሚያምን ማን ይኖር ይሆን? ግን ሆኗልና የሆነውን ትገልጽልን ዘንድ ዳግም ጋበዝናት፡፡ በሀዘን በተሰበረ ድምፀት ቀጠለች፡፡ ጽጌ ገ/ኪዳን የተባለችው ይህቺው የተጎጂዋ እህት ፋንታዬ ገ/ኪዳን የተባለችው ተጎጂ እህቴ ከተጠርጣሪው ጋር ተጋብተው ሲኖሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል ትላለች፡፡ እኒህ ጥንዶች ከባል ቤተሰብ የመኖሪያ ቤት አጠገብ ባገኙት ባዶ ቦታም በህገ-ወጥ መንገድ ጊዜያዊ ማረፊያ እንደሰሩ ትገልፃለች፡፡ “ይሁንና ከጊዜ በኋላ” ትላለች መውለድ ስላልቻለች ይሆናል የሚል ግምት የያዘችው ቅሬታ አቅራቢዋ የተበዳይ እህት ባለቤቷና ቤተሰቦቹ ጥላቻ ማዳበር ጀመሩ፡፡
ቤቱን ለቅቃ ትወጣ ዘንድም ከትንኮሳ እስከ ክስ ያመራ እርምጃ ወስደው ፍርድ ቤቱ ቤቱን በይገባኛል ያነሱት የባለቤቷ እናት እንደማይገባቸው ፈርዶባቸው መኖር እንደጀመረችም ትናገራለች፡፡ይሁን እንጂ በባለቤቷና በእርሷ መካከል የተፈጠረው መካረር ግን ሊበርድ አልቻለም ነበር የምትለው ጽጌ
ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ ያልነበራት እህቴ የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ተቋቁማ መኖር ጀመረች ትለናለች፡፡በዚህም ሳታበቃ ቦሌ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ቦታ በጽዳት ሠራተኛነት ተቀጥራ ከምታገኘው ገንዘብ አጠራቅማ ኑሮዋንና ቤቷን ለማሸነፍ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማሟላት “አንድ ቀን ልቡ ይመለሳል” በሚል ተስፋ መኖር ጀመረች ስትልም ትገልፃለች፡፡ ተጠርጣሪው ግለሰብ ወይም የተጎጂ ባለቤት ግን ጥላቻው ከቀን ቀን እየበረታና እየጨመረ ሄደ የምትለው ጽጌ የፋሲካ ዕለት ምሽት ግን ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ ትላለች፡፡ በዚህ ዕለት እህቴ እናቷ ቤት ቆይታ ከምሽቱ 2፡ዐዐ አካባቢ ወደ ቤቷ ስታመራ ቤቷ ያለ ወትሮው ክፍት ሆኖ አገኘችው፡፡ በመደናገጥም ቤቱን ከፍታ ስትገባ ቤቱ በጭለማ ተውጦ እንደነበር ተጎጂ እህቷ የነገረቻትን ዋቢ አድርጋ ታስረዳለች፡፡ ከትንሿ ቤት አልጋ ላይ አረፍ ያለውን ሰው ጥላ እንደተመለከተችም ማነህ ስትል እንደጠየቀች ትናገራለች፡፡ “እኔ ነኝ” ሲል የመለሰው ተጠርጣሪ ግለሰብም “ዛሬ የመጣሁት ለነገር ነው”ብሎ እንደመለሰላት እህቷ የነገረቻትን ዋቢ አድርጋ ታስረዳለች፡፡አርፋ እንድትተኛ ካስፈራራት በኋላ ስትተኛም ጋዝ እንዳርከፈከፈባትና ሰውነቷ ላይ እሳት ሲለኩስባትም “እባክህ አድነኝ” ስትል እራሱን ስትማፀነውም ቁጭ ብሎ ሲጋራውን እያጨሰ ያያት እንደነበረ እህቷ የተናገረችውን ጠቅሳ ትገልፃለች፡፡
ወጥታ መሬት ላይ በመንከባለልና በቅርበት ወዳለው ወደ እናቷ ቤት ያመራችው ፋንታዬ ገ/ኪዳን የእናቷ ጎረቤት የሆኑት ሻምበልና አዛውንቷ እናቷ ደርሰው ባይረዷት ኖሮ በህይወት ባልተረፈች ነበርም ትላለች ጽጌ፡፡ አደጋው በደረሰ ዕለት በነጋታው እዚያው ቤት እንደተኛ የተያዘው ተጠርጣሪ ለጊዜው በፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰር ሆኖ ነበርም ትላለች፡፡ እኔና አዛውንቷ እናታችን ፋንታዬን ለማዳን ከመሯሯጥ ጎን ለጎን የክሱን ሂደት እየተከታተልን ነበር በወቅቱ በአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ የአራት ኪሎ ፖሊስ የምርመራ ባለሙያ የሆነውን የፖሊስ ባልደረባ ተጎጂዋን እንድናመጣለት ክስ በመሰረትንበት ወቅት ገልፆልን ነበር፡፡ አምጡ ባለን ዕለት ጠዋት ደውዬለት “ላምጣትወይ?” ስል ጠይቄው “አታምጪያት” ሲል ፎቶዋ የጉዳቱዋን መጠን ስለሚገልጽ እንዳንጨነቅ ነገረን ትላለች፡፡ እህቴ የውስጥ ሱሪ እንኳ አልነበራትምና ቁልፉን ሰጥተውን ልብሷን እንድናወጣላት ፖሊስን ብንጠይቅ እርሱ ፈቃደኛ እስካልሆነ አንሰጥም ብለው ቁልፍ ከልክለውን ሆስፒታል ቦታ ጠፍቶ ቤቷ እንኳን ተኝታ ህክምና መከታተል እንዳትችል ተደርጎ እናታችን ማድቤት ውስጥ ለመተኛት ተገዳለች ብላለች፡፡
እኛ ትኩረታችንን ማረፊያዋ ላይ አድርገን ከቀበሌው ፍርድ ቤት ከሴቶች ጉዳይ ጋር እና ከፖሊስ ጋር እየተሯሯጥን መፍትሄ በማፈላለግ ላይ ሣለንም ተጠርጣሪው በ2 ሺህ ብር ዋስ እንደተለቀቀ ፖሊስ አረዳን ስትልም ዳግም ልትመልሰው ያልቻለችውን እንባ እየዘራች “በእኛ የደረሰ በማንም አይድረስ” ትላለች፡፡ እንዴት ሊለቀቅ እንደቻለ የምታውቀው እንዳለ ጠይቀናትም የአራት ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ የሆኑትን ኮማንደር አነጋግሬ ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ባደረጉበት ወቅት መረጃ በሚገባ ባለማደራጀቱ እና የእህቴን የጉዳት መጠን በሚገልጽ ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ ባለማቅረቡ ፍርድ ቤቱ ሊይዘው የሚገባውን ነጥብ ባለማስያዙ የዋስትና መብት እንደተፈቀደለት ትናገራለች፡፡ እንደ አጠቃላይ በምርመራ ሂደቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላት የምትገልፀው ይህቺው ቅሬታ አቅራቢ አሁንም ማረፊያ ባጣችው እህቴ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በተመለከተ ዋስትና የሌለን ከመሆኑም በላይ ከብዙ ትግል በኋላ ልብሷን እንድናወጣ የተደረገ ይሁን እንጂ አሁንም በገዛ ቤቷ እንዳታርፍ እጥፍ ድርብ በደል በእህቴ ላይ ደርሶባታል ትላለች፡፡