(ዘ-ሐበሻ) በጭንቀት ውስጥ እንዳለ የሚነገርለት የሕወሓት/ኢሕአዴግ አስተዳደር የሚገባበት ሲጠፋ በተለይ ወጣት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ጠራርጎ ወደ እስር መክተቱን እና የግንቦት 7 አመራሩን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አፍኖ መውሰዱን በመቃወምና ሕዝቡም ቁጣውን እንዲገልጽ በማሰብ በሚኒሶታ የፊታችን አርብ ጁላይ 11 ቀን 2014 ዓ.ም የተቃውሞ ሰልፍ ተጠራ።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከየመን አውሮፕላን ማረፊያ ወስዶ በሃገሪቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ አጎሳቁሎ ያሳየው ስርዓቱ በተመሳሳይ ቀን የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲ ወጣት አመራሮችን ለቃቅሞ የዲሞክራሲ በርን ጥርቅምቅም አድርጎ መዝጋቱን በመቃወም በሚኒሶታ በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲገኝ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ በሚኒሶታ ዋና ከተማ ስቴት ካፒቶል ደጃፍ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ተጠርቷል።
የፊታችን አርብ ጁላይ 11 ቀን 2014 ከጠዋቱ ከ10 ሰዓት ጀምሮ በስቴት ካፒቶሎ አቅራቢያ በሚገኘው ሲርስ ደጃፍ በመገናኘት ወደ ካፒቶሉ በሚያመራው በዚህ ሰልፍ ላይ የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችች እና ነፃ አሳቢ ዜጎችና የሃይማኖት መሪዎች እንዲፈቱ ይጠየቃል፤ የአሜሪካ መንግስትም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆም ጥሪ ይቀርባል።
ሰልፉ የሚደረግበት አድራሻ: 75 Rev Dr Martin Luther King Jr Boulevard., St Paul, MN 55155,
ጠዋት ከ10 ሰዓት ጀምሮ፤ የኢትዮጵያ ባንዲራና ጥቁር በጥቁር ለብሰው እንዲገኙ ይመከራሉ ይላሉ አስተባባሪዎቹ።