ከባለቤታቸው ህልፈት በኋላ ከፖለቲካው መድረክ እየተገለሉ የመጡት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በጠና መታመማቸውን ቅርበት ያላቸው ታማኝ ምንጮች አስታወቁ። በስኳር ህመምና በደም ግፊት እየተሰቃዩ የሚገኙት አዜብ መስፍን የሰውነት ክብደታቸው እንደቀነሰና የመጎሳቆል ሁኔታ በገጽታቸው እንደሚታይ የጠቆሙት ምንጮቹ ለስኳር በሽታ በየእለቱ ከሚወስዱት መድሃኒት በተጨማሪ ለደም ግፊትም እንክብሎችን እንደሚወስዱ ምንጮቹ አረጋግጠዋል። አዜብ በመኖሪያቸው አብዛኛውን ቀናት እንደሚያሳልፉ የጠቆሙት ምንጮቹ በፖለቲካው የደረሰባቸው ኪሳራ ብስጭት ውስጥ እንደከተታቸውና ለበሽታ እንደዳረጋቸው አያይዘው ገለጸዋል።
ቦሌ ከሳይ ኬክ ቤት ወደ ውስጥ ገባ ብሎ የሚገኘውና አቶ ስዩም መስፍን ለ19ዓመት የኖሩበት እንዲሁም አቶ ሙክታር ከድር ለሁለት አመት የኖሩበት መኖሪያ ቪላ ውስጥ የሚኖሩት አዜብ መስፍን ከዚህ በተጨማሪ ቦሌ ሩዋንዳ መታጠፊያ ላይ የሚገኘውን የቀድሞ የደህንነት ቢሮ ለአዜብ በቢሮ መልክ እንደተሰጣቸው ምንጮቹ ጠቁመዋል።
ቀን ቀን በዚህ ቢሮ ለብቻቸው ያሳልፉ የነበሩት አዜብ መስፍን በጠና ከታመሙ ወዲህ ላለፉት አምስት ሳምንታት ወደዚህ ቢሮ ገብተው እንደማያውቁና በቤታቸው እንደሚያሳልፉ ያስታወቁት ምንጮቹ አክለውም ፓርቲው በሚያካሂዳቸው ስብሰባዎች መገኘት እንዳቆሙና ለመጨረሻ ጊዜ የተገኙት ከሁለት ወር በፊት ኢህአዴግ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል። በዚሁ ጉባኤ ከተሰብሳቢው ኋላ ለብቻቸው ተቀምጠው የታዩት አዜብ ምንም ሳይናገሩና አስተያየት ሳይሰጡ ስብሰባውን ከመጨረሳቸው ባሻገር ከስተውና ተጐሳቁለው እንደነበር ምንጮቹ አስታውሰው ከዚያ ወዲህ ህመሙ እየጠናባቸው እንደሄደ አያይዘው ገለፀዋል። አዜብ የባለቤታቸውን ቦታ በመተካት የጠ/ሚ/ርነቱንና ፓርቲውን የመምራት እቅድና ምኞት በተቀናቃኛቸው ስብሃት ነጋ ከከሸፈባቸውና የሚተማመኑባቸው የደህንነት ባለስልጣናትና የፓርቲው ቁልፍ ሰዎች እስር ቤት መወርወርና መባበረር ለከፍተኛ የሞራል ድቀትና ለበሽታ እንደዳረጋቸው ምንጮቹ አመልክተዋል። አዜብ የኤፈርት ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር ተብለው ቢሰየሙም ምንም አይነት የአመራር ሚና እንደሌላቸው የጠቆሙት ምንጮቹ በነስብሃት ተመድበው ተቋሙን ሲመሩ የቆዩት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ወደ ራዲዮና ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ እንደሆኑና ከርሳቸው በኋላ ደግሞ የአርከበ እቁባይ ታናሽ ወንድም ጌታቸው እቁባይ እየመሩት መሆኑን አያይዘው ገልፀዋል።
ከአዜብ ጋር በተፈጠረ ያለመግባባት ከኤፈርት ለቀው የቆዩት ጌታቸው እቁባይ የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ እንዲመለሱ መደረጉን አመልክተዋል። አዜብ ወደ ትግራይ -መቀሌ ከተጓዙ 6 ወር እንዳለፋቸው አክለዋል። በኤፈርት ውስጥ የአዜብ ደጋፊዎች በነስብሃት ተለቅመው መውጣታቸውን ያስታወሱት ምንጮቹ በቅርቡ ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር የሚለውን የአዜብ ስልጣን በመግፈፍ ሊያባርሯቸው መሆኑን አረጋግጠዋል። …ይህ በእንዲህ እንዳለ የአባዱላ ገመዳ ልጅ ወጣት ኮሚያስ አባዱላ ከዚህ አለም በሞት እንደተለየ ታውቋል። የ26 አመቱ ወጣት ኮሚያስ አባዱላ በጉበት በሽታ ምክንያት ወደ ታይላንድ- ባንኮክ ተልኮ ለአንድ አመት ሲታከም ከቆየ በኋላ ሊድን ባለመቻሉ ከአራት ሳምንት በፊት ህይወቱ አልፏል። በባንኮክ ለአንድ አመት የሆስፒታል ቆይታው ለህክምና ብቻ ከ880ሺህ ዶላር ወጪ እንደተረገለት ታውቋል። በተመሰሳሳይ ሶስተኛ ታናሽ እህቱ (የአባዱላና ራሄል ልጅ) ከአምስት አመት በፊት በገጠማት የሳንባ፣ የአንጀትና የአእምሮ በሽታ በባንኮክ ሆ/ል ለሁለት አመት ህክምና የተከታተለች ሲሆን፣ ለህክምናው ጠቅላላ የወጣው 2.5ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ከዚህ ቀደም ይፋ በተረገው መረጃ መገለፁ ይታወሳል። ይህ ሁሉ ገንዘብ ከህዝብ የተዘረፈ ለመሆኑ አያጠያይቅም። ይህቺ ናት አገሬ! ..ለማንኛውም የአባዱላ ወንጀል ልጁን አይመለከተውም። ወጣት ኮሚያስ በአባቱ ድርጊት ነፃናነት ስለማይሰማው – በየእለቱ አልኮል ይጠጣና ይበሳጭ እንደነበረ ቅርብ የሆኑ ጓደኞቹ ተናግረዋል። የጉበት በሽታውም መንስኤ ይኸው ነው። ነፍስ ይማር!