(ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌ)
የግንቦት7 ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ የሆኑት የአቶ አንዳርጋቸው በየመን መታፈንን ከሰማን ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው ሀገር ወዳድና የኢትዮጵያን የነጻነት ቀን ናፋቂ ወገኖችን ያሳሰበና እረፍት የነሳ ጉዳይ እንደሆነ በየቀኑ በየማህበራዊ ድህረ ገጽ ከሚወጡት ነገሮች መረዳት እንችላለን :: በርግጥ ወያኔ በስልጣን በቆየባቸው በእነዚህ ሃያ ሶስት አመታቶች ብዙ የተማሩ ኢትዮጵያን ሙህሮች፣ ብዙ የፖለቲካ ሰዎች በወያኔ የተቀነባበረ ሴራ ለብዙ ነገር ሰላባ ሲሆኑና ህይወታቸውን እስከሚያጡ ድረስ ሆነዋል :: ሰሞኑን ግን በነጻነት ታጋያችን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ በወያኔ የተቀነባበረ ሴራ በየመን የደረሰው እገታና ለነብሰ በላው የወያኔ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱ እውን እንደሆነ ስሰማ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእኔም ላይ በጣም ከባድ የሆነ የሀዘን መንፈስ የፈጠረብኝ ሲሆን በወያኔ መንግስት ላይ ያለኝን ጥላቻ ይበልጥኑ ከፍ እንዲል ያደረገ ክስተት ሆኖል እንዳርጋቸው ወደ ትግል ሲገባ እራሱን ለሞት በማዘጋጀት ሊደርስበት ያለውን ማንኛውንም መሰዋትነት ለመክፈልና ሁሉንም መከራ ለመቀበል ዝግጅነቱን በማሳየት እንደሆነ ከሚሰራቸው ስራዎች መረዳት ይቻላል ::በርግጥ እውነተኛ ትግል መስዋህትነትን እንደሚያስከፍል ባውቅም የእኝህ እድሜያቸውን በሙሉ ለነጻነት ሲታገሉ የኖሩ የነጻነት ታጋይ ላይ የደረሰው ነገር ግን በውስጤ ሁለት ነገሮችን ጭሮብኛል ያለፈ ሲሆን አንድን ነገር ግን እንዳውቅ ረድቶኛል:: አንዱ እንዳርጋቸው ቢታሰርና የፈለገው ነገር በእሱ ላይ ቢደርስ እንኮን ለወያኔዎች የእግር እሳት የሆኑ እንዳርጋቸው የወለዳቸው ብዙ ሚሊዩኖች የነጻነት ታጋዮች ኢትዮጵያኖች በየስፍራው ተወልደዋልና ደስ ይለኛል::
አሁን ላይ ነገሮች ሁሉ የተቀየሩ ነው የሚመስለው የአቶ እንዳርጋቸው ጉዳይ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ከመሆን አልፏል :: በአሁኑ ሰአት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ እና የአመለካከት ልዩነቱን ወደ ኋላ በመተው እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ በሚል ቃል ጉዳዮን በንቃት እየተከታተለው ሲሆን የታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን መያዝና በወያኔ እጅ ላይ መውደቅ ለአንዳንድ ሆድ አደር ወያኔዎች ብቻ ፈንጠዝያ የፈጠረና ያስደሰተ ቢመስልም ብዙ ኢትዮጵያ ወገኖችን ግን ከሌላዉ ጊዜ በተለየ መልኩ በእልህና በቁጭት ለትግል እንዲነሳሱ ያደረገ ክስተት እንደሆነ በፊስ ቡክ በውስጥ መልክት ከሚደርሰኝ ደስ የሚልና የሚያበረታታ ጽሁፍ ለመረዳት ችያለው::ድርጊቱ ለተቃዋሚዎች የማንቂያ ደውል መሆን ይገበዋል ለነጸነት እንታገላለን የሚሉ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ለነጻነት እየታገልን ያለን ኢትዮጵያኖች የወያኔን መሰሪነት አውቀን ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ በቁጣ በወያኔ መንግስት ላይ መነሳትና በወያኔ ላይ ያለንን የከረረ ጥላቻ በእንቢተኝነትና በሕዝባዊ አመጽ ልንገልጽ ይገባናል ::የወያኔ መንግስት ስልጣኑን በሀይልና በጉልበት ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ እሱን በሚቃወሙ ባሉ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ላይ ሁሉ ይኼው አረመኔው የወንበዴ ስብስብ እየወሰዳቸው ያለው በግፍ የተሞሉ እርምጃዎች ምን ያህል አንባገነን መንግስት እንደሆነ አመላካች ሲሆን የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን መታፈንም የዚሁ አመላካች ነው::ዛሬ ላይ የአንዳርጋቸው መታፈን በርግጥ የወንበዴዎችን ቡድን ጮቤ እያስረገጣቸው እንደሆነ አስባለው የወያኔ መንግስት ማወቅ ያለበት ነገር ቢኖር በነፃነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ላይ የሆነው ነገር የኢትዮጵያን ሕዝብና ተቃወሚዎችን ይበልጥ የሚያጠነክርና ለትግል በጥንካሬ እንዲነሳሱ የሚያደርግ መሆኑ ነው:: የእንዳርጋቸው በየመን መታገትና በወያኔዎች የተቀነባበረ ሴራ ለወያኔዎች ተላልፎ መሰጠት የየመንን መንግስት ባደረገው ከህግ ውጭ የሆነ አሳፋሪ ድርጊት ለወደፊት የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርገው ቢሆንም የመኖች በሰሩት ስራ ወደ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆኑበት ምንም ጥርጥር የለኝም::ዋናው መታወቅ ያለበት ግን ድርጊቱ ለተቃዋሚ መሪዎች ትልቅ የቤት ስራ የሰጠና ሊያነቃቸው ያለ ደውል የተደወለ ነው የሚመስለኝ ::
በሀገርም ውስጥ በውጭም ያሉ የተቀዋሚ ድርጅቶች በስሜትና፣ በደመነብስ የምንጓዝበት ዘመን ያብቃ፣ እየሰራን ያለውንም ስራ እንመርምር ፣እንንቃ የወያኔን መሰሪ ሴራ ለማክሸፍ አንድ በመሆንና በመተባበር ልዮነታችንን ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያ ሕዝብንም በማስተባበር ነጻነታችንን ህውን ለማድረግ በጋራ ጠላታችን ላይ በመዝመት ይሄን አረመኔ መንግስት ለማስወገድ በጋራ እንናሳ::
በመጨረሻም ለወያኔዎች የማስተላልፈው መልእክት ቢኖር እውነተኛ ታጋይ ሊታሰር ሊሞትም ይችላል የተጀመረውን ትግል ግን ልታስሩትም ሆነ ልትገሉት ከቱ አትችሉም ::ኢትዮጵያ አንድ እንዳርጋቸው ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን እንዳርጋቸው ፈጥራለችና በከንቱ አትደከሙ:: ወደዳችሁም ጠላችሁም የእንዳርጋቸውን ፈለግ በመከተል ሁላችንም የነጻነት ታጋዮች ነን!!!
አቶ አንዳርጋቸው አምላክ ከአንተ ጋር ይሁን
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
gezapower@gmail.com