በዓለማችን ላይ እጅግ በርካታ ሰዎች በመጥፎ የአፍ ጠረን የተነሳ ከፍተኛ መሳቀቅና መሸማቀቅ እንደሚደርስባቸው መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን የጉዳዩ አስገራሚ ገፅታ ደግሞ እነዚህ መጥፎ የአፍ ጠረን ያላቸው ሰዎች የገዛ የአፍ ጠረናቸው ችግር እንዳለበት ፈፅሞ አለማወቃቸው ነው፡፡ በሳይንሳዊ አጠራር “halitosis” ሃሊቶሲስ የሚሰኘው መጥፎ የአፍ ጠረን ሰዎች እንዲርቁን እና በራስ የመተማመናችንን እንድናጣ ከሚያደርጉ ችግሮች ዋነኛው ስለመሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በዛሬው የገመና አምዳችን መጥፎ የአፍ ጠረንን በተመለከተ ዝርዝር ፅሁፍ እናቀርባለን፡፡
መጥፎ የአፍ ጠረን ምንድን ነው?
መጥፎ የአፍ ጠረን በአፋችን፣ በምላሳችን ወይም በቶንሲላችን ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ ባክቴሪያዎች የሚፈጥሩት ውጤት ሲሆን እነዚህ ባክቴሪያዎችም በሁላችንም አፍ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ባክቴሪያዎቹ በደህናው ጊዜ ምንም ሳይለወጡ ባሉበት ሁኔታ የሚዘልቁ ቢሆኑም የተለያዩ አካባቢያዊ
ምክንያቶች ግን እንዲለወጡ ሊያደርጓቸው ይችላሉ፡፡ በዚህ የተነሳም የሚያደርጉት ለውጥ የተለየዩ የኬሚካል ውሁዶችን እንዲያመነጩ የሚያስገድዳቸው ሲሆን የእነዚህ ኬሚካሎች ጠረንም ልክ እንደ ሃይድሮጅን ሰልፋይድ የሚከረፋ የበሰበሰ ዕንቁላል ሽታ የሚመስልና እና ሌሎችም አስቀያሚ ጠረኖችን ሊያመነጭ ይችላል፡፡
መጥፎ የአፍ ጠረን ምን ያስከትላል?
• የጥርስ (ድድ) እብጠት ወይም ቁስለት (Abscessed Tooth) ጥርሳችንን ከበው እና አቅፈው የሚገኙ የሰውነት ህዋሳት ቡድኖች (tissues) ላይ የሚፈጠር የቁስል መመርቀዝ (infection) እንደ መግል (pus) ያለ ፍፁም አስቀያሚ ጠረን ያለው ፈሳሽ እንዲፈጠርና የአፍ ጠረንን እንዲቀየር ያደርጋል፡፡
የመጥፎ አፍ ጠረን መንስኤዎች
•የአልኮል ሡሰኝነት (Alcoholism) ከልክ ያለፈ የአልኮል ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መጠን ያለው የምራቅ መመንጨት እንዲከተልና አፍ እንዲደርቅ በተያያዥም የአፍ ጠረን እንዲበላሽ ያደርጋል፡፡ የአፍ ድርቀት ከሁሉ በተለየ ቀዳሚ የአፍ ጠረን መበላሸት ሰበብ ነው፡፡
• የአፍንጫ ውስጣዊ ቁስለት
ይህ የአፍንጫችን ንፍጥ አመንጪ አካል በጉንፋን የተነሳ በሚደርስበት ቁስለት የተነሳ በአፍንጫችን ለመተንፈስ እንዳንችል በሚያስገድድ ሁኔታ የሚደፈንበት ክስተት ሲሆን በዚህ ምክንያትም አየርን ደጋግመን በአፋችን የማስገባት ብሎም የማስወጣት አማራጭን እንድንከተል እንገደዳለን፡፡ ይህ ከላይ በተጠቀሰው የአፍ ድርቀት ሰበብ የአፍ ጠረን እንዲለወጥ ያደርጋል፡፡
• ነቀርሳ (cancer)
እንደ የጨጓራ ካንሰር፣ የአፍ ዕጢ፣ የነጭ ደም ሴል መብዛት እና ሌሎች መሰል በሽታዎች ባሉ ህመሞች የሚጠቁ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ የመጥፎ የአፍ ጠረን ችግር የሚገጥማቸው ሲሆን የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሰውነት ውስጥ የሚካሄደው የመበስበስ ሂደት እንዲሁም ለበሽታዎቹ የሚሰጡት የህክምና አገልግሎቶች ናቸው፡፡
• የአፍ ቁስለት (Oral Candida)
ይህ በተለይም በህጻናት፣ በስኳር ህመምተኞች እና የኤች አይ ቪ ኤድስ ህመምተኞች ላይ የተለመደ እና በብዛት የሚከሰት ነው፡፡ ይህ አይነቱ በፈንገሶች የተነሳ የሚፈጠር የአፍ ቁስለት ሲሆን ይህም በቀላሉ የአፍ ጠረን እንዲበላሽ ምክንያት ይሆናል፡፡
• የጥርስ መገጣጠሚያ ክፍተቶች (Cavities)
በአንዱና በሌላኛው ጥርሳችን መሃከል ባሉ ክፍተቶች (Cavities) ውስጥ የተለያዩ ነገሮች የሚሰገሰጉና በየዕለቱ ያልተፀዱ እንደሆነም ተከማችተው ወደ ብስባሸነት በመለወጥ መጥፎ የአፍ ጠረንን ያስከትላሉ፡፡
• ሰው ሰራሽ ጥርስ (Dentures)
ሰው ሰራሽ ጥርስ የሚጠቀሙ ሰዎች ጥርሳቸውን እንደ ተፈጥሮ ጥርስ ሁሉ በነፃነት ለማፅዳት የማይችሉ በመሆኑ ጥርሳቸው እንዲቆሽሽና የአፍ ጠረናቸው እንዲበላሽ ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰው ሰራሽ ጥርስ ተጠቃሚዎች ተደጋጋሚ በሆነ የአፍ ድርቀት እንደሚቸገሩና ይህም ለአፍ ጠረናቸው መበላሸት ሌላ ተጠቃሽ ሰበብ እንደሆነ ይገለፃል፡፡
•የስኳር በሽታ (Diabetes)
የስኳር ህመምተኛ የሆኑ ሰዎች በመጥፎ የአፍ ጠረን ሊቸገሩ እንደሚችሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ህመምተኞቹ ሊቆጣጠሩት የሚገባቸውን የደማቸውን ግሉኮስ መጠን ለመቆጣጠር ሲሣናቸውና ሲያሻቅብ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም የድድ ቁስለት እና የጥርስ ህመም የበርካታ የስኳር ህመመተኞች ችግር ሲሆን ይህም የአፍ ጠረናቸውን ሲያበላሽ ይስተዋላል፡፡
• ደካማ የጥርስ ንፅህና (Poor dental hygiene)
ከላይ የጠቀስናቸው እጅግ በርካታ የአፍ ጠረን መበላሸት ምክንያቶች ቢኖሩም አንዳቸውም ግን የደካማ የጥርስ ንፅህና አጠባበቅን ያሀል ለአፍ ጠረን መበላሸት ግዙፉን ድርሻ አይወስዱም፡፡ ጥርስን ዕለት በዕለት አለመከታተል አለመቦረሽ (አለመፋቅ) ለችግሩ በርን ወለል አድርጎ መክፈት እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁሟሉ፡፡
• እርግዝና
በእርግጠኝነት ምክንያቱ ባይታወቅም በእርግዝና ወቅት የአፍ ጠረን ሊለወጥ እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
• ሲጋራ ማጤስ (Tobacco Smoking) ሲጋራ ማጤስ አፍን በማድረቅ የባክቴሪያዎችን ጦር በአፍ ውስጥ እንዲያድግና እንዲባዛ በማድረግ የአፍን ጠረን ከተወዳጅነት ወደ አናዳጅነት ይቀይራል፡፡ ለአፍ ጠረን መበላሸት የሚጠቀሱት መንስዔዎች ከላይ የተዘረዘሩት ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎችም ጥቂት የማይባሉ የችግሩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የምክንያቱን ጉዳይ በዚሁ እንግታና ወደ ቀጣዩ ነጥብ እናምራ፡፡
መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤውና መፍትሄው ምንድነው?
የመጥፎ አፍ ጠረን መዘዞች ምን ምን ናቸው? በርካቶች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ “ግለሰቡ የገዛ የአፍ ጠረኑን መበላሸት ማወቁና መሸማቀቁ ነዋ!” የሚል ነው፡፡ ጥናቶች በሚያሣዩት መሰረት ግን የአፍ ጠረናቸው የተበላሸ ሰዎች ስለ ገዛ የአፍ ጠረናቸው አንዳችም ነገር የማያውቁ እና እንዲያውም በአፍ ጠረናቸው የሚተማመኑ ናቸው፡፡ ከልምድ አንድ ሰው የገዛ አፍ ጠረኑን ለማወቅ መዳፎቹን ወደ አፉ በማስጠጋት እና ወደ መዳፎቹ ውስጥ በመተንፈስ ማሽተት እንደሚቻል ቢታመንም ጥናቶች ይህ ዋጋ የሌለው ሙከራ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰውነታችን በተፈጥሮ የገዛ ራሳችንን ጠረን የመላመድና የመዋሀድ ባህርይ ስላለው ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ማንኛውም ሰው ስለ አፍ ጠረኑ ሁኔታ ለማወቅ ከፈለገ ውስጣዊ ሣይሆን ተከታዮቹ ውጪያዊ ምልክቶች ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡
- የአፍንጫ መደፈን ያጋጥምዎታል?
- የሰውነት መቆጣት (Allergy) ያስቸግሮታል? – ከፍተኛ የሆነ የአፍ ድርቀት ችግርያጋጥምዎታል?
-በአፍዎ ውስጥ የመምረር ስሜት ያጋጥምዎታል? ምላስዎት ላይ እንደ ቅባት ያለ ነገር ያገኛሉ?
- ጓደኞችዎት ማስቲካ እና ሚንት ከረሜላዎች ይሰጡዎታል?
- የተለያዩ ሰዎች እርስዎ በሚናሩበት ጊዜ አንገታቸውን ከእርሶ ዞር ያደርጋሉ?
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ጥያቄዎች እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ሲሆኑ ከጥያቄዎቹ ውስጥ ለብዙዎቹ የሰጡት ምላሽ “አዎ” ከሆነ የአፍ ጠረን ችግር ያለብዎ ለመሆኑ ከፍ ያለ ዕድል እንደሚኖር ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
ለጥያቄዎቹ የሠጡት ምላሽ “አላውቅም” የሆነ እንደሁ ደግሞ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነገሮችን ልብ በማለት እና ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የአፍ ጠረንዎ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ ይጣሩ፡፡ በዓለም ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ አንድን ሰው “አፍህ ጠረኑ ተበላሽቷል” ለማለት ወደኋላ የማትለው የገዛ እናቱ ብቻ ነች፡፡ በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች መመለስ ከሰው እስኪመጣ ሣይጠብቁ የራስን እርምጃ ለመውሰድ ይረዳል፡፡ አንዳንድ ለየት ያሉ የአፍ ጠረኖች የበሽታ ምልክቶች እንደሆኑ በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ይገልፃሉ፡፡ የተወሰኑትን ለማየት ያህልም፡፡
የፍራፍሬ ሽታ ያለው የአፍ ጠረን ይህ በስኳር ህመምተኞች ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን በሰውነታችን ውስጥ የኢንሱሊን እጥረት ሲኖርና ስብን ለመተካት ሰውነት ሲጥር የሚከሰት ለህይወትም አስጊ የሆነ ደረጃ ላይ የመገኘት ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ የአሣ ሽታ ያለው የአፍ ጠረን ይህ ዓይነት የአፍ ጠረን አደገኛ ከሆነ የኩላሊት ችግር (Chronic kidney failure) ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡
መጥፎ የአፍ ጠረንን እንዴት ማስወገድ ይቻላል በዚህ ፅሁፍ ለመጠቆም የሚሞከረው የመጥፎ አፍ ጠረን ማስወገጃ ዘዴ የአፍ ጠረን ችግሩ ከልክ አልፎ ስር ላልሰደደባቸውና በመሃከለኛ የችግሩ ደረጃ ላይ ለሚገኙት ብቻ ነው፡፡ በችግሩ ከዚህ በበለጠ የተጠቃ ማንኛውም ሰው የጥርስ ሃኪም ማማከርን ብቸኛ አማራጩ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ የአፍ መታጠቢያ ፈሳሽ (mouth wash) በርካቶች የአፍ ጠረናቸው መበላሸቱን እንዳወቁ የሚጠቀሙት ፈሳሽ ነው፡፡ በዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገለፀው “mouth wash” በአፍ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎችን የሚገድል እና ለአፍም መልካም ጠረንን የሚሰጥ ቢሆንም በአፍ ውስጥ ያሉ ባክቴሪያዎችን የሚገድለው ግን በውስጡ ያለው አልኮል ነው፡፡ በመሆኑም አልኮል አፍን የማድረቅ ባህርይ ስላለው ዳግም ለባክቴሪያዎች መፈጠርና ለችግሩ ይበልጡኑ ማገርሸት ቀላል ያልሆነ ሚናን ይጫወታል፡፡ በዚህ የተነሳም “የአፍ መታጠቢያ ፈሳሽን (mouth wash) አለመጠቀሙ ተመራጭ ነው፡፡ ፈሳሹን አብዝቶ መጠቀም የድድ መቆጣትንና የምላስ ቁስለትን በማስከተል የአፍ ጠረን መበላሸትን እንደሚያመጣም ይገለፃል፡፡ በመሆኑም የአፍ መታጠቢያ ፈሳሽ (mouth wash) ችግሩን ያጠፋን እየመሰለን እንዲያገረሽ ከማድረግ ውጪ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ይልቅም የቁንዶ በርበሬ ዘይትን፣ የዝንጅብል ዘይትን፣ የቅርንፉድ ዘይትን ሁለት ጠብታዎች በመጠነኛ ውሃ ቀላቅሎ ለአፍ መጉመጥመጫነት ማዋል ውጤታማ መሆኑ ይታመናል፡፡ ጨውን በውሃ ውስጥ በማሟሟት በውሀው መጉመጥመጥ ደግሞ ሌላው የመጥፎ አፍ ጠረን ማስወገጃ መንገድ ነው ይህ ካልተስማማዎት ደግሞ በጨው ፋንታ በውሃው ውስጥ ሎሚ አልያም ኮምጣጤ በመጨመር ተመሳሳይ ጥቅም ለማግኘት ይችላሉ፡፡
ማስቲካ ማኘክ የመጥፎ የአፍ ጠረንን ለማስወገድ አማራጭ አይሆንም፡፡ ማስቲካ ችግሩ እያለ ግን እንደሌለ ሸፋፍኖ ለማቆየት ካልሆነ በስተቀር ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ጥናቶች እንደሚጠሙት ከሆነም አንድ በመጥፎ የአፍ ጠረን የሚቸገር ሰው ችግሩን ለማስወገድ ከማስቲካ ይልቅ ቅርንፉድ ቢያኝክ የተሻለ ውጤትን ሊያገኝ ይቻለዋል፡፡ ፓርስሊ የተሰኘውን የምግብ ማጣፈጫ ቅጠል ማኘክም የሚመከር መፍትሄ ነው፡፡ የጥርስን ንፅህና መጠበቅ ከሁሉ በላይ ወሣኝና ተመራጭ መፍትሄ ሲሆን አንድ ሰው ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ያህል ጥርሱን ማጽዳት ይኖርበታል፡፡ ጥርሱን በሚቦረሽበት ወቅት ድድን እንዲሁም ድብቅ የሆኑ የጥርስ ስፍራዎችን ጎን ለጎን ማጽዳት ይኖበታል፡፡ ከእያንዳንዱ ማዕድ በኋላ ጥርስን ማጽዳት በባለሙያዎች የሚመከር ሲሆን ይህን ማድረግ ባይቻል እንኳ በደንብ አድርጎ መጉመጥመጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ብዙዎች የማያደርጉት ቢሆንም ምላስን በየቀኑ ማፅዳት (መቦረሽም) የሚመከር ተግባር ነው፡፡ የመጥፎ የአፍ ጠረናችን ዋነኛ መመንጫ የሆነው የምላሳችን የኋለኛው (ወደ ጉሮሯችን) አካባቢ ያለው ክፍል በመሆኑ እስከተቻለው ድረስ ይህን የምላሳችንን ኋለኛ ክፍል ለማፅዳት መሞከሩ ይመከራል፡፡
ሌላው መጥፎ የአፍ ጠረን ማስወገጃ ዘዴ “በተራቡበት ሰዓት ወዲያውኑ መመገብ” ነው፡፡ ምግብ በሆድ ውስጥ ከሌለ የምራቅ እጥረትና የአፍ ድርቀት የሚከሰቱ በመሆኑ ለአፍ ጠረን መቀየር ምክንያት ይሆናል፡፡ ሻይን መጠጣት መጥፎ የአፍ ጠረንን ለማስወገድ እንደሚረዳ በቅርቡ የወጡ ምርምሮች ይጠቁማሉ፡፡ “ፓሊፌኖልስ” (Polyphonies) የተሰኘው በሻይ ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል በአፍ ውስጥ የሚገኙ ሰልፈር በማመንጨት የአፍ ጠረንን የሚያበላሹ ባክቴሪያዎችን በመከላከሉ ረገድ ላቅ ያለ ሚና እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የወተት ውጤቶች በተለያዩ ሰዎች ላይ የተለያዩ የአፍ ጠረን ውጤቶችን እንደሚያስከትሉ የተለያዩ ምርምሮች የሚጠቁሙ ሲሆን አንድ በመጥፎ የአፍ ጠረን የተቸገረ ሰው ለአንድ ሳምንት ማንኛውንም የወተት ውጤት ሣይጠቀም በመቆየት ለውጥ ያገኘና መሻሻልን ያየ እንደሁ ደጋግሞ እንዲሞክር ይመከራል፡፡ በመጨረሻም አንድ የአፍ ጠረን ችግር ያለበት ሰው በምንም ዓይነት አፉ እንዲደርቅ ሊያደርግ አይገባም፡፡ ይህ የነበረው ችግር ክፉኛ እንዲባባስ የሚያደርግ በመሆኑ ግለሰቡ (ቧ) በርከት አድርጎ ውሃ መጠጣት የሚመከር ተግባር ነው፡፡
ምንጭ፡ ለውጥ ከተሰኘው መጽሔት ላይ በአቶ በረታ ወርቁ ማሞ የተጻፈ