አብርሃ ደስታ ከመቀሌ
ዓረና መድረክ ቅዳሜ ሰኔ 21, 2006 ዓም በመቐለ ከተማ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ያካሂዳል። ለሰልፉ የሚሆን ሙሉ ዝግጅት ተጠናቋል። የመቐለ ህዝብ በሰልፉ ለመሳተፍ ተዘጋጅቷል። ቅዳሜ ጥዋት ከአምስት ሺ በላይ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰልፉ የጠራንበት ዋነኛ አጀንዳ መድረክ በአዲስ አበባና በክልሎች ዋና ከተሞች እያደረገው ካለው የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ አካል ሲሆን የሰልፉ ዋነኛ አጀንዳዎች ደግሞ የፍትህ እጦት፣ የነፃነት እጦት፣ የዉሃ ችግር፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ የመሬት ጉዳይ፣ የግብር ጉዳይ፣ የማዳበርያ ጉዳይ ወዘተ ናቸው።
ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትም ሰለማዊ ሰልፍ በማድረግ ይረጋገጣል። የትግራይ ህዝብ እስካሁን ድረስ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ ተነፍጎ ይገኛል። በአላማጣ፣ ኲሓ፣ አይናለም፣ መቐለ (ገፊሕ ገረብ)፣ ሓውዜን፣ ዓዲግራት ወዘተ ዜጎች ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ መክረው በፌደራል ፖሊስ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል። ስለዚህ ቅዳሜ ጥዋት ሰለማዊ ሰልፍ የሚጀመርበት ታሪካዊ ቀን ይሆናል። በመቐለ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ የተፈቀደ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ይደረጋል ማለት ነው።
ስለዚህ የመቐለው የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ከዉሃ ጥያቄ የዘለለ ነው። የዉሃ ጥያቄ አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ሁኖ ሌሎች አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ። ሰዎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እየተገደሉ ነው። በሌሎች ክልሎችም እየተገደሉብን ነው። ንፁሃን ዜጎች ያለ ፍርድ እየታሰሩ፣ በድንጋይ እየተወገሩ፣ በፖሊስ እየተደበደቡ፣ በመርማሪዎች እየተገረፉ፣ ያለ ምንም ወንጀል በሽብር እየተከሰሱ ነው። ከዚህ በላይ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ የሚጠይቅ ጉዳይ የለም።
ከሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ከመገረፍ፣ ከመታሰር፣ ከመገደል በላይ ምን ሊያደርጉን ይችላሉ? በሌሎችስ ከዚህ በላይ ምን ተደረገ? ስለዚህ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ በቂ ምክንያት አለን። የመቐለ ህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ በሰለማዊ ሰልፍ ማክበር አለበት። የመቐለ ህዝብ እንደነ አዲስ አበባዎች፣ ባህርዳሮች፣ ደሴዎችና ሀዋሳዎች የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብቱ ሊከበርለት ይገባል።
የመቐለ ህዝብ ነፃነት ይፈልጋል። ስለዚህ ይሰለፋል። የቅዳሜ ሰልፍ በገዥው መደብ ካልተስተጓሆለ በቀር ኃይለኛ ሰልፍ ይደረጋል። በአደባባይ ስለሚደረግም ማንም ሰው አይቶ ይመሰክራል። የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ እንዳልሆነ ያስመሰክራል። ፎቶዎችና ቪድዮች እንቀርፃለን። ትመለከታላቹ።
ሰልፉ ቅዳሜ ጥዋት በ3:00 ሰዓት ከአደባባይ ዘስላሴ (ባዛር) ተነስቶ በሓውዜን አደባባይ አልፎ ሮማናት አደባባይ አቋርጦ አብርሃ ካስትል ሆቴል ከደረሰ በኋላ ወደ ናሽናል ሆቴል ታጥፎ በጤና ጣብያ በኩል ላዕለዋይ ፍርድቤት ደርሶ ሮማናት አደባባይ ላይ ይጨረሳል። የመድረክ መሪዎች ንግግር ያደርጋሉ። በ6:00 ሰዓት ይጠናቀቃል።
ህወሓት የሀዋሳውን፣ የባህርዳሩን፣ የአዲስ አበባውን ወይ የደሴውን ያህል ከፈቀደልን የቅዳሜ ሰልፍ በእርግጠኝነት የተዋጣለት ይሆናል። እስቲ ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ሰልፍ ከፈቀደ እንይ። መቐለ ሰልፍ ልትጀምር ነው። ህዝብ ዓረና መድረክ ያለውን ድጋፍ ባደባባይ የሚገልፅበት ቀን: ቅዳሜ።
ህወሓት ሰልፉ እስኪጠናንቀቅ ድረስ ፀጥታ ካስከበረ ህወሓትን በፅሑፍ ነው የምናመሰግነው። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ እንደሌላው ህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ አስከብሮለታል ማለት ነውና። ሰለማዊ ሰልፍ መፍቀድ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። ሰልፍ ለትግራይ ህዝብ ተአምር ነውና። ምክንያቱም ተፈቅዶልን አያውቅም።
እስቲ ህወሓት ትፈተን። እስቲ ህወሓት የህዝብ ድጋፍ አለኝ ብሎ የሚተማመን ከሆነ ሰልፉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሰልፉን ለማየት ዝግጁ ይሁን።
ለማንኛውም ቅዳሜ እንገናኝ። የዉስጥ ለውስጥ ቅስቀሳው አልቋል። ነገ ዓርብ ፎርማል ቅስቀሳ ይደረጋል። በህዝብ ያለን ድጋፍ ለማወቅ ተከታተሉን።