ቪያግራም እንደ ራስ ምታት ክኒን?
ፋርማሲስት ወይዘሪት ዙፋን በቅርብ ጊዜያት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡትን የወሲብ ማነቃቂያ እንክብል ተጠቃሚዎች መብዛት ቢያስገርማትም ምክንያቱን ከብዙዎቹ ተጠቃሚዎች ትሰማለች ነገር ግን ብዙ ጊዜ ያለማዘዣ በድፍረት መጥተው ለመግዛት የሚከራከሩ ተማሪዎችን ስታይ ግን ይበልጠ ቢገርማትም ተማሪዎቹን አስረድታ ከመሸኘት ውጭ ምንም ማድረግ ባለመቻሏ ታዝናለች፡፡
«አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ታዳጊዎች ግን የሚቆጣጠራቸው የለም እላለሁ ለራሴ» ትላለች ደግሞ ከዛ የባሰውን ሁኔታ ስታስበው «ዘንድሮ ወላጅም እኮ ተቆጣጣሪ ያስፈልገዋል አሁንማ እነሱም ፋርማሲያችንን የሚያጨናንቁት በዚሁ ቪያግራ ክኒን የተነሳ ነው፡፡» በማለት አሁን ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች፡፡
በአንዳንድ ፋርማሲዎቻችን ውስጥ ያለማንም ከልካይ ይሸጣል፡፡ ገበያ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በመላው ዓለም ላይ ተስፋፍቷል፡፡ በሃገራችን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ በስፋት ይታወቃል፡፡ የተጠቃሚውም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ የትየለሌ እየሆነ መጥቷል፡፡
እኔም የሚነገረውን የአደባባይ ምስጢር ልፈትሽ በመነሳሳት ወደ አንዳንድ ፋርማሲዎች ጎራ አልኩ፡፡ በመጀመሪያም ያቀናሁበት ፋርማሲ እጅግ ብዙ ተገልጋይ የሚመላለስበት ቤት ነው፡፡ በቅርብ ያገኘሁትን ፋርማሲስትም ጠጋ ብዬ ቪያግራ መኖሩን ስጠይቀው፣
‹‹አዎን የውጩን ነው ወይስ የሃገር ወስጥ ነው የምትፈልገው?›› ሲለኝ
‹‹ የሃገር ውስጥ›› በፍጥነት መለስኩ
‹‹ማዘዣ ይዘሃል?›› ጠየቀኝ ፋርማሲስቱ በትኩረት እየተመለከተኝ
‹‹አልያዝኩም ግን ደንበኛ ነኝ›› በፈግግታ መለስኩለት፡፡ በጥርጣሬ ዓይን መልከት አድርጎኝ በፍጹም ያለማዘዣ እንደማይሸጥልኝ ቢነግረኝም በሂደት ማሳመን ስለቻልኩም ያለማዘዣ ሊሸጥልኝ ተስማማን፡፡
በሌላኛው ፋርማሲ ግን ብዙም ሳልቸገር የትኛውን ዓይነት እንደምፈልግ ጠየቀኝ፤የጥራት ደረጃውም ሆነ የዋጋው ሁኔታን እንደ ደንበኛ ሳይሆን እንደገበያተኛ አስረዳኝ፡፡ በመቀጠልም ሕንድ ሃገር የሚመረተውን ሊሸጥልኝ ተስማማን፡፡
ከ9 ብር እስከ 160 ብር የሚደርሱ የተለያዩ አይነት የወሲብ ማነቃቂያ እንክብሎች ዋጋና አይነት አስረድቶኝ እንድመርጥ ፈቀደልኝ፡፡ እኔ ካየኋቸው በዋነኛነትም በሃገራችን ውስጥ በሕንድ ኩባንያ የሚመረተው ኩፒድ የተሰኘው የቪያግራ ዘር የሆነ እንክብል በብዛት ተጠቃሚ እንዳለውም ለማወቅ የዋጋውን ርካሽነት መገንዘብ ቀላል ነው፡፡ይህን መሰል የአደባባይ ምስጢሮች በከተማችን የመድሐኒት መሸጫ መደብሮች ሁሉም ጋር ባይሆን በአንዳንድ ቦታዎች ይታያሉ፡፡ ከአዛውንት አንስቶ እስከ ወጣት እና ተማሪዎችም ተጠቃሚዎቻቸው ናቸው፡፡
ዳንኤል አለምነህ ይባላል፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡ የኩፒድም ሆነ የሌሎች የቫያግራ እንክብል ዓይነቶች ቋሚ ደንበኛ ነው፡፡ ‹‹ባለቤቴን እወዳታለሁ፤እሷን ማጣት አልፈልግም፤በተለይ በወሲብ የተነሳ ትዳሬ እንዲናጋ አልፈልግም ምክንያቱም ሥራዬ ጫና የበዛበትና ፋታ የማይሰጥ ነው፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና እያልኩ ሳለ ባለቤቴን ማስደሰት አለመቻሌ ደግሞ ለኔ ከሁለት ያጣ መሆን ነው፤ ስለዚህ ተያያዥ ችግሮች እና በየጊዜው ያልጠበቅኳቸው ሕመሞችን ቢያስከትልብኝም ከመጠቀም ወደ ኋላ አልልም፡፡ ይህ ለትዳሬ ስል ያደረግኩት ነገር ስለሆነ ምንም አይፀፅተኝም›› ይላል ጠንከር ባለ ስሜት፡፡
ተዘዋውሬ ከቃኘኋቸው ትምህርት ቤቶች መካከል በአንድ የግል ትምህርት ቤት የሚገኝ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀኝ መምህር እንዲህ ሲል ሃሳቡን አጋርቶኛል፡፡ ‹‹ይህ የወሲብ ማነቃቂያ መድኃኒት እንዲህ በስፋት በሃገር ውስጥ እንደሚሸጥ እንኳን አላውቅም ነበር ነገር ግን ከራሴ ተማሪዎች ይህን ነገር በመስማቴ ተደንቄያለሁ፡፡ እነሱ ለእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ከኛ ይልቅ ቅርብ ናቸው በተለይም እነዚህ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በብዛት የሚጠቀሙ መኖራቸው የትምህርት ቤቶች ሚስጢር ነው›› ይላል:: ተማሪዎችም ይህን እንክብል እንዴት በቀላሉ ሊያገኙት እንደሚችሉም ግምቱን ሲያስቀምጥ ‹‹ፋርማሲዎች ያለማዘዣ እንደሚሸጡላቸውም እሰማለሁ፡፡ ከሱ በባሰ ግን በተለይ በመካከለኛም ሆነ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ያሉ ወላጆች በብዛት ይጠቀማሉ እነዚህ ተማሪዎችም ከወላጆቻቸው ሰርቀው መጠቀማቸውና በራሳቸውም እየገዙ መጠቀም መቻላቸው ይመስለኛል›› ይላል፡፡
መምህር ይስሃቅ ደረሰ ግን ይህ ብቻ አይደለም ይላል ‹‹ እንደኔ እምነት ተማሪዎች ለልቅ ወሲብ ፊልሞች መጋለጣቸው ነው፡፡ በፊልሞቹ ላይም የሚያዩት ትዕይንት ይህን መድኃኒት በመጠቀም እንደሆነ ሲረዱና ለረጅም ሰዓታት ወሲብ ሲፈፅሙ እንደሚያዩዋቸው የፊልም ተዋናኞች መሆን ሲያሰኛቸውም ለመጠቀም ይነሳሳሉ›› በማለት ይናገራል፡፡
ተማሪዎች፣ሠራተኞች፣ወጣቶች፣አዛውንቶችም ሆኑ ጎልማሶች በብዛት ወደ መደብራቸው እንደሚመጡ ያጫወተችኝ ፋርማሲስት ወይዘሪት ዙፋን ደግሞ ያለማዘዣ መደብራቸው እንደማይሸጥና ይህን መሰል እንክብል ያለማዘዣ መሸጥ ከህክምና ስነምግባር የራቀ ተግባር እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ነገር ግን እንደሷ አባባል ለተማሪዎችም ሆኑ ለወጣቶች ማዘዣውን በግድየለሽነት የሚፅፉ የሕክምና ባለሞያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳትጠቅስ አላለፈችም ‹‹አለበለዚያ ግን እነዚህ ታዳጊዎች የወሲብ ማነቃቂያ እንክብል በፍጹም የሚያገኙበት ምክንያት ሊኖር አይችልም›› ትላለች፡፡
ከዚህ ባሻገር የስኳር፣ደም ግፊትና የልብ ሕሙማን የወሲብ ስንፈት በሚያጋጥማቸው ወቅት መድኃኒቱን በመውሰድ ባልታሰበው መልኩ ብዙ ባለትዳሮችም ሆኑ ወጣቶች ሕይወታቸው እያለፈ ነው፡፡ ይህን በተመለከተም ይህችው ፋማሲስት ቀደም ሲል የምታስታውሰውን ታሪክ አጫወተችኝ ‹‹የግፊት ሕመምተኛ ነው፡፡ ለግፊት ማስታገሻ መድኃኒቱንም እየወሰደ ነው፤የሚወስደው መድኃኒት ሥንፈተ ወሲብ ስላስከተለበትም ቪያግራ መጠቀም ይጀምራል፡፡ ከብዙ ጊዜያት በኋላ ባልታሰበው መልኩ የደም ግፊቱና የልብ ምቱ መስመሩን ስቶ ግለሰቡ ሕይወቱ አልፏል፤ይህን ያደረገውም ኃኪሙን አማክሮ መሆኑ ኃኪሙም እንዲጠቀም መፍቀዱ በሞያዊ ጥፋት ሊያስጠይቀው በተገባ ነበር›› ስትል በኃኪሞች ዙሪያ የሚከሰተውን ችግርና አደጋ ምን ያህል እንደሆነ ታስረዳለች፡፡
ኃኪሞች የመድኃኒት ማዘዣ ይቅርና የእረፍት ፍቃድ እንኳን ሲሰጡ ብዙ ነገሮችን ከግምት አስገብተው እንዲሆን የሳይንሱ ስነምግባር ያዛል፡፡ ከአካላዊ ምርመራ አንስቶ፣የታማሚውን ችግር ምን ያህል መድኃኒቱ እንደሚያስፈልገው ሙያዊ ውሳኔ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ይህን መሰል ከስነ ምግባር የወጡ ሥራዎችን የሚፈጽሙ የሕክምና ባለሙያዎች ካሉም ሰፊ ቁጥጥርና ክትትል የሚያስፈልገው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ይህን መሰል ስህተት አውቀውም ሆነ በግድ የለሽነት የሚፈጽሙ ባለሙያዎች ካሉም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
ሲንድናፊል፤ድንገተኛው ዱብዕዳ
የወሲብ ማነቃቂያ እንክብል በተለያዩ ስያሜዎች በዓለማችን ላይ ቢስፋፋም ዋነኛ መጠሪያውና ሳይንሳዊ ስሙ ሲንድናፊል ሲሆን እንክብሉን ለዓለም በስፋት ያስተዋወቀው ኩባንያ ቪያግራ በሚል ስያሜ ስለሆነም ከሳይንሳዊ ስሙ ይልቅ የንግድ ስሙ በሁሉም ሰው ዘንድ በስፋት ይታወቃል፡፡
ቪያግራን ለገናናነት ያበቃው አንድ አጋጣሚ ነው፡፡ ከመነሻው የመድሃኒት አምራቹ ፒፋየዘር ለከፍተኛ የደም ግፊትና ለሌላ ህመም መፍትሄ ይሆናል የሚል ተስፋ ነበረው፡፡ እናም ለሙከራ አቀረበ፡፡ ኋላ ላይ ግን በሙከራው ውስጥ የተሳተፉት ወንዶች የናሙናቸውን ውጤት አንመልስም በማለታቸው ተመራማሪዎቹ አንዲት እንግዳ ነገር መፈጠሩን ጠረጠሩ፡፡
በእርግጥም ልክ ነበሩ፡፡ የምርምር ሙከራዎቹ በቀጠሉ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሰማያዊ ክኒን ተዓምራዊ መሆኑ ተደረሰበት፡፡ ተስፋ ላጡት ብዙዎችም ተስፋቸውን መለሰ፡፡ ቀደም ያሉ ጥናቶች በአሜሪካ በየቀኑ ከ50 ሺህ በላይ የቪያግራ ኪኒኖች እንደሚወሰድ ያሳያሉ፡፡ቪያግራን መጠቀም በተለይ በአሜሪካ እ.እ.እ ከ1998 ወዲህ አንድ ባህል ሆኗል፡፡ አሜሪካ የቪያግራ ማህበረሰብ እስከመባልም ደርሳለች፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ በመላው ዓለም ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ በአጭር ዓመታት ውስጥ መስፋፋት የቻለና በተለያየ መጠንና ስያሜ በገፍ መቸብቸብ ችሏል ለኩባንያውም ትልቅ ትሩፋትን ፈጥሯል፡፡
በሀገራችንም በተመሳሳይ መልኩ የተጠቃሚው ቁጥር እጅግ እየጨመረና ርካሽ በሆነ ዋጋ መሸጥ ከጀመረም ዓመታቶች ተቆጥረዋል፡፡ በከተማችን አዲስ አባባም በተለያዩ የመድኃኒት መደብሮች የሚገኘው ይህ እንክብል ከወጣት እስከ አዛውንት ከፍተኛ ተጠቃሚ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች መሃከል የህንዱ ካዲላ ፋርማዮቲካልስም ይገኝበታል፤ኩባንያውም ኩፒድና ሌሎች የቪያግራ ዘሮችን አምርቶ ያቀርባል፡፡
ተጠያቂው ማን ይሆን?
በሃገራችን ስላለው የመድኃኒት ቁጥጥር ሁኔታ ሰፊ መረጃ ለማግኘት በማሰብም የኢትዮጵያ ምግብ፣የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የሚመለከተውን ኃላፊ ለማግኘት በማሰብም ለሁለት ሳምንታት ቀጠሮ ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ በተለይ ዋና ዳይሬክተሩን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ የማይታሰብ ሙከራ ይመስል ነበረ፡፡
ተቋሙ ባለስልጣን መስሪያ ቤት እንደመሆኑ ቁጥጥሩንም የሚከታተልበት የራሱ መንገድ ይኖረዋል፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በሕዝብ ግንኙነቱ አቶ ሳምሶን አማካኝነት የሚመለከተውን አካል ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካበትም ዋነኛ ምክንያት በሥሩ ባሉ በተለያዩ ክፍሎችና ኃላፊዎች መካከል ቅንጅት ባለመኖሩና አንዱ እንደማይመለከተው በመጥቀስ ወደ ሌላው በመጠቆም ሌላኛው መልሶ ወደ አንዱ በመምራት ለሁለት ሳምንታት ያህል ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይህን መሰል የአሠራር ዝርክርክነትና ኃላፊነትን የመሸሽ ባህሪ የተላበሰ ተቋም በሃገር ደረጃ ሃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም እንዴትስ ብሎ በከተማችን ስላለው የመድኃኒት ዝውውር ሁኔታ ከከተማዋ የጤና ቢሮ ጋር በቅንጅት መሥራትስ ይችላል ተብሎ ይታሰባል?
ቪያግራን ማን ይጠቀምበት?
የወሲብ ማነቃቂያ እንክብል ወይም በሳይንሳዊ አጠራሩ ሲንድናፊል በከተማችን የመድኃኒት መደብር እንደ አሸን የመፍላቱ ምስጢርም አምራች ኩባንያ በሃገራችን መኖሩና የዋጋው መርከስ ብቻም ሳይሆን የተጠቃሚው ቁጥር መጨመሩ ነው፡፡ ፋርማሲስት ወይዘሪት ዙፋን በንፅፅር ስትናገር ‹‹ የቪያግራ እንክብል ከአስፕሪን እኩል የሚሸጥበት ወቅት አለ›› ትላለች የተጠቃሚው ቁጥር ምን ያህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ስትናገር፡፡
ይሁንና የእንክብሉን አጠቃቀምና ማን መጠቀም እንደሚችል አደጋውንና ተያያዠ ጎኑን በተመለከተ ከፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር ጋር ቆይታ ለማድረግ ወደድን፡፡ ፕሮፌሰር ጀማል የስኳር ሕሙማን ማሕበር የክብር ፕሬዝዳንትና የሄልዝ ፈርስት ከፍተኛ ክሊኒክ የስኳር ኃኪም ናቸው፡፡ ከእርሳቸውም ጋር ባደረግነው ቆይታ ሰፊ ማብራሪያ እንዲህ ሰጥተውናል፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች ይህን መሰል ችግር ሲያጋጥማቸው ኃኪሞችን ከማማመከር ይልቅ ገዝተው የመጠቀም ዝንባሌ አላቸው ነገር ግን ይህ በብዙ ምክንያት አይመከርም አንደኛ የወሲብ ችግር ምንድን ነው? ያንን መለየት የሚችለው ሃኪም ብቻ ነው፡፡
ማንም ሰው ስንፈተ ወሲብ አለብኝ ብሎ እንደ ቪያግራ ያሉ እንክብሎችን መውሰድ የለበትም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ እንክብል እንደሚገባው መወሰን የሚችለው ኃኪም እንጂ ማንም አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ይህን ባለማድረጋችንም ለአላስፈላጊ የጎንዮሽ ችግር ጠንከር ሲልም ለሞት እየተዳረግን ነው፡፡
ሁለተኛ ነገር በስኳር ሕመምም ሆነ በሌላ ነገር የተነሳ የነርቭ መጎዳት አልያም ሌላ ሌላ የጤና ችግር ካለበት ፣ለልብ ሕመም የሚሆን መድሃኒት የሚወስድ ከሆነ፣የኩላሊትና መሰል ጉዳት ካለበት ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ወይ መጠኑን መቆጣጠር ያስፈልጋል አልያም ከነጭራሹኑ አለመውሰዱ ይመረጣል፡፡ ይሄም ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን መጀመሪያ ሃኪም ጋር መታየት እንዳለበት ፕሮፌሰር ጀማል ያስረዳሉ፡፡
ፕሮፌሰርም ‹‹በመሰረቱ የወሲብ ችግራችን እኛ እንደምንሰጋው ከባድ ሳይሆን ቀላል የስነልቦና ችግር ሊሆን ይችላል፤አልያም ያላስተዋልነው ሌላ ቀላል ጉዳይ ሊሆን ይችላል እናም ይህን መወሰን የሚችለው ኃኪሙ ብቻ ነው፤ኃኪሙም ሙሉ ምርመራ አድርጎ እንጂ በዘፈቀደ አይደለም›› በማለት ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚስፈልገውም ያሳስባሉ፡፡
መድኃኒቱን ከመውሰዱ በፊት ያለበትን ችግር ከተለየ በኋላ መውሰድ እንደሚችልና እንደማይችል ኃኪሙ ይወስናል፡፡ ችግር ከሌለበት ደግሞ በሳምንት ምን ያህል ጊዜ መውሰድ እንዳለበት እንደገና ልዩ ልዩ ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት መድኃኒቱን መመጠን ያስፈልጋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ቪያግራን የሚወስድ ማንኛውም ግለሰብ ጠቅላላ ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ አስፈላጊ ክትትል እየተደረገለትም ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ጠቅላላው የጤና ሁኔታ፤የሚወሰዳቸው መድኃኒቶች፤ሌሎች ሕመሞች ካሉበት ይለያሉ፡፡ ይህን መድኃኒት እየወሰደ ከሆነ ችግር እንደማያመጣበት ካተረጋገጠ በኃላ መድኃኒቱን ታዞለት ነው መቀጠልም ያለበት፤ለመጀመሪያ መድኃኒቱ ሲታዘዝለትም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው መውሰድ ያለበት፡፡ ለምን ቢባል ችግሩን ፈትቶለት ይሆናል ወይም ደግሞ የጎንዮሽ ችግር አምጥቶበት መሆኑን ለመለየት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ከምንም ተነስቶ መውሰዱ በራስ ላይ አደጋ ማምጣት ነው፡፡
ሥንፈተ ወሲብ፣ ስኳር፣ ደምግፊትና የልብ ሕመም
እንግዲህ የስኳር ሕመምተኛ የወሲብ ችግር ሲኖርበት ሌሎች ብዙ ነገሮች ችግሩን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም የስነልቦና ችግር ሊሆን ይችላል ስለዚህ ሃኪሙ የችግሩን ዓይነት ባግባቡ በመለየት እንጂ በደፈናው ማዘዝ የለበትም የስኳር ሕመምተኛ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ በሌላ ምክንያት የወሲብ ችግር ሊታይበት ይችላል፡፡ እንግዲህ ይህን መለየት የሃኪሙ ፈንታ ነው ፡፡
ሁለተኛው የስኳር ሕመም አንዳንድ ጊዜ የወሲብ ችግር የመጀመሪያ መንስዔ ሊሆን ይችላል፡፡ ነርቭ በመነካቱ ነው ብዙ ጊዜ ይህ ችግር ሊከሰት የሚችለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የደም ስሮች በመጥበባቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡መድኃኒቱን ከመውሰድ ጋር ሌላ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር መድኃኒቱ ጠቃሚ ጎን እንዳለው ሁሉ ጎጂ ጎን አለው፡፡ ያ ጎጂ ጎን ከሰው ሰው ይለያያል፡፡መድኃኒትንም አብዛኛውም ጊዜ ከጎጂ ጎኑ ይልቅ ጠቃሚ ጎኑ ስለሚያመዝን ነው የምንጠቀመውም፡፡ ፕሮፌሰር በምሳሌም ሲያስረዱ ‹‹ለምሳሌ የልብ መድሃኒት የሚወስድ ከሆነ ያ መድኃኒት ከዚህ ጋር አይሄድም ከዚህ ባሻገር ከሰው ወደ ሰው በሚለያይ መልኩ የጎንዮሽ ችግር ሊከሰት ይችላል እናም ከጀመረ በኋላ እንኳን ክትትል ያስፈልገዋል›› ይላሉ፡፡
ነገር ግን እርግጥ ነው በስኳር ሕመምተኞች ላይ የወሲብ ችግር ከመጣ ብዙ ጊዜ የስኳር ሕመሙ ነው መንስዔው፡፡ አንዳንድ ጊዜም የደም ስር ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ቪያግራ የሚባለው በነርቭ ችግር ምክንያት የወሲብ ችግር ሲኖር ነው ጥቅም ላይ የሚውለው፡፡
የስኳር ሕሙማን የሚያጋጥማቸውን የወሲብ ችግር ሰፊነት ሲያስረዱም ‹‹መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የስኳር ሕመም ከተከሰተ የዕድሜ ልክ ሕመም ስለሆነ በስኳር ሕመም የሚመጣ የወሲብ ችግርም የዕድሜ ልክ ይሆናል ምክንያቱም በችግሩ የተጎዳ የነርቭ አካል ተመልሶ ሊስተካከል አይችልም፡፡ ቋሚ ክትትል ማድረግ ይገባዋል፡፡ ግለሰቡም ጤናውን በሦስት ወር በሚመጣ በስድስት ወር በሚመጣ ክትትል ኃኪሙ በሚያዘው መሠረት እየተከታተለ ሊጠቀም ይችላል›› ይላሉ፡፡
በማከልም ‹‹እንደ ኃኪም የምንመክረውም ግለሰቡ የራሱን የስኳር መጠን እየተቆጣጠረና እየለካ መዝግቦ ኃኪም ጋር ሲደርስ ማሳየቱ የቁጥጥር ደረጃው ምን ላይ እንዳለ ለማወቅ ይረዳል፡፡ አሁንም ቢሆን አንዳንድ ዓይነት የልብ መድሃኒቶች እየወሰደ ከሆነ እና ሌሎች ተመሳሳይ ህክምና ላይ ካለ የወሲብ ማነቃቂያ እንክብሉን እንዲወስድ አይመከርም›› በማለት ያሳስባሉ፡፡
እንዲሁም ሌሎች እንደ ደም ግፊት ላሉ ሕመሞች የሚወሰዱ መድኃኒቶች ያንን ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡እንደዛ ከሆነም የደም ግፊቱን መድኃኒት መቀየር ያስፈልጋል ምክንያቱም በርከት ያሉ የደም ግፊት መድኃኒቶች ለስንፈተ ወሲብ ሊዳርጉ ስለሚችሉ ነው፡፡ እንደታማሚው ሁኔታ በማየትም ለደም ግፊት የሚሰጠውን መድኃኒት መለወጥ ነው፡፡ በዛ ችግሩ ከተፈታ ቪያግራ እንኳን አያስፈልግም ማለት ነው፡፡
የስኳር መድኃኒቶች እስከሚታወቀው ድረስ ለዚህ የሚዳርጉ የሉም፡፡ ከልብ መድኃኒቶች መካከል ለዚህ የሚዳርጉ አሉ፡፡ለምሳሌ የልብ ደምስሮች በመጥበባቸው ምክንያት የሚመጣ ህመም አለ ያንን ለማስታገስ የደም ስር ሰፋ ለማድረግ የሚረዱ ናይትሬት የሚባሉ መድኃኒቶች ሲወሰዱ ከቫያግራ ጋር ላይስማሙ ይችላሉ፡፡
በደም ግፊት በኩል ይህን ችግር የሚያመጡ ብዙ መድኃኒቶች አሉ፡፡ይህ አይነት ችግር በመድኃኒቱ ምክንያት ተከስቶ ከሆነ መድኃኒቱን ከመጀመሩ በፊት ስንፈተ ወሲብ አልነበረበትም ማለት ነው፡፡ መድኃኒቱን ከጀመረ በኋላ የሚመጣ ከሆነ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ይታወቃል፡፡ስለዚህ ኃኪሙ ዋነኛ ተግባሩ ምን ምን መድኃኒት እንደሚወስድ ጠንቅቆ እንዲያውቅና እንዲወስድ ማድረግ ነው፡፡መድኃኒት መውሰድ ከመጀመሩም በፊት ኃኪሙ የሚሰጠው ሁኔታም ይወስናል፡፡አጠቃላይ ሕሙማንንም ሆነ ጤነኛውን ግለሰብ ለጊዜውም ቢሆን ቪያግራና ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው መድኃኒቶች መፍትሔ ሊያመጡለት ይገባል ካልሆነ ግን በሌሎች ዓለማት በቀዶ ጥገና የሚደረግም አለ ነገር ግን እንደ ፕሮፌሰር ጀማል እምነት ይህ አይመከርም፡፡
ሌላ መፍትሔ?
ለምሳሌ የስኳርም ችግር ሆነ ጤናው በጠቅላላ ጉዳት የደረሰበት በተለይ ጠቅላላ ድካም ያለበት ሰው በዚህ አይነት ችግር ሊጠቃ ይችላል፡፡ ስንፈተ ወሲብ ደግሞ ብዙ ጊዜ ከጤና መጓደል ጋር የተያያዘ ነው ስለዚህም በስፖርትም ሆነ በሌላ እንቅስቃሴ ሊፈታ ይችላል፡፡ በተለይ የአካል መዳከም ከሆነ በስፖርት መነቃቃት እንደሚቻል ፕሮፌሰር ጀማል ይጠቁማሉ፡፡
‹‹አንድን ችግር በተናጠል ማየት አደጋ አለው፡፡ ሁሉንም ችግር ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ መድኃኒቱን ልንወስድ ይገባል እንጂ ችግሩ ስላለብን ብቻ መጠቀም የለብንም›› በማለት ሃሳባቸውን ይቋጫሉ፡፡
የቪያግራ ተጠቃሚዎች ሊያውቁት የሚገቡ እውነታዎችና ጥንቃቄዎች
የወሲብ ማነቃቂያ እንክብሎችን ስንወስድ የሚመጡብን ተያያዥ ጉዳቶች እንዳሉ አስቀድመን ልናውቅ ይገባል ነገር ግን እነዚህ ጉዳቶች ከሰው ሰው ይለያያሉ፡፡ በስፋትና በአብዛኞቻችን ላይ የሚታዩ ችግሮችም ይኖራሉ፡፡ መድኃኒቱንም ስንወስድ ማወቅ ያለብን እውነታዎች ቢኖሩ፤ የሚጠበቁ የህመም ስሜትችና አንዳንድ ድንገተኛ የሆኑ ጤና ነክ ክስተቶች ናቸው፡፡ ይህ እንክብልንም ያለ ኃኪም ትዕዛዝ መውሰዱ ብዙ ጉዳቶች እንዳሉት ከግንዛቤ ማስገባት ብቻ ሳይሆን እየወሰድነውም ቢሆን የኃኪም ክትትል አስፈላጊ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም፡፡
መድኃኒቱን እየወሰዱ ከሆነ ሊጠነቀቁና ሊያውቁት የሚገባዎ እውነታዎች፡-
የአይን ማቃጠልና ማሳከክ፣የራስ መክበድና ሕመም ሲያጋጥምዎ
የሽንት መቆራረጥና ለመሽናት ሲሞክሩ ከባድ ሁኔታ ካጋጠመዎት
የዕይታ መጋረድና የተለያዩ ቀለማቶችን ማየት ብርሃንን አለመቋቋም፤ጠንከር ሲልም በከፊል የማየት ችግር ሲከሰትብዎ
ወደ ኃኪም መሔድዎን አይዘንጉ፡፡
1.የልብ ምትዎ ወጥ አለመሆንና መቀያየር፣የደረት ሕመምና የትንፋሽ ማጠር ወሲብ ሲጀምሩም ሆነ በወሲብ ወቅት ካጋጠመዎት
2. ከ4 ሰዓት በላይ የብልት መቆም ወይም ሕመም ያለበትና ያልተለመደ አይነት የብልት መቆም ሲያጋጥምዎት
3. የአለርጂ ችግር ኖርብዎትም ሆነ ሳይኖርብዎት መድኃኒቱን መውሰድ ከጀመሩ በኋላ በስፋት በፊትዎም ሆነ በገላዎ ላይ የአለርጂ ምልክት ሲታይብዎት
አንክብሉን በፍጥነት እንዲያቆሙ ይመከራል፡፡ ከሕይወትና ከጤና የሚበልጥ የለምና ለሚወስዱትም ሆነ ለሚጠቀሙት ነገር እጅግ ጥንቃቄና ኃላፊነትን በተላበሰ ሊሆን ይገባል፡፡
ምንጭ፡ ሜዲካል ጋዜጣ