እርሳሱ መሬ
Ersasumere@gmail.com
በኢህአዲግ ውስጥ ካሉት ቁንጮ ባለስልጣናት መካካል በሞጋችነታችው እና የተሳካለት የቃላት መደርደር ችሎታቸው አቶ ሬድዋን ሁሴንን የሚተካከላቸው አለ ብዬ አላምንም:: እናም በዚያን ሰሞን የአውራምባው ጋዜጣ ባለቤት አቶ ዳዊት ከበደ እኝሁን ባለስልጣን ቃለ መጠይቅ ሲያደርግላቸው የተለመደውን ባዶና ካድሬያውዊ መልሳቸውን አፈሰሱት:: ታዲያን የእኔን ቀልብ የሳበው ነገር ደጋግመው የጠቀሱት ”Corporal Interest” ብለው የደነቀሩት ቃላትና ስለ ምንነቱም የእኔ መንግስት ጭብጥ ግንዛቤ ነው ብለው ያሉት ነገር ነበር:: አዎን ቃላቱ ልክ እዚህ እንደምታነቡት ነው ጥቅም ላይ የዋለው። ለእንደኔ ብጤው እንግሊዝኛ እንደ ቁምጣ ለሚያጥረው አንድ በቋንቋው ተክኛለሁ የሚል የዚህን ቃል ትርጉምና አጠቃቀም እስካላስረዳኝ ድረስ አባባሉ ሰውየው እንደተጠቀሙበት አይነት አጠቃቀም አንብቤም ሰምቼም ነበር ለማለት ድፍረቱ የለኝም። ትልቁ ትዝብት ያለው ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ እየገዛ ካለ መንግስት አፈ ቀላጤ አሳፋሪ ሊባሉ የሚችሉ የአቅም ማነስና የብስለት መታጣት መንፀባረቃቸው ላይ ነው። ለነገሩ በዚያች ሀገር ማፈር ከጠፋ ሰንበትበት ብሏል።ሌላው ቢቀር ቢሯቸውና የስልጣን ቦታቸው የሰጣቸው አጋጣሚና የተመቻቸ ዕድል ከጥቅም ላይ አውለው የራሳቸውን ግላዊና ቡድናዊ የዕውቀት አድማስ ማበልፀግ አለመቻላቸው ወይም አለመፈለጋቸው ዋነኛው አሳዛኝ ነገር ነው። በጣሙን የምንሽማቀቀው ደግሞ ይህን መሰሉ ክስተት ምሁር ነን ፣ ተምረናል ከሚሉ የመንግስቱ ባለሟሎች ጎራም ስናያ ነው።
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህግ ምሁሮች በአሜርካን የተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ዲሞክራሲና ተጠያቂነት እንዲኖር ሊደነግጉት ባሰቡት ሰነድ ላይ ሊተቹ ከተሰበሰቡት መካከል አንዱ ሰነዱን የ”Human Right (watch)” ያቀረበው ነው ብሎ ንግግሩን ሲጀምር ብዙዎች ስል እሱ አፈር በገባሁ ብለው እንዳሉ አስታውሳለሁ። በምሁሩ ዘንድ “HR 2003” ከአሜርካን “House of Representatives “ የወጣ ሰነድ መሆኑን አጣርቶ ሳያውቅ ነው እንግዲህ ምሁራዌ ትችት ልስጥ ብሎ የተነሳው። እንዲም ሆኖ ዝርዝሩ ላይ ፍሬ ያለው ነገር ቢናገር ደህና ነበረ። ሰነዱ ዳግም ውጫሌን ሊያመጣብን ነው ፣ ቅብርጥሴ ሲል ነው የተደመጠው። በዚህ ዙሪያ አንድ በለን ካላችሁኝ በዚያኛው ሰሞን ስለ ፕሬስ ነጻነት ሲውያዩ አንዱ የምዕራቡን አለም አውቀዋለሁ የሚል የሚመስል ተከራካሬ በሙሉ ልብ ሲደሰኩረው የነበረውን ላካፍላችሁ። እንደ ሰውየው አባባል አሜርካን ኢራቅን እንድትወር ያደረጉት ጋዜጠኞችና የሚዲያ አባላት ናቸው።ይህን ሰው ጨምሮ በርካታ የኢህአዲግ ባለስልጣኖች ለንጽጽር ይረዳቸው ዘንድ የአሜርካንን ሚዲያ በተለይም “CNN” እና “FOX NEWS”ን እንደ ምሳሌ ሳያጣቅሱ ያለፉበትን ጊዜ አላስታውስም:: እነዚህ ሁለት ተቋማት ተቃራኒ የሚመስሉ ሃሳቦች ያናጸባርቃሉ ማለቱ ተገቢ ቢመስልም የኢህአዲጎቹ ችግር ግን የአሜርካን ሚዲያ ማለት ቆጥረው የሚጨርሱት፣ልክ በኪሳቸው እንዳለው እና እነሱ ብቻ እንደሚዘውሩት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን አድርገው መውሰዳቸው ላይ ነው::
ስለ ቃላትና ሃሳብ አገላለጽ ግድፈት ይህን ያህል ካልን ከላይ የጠቀስናቸው አቶ ሬድዋን ሁሴን ለማሳተላለፍ ስለፈለጉት ፍሬ ነገር እናውራ። እኔ እንደገባኝ ሚንስቲሩ የሚያወሩት የነበረው የጊዜው የኢህአዲግ ነጠላ ዜማ ሆኖ ዳናኪራ የሚመታበት ጋዜጠኝም ይሁን ሌላ “በነውጥ ስርአቱን ሊያፈርስ” የሚነሳውን ቡድን ከውጪ ሃይሎች ጋር የማያያዝ ጨዋታ ነው።የሚገርመው ነገር ይህ የውጪ ሃይል የተባለው ከወደ አሜሪካን የሚመነጨው የ”Corporate Interest” ተደርጎ የመወሰዱ ፌዝ ነው:: ኢህአዲጎች በአጭሩ የሚሉት ከዩክሬኑ የቀለም አብዮት እስከ አረቡ ስፕሪግ የተደረገውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከኋላ ሆነው የመሩት አሜሪካን ሃገር የሚገኙ ተቋማት ናቸው:: እንደ የአቶ ሬድዋን ሁሴን መንግስት እምነት የነዚህ ተቋማት ቀዳሚ ፍላጎት በሃገሮች ውስጥ እነሱ እንደሚሉት ዲሞክራሲ ለማምጣትና ሰባዓዊ መብቶችን ሊያከብሩ የሚችሉ ቡድኖች መንግስት እንዲሆኑ ለማስቻል ሳይሆን የገዛ ራሳቸውን የ”Corporate Interest” ለማሳጠበቅ ብቻ ነው። ያም ሆኖ ግን ጥረታቸው ሁሉ ሳይሳካ እንደቀረና ይልቁንም አብዮት የተደረገባቸው ሃገራት ወደ ከፋ ችግር ውስጥ እንደገቡ ነው ለማሳየት የሚሞከረው። ዞሮ ዞሮ ይህ የኢትዮጵያ መንግስት አመለካከት ከምን እንደመነጨ ማንም ሰው የሚያውቀው ነው። ኢህአዲጎችም በደንብ እንድናውቀው ነው የሚሹት::ለምን ቢባል የዞን ዘጠኝ አባላትን ወንጀለኛ ለማድረግ አዋጪ መስሎ የታያቸው ይህንኑ ውሃ የማይቋጥር ክርክራቸውን በህዝቡ ጭንቅላት ውስጥ ማስገባት ስለሆነ ይመስለኛል።ህዝቡ ይቀበለዋል አይቀበለውም ሌላ ጨዋታ ነው:: ባይቀበልስ ምን ያመጣል የሚለውም እንደዚሁ::
ይህን በመሰለው ህሳቤ ነበር አቶ ሬድዋን በቀጥታም ባይሆንም “Human Right Watch” ፣ “Freedom House” እና መሰሎቻቸው የዞን ዘጥኝ አባላትን በማስልጠንና በገንዘብ እየረዱ ነው የምትል ክስ ብጤ የሰነዘሩት:: ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የራሳቸውን ርዮት አለም ለማስፋፋት ነው ብለዋል:: የዚህ እውነታማ እስከዛሬ ድረስ እንዴት እንዳልተገለጠላቸው ከገረሙኝ ነገሮች አንዱ ነው:: መጋፈጥ የነበረባቸው ይህ ጊዜ የፈተነውንና ብዙዎች የአለማችን ሃገሮች እሰየው ብለው የተቀበሉት ርዮት አለም ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ወይም አይጠቅምም የሚለውን ክርክር ነበረ:: አይጠቅምም ብለው የሚሉበት አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ስለማይችሉ ይህቺን መሰሏን ክርክር ደፍረው አይነኳትም:: እረስተውት እንደሆነ ነው እንጂ የራሳችው ፓርቲ የአልባንያና የሌላም ሶሻሊዝም ዝባዝንኬ እርግፍ አርጎ ትቶ ነበር እኮ የምዕራቡን ርዮት አለም ተቀበልኩ ያለው:: እንዲያው ለመሆኑ ይህ ከውጪ ሊጫንብን ነው ከሚሉት ርዮት አለም የትኛው ይሆን ለሃገራችን የማይጠቅመው ወይም የሚጎዳው:: ዲሞክራሲ አስፍኑ ፣ የሰውን ልጅ እንደሰው በእኩልነት ተመልከቱት ብሎ ማለት ምኑ ላይ ይሆን የሚያስፈራው? ርዮት አለሙ ሲሰራጭ አብሮት ስርጭቱን የሚያቀላጥፍ ብዙ ገንዘብ ይሰጣል።ህይወት አትራፊው ስንዴማ ያለ ርዮት አለሙም ይመጣል:: አቶ ሬድዋን ዳር ዳሩን እያሉ የፎክሩትማ እንዳው በታሪካችን የውጪ ሃገሮች በሚሉን ስለማንሄድ አሁንም የባህር ማዶ ሰዎች አድርጉ ለሚሉል ነገር ደንታ የለንም የሚሉ ይመስላሉ:: እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ጥቂት አመታት ብዙ ቢሊዮን ዶላር እርዳታ የጎረፈለት ምዕራባውያኑ ለእነሱ የሚበጃቸውን ተግባሮች አድርግ ሲሉት እሺ ጌቶች ብሎ ተግባሮቹን ስለፈጸመ ብቻ ነበር::
አቶ ሬድዋን እዲህና እንዲያ እያሉ ነበር ቃለ መጠይቃቸውን ገፍተው አንድ እሳቸውንም ሆነ የሚውክሉትን መንግስት በእጅጉ የሚያሳንስ አስተያየት የሰነዘሩት:: ሚንስትሩ “Human Rights Watch” እና “Freedom House” ከመሰሎቻቸው ጋር በመሆን በመንግስታቸው ላይ ሊሰሩት የተዘጋጁትን ክፉ ነገር እናውቃለን በሚል እንድምታ በድርጅትቹ ውስጥ ያሉት እያንዳዳቸው ግለሰቦች ማን ማን እንደሆኑና ከዚህ ቀደም ምን እና የት ይሰሩ እንደነበረ ጭምር መንግስታቸው ጠንቅቆ እንደሚውቅ ከእኛ ወዲያ ላሳር በሚል መተማመን ተናገሩ:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም ይህን ስሰማ በአእምሮዬ ድቅን ያለብኝ ያ የቦሌው ፖሊስ የቪኦኤን ጋዜጠኛ ያለህበት መጥቼም ቢሆን አስርሃለሁ ያለው ነገር ነበረ:: ምናልባትም አቶ ሬድዋንም ፣ ያም ፓሊስም የሚናገሩትን የማያውቁና የማመዛዘንና ጉድለት ያለበት አእምሮ ተሸካሚዎች ስለሆኑ ይሆናል:: ለነገሩ ኢህአዲግ ያፈራቸው ደናቁርት ባለስልጣኑ የተናገሩትን ከጠቢብና ምሁር እንደወጣ አድርገው ሊወስዱት እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም:: ነገር ግን እንደው አገሪቷ ውስጥ ሰው ከተገኘ ስለተቋማቶቹ ማንነትና ስለሰዎቻቸው በቀላሉ እየድህረ ገጾቻቸው ሄዶ ማወቅ ይችላል:: የእናቶ ሬድዋንን ለእኛ ብቻ ነው የተገለጥን የሚባለውን ዲስኩር ሳይሰማ ማለት ነው:: እኔም ያደረኩት ይኸው ነበረ:: በሁቱም ተቋሞች ድህረ ገጾች ላይ ድርጅቶቹ መቼና እንዴት እንደተመሰረቱ መርሆቻቸዎ ምን እንደሆኑ ምን እንደስሩና ማን ገንዘብ እንደሚለግሳቸው በግልጽ ተቀምጧል:: የቦርድ አባላቶቻቸውና መሪዋቻቸው ማን እንደሆኑ የት ይሰሩ እንደነበረ በይፋ ይታያል:: ሰዎቻቸው በመንግስትም ይሁን በግሉ ዘርፍ በጣም ውጤታማ ስራ ሰርተው የተደላደለ ኑሮ እንዳላቸው ይገመታል:: አዋን አሚሪካኖች ከግል ምቾታቸው ባላነሰ ለሰው ልጅ ደህንነት ሲባል የሚችሉትን ሲረዱ የህሌና እረፍት ያገኛሉ:: ለዚያም ነው እነዚህ ተቋማት እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሃገሮች የሰው ልጅ መብት ይከበር ዲሞክራሲም ይበጃችኋል እያሉ ሃባታቸውን የሚያፈሱት::የመርህ ሰዋችና ፈሪሃ እግዛብሔብር ያደረባቸው ስለሆኑና በስራቸውም የህሌና ደስታን ስለሚያገኙ ብቻ:: የለም ለእነ ሬድዋን ይህ አይደለም ምክንያቱ:: ሌላ “Corporate Interest” የሚሉት ድብቅ አላማ አለ:: አቶ ሬድዋን ይህ ድብቅ አላማ ምን ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል:: እንድ እሳቸው ከሆነ እነዚህ ድርጅቶች ጠንክረው የሚንቀሳቀሱት በማዕድን ሃብት በተንበሸበሹ ሀገሮች ላይ ነው:: መዕልክቱ ልክ እንደ ድሮው ዘመን የደሃ አገሮችን ሃብት ሊዘርፉ ነው የሚል ይመስላል:: ጉድ በሉ አንባብዮች:: አቶ ሬድዋን አክለውም ተቋማቱ የኢትዮጵያን የመንግስት ባንኮችንና ቴሌን ወደ ግል ይዞታ ቀይሩ ብለው የሚወተውቱት እራሳቸው ሊግዙት ስለ አሰቡት ነው ብለው ያምናሉ። እንደዛማ ካልሆነ ሪፎርም አድርጉ እያሉ መጨቅጨቅ፣የዞን ዘጠኝ አባላትን ማሰልጠንን ምን አመጣው ብለው ይጠይቃሉ::
የተፈጥሮ ሀብት ፍለጋ አሜርካኖች አለምን ሲያስሱ የነበረበትን ዘመን አላስታውስም:: ያ ዘመን አለ ቢባልም እንኳን አፍሪካ ላይ እምብዛም ነው ባይ ነኝ:: እንዲው ለነግሩ በጣም የሚፈልጉትን ነዳጅ እንኳን በሱዳን ላይ እያዩት አልፈውት የለም:: እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት የአሜርካን ኩባንያዏች የአለም ሃገራት በሙሉ ወደ ሃገራቸው መጥተው መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ሲለምኗቸው ነው የሚታየው:: እስኪ የአቶ ሬድዋንና የመንግስታቸውን የአስተሳሰብ ችሎታ መዝኑልኝ:: እስከ ትሪሊየን ዶላር በ”Asset” የሚያንቀሳቅስ አንድ የመሜሪካን ባንክ ይህችን ከትንሽ ምንዛሪ በላያ የማታወጣን የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ለመግዛት ሲል በእነዛ ተቋሞችና ዘጠኝ ብሎግሮች በኩል መንግስት እንዲወድቅ ሲያግዝ ይታያችሁ:: ወይም በመቶ ሚቆጠሩ ሃገራት እየሰራ ያለ የሜሪካን የስልክ ኩባንያ የኢትዮጵያውን ቴሌ ለመግዛት ሲል ስርአቱና የስርዓቱ ፓሊሲዏች ይቀየሩ ብሎ ሲለፋ አስቡት:: የሚግርመው ነገር እንዲህ የውጪን “Corporate Interest” ፈራነው የሚሉት እነሬድዋንና መንግስታቸው ከነጻ ቀጥሎ ባለ ዋጋ የሃገሪቱን ለም መሬት ገበሬና ሰራተኛ ሳይቀር ይዘው ለመጡት ህንዶችን ቻያናዋች መቸብቸባቸው ነው:: እግዛብሔር ብሎትማ አሜሪካኖቹ ወደ ሀገራችን መዋለ ንዋይ ሊያፈሱ ቢመጡ ሌላው ቢቀር ፍታሃዊ ክፍያ፣ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በርካታ ስራና የመንግስት ገቢ ያመጡ ነበር::
በመጨረሻም የዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነውን ካለ መጠይቅ ያደረገው የአውራምባ ታይምሱ አቶ ዳዊት ከበደ ይህቺንም መጣጥፍ በድህረ ገጹ ላይ በመለጠፍ ሚዛናዊነቱን እንድናወድስ ቢያደርግ ደስ ይለኛል::