Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

መድረክ በሐዋሳ የጠራው ሰላማዊ ሠልፍ በእንግልት ተካሄደ

$
0
0

61

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ መድረክ (መድረክ) እና አባል ድርጅቶቹ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ የኢትዮጵያ ማኅበረ ዲሞክራሲ ደቡብ ኅብረት አንድነት ፓርቲ

(አማዲደህአፓ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ (አረና) ጋር በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሐዋሳ ያካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ በእንግልት መካሄዱን አስታወቀ፡፡ 

የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ‹‹ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ተቃውሞዎችን በኃይል ማፈን ይቁም›› በሚል ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ያካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ በሰላም ቢጠናቀቅም፣ ገዥው ፓርቲ ሕዝቡ ወደ ሠልፍ እንዳይወጣ የተለያዩ ማነቆዎችን መፍጠሩን መድረክ ገልጿል፡፡ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው፣ ‹‹ገዥው ፓርቲ አፈና ሲያደርግብን ነበር፡፡ ቅዳሜ ልናካሄድ ላሰብነው ሰላማዊ ሠልፍ የዕውቅና ደብዳቤ የሰጠን ሐሙስ 11 ሰዓት ላይ ነው፤›› በማለት ገዥው ፓርቲን የኮነኑ ሲሆን፣ ‹‹ቢሆንም ግን ሕዝቡ ይህን አፈና ተቋቁሞ በመውጣት የተሳካ ሠልፍ አካሂደናል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡   

ፓርቲው አገሪቱ ውስጥ ተፈጥረዋል ያላቸውን መሠረታዊ ችግሮች በዝርዝር ለሕዝብ ያቀረበ መሆኑን፣ በሕገ መንግሥቱ ተደንግገው ነገር ግን መፈጸም ያልተቻሉ ያላቸውን ዝርዝር ጉዳዮች እንዲሁ ለሕዝቡ ማቅረቡን ገልጿል፡፡ 

መሠረታዊ ችግሮች በሚል ፓርቲው በዝርዝር ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል የሕዝቡ የሥልጣን ባለቤትነት እውን እንዳይሆንና የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲ በትክክል ሥራ ላይ እንዳይውል የምርጫ ቦርድ ለኢሕአዴግ ወገንተኛ መሆኑን፣ በነፃነት በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ በሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ልዩ ልዩ የማቀጨጭ ሥልቶችን ተጠቅሞ ተፅዕኖዎችን ማድረጉን፣ በብልሹ አስተዳደርና በከፋፍለህ ግዛ ሥልቱ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል በተለያዩ ክልሎች በርካታ ግጭቶች ተፈጥረው የብዙ ዜጐች ሕይወትና ንብረት መውደሙን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀም በጽሑፍ፣ በንግግርና በሰላማዊ ሠልፍ ለመግለጽና ኢፍትሐዊና ኢሕገ መንግሥታዊ በሆነው አገዛዝ ላይ ተቃውሞዎችን ለማሰማት ጥረት የሚያደርጉ ዜጐችን ለእስራትና ለተለያዩ ሥቃዮች መዳረጉን፣ ዜጐች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ማድረጉንና በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ መሠረታዊ የሆኑ የሕዝብ አገልግሎቶች ማለትም ኤሌክትሪክ፣ ውኃ፣ ስልክና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ኃላፊነት በጐደለው አሠራር አቅርቦታቸው እየተዛባ ሕዝቡ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጉንና ማማረሩን መድረክ ጠቃቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው ለዘረዘራቸው ችግሮች መፍትሔ ያላቸውን ሐሳቦች ያቀረበ መሆኑን፣ ከእነዚህም ውስጥ ለትክክለኛ የመድበለ ፓርቲና ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተግባራዊነት፣ ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃና ሕጋዊ እንቅስቃሴዎችና ነፃ የውድድር ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በዜጐች መካከል የሚደረግ የፖለቲካዊ ወገንተኝነት አሠራር እንዲቆምና ፍትሐዊና እኩልነት የሰፈነበት አስተዳደር እንዲኖር ማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀና የፓርቲዎችን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ገለልተኛ የምርጫ ቦርድና ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎችን ያካተተ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ እንዲኖርና በትክክል ተግባራዊ ማድረግና ለፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን የድጋፍ ገንዘብ በእኩልነትና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ ማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ 

ይህ በሐዋሳ የተካሄደው ሠልፍ አዲስ አበባ ላይ ተደርጐ ከነበረው ሠልፍ ጋር ተመሳሳይ ዓላማ እንዳለው የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ በቀጣይም በሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ሠልፎች እንደሚካሄዱም አክለው ገልጸዋል፡፡        

Source: Ethiopian Reporter     


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>