Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የልብ ርትዑ አንደበት! (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 17.06.2014 (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)
Haile Medhin Aberaልክ የዛሬ አራት ወር ይህችን ዕለት ነበር ጀግና ካፒቴን አበራ ሀይለመድህን ሲዊዘርላንድ ጄኔባ ላይ ካለምንም እንከን፤ ካለምንም ግድፍት፤ ከለምንም ጥፋት ልቡ የተናገረውን ስኬታማ ክንውን ያደመጥነው።

የልቡ ርትዑ አንደበት መድረኩ ሆነ አድማጩ ድርጊቱ ብቻ እንዲሆን ወስኖ የማድረግ አቅሙን፤ የልቡን ፈቃድና ውሳኔ እንድናይ፤ እንድንማርበት ፈቀደልን። ተባረክ የእኔ ጌታ!

እንሆ የተባ ርትዑ የልብ አንደበት በሙሉ መስናዶ ተደራጅቶ የልብ ካደረስ ልክ ዛሬ አራት ወር ሆነው።

በዚህ በተሸኙ ወራቶች ስሜቱን? ፍላጎቱን? ውስጡን ማዬት ባይቻልም ልቡ የነገረውን፤ ልቡ የወሰነለትን፤ ዘመን የፈቀደለትን ተግባር ከዋኝ በመሆኑ መንፈሱ እረፍት ላይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአንድም ፍጥረተ – ህይወት አካል ሆነ መንፈስ አደጋ ላይ ሳይጥል፤ ቂም ሳይተክል፤ ደም የሚያጋባ እርግማን ሳይፈጥር በጸጥታና በዝምታ የተከወነ መሆኑ ቁጭ ብሎ ሲያስበው ሆነ ሲመረምረው ሊጸጽተው የሚችል አንዳችም ነገር ከቶ እንደማይኖር ይሰማኛል።

ጀግና አበራ ሀይለመድህን የልቡ አንደበት ጥሩ ተናጋሪ የመሆኑን ያህል ጥሩ አድማጭም መሆኑን በቅደም ተከተል የወሰዳቸው እርምጃዎችና ፍሬዎቹ እራሳቸው መስካሪዎች ናቸው። ትውልዱ ከዘመኑ መቀደም ነገን አስልቶ ጥንቃቄን – በብልህንት፤ ብልህነትን – በማስተዋል፤ ማስተዋልን – በድርጊት ማስጌጥ አብነቱን አንቱ ያሰኘዋል። ዛሬ በዬዩንቨርስቲዎች የሚያልቁት ወጣቶች፤ በገፍ ወደ እስር ቤት የሚጣሉት ቀንበጦች፤ አብሶ ሴቶች ከግፉ በተደራቢነት በእዬስር ቤቱ የሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃቶች እና እንግልቶች ሁሉ ሲሰሉ ወጣት አበራ ሀይለምድህን ዬወሰደው እርምጃ አስፈላጊና የተገባ ወቅታዊ መሆኑን ያመሳጥርልናል።

ዕለታዊ ህይወት ለመምራት በስጋት ታፍኖ ራህብን ማስተናገድ፤ የመኖርን ነፃነት በጠራራ ጸሐይ ተቀምቶ ከሁለተኛ ዜግነት ደራጃ በታች መማቀቅ፤ የሰው ልጅ ለትንፋሹ እንኳን ይለፍ ደጅ ጥናት ወረፋ የሚጠይቀብት ቀን ላይ መደረስ፤ ዜጋ ለሚለብሰው ልብስ ቀለምን እንኳን ተሳቆ መሆኑ ሁሉም ሲጠቃለሉ በተለይ ነገ ኢትዮጵያን የሚረከቡ የብሩህ ራዕይ ባለቤት ወጣቶች „አሻምን“ በተገኘው መንገድ ሁሉ ለመግለጽ ቆርጠው በዬደቂቃው መሰዋታቸው ሲታሰብ ይህ ብርቅ ወጣት የወሰደው እርማጃ ሃቅን ያበራ፣ እውነትን ያነገረ፣ ለእውነት ዘብ አደር የሆነ ስለመሆኑ አስተርጓሚ ፈጽሞ አያስፈልገውም።

ዛሬ ዘመን ባመጣው የቴክኖሎጂና ሳይንስ የመረጃ ፍሰት የኢትዮጵያ ወጣቶች ትውልዳዊ ድርሻቸውን ለመወጣት ሌትና ቀን ሲባትሉ፤ ወያኔ ግን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት በመከተር ለእስር የዳረጋቸው ወጣት የብሎገር ትንታጎች፤ የሚረዷቸው ወላጆቻቸውን ሆነ የሚሳደጓቸውን ታናናሾቻቸውን ሜዳ ላይ ካለ ባሊህ ባይ ሲበተኑ ለሚያይ ህሊና በእርግጥም ጀግና አበራ ሀይለመድህን ዬወሰደው እርምጃ የጠራ – እውነትን የተንተራሰ ስለመሆኑ ያለ ይግባኝ ሊያስማማ የሚችል ፍሬ ነገር ሊሆን ይገባል።

ወጣት ጋዜጠኞች ብእራቸውና ጸጋቸው ያዬውን – ያደመጠውን ነው የጻፉት። ከዚህ ውጪ የፈጸሙት አንዳችም በደል የለም። ነገር ግን ከቅርብ ስለተገኙ ብቻ የቋሰኛው ወያኔ የጥቃት ሰለባ ነው የሆኑት። ታስረው በእግር ብረት እንደ ወንጀለኛ መቀጣጫ እንዲሆኑ ሲንገላቱ ቀን እራሱ ደም ያነባል። ምን አደረጉ እነዚህ ንጹኃን? ዘመን የሸለማቸውን ተጋሪ በመሆናቸው እንዴት እንደ ወንጀለኛ በሰንሰለት ይታሠራሉ?!

ስለሆነም ትውልዱ በወል መከራው – በጋራ እንባው፤ በሁለገብ ፍዳው ላይ ቢያንስ መስማማት ያለበት ይመስለኛል። ትውልዱ በተወለደበት በሀገሩ በመገለሉ – በመሬቱ ባይተር መሆኑ – በቀዩ መገፋቱ – በባዕቱ በጥቂቶች በመገላመጡ  እነዚህን ጉልህ ጥቃቶቹ አቅምን ፈጥረው የራዕይን ስምረት ሊያሳኩ የሚችሉ መንገዶችን እንዲጠረጉ መትጋት እንዳለበት ደወሉ ሊሆኑለት ይገባል እላለሁ፤ ካፒቴን አበራ ሀይለመድህን አበራ ያደረገው ይህንን ነው። ያደመጠውን — ያነበበውን —- አመሳጥሮ በተባ ድርጊት ተረጎመው። የልቡ አንደበት ማይክራፎን ወይንም ድምጽ ማጉያ ወይንም መንበር መድረክ አላስፈለገውም – በፍጹም። አጃቢም አላሰኘውም። የፕሮቶኮል ሥነ ምግባር ቅደመ ሁኔታ አልጠዬቀም – በፍጹም። ቁልፍ ከእጁ ነበር – መግል የሚያነባ የግለት ፍዳና ዕንባ። ስለሆነም በማድረግ ብቃት መሪነት „አሻፈረኝን“ ገለጸ።

የልብ ንግግር ህብር ነው። የልብ ንግግር – መስመር ነው። የልብ ንግግር – ደንበር ነው። የልብ ንግግር – የቁስለት ብር አንባር ነው። ዬልብ ንግግር ጥቃት አውጪ – የንቁ መንፈስ ሥር ነው። የልብ ንግግር አጃቢ አልቦሽ – ትጥቀ ሙሉ አሸናፊ ግብር ነው። የልብ ንግግር ለሽ ብሎ በተኛ በጠላት ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈጽሞ ገዢ መሬቱን መቆጣጠር የሚያስችል ጉልተ ድል ነው። ረዳት ካፒቴን አበራ ያሰተማረው ምስክር ተግባሩ ይሄውን ነው።

ስለሆነም በተወሰን ደረጃ የእሱ ጉዳይ መልክ የያዙ ሁኔታዎች እንዳሉ ቢደመጡም በዚህ ዙሪያ አቅም ያላቸው ወገኖች ተግተው መሥራት ግን ይኖርባቸዋል። እርግጥ መረጃው እንደ ጠቆመው ፍሬ ነገሩ ትንፋሽን መሰብሰብ ያስችላል። ትንፋሹን በእርግጠኝነት እንዲቀጥል ለማድረግ ግን ጠንካራ ተከታታይነት ያለው ተግባር መሠራት አለበት።  ጊዜያዊ ነገር ጊዜያዊ ቋሚ ደግሞ ቋሚ ነው። ለቋሚ ዕውቅና በርትቶ መትጋት ያስፈልግ ይመስለኛል። ነገ ሌላ ቀን ነው። ሰው ይቀዬራል። ሁኔታም እንዲሁ። ቋሚ ከሆነ ግን መሬት ዬያዘ ይሆናል – እርግጠኝነትንም ያስውባል።

እግዚአብሄር ይመስገን ከሙያ አንፃር ዶር/ ሼክስፔር ፈይሳ ህይወታቸውን የሰጡበት ተግባር ከውነዋል። ጉዳዩ እትብታዊ ባለቤት ከሙያ አንጻር አለው። ይህም ቢሆን ጎን ለጎን እገዛው ፊርማ ማሰባሰቡ ወዘተ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ዘነፍ ያለች ነገር ቢፈጠር ጥቃቱ ብዙ ነገር ነው የሚያደቀው አምክንዮም እንዲሁ። ብዙ ተስፋን ነው የሚያራቁተው። ብዙ ነፍስ ነው ጥግ አልባ የሚሆነው። ስለሆነም እኔ እላለሁ ማሸነፍን በሁለት እግሩ ማቆም በእጅጉ ያስፈልግ ይመስለኛል። ሀገሩ ሲዊዝ ነውና።

በተረፈ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች የመወያያ መድረክ በቀጥታ ጉዳዩ ለሚመለከተው የሲዊዝ መንግሥታዊ አካል የጻፈው ደብዳቤ ከልብ የሚገባ ነው። አምላካችን የሰውን ልጅ ሲፈጥር እንዲያመሰግነው ብቻ ነው እንጂ ጌታችን መዳህኒታችን እዬሱስ ክርስቶስ ሁሉም ያለው የሁሉም ጌታ ልዑል ነው። የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች የመወያያ መድረክ በማህጸረ ስሙ ከረንት  ኃላፊነቱን ወስዶ እሳከሁን የሲዊዘርላንድ መንግሥት በረዳት አውሮፕላን አብራሪ አበራ ሀይለመድህን ጥያቄ ዙሪያ ለወሰዳቸው በጎ ምላሻዊ  ተግባራት እንዲሁም ቀጣይ እንክብካቤም ሁኔታውን ዘርዝሮ ምስጋና መጻፉ የላቀ ሥልጡን ተግባር ነው። ብልህነትም – መብልጥም፤ እንዲሁም ማስተዋልም ነው። ይህ በኸረ ተግባር ቀላል ሊመስል ይችል ይሆናል። እንደ እኔ በጥቂቱ ስሜቴ እንዲህ ነው ያዬው —-

  1. የጉዳዩ ባለቤትነትን አመሳጥሯል፤ አለሁ ባይነት ሲታደሉት ብቻ የሚገኝ ምርቃት – እናትነት!
  2. መስዋዕትንት ለመቅደም ፈቅዷል፤ በከፋ ቀን መገኘት – ማተበኝነት – ኪዳንም፤
  3. የጀግናውን ችግር ፈቅዶ በይፋ ተጋርቷል፤ አካላዊነትን በመሆን አቅልሟል።
  4. ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን አብራርቷል፤ የታሪካዊት ሀገርን የኢትዮጵያ ክብር ጠብቋል። አደራ አውጪነት!
  5. የመንፈስ ሥልጡን ህዝብ አምከንዮ በሚገባ ገልጧል፤ የራቀ የበለጠ አቅምን ማሳዬት ግልጽነት በብልህነት።
  6. የወገኖቹን ወላዊ የዕንባ አጋርነት ተስፋነትን አመሳክሯል፤ ብቻውን አለመሆኑን በቅኔ – ቃኝቷል።
  7. የጉዳዩ ተከታታይ ሂደትን – ወገኖቹ በንቃት መታደማቸውን  አሳምሮ ተርጉሟል፤
  8. ለነገን ቀና መንገድን ጠርጓል – ድልዳል አበጅቶለታል ለቀጣይ ፍላጎቱ — በትህትና።
  9. ለፈጣሪ አምላክም ተመችቷል። „ተመስገን!“ ማለት መምህር ነውና። „እናመሰግናለንም“ ትህትና በአክብሮት ነው።

http://ecadforum.com/2014/06/06/switzerland-thank-you-for-granted-resident-status-to-ethiopian-airlines-co-pilot/ ከረንት እኮ ከምሥረታው ጀምሮ እኔ ነኝ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ባለነሰ እጅግ የላቀውን  ትውልዳዊ ሃላፊነት የከወነ የመወያያ መድረክ ነው። ሀገራዊ ጉዳዮች መሬት ይዘው በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ –  መንፈስን በማደራጀት፤ ከግለሰብ ህይወት ጀምሮ እስከ ግዙፉ የፖለቲካ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ድረስ በመሆን ሸማ የከበረ ነው። መሬት የያዘ ጉልበታማ ሁለገብ  ክንውን ያበራ የመወያያ መድረክ ነው። የከረንት አንድ ሰው ባለበት ቦታ – አንድ እራሱ ግን እንደ አስር ነው። ከከረንት በፈለገው መልክና ሁኔታ አባልተኛው ቢለቅ እንኳን የከረንት ቤተኝነት ስሜትን ሆነ ንጹህ ፍቅር እኔ ነኝ ያለ ጀግና መፋቅ ከቶውንም አይችልም – ከረንት ባዕት ነው እንደዚህ ልበለው። እኔም የከረንት – ከረንትም የእኔ። እንደዚህ ባሉ ባለቤት ባጡ ጉዳዮች ደግሞ ከረንት እንዲህ የግንባር ሥጋ መሆኑ እጅግ ያስመሰግነዋል። የእኔም ብትሆኑ እግዚአብሄር ይባርካችሁ።

እርገት ይሁን — ልብ ያዘዘውን – ልብ የተለመውን – ልብ ያቀደውን – ልብ የቆረጠበትን – ልብ የወሰነለትን – ልብ የቆረበበትን የምልእተ ድምጽ ግፍ አድማጭ ሰው እራሱ ልብ ነው! አዎን! ጀግና አበራ ሀይለምድህን ልብም – የልብ -ልብም – ልባምም ነው። ሙያን በልብ የሞሸረ ጽናታዊ ዓዕማድ!

የኔዎቹ የፊታችን ሃሙስ በተለመደው ሰአት ከ15 እስከ 16 Radio Tsegaye  Aktuell Sendung www.tsegaye.ethio.info  አብረን ናፍቆትን እንታደም። ስለሆነም የቻላችሁ አዬር ላይ ያልቻላችሁ በማግስቱ ሲለጥፉት ከቻላችሁ አዳምጡ – በትህትና። በተረፈ ይህቺን ቀነ 17.06.2014 የጀግናን ፎቶ መንበር ላይ ማደረጉን አትዘንጉ እሺ! ሺዎችን ማፍራት የሚቻለው ከእጅ የገባን ድንቅ ማክበር ሲቻል ብቻ ነው …. ቸር ያሰማን –  ቸር እንሁን። አሜን!

 

ፈተናን ከመፈጠሩ በፊት አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጥር – ኢትዮጵያዊነት!

ልብ ያለው ጀግና የልቡን የሚያደርስልት እሱ እራሱ ብቻ ነው!

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>