አብርሃ ደስታ ከመቀሌ
በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ክልተ አውላዕሎ ወረዳ “አይናለም” የተባለ ጣብያ (ንኡስ ወረዳ) አለ። በዛ አከባቢ ያለው ደን “የመለስ ፓርክ” ተብሎ ተከልሏል። ኗሪዎቹ “የመለስ ፓርክ” መባሉ አልተዋጠላቸውም፤ ተቃውመውታል።
ባለፈው ወር ነው። “ከመለስ ፓርክ” የተወሰነ ዛፍ ይቆረጣል። በዚህ ጉዳይ የተቆጡ ካድሬዎች የአይናለም ኗሪዎችን ሰብስበው ዛፉ የቆረጠው ማን እንደሆነ ይጠይቃሉ። አውጫጭ መሆኑ ነው። ህዝቡ ላለመናገር አደመ። ህዝቡ ስላልተናገረ ለስምንት ተከታታይ ቀናት ታሰረ፤ ቅጣት መሆኑ ነው። ህዝቡ የታሰረው ፖሊስ ጣብያ አልነበረም፤ ፖሊስ ጣብያ አይበቃውማ። በብዙ ሺ የሚቆጠር ህዝብ (ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ እናቶች በቃ ሁሉም) በረኻ ላይ በፖሊሶች ተከቦ ታስሮ ይውላል። ዝናብ ይደበደባል፤ ፀሓይ ይመታል። ህዝቡ ግን ይህን ሁሉ ስቃይ ችሎ በቃሉ ፀና። ካድሬዎቹ ከስምንት ቀናት በኋላ ተስፋ ቆርጠው ተውት። ህዝቡ ግን ተቀይሟል።
ከተወሰነ ግዜ በኋላ የማዳበርያ ጉዳይ መጣ። መዳበርያ ዉሰዱ ተባሉ። አንወስድም አሉ፤ በአንድ ቃል። ህዝቡ ያቀረበው ምክንያት መዳበርያ ለመግዛት ገንዘቡም ፍላጎቱም የለንም የሚል ነው። ካድሬዎች ህዝቡን ለማስፈራራት ሞከሩ፣ አሰሩ፣ አዋረዱ። አልተሳካላቸውም። የካድሬዎች የመጨረሻ ሓሳብ ህዝቡ ለማዳበርያ የሚሆን ገንዘብ ከሌለው ከቤተክርስያን ታቦት እንዲበደር ጠየቁት። ህዝቡ አሻፈረኝ አለ። ከታቦት ተበድረን ማዳበርያ አንገዛም፣ ከእግዚአብሄር ቤት ተበድረን ለመንግስት አንሰጥም አሉ።
ካድሬዎችም ማዳበርያው በተሽከርካሪ ጭነው ጣብያው (ቀበሌው) ላይ አራገፉት። ህዝቡም የምንከፍለው ገንዘብ የለንም አለ። ካድሬዎቹ ደግሞ የአይናለም ህዝብ ታቦት የሚገኝበት “መድሃኔዓለም ቤተክርስትያን” ጋ በመሄድ ለማዳበርያው ዋጋ የሚሆን ገንዘብ ይወስዳሉ። የታቦቱ ቄሶች ዝርፍያ ተፈፅሞብናል በሚል ተግባሩን ይቃወማሉ። ቄሶቹ አርፈው እንዲቀመጡ ይነገራቸዋል። አሁን ለማዳበርያው የሚሆን ገንዘብ በቤተክርስትያኑ ተወስዷል። ህዝቡም ተቃውሟል። አሁን የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ህወሓትም እያስፈራራቸው ነው። ቤተክርስትያን ተዘርፏል ብለው ተቃውሞ ያሰሙ ቄሶች ግን ታስረው ይገኛሉ።
እንዲህ ነው ዝርፍያ። ህወሓት የዝርፍያ ባህሏን እስካሁን ድረስ አጠናክራ ቀጥላለች ማለት ነው።