(ነገረ ኢትዮጵያ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ሲሶነሴ ወረዳ አርሶ አደሮች በፖለቲካ አመለካከታቸው ልዩነት ምክንያት ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እየተከለከሉ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች አስታወቁ፡፡ መንግስት ለአርሶ አደሮች በህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ግብዓትና ግብይት በኩል የሚያቀርብ ሲሆን ይህም ማዳበሪያ የሚሸጠው የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ላይ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም አርሶ አደሮች የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት የማያገኙና ይህም ከአመለካከት ጋር በተያያዘ መሆኑን ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡
አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዳያገኙ ከተደረጉባቸው ምክንያቶች የመጀመሪያ ተብሎ የተቀመጠው ለመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን መዋጮ ያላዋጡት ሲሆን፣ በ1997 ምርጫ ተቃዋሚ የነበሩ እንዲሁም ገዥው ፓርቲ በአርሶ አደሩ ላይ ባደራጃቸው 1ለ5 አደረጃጀት ጥናት መሰረት ‹‹ተቃዋሚ ናቸው›› የተባሉ አቅርቦቱን እንዳያገኙ ተደርጓል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ህገ ወጥ የቤት ግንባታ በሚል የሚፈርሱ ቤቶች ከከተማ ወደ ገጠር እየተስፋፉ እንደሚገኙም ተገልጾአል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከገጠር ወደ ከተማ እንዲገቡ የታቀዱና የገቡ እንዳሉና አርሶ አደሮች የይዞታ መብታቸውን ሳይነጠቁ መሬታቸውን እየተቀሙ እንደሆነ ተጠቆሟል፡፡
ለምሳሌ ያህልም በደብረ ማርቆስ አካባቢ የእርሻ መሬት ይዞታቸው እንደተጠበቀ ነገር ግን ወደ ከተማ የተከለሉ፣ ወደ ፊት ሊገቡ የተከለሉ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቅሰዋል፡፡ በተመሳሳይ እናርጅናውጋ ውስጥ ወደ ከተማ እንዲገቡ ያልተወሰኑ የአርሶ አደሩ መሬቶች ላይ ቤት ሲገነባ ‹‹ህገ ወጥ›› እየተባለ ነው፡፡ በዚህም አርሶ አደሮቹ ለመሬታቸው ካሳ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ ምንጮች ጨምረው አመልክተዋል፡፡