ሚልዮኖች እንደመሆናችን በተለያዩ አቀራረቦች እና ስልቶች የሀገራችን ምሁራን ሊያንፁን ይገባል።ያደጉትን ሀገሮች ትተን የአፍሪካ ሃገራትን ለምሳሌ እንደ ዑጋንዳ ያሉ ሀገሮች በዋና ከተማቸው ብቻ ከሃምሳ በላይ ኤፌ ኤም ራድዮኖች አሉ።ሕዝብ እንደምርጫው ይሰማል እራሱን ያይበታል።መገናኛ ብዙሃኗ በአፈና መንግስት በታገተባት ሀገራችን ኢትዮጵያማ ምን ያህል እንደሚቀረን ከእዚህ መረዳት ይቻላል።ኢትዮጵያ ወጣቶቿ እየደረሱላት ነው።ሁለት አዳዲስ የራድዮ መርሃግብሮች ወደ መስመር ገብተዋል።የመገናኛ ብዙሃን በተለያየ አቀራረብ እና ፈጠራዎች በተለይ በዲያስያስፖራው እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ለሚሰማው የሃገርቤት ነዋሪ የራሳቸውን በጎ ተፅኖ መፍጠራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።እናም እናበረታታቸው።አይዟችሁ ምን እናግዝ? እንበላቸው።እኛ መናገር ቢያቅተን የሚናገሩልንን ሃሳብ የሚያመነጩትን ማበረታታት ተገቢ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ቀደም ብለው ለነበሩ ኢትዮጵያውያን የብሮድካስት ስርጭቶች ተጨማሪ እገዛ የሚያደርጉ ግን ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ አዳዲስ የራድዮ መርሃግብር ስርጭቶች ተጀምረዋል።
የመጀመርያው ”ዋዜማ” የተሰኘ ራድዮ ሲሆን ስለ ዋዜማ / About Wazema በሚለው አርዕስት ስር እንዲህ ይላል -
“ዋዜማ ሬዲዮ” በስደት ባሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ሳምንታዊ የፖድካስት ሬዲዮ ስርጭት ነው። ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ልንጨዋወት መክረናል። እግረመንገዳችንን ጎረቤቶቻችንን የሚመለከቱ ጉዳዮች ስናነሳ ብንገኝም የእንግዳ ተቀባይነት ወጋችን ሆኖብን ነው።
አዘጋጆቹ መስፍን ነጋሽ፣ ደረሰ ጌታቸው፣ አርጋው አሽኔ እና መዝቡ ኃይሉ ነን። ብቻችንን ግን አይደለም፣ አብረውን የሚጓዙ መደበኛ ተሳታፊዎችም ይኖሩናል።
ዝግጅቶቻችን አገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ እንድትችል የሚመኙ ናቸው። ዓላማችን ማንኛውም የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም ሌላ አይነት ቡድን የማይቆጣጠረው አንድ ተጨማሪ የውይይት መድርክ መፍጠር ነው።
ዋዜማ ሬዲዮ!
”ዋዜማ” ራድዮ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ማኅበራዊ እና ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችም ተካተውበታል።
ድረ-ገፁን ከእዚህ በታች ያለውን በመንካት ማዳመጥ ይችላሉ http://www.wazemaradio.com
ሁለተኛው በተለይ በኖርዌይ እና አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ ላይ የሚያተኩር ነገር ግን ለመላው ዓለም በኢንተርኔት የሚዳረሰው ‘‘የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ” በተሰኘ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሰሩ ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶች በተለያየ መንገድ የሚደግፍ ድርጅት የተጀመረ ነው።
በድረ-ገፁ ላይ ”የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ” እንዲህ የሚል አረፍተ ነገር አለ -
”ሰላም ጤና ይስጥልኝ መላው የስርጭታችን ታዳሚዎች ዛሬ ወረሃ ግንቦት 23ኛ ቀን ላይ እንገኛለን የዴሴሶን ራዲዮ የሙከራ ፐሮግራም ለመጀመሪያ ግዜ ለአድማጭ የሚደርስበት ቀን ነው ::ክብራትና ክቡራን ኢትዮጲያውያን ወገኖቻችን ለዘመናት ያጣነውን ስላምና እኩልነት ለማስመለስ የሚታገለው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የራዲዮ ስርጭቱን ለአየር ማዋል የቻልበት የመጀመሪያ ቀን ላይ በመድረሳችን በመላ ኖርዌይ ለሚገኙ አባላትና ለደጋፊዎቻችን የደስታ መልእክታችን ይደረሳችሁ::
ዝግጅቶቻችን ዘወትር ቅዳሜ ለአድማጭ ይደርሳል በቅርቡ ቆሚ ዝግጅቶቻችንን እናቀርብላችኋለን ይጠብቁን !!”
”የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ” ራድዮ ድረ-ገፅ http://www.dceson.no/news/2014/05/31/dceson-radio-opening-program-may-31-05/ ነው።
ከላይ የተጠቀሱት ራድዮኖች ለኢትዮጵያውያን በጎ መንገዶችን ማመላከት ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው ለነበሩ የብሮድካስት አገልግሎቶችም ሆነ በኢትዮጵያዊነት ዙርያ የተሻለ ለሚያልሙ ሁሉ አጋዥ፣መንገድ አመላካች፣እና አዳዲስ ሃሳቦች አመንጪ እንደሚሆኑ ይታሰባል።ይበርቱልን!
ጉዳያችን
ግንቦት 25/2006 ዓም (ጁን 02/2014)