የተስተካከለ የሰውነት አቋም ለመያዝ እና ሸንቀጥ ባለ ቁመና ለመታየት ከአመጋገብ በተጨማሪ የሰውነት እንቅስቃሴን ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ አሌ የሚባል ሀቅ አይደለም፡፡ ይህንን ስንል ለየትኛው ሰውነት ክፍል ምን አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል ማለት ነው፡፡
በተለይ ለሴቶች ሸንቀጥ ብሎ እና አምሮ መታየት ከዘመኑ ጋር እንደመራመድም ይቆጠራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ቦርጭን ለማጥፋት መሰራት ያለባቸው የሰውነት እንቅስቃሴዎች በተለያየ መንገድ ከፋፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡
ለሆድ ከሚሰሩ የስፖርት አይነቶች ውስጥ አንዱ ወለል ላይ በጀርባ በመተኛት እግርን በቀስታ ወደ ላይ በማንሳት እንዲሁም በቀስታ ወደ ነበረበት በመመለስ የሚሰራ የስፖርት አይነት ሲሆን ይህም ለታችኛው የሆዳችን ክፍል የሚሰራ ነው፡፡ ይህ የስፖርት አይነት የሆዳችን ጡንቻ ለረዥም ጊዜ ተሰብስቦ እንዲቆይ ይረዳናል፡፡
ሌላኛው የሆድ ስፖርት አይነት ‹ሳይክል› የምንለው ሲሆን ይህንንም ለመስራት በጀርባችን በወለል ላይ በመተኛት ከዚያም አንደኛውን እግራችንን ወደ ላይ በማንሳት ሌላኛውን እግራችን በማጠፍ እና ወደ ደረታችን በማስጠጋት እየቀያየርን የምንሰራው የስፖርት አይነት ነው፡፡ ይህንን ስፖርት ቢያንስ ለአስር ጊዜ ያህል ደጋግመን መስራት ይኖርብናል፡፡
ከላይ ከገለፅናቸው የስፖርት አይነቶች በተጨማሪ በእንግሊዝኛው (Set up) የሚባለው የስፖርት አይነት ሌላው የሆድ ስፖርት ሲሆን ይህንንም ለመስራት በመጀመሪያ በጀርባችን መሬት ላይ እንተኛለን፡፡ በመቀጠልም ከወገባችን በላይ ያለውን የሰውነታችንን ክፍል ቀና በማድረግ እና እግራችንን እንደዚሁ ቀና በማድረግ የምንሰራው ስፖርት ነው፡፡ ይህም በቀጥታ ለሆድ የሚሰራ ስፖርት በመሆኑ ለውጡን በአጭር ጊዜ ማወቅ እንችላለን፡፡
ከእነዚህ የስፖርት አይነቶች በተጨማሪ ለሆድ እንዲሁም ለእግር የሚሰሩትን የስፖርት አይነቶች እንጨምርላችሁ፡፡
ለዚህ ከሚረዱ የስፖርት አይነቶች ውስጥ አንዱ በጎን በመተኛት እና እግርን በማንሳት የሚሰራ ሲሆን ይህን ስፖርት ለመስራት በመጀመሪያ በጎናችን በመተኛት እንዲሁም ግራ እጃችንን አጥፈን በመንተራስ እና የቀኝ እጃችንን ደግሞ በመሬት ላይ በማሳረፍ የሚሰራ ነው፡፡ እግራችንን እኩል ማነባበር ይኖርብናል፡፡
በመቀጠልም ሌላውን ሰውነታችንን ክፍል ሳናንቀሳቅስ በቀስታ የቀኝ እግራችንን እስከምንችለው ከፍታ ድረስ በማንሳት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ባለበት አቆይተን በቀስታ መመለስ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው እና ለሆድ እንዲሁም ለእግር የሚሰራው የስፖርት አይነት በእንግሊዝኛው ክላምሼል የምንለው ሲሆን ይህ የስፖርት አይነት የሚሰራው እንደ መጀመሪያው የስፖርት አይነት በጎናችን በመተኛት ቀጥሎም ጉልበታችንን 45 ዲግሪ በማጠፍ ሲሆን የቀኝ እግራችንን የግራ እግራችን ላይ በማነባበር የሚሰራ ነው፡፡ በመቀጠልም የግራ እግራችንን ባለበት ሆኖ የቀኝ እግራችንን በቀስታ እስመክንችለው ከፍታ ድረስ ከፍ በማድረግ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ማቆየትና ወደ ቦታው በቀስታ በመመለስ የሚሰራ የስፖርት አይነት ነው፡፡ ይህንን በድጋሚ በቀኝ ጎናችን በመተኛት መድገም እንችላለን፡፡
ሶስተኛው የስፖርት አይነት ደግሞ ሂፕ ሬስ ወይም በዳሌ አካባቢ የሚሰራ ስፖርት ሲሆን ይህንንም ለመስራት በመጀመሪያ በወለል ላይ በጀርባችን በመተኛት በመቀጠልም ጉልበታችንን እኩል በማጠፍና በመዘርጋት የሚሰራ ስፖርት ነው፡፡
በመቀጠልም ከትከሻችን እስከ ጉልበታችን ድረስ ያለውን አካላችንን በቀስታ ከፍ በማድረግ ቀጥ ያለ መስመር በመስራት ለተወሰኑ ደቂቃዎች መቆየትና ቀስ ብለን ወደ ቦታችን በመመለስ ይህንኑ በተደጋጋሚ መስራት፡፡ በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው የሆድ ስፖርት አይነት ክሮስ ቦዲ ማውንቴን ክላይምበር (Cross body mountain climber) ሲሆን ይህንን ስፖርት ለመስራት በመጀመሪያ ሁለቱ እጆቻችንን መሬት ላይ በማሳረፍ ቀጥሎም እግራችንን ወደኋላ በመዘርጋት ቀጥ አድርገን ፑሽ አፕ በምንለው የስፖርት አይነት ሰውነታችንን በማዘጋጀት እጃችን ካለበት ሳይንቀሳቀስ የቀኝ ጉልበታችንን በማጠፍ ወደ ግራ ትከሻችን በማስጠጋት እንዲሁም የቀኝ እግራችንን ወደ ቦታው በመመለስ የግራ ጉልበታችንን በማጠፍ ወደ ቀኝ ትከሻችን ማስጠጋት ይኖርብናል፡፡ ይህንንም በተደጋጋሚ መስራት ይኖርብናል፡፡
ከላይ የዘረዘርናቸው የስፖርት አይነቶች በተደጋጋሚ እና በአንድ ጊዜ እየቀያየርን መስራት የምንችላቸው ስፖርት አይነቶች ሲሆኑ በአጭር ጊዜ ለውጥ ልናገኝባቸው እንችላለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቀለል ያሉ እና በየትኛውም ቦታ ልንሰራቸው የምንችላቸው ስፖርቶች ስለሆኑ በተከታታይ ሳናቋርጥ መከወን ይኖርብናል ሲል ውመንስ ሄልዝ የተባለው መፅሔት ያሳስባል፡፡