Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: ከኦልድ ትራፎርድ የሚሰናበቱ ተጨዋቾች (ግምታዊ የባለሙያ ትንታኔ)

$
0
0

ማንችስተር ዩናይትድ በአውሮፓም እጅ ሰጥቷል፡፡ በባየርን ሙኒክ ሲሰናበት ግን ሽንፈቱ የክብር እንጂ የውርደት አልነበረም፡፡ የዘንድሮውን የቡድናቸው ሁኔታ ጠንቅቀው የሚያውቁት የክለቡ ደጋፊዎችም አስቀድመው ከዚህ የላቀ ነገር አልተመኙም፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት እንግሊዝን ሊግ በአሳማኝ ብርታት ያሸነፈው ቡድን ዘንድሮ ብዙ ድክመቶችን እያሳየ ቆይቶ የውድድር ዘመኑን ሊያጠናቅቅ ተቃርቧል፡፡

man united
ዘንድሮ የሚፎካከርበት ምንም ዋንጫ ያልቀረለት ዩናይትድ አሁን ለከርሞው ለመዘጋጀት በቂ ዕድል ተፈጥሮለታል፡፡ የዝግጅቱ አንድ ስራ በክለቡ ሰፊ ለውጥ ማድረግ ነው፡፡ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በርካታ አዳዲስ ተጨዋቾች በቀዩ ማሊያ ሊታዩ እንደሚችሉ ሁሉ ከክለቡ ጋር በርካታ ስኬቶች ያገኙ ነባር ከዋክብትም ይሰናበታሉ፡፡ በ2014/15 የውድድር ዘመን በኦልድ ትራፎርድ አይታዩም ተብለው የሚታሰቡትን ተጨዋቾች እንደሚከተለው መቃኘት ይቻላል፡፡

የጀግኖቹ ስንብት

የሪዮ ፈርዲናንድ፣ ኒማኒያ ቪዲች እና ፓትሪስ-ኤቭራ የኋላ ክፍል ጥምረት ማንችስተር ዩናይትድን በእንግሊዝ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ለተከታታይ ዓመታት ውጤታማ አድርጓል፡፡ ቪዲች ክረምቱ ሲመጣ ኦልድ ትራፎርድን እንደሚለቅቅ አረጋግጧል፡፡ ኤቭራም የመሰናበቱ ነገር አይቀሬ ይመስላል፡፡ ፈርዲናንድ አካሉ እንደሚገባ አልታዘዝ ካለው ቆይቷል፡፡ ቀድሞ ከአውሮፓ ድንቅ ተከላካዮች አንዱ የነበረው ኮከብ አሁን ፈጽሞ ራሱን አይመስልም፡፡

እነዚህን ሶስት ተጨዋቾች መተካት ቀላል አይሆንም፡፡ ተከላካዮቹ እርስ በርስ ከነበራቸው ድንቅ ውህደት እና አስገራሚ የመከላከል ችሎታ በተጨማሪ በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ቡድናቸውን የመምራት አቅም ነበራቸው፡፡ በቀደሙት ዓመታት ዩናይትድ የኤድዊን ቫን ደር ሳርን አገልግሎት ከማጣቱ በፊት በጋራ የፈጠሩት እጅግ ጠንካራ የኋላ ክፍል አሁን በዕድሜ ተፅዕኖ ቦታውን የመልቀቂያ ጊዜ መጥቷል፡፡ ጊግስ የእነዚህን ተጨዋቾች ችሎታ የያዙ ፈራሚዎችን ብቻ ሳይሆን እነ ቪዲች ከቡድኑ የተከላካይ መስመር የሚያጎድሉትን የካበተ ልምድ የመተካት ከባድ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡

የመሀል አማካይ ክፍል

በማንችስተር ዩናይትድ ለዓመታት ተገቢውን ትኩረት ያላገኘው ክፍል ብለው የሚጠቅሱት አሉ፡፡በተለይ ከጃንዋሪ የሁዋን ማታ ከፍተኛ ዝውውር በፊት በክረምቱ ማርዋን ፌላይኒ ተገዝቶም የዩናይትድ የመሀከል ክፍል ደካማ ነበር፡፡ በእርግጥ የቤልጅየማዊው መምጣት የቡድኑን አማራጭ ጨመረ እንጂ የቡድኑን ጥራት ከፍ አላደረገውም፡፡ ማይክል ካሪክ የአምናውን ድንቅ ብቃቱን መልሶ ማግኘት አልቻለም፡፡ ሆኖም እንግሊዛዊው አሁንም ለቡድኑ በሚያበረክተው የሜዳ ላይ አስተዋፅኦ ከሌሎቹ አጣማሪዎቹ በእጅጉ የተሻለ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ካሪክ ለከርሞ ከቡድኑ ጋር አብረው እንደሚቆዩ ከሚታመንባቸው ተፈላጊ ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡

የዳረን ፍሌቸር እና ቶም ክሌቨርሊ ቆይታ አጠራጣሪ ቢሆንም ስኮትላንዳዊው ሙሉ ጤንነቱን መመለስ ከቻለ ማንቸስተር ዩናይትድን ለመርዳት በቂ ችሎታ እና ጠንካራ ልምድ አለው፡፡ በአንፃሩ ክሌቨርሊ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት የበዛ ትችት ያስተናገደ እና በደጋፊዎች ዘንድም ተቀባይነቱን ያጣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከእርሱ ድክመት የበለጠ ወጣቱ ዘንድሮ ለቡድኑ ውጤት ማጣት እንደ ሰበብ መነሳቱ እንደተጋነነ የሚያምኑ ትቂት አይደሉም፡፡ እንግሊዛዊው በኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲን ሲገጥሙ ትኩረት ከሳበ በኋላ ብቃቱ ሊሻሻል አልቻለም፡፡ ሌላኛው ቡድኑን መልቀቁ አይቀሬ የሚመስለው ተጨዋች ጫማውን ይሰቅላል ተብሎ የሚጠበቀው ሪያን ጊግስ ነው፡፡ በብሪታኒያ የትውልዱ እጅግ ስኬታማ ኮከብ የሚሰኘው ዌልሳዊ ዘንድሮ እንዳበቃለት የሜዳ ላይ ደካማ ብቃቱ አሳብቆበታል፡፡ ከዚህ በኋላ በተጨዋችነት ሳይሆን ምናልባት ለወደፊቱ በዩናይትድ የአሰልጣኞች መቀመጫ የመታየት ዕድል እንደሚኖረው ግምቶችን አግኝቷል፡፡

የአጥቂ አማካዮች /የክንፍ ተጫዋቾች/

ማንችስተር ዩናይትድ በመሀል ሜዳ ያሉት የተጨዋቾች እጥረት በሌሎች ቦታዎች አይንፀባረቅም፡፡ ቡድኑ በተቀሩት ሚናዎች ጥሩ አማራጮች ነበሩት፡፡ ሳይጠበቅ አስደናቂ የውድድር ዘመን ያሳለፈው አድናን ያኑዛይ በምርጥ ብቃቱ ራሱን እና ቡድኑን ብቻ ሳይሆን ጫና ውስጥ የቆዩትን ሞዬስም ጠቅሟል፡፡ እንዲያውም በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ወራት ወጣቱ የቡድኑ እውነተኛ አደጋ ፈጣሪ እና ብቸኛ በጎ ነገር መስሎ ነበር፡፡

የሁዋን ማታ ዝውውር ድንቅ ግዢ ነበር፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ማንቸስተር ዩናይትድ ከተቀናቃኙ ቼልሲ ያመጣው ስፔናዊ በቶሎ ውጤታማ ብቃት ለማሳየት የተቸገረ ቢመስልም ቀስ በቀስ ከቡድኑ ጋር መዋሃዱን በተግባር ማሳየት ጀምሯል፡፡ ዌይን ሩኒም በ10 ቁጥር ሚና ማጫወት የሚችለው ቡድ በዚህ ቦታ ብዙ አማራጮች አሉት፡፡ በኦልድ ትራፎርድ የአቅሙን እንዲጫወት እድሉ ያልተሰጠው እና በማይመቸው ቦታ እንዲጫወት እየተደረገ የቆየው ሺንጂ ካጋዋ ሌላኛው የቦታው ድንቅ አማራጭ ነው፡፡ ዩናይትድ ምናልባት በሁኔታዎች ተገድዶ ባለተሰጥኦውን ጃፓናዊ በክረምቱ ሊለቀው እንደሚችል መገመት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከሩኒ እና ሮቢን ቫን ፔርሲ ጉዳት በኋላ እስያዊው ከማታ ጋር ያሳየው ድንቅ መግባባት ምናልባት ለመቆየቱ ሰበብ ሊሆን ይችላል፡፡

የክንፍ ተጨዋቾቹ ጉዳይ ግራ አጋቢ ነው፡፡ በማንቸስተር ዩናይትድ በቁጥር ጥቂት የማይባሉ የመስመር ተጨዋቾች ቢኖሩም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጤታማ መሆን ከብዷቸዋል፡፡ በተፈጥሯዊው የክንፍ ሚና ድንቅ ችሎታ ያላቸው አንቶኒዮ ቫሌንሲያ፣ ሉዊስ ናኒ እና አሽሊ ያንግ የሚችሉትን እንኳን ለመስራት የተቸገሩበት እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ የሶስቱም ብቃት ለረጅም ጊዜ ወርዶ የመቅረቱ ሰበብ ብዙ ግልፅ አይደለም፡፡ በተለይ ያንግ ወደ ክለቡ ከመጣ ጀምሮ ይህን ነው የሚባል ያልዋዠቀ ብቃት ማሳየት አልቻለም፡፡ የዩናይትድ ደጋፊዎች ከልባቸው ስንብታቸውን በጉጉት ከሚጠብቁባቸው ተጨዋቾች ቀዳሚው ያንግ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ካስቆጠራቸው ጎሎች እና ለጎል ካቀበላቸው ኳሶች ይልቅ ስሙ በይበልጥ ሳይነካ አስመስሎ ከመውደቅ ጋር በተደጋጋሚ መነሳቱም ለክለቡ አፍቃሪዎች ጥሩ ስሜት አልፈጠረም፡፡

ናኒ እና ቫሌንሲያ ቀደም ባሉት ዓመታት ከያንግ በተሻለ ቡድናቸውን ቢጠቅሙም የሚገባቸውን አገልግሎት ሰጥተዋል የሚባሉ አይደሉም፡፡ የፖርቹጋላዊው የኦልድ ትራፎርድ ህይወት ብዙ ተስፋ ተደርጎበት ኖሮ አሁን ወደ ተስፋ አስቆራጭነቱ ቀርቧል፡፡ በክረምቱ ናኒ ከተሰናባቾቹ መካከል ቢገኝ የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ እንደ ናኒ ሁሉ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ሊተካ ይችላል ተብሎ መጠነኛ ግምት አግኝቶ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ብዙ ዕድል የተሰጠው ኢኳዶራዊው ከተፈጥሯዊ የክንፍ ሚናው ይልቅ ፉልባክ ሆኖ መጫወት ወይም ይበልጥ አፈግፍጎ የመስመር ተከላካይን የሚያግዝ አይነት ተጨዋች ሆኗል፡፡

አጥቂዎች
Danny-Welbeck-2011-manchester-united-218x300
ጊግስ የተጫዋች እጥረት ሳይኖርበት ብዙ የተቸገረበት የቡድኑ ክፍል ነው፡፡ ሩኒ እና ቫን ፔርሲ በግላቸው ድንቅ አጥቂዎች ቢሆኑም እርስ በርስ ሲጣመሩ ግን ውጤታማነት ሳይጎላቸው ለቡድኑ የመጨረሻ አቅማቸውን እንዳይጠቀሙ የሚያግዳቸው እንከን አላጡም፡፡ የሁለቱ በጋራ መጫወት በከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ የተገዛውን ማታ ወደ ክንፍ ይገፋል፡፡ ብሎም ቡድኑ ከስፔናዊው ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም እያጣ ነው፡፡ ምናልባት ዩናይትድ እጅግ ፈታኙን እና ከባዱን ውሳኔ የሚያስተላልፍ ከሆነ እርምጃው የሚጀምረው በዚህ ቦታ እንደሚሆን መናገር ይቻላል፡፡ ኮንትራቱን በቅርቡ ካራዘመው እና በቀጣይ ክለቡን ለዓመታት የማገልገል አቅም ከያዘው ሩኒ ይልቅ ቫን ፔርሲ በክረምቱ ድንገት ሊሰናበት ይችላል፡፡

ዳኒ ዌልቤክ እና ሀቪዬር ሄርናንዴዝ የቋሚ ተሰላፊነትን ዕድል ለማግኘት ብዙ ቢመኝም እስካሁን ብዙ ጨዋታዎችን እያደረጉ ያሉት ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ነው፡፡ ዌልቤክ እንደ አስፈላጊነቱ ከክንፍ እየተነሳ ማጥቃት ቢችልም ቺቻሪቶ እንደ ጎል ጨራሽነቱ ከፊት መስመር ሌላ ሚና መውሰድ አይችልም፡፡ ማክሲኳዊው በኦልድ ትራፎድ በዋና ቡድኑ ድንቅ ብቃት ማሳየት የጀመረው የዛሬ ሶስት ዓመታት ቢሆንም እስካሁን ቋሚ ተሰላፊ አይደለም፡፡ እንዲያውም በሞዬስ ስር የሚሳተፍባቸው ጨዋታዎች ብዛት ቀንሶበት ነበር፡፡

ሄርናንዴዝ የትኛውም ክለብ በቡድኑ ሊኖረው የሚመኘው አይነት ተጨዋች ነው፡፡ ከሜዳ ላይ ብቃቱ ሌላ ሁልጊዜም ፊቱ ላይ ፈገግታ አለመታጣቱ ጥሩ የመልበሻ ክፍል ሰው ያደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በወሳኝ ዕድሜው ላይ የሚገኘው አጥቂ የተሻለ የመጫወት ዕድል ለማግኘት ወደ ውጪ ቢመለከት አያስደንቅም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>