በጣልያን የክለብ ባለቤቶች ለበርካታ ዓመታት የሚፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ ከወለሉ በታች ሲሸሽጉ ከርመዋል፡፡ ኪሳራው በሚፈርሙ ውድ ተጨዋቾች እና ለይምሰል በሚታየው ሀብት ተጋርዷል፡፡ ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ሊጉ እየተጎዳ እና እየጠወለገ ሲሄድ በቀላሉ እንዳይታወቅ ያደረገውም ይኸው ሃቅ ነው፡፡ በ1990 ጀርመን በጣሊያን የተዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ አሸነፈች፡፡ ከቡድኑ አባላት መካከል ደግሞ ዘጠኙ የሚጫወቱት በጣሊያን ነበር፡፡ በብዙሃኑ ይታወቁ ከነበሩት መካከል የርገን ክሊንስማን፣ ሎተር ማታየስ እና ቶማስ ሃስለር ይጠቀሳሉ፡፡ በእግርኳስ ዓለም ምርጡ ስፍራ ሴሪአው ነበር፡፡ የጣሊያን ክለቦችም ለቡድናቸው የሚመለምሉት ከደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ የተገኙ በጣም ምርጥ ተጨዋቾችን ብቻ ነበር፡፡ ዲያጎ ማራዶና፣ ካሬካ፣ ዚኮ፣ ሚሼል ፕላቲኒ፣ ማርኮ ቫንባስተን እና ሩድ ጉሊትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚያን ወቅት የጁቬንቱስ፣ ናፖሊ፣ ኤሲ ሚላን እናኢንተር ሚላን ተጨዋቾች ስም ዝርዝር ሲጠራ ሃሳባዊ የዓለም ምርጥ 11 ይመስላል፡፡ በዚያ ወርቃማ የእግርኳስ ዘመን የሀገሪቱ ነዋሪ በሙሉ የእግርኳስ ደጋፊ ይመስል ነበር፡፡ ስታዲየሞችም ቡድናቸው ሲያሸንፍ መመልከት በለመዱ ደጋፊዎች ጢም ብለው ይሞሉ ነበር፡፡ ጣልያን የእግርኳስ ገነት ነበረች፡፡ ሴሪአውም የዓለማችን ምርጡ ሊግ የሚል ስያሜ አግኝቶ ነበር፡፡
የከዋክብት ፍልሰት
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ እውነታው የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጣሊያን ክለቦች ከሚጫወቱ የውጭ ሀገር ተጨዋቾች መካከል ካርሎስ ቴቬዝ እና ፈርናንዶ ሎሬንቴ ላቅ ያለ ዝና አላቸው፡፡ አንዳቸውም ግን በመጪው ክረምት በሚደረገው የዓለም ዋንጫ ሀገራቸውን ወክለው ስለመጫወታቸው በእርግጠኝነት መናገር አይችሉም፡፡ አሁን አሁን ኮከብ ተጨዋቾች በሴሪ አው አይማረኩም፡፡ በዚያ እየተጫወቱ ያሉትም ለመልቀቅ ፅኑ ፍላጎት አላቸው፡፡
ከኤሲ ሚላን ጋር ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት ያለው ካካ ሪያል ማድሪድን ለቅቆ ሚላንን ዳግመኛ ለመቀላቀል በዓመት ያገኘው ከነበረው 10 ሚሊዮን ዩሮ ከፍተኛ ቅነሳ አድርጎ በዓመት 4 ሚሊዮን ዩሮ ብቻ እየተከፈለው ለመጫወት ተስማምቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ደመወዙ አሁንም ዳግም ቅነሳ ሊደረግበት የመሆኑ ነገር አልተዋጠለትም፡፡ በቅርቡ ወደ ፍሎሪዳ ማምራቱ አይቀሬ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡
ከ1994 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ውስጥ ለአውሮፓ እግርኳስ ማህበረሰብ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻሉ የጣሊያን ክለቦች 17 ናቸው፡፡ በአንፃሩ ግን ከ2004 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ሩብ ፍፃሜውን መቀላቀል የቻሉት አምስት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም የጣሊያን እግርኳስ ምን ያህል እንደተቀዛቀዘ አመላካች ነው፡፡ ‹‹በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ያለው የእግርኳስ ፍጥነት በጣሊያን ጨዋታው ከሚካሄድበት ፍጥነት የተለየ ነው›› በማለት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቼዛሬ ፕራንዴሊ በቅርቡ ሲማርሩም ተደምጧል፡፡ በርካታ ታዛቢዎች በሀገሪቷ የሚከናወኑ የእግርኳስ ጨዋታዎችን ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት በጨዋታ ዕለት ደጋፊዎች ምን እንደሚውጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ጨዋታዎች የሚደረጉት አብዛኛዎቹ መቀመጫዎች ሰው አልባ በሆኑ ስታዲየሞች ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሚላን ደር አሊያም ጁቬንቱስ ከኤሲ ሚላን ባደረጉት ጨዋታ እንኳን ትኬቶች ሙሉ በሙሉ አልተሸጡም፡፡ በእነዚህ ዓመታት ጁቬንቱስ ከኤሲ ሚላን ያደረጉትን ጨዋታ በአማካይ 44 ሺ ተመልካቾች ተመልክቶታል፡፡ የቦሩሲያ ዶርትሙንድን ጨዋታ የሚከታተሉ ተመልካቾች ቁጥር ግን የዚህን እጥፍ ይሆናል፡፡
ኢንቨስተሮች በጥብቅ ይፈለጋሉ
በአንድ ወቅት በእግርኳስ አብዳ በነበረችው ሀገር የክለብ ባለቤቶች እያደር ነጭናጮች ሆነዋል፡፡ በከፍተኛ ዕዳ ተዘፍቀው እና ተበሳጭተው ምንም አይነት የተለያዩ የዕድገት ስትራቴጂ ሳይዙ እንዳው በደመነፍስ ከአንዱ ስምምነት ወደ ሌላው ለዓመታት ሲቅበዘበዙ ከርመዋል፡፡ እያንዳንዱ የውድድር ዘመን ባለፈ ቁጥርም እራሳቸው በፈጠሩት ችግር ይሰቃያሉ፡፡ አሁን አሁን ግን ቡድናቸው በችግር ውስጥ ሲሆን ዝምታን መምረጥ ትተዋል፡፡ እንዳውም ያለምንም ፍርሃት ክለቡን መግዛት የሚፈልግ ካለ ቡድኑ ለሽያጭ እንደሚቀርብ ይናገራሉ፡፡ አሊያም ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን ሸሪክ ሊሆን የሚችል የፈረጠመ የፋይናንስ አቅም ያለው ወገን ያፈላልጋሉ፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ኤንሪኮ ፕሬዚዩሲ ‹‹ጄኖዋን ለመግዛት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሊያነጋግረኝ ይችላል›› ሲሉ ከ1 ሚሊዮን ዩሮ ባነሰ ገንዘብ የግላቸው ስላደረጉት ክለብ ተናግረዋል፡፡ ማሲሞ ቼሊኖ በበኩላቸው የሰርዲኒያውን ክለብ ካግሊያሪ ካልቺዮ ለአንድ ሼክ አሳልፈው ለመሸጥ ተነሳስተው ነበር፡፡ ፍላጎታቸው አሁን ተቀዛቅል፡፡ ነገር ግን በአንድ ወቅት የሚዲያዎች ትኩስ ወሬ የነበረ እና አሁንም ድረስ በደጋፊዎች አዕምሮ ውስጥ የሚመላለስ ነው፡፡ የኢንተር ሚላኑ ፕሬዝዳንት ማሲሞ ሞራቲም ቢሆኑ ከ2011 ጀምሮ ገዢ ሲያፈላልጉ ነበር፡፡ በለስ ቀንቷቸውም ባለፈው ዓመት በክለቡ ከነበራቸው ድርሻ 75 በመቶ ያህሉን ኢሪክ ቶሂር ለተባሉ ኢንዶኔዢያዊ ባለሀብት በ250 ሚሊዮን ዩሮ ሸጠዋል፡፡ ሞራቲ በፕሬዝዳንትነት ባለፉባቸው 18 ዓመታት የተቆለለውን የክለቡን ዕዳ በሂሳብ መዝገብ ላይ ለማስተካከል በማሰብ እየተመናመነ ከመጣው የቤተሰባቸው ሀብት ከ1.2 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ በማድረግ ክለቡ ላይ አፍስሰዋል፡፡ አሁን ደግሞ የክለብ ባለቤቶች ቁንጮ የሆኑት የኤሲሚላኑ ሲልሲዮ ቤርሎስኮኒ ክለቡን ለመልቀቅ እየተዘጋጁ ነው፡፡
‹‹በየዓመቱ 50 ሚሊዮን ዩሮ ከሚላን ጋር እከሰራለሁ ሲሉም ከጥቂት ቀናት በፊት ለጋዜታ ዴሎ ስፖርት ተናግረዋል፡፡ ቤርሎስኮኒ በታክስ ማጭበርበር እና ሌሎች ጥሰቶች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ወደ 100 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ እንዲከፍሉ ተበይኖባቸዋል፡፡ ሞንዳደሪ ፐብሊሺንግ ግሩፕ የተባለው ድርጅታቸውም ለከፍተኛ ኪሳራ ተጋልጧል፡፡ ለቀድሞዋ ባለቤታቸው ቬሮኒካ ላሪዬም በቀን ወደ 50 ሺ ዩሮ ተቆራጭ እንዲያደርጉም ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡
በ1986 ቤርሎስኮኒ ኤሲ ሚላንን ሲረከቡ እንዲህ አይነቱ ጥብቅ ቁጥጥር አልነበረም፡፡ እርሳቸው እና ጓደኛቸው እንደዚሁም የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አድሪያኖ ጋሊያኒ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በክለቡ ላይ አፈሰሱ፡፡ በጄናሮ ጋቱሶ፣ አንድሪያ ፒርሎ፣ ካካ፣ ፓውሎ ማልዲኒ፣ አሌሳንድሮ ኔስታታ ሊዮናርዶ፣ ፊሊፖ ኢንዛጊ እና ክላረንስ ሲዶርፍ የተዋወቀር ቡድን በቤርሉስኮኒ ድጋፍ ጎመራ፡፡ የ77 ዓመቱ አዛውንት አሁን ላይ ሆነው በኃላፊነት ዘመናቸው በግትርነት ሊቀበሏቸው ያልፈለጓቸውን ሀሳቦች መለስ ብለው ማስታወሳቸው የማይቀር ነው፡፡ ለክለቡ የራሱ የሆነ ስታዲየም አለማስገንባታቸው፣ የራሳቸውን ትሩፋት ሳያኖሩ ማለፋቸው እና የታዳጊዎችን አካዳሚ በተገቢው መጠን አለመደገፋቸው ሳይፀፅታቸው የሚቀር አይመስልም፡፡
ሴሪ አው መሸጋሪያ ብቻ ነውን?
ከአባቷ ኃላፊነቱን የምትረከብ ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት እንከኖች ለባርባራ ቤርሎስኮኒ ህይወትን አስቸጋሪ ያደርግበታል፡፡ ኤሲ ሚላን ስኳዱን ለማጠናከር በቀላሉ ቼክ መፃፍ እንደማይችል ታውቃለች፡፡ ታዳጊዎችን በማጎልበትም ቢሆን ፍሬያማ ለመሆን ጊዜ እንደሚጠይቅ ትገነዘባለች፡፡ ቢያንስ ለሶስት ዓመታት ከወጣት ማዕከሉ የሚወጡ ተጨዋቾች በዋናው ቡድን ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንደማይችሉም ግንዛቤው አላት፡፡ ይህም ሚላን ከማሪዮ ባሎቴሊ በስተቀር በክለቡ ያደገ ተጨዋች በሌለበት በማንሰራራት ላይ ያለውን ጁቬንቱስ እንዲከተል ያስገድደዋል፡፡
መልካሙ ነገር ሚላን ወጪውን ከገቢው ለማስተካከል ሙከራ ያደርግ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት በተጫዋቾች ዝውውር ሂደት ያስመዘገበው 16 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራ በንፅፅር ትንሽ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ለንፅፅር ባርሴሎናን ማቅረብ እንችላለን፡፡ የካታላኑ ክለብ ባለፉት 10 ዓመታት ለተጫዋቾች ዝውውር ከ300 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ተጨዋቾችን ሸጦ ካገኘው ገንዘብ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ‹‹ከስፔን አልያም ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ሲነፃፀር የጣሊያን ክለቦች ያለባቸው ዕዳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ መልካም ነገር ነው›› ሲል የቀድሞው የኤሲሚላን አማካይ እና የጣሊያን እግርኳስ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዴሜትሪዮ አልበርቲኒ ተናግሯል፡፡ ‹‹ምን መሆን እንደምንፈልግ መወሰን አለብን፡፡ ለሌሎች ሊጎች ተሰጥኦን አጎልብተን የምናበረክት ወይስ ራሳችን የትልቅ ሊግ ባለቤት መሆን የምንችል?›› ሲልም ሀሳቡን በግልፅ ያስቀምጣል፡፡
የለውጥ አየር እየነፈሰ ነው
እንደ ቤርሎስኮኒ ሁሉ ከ1986 ጀምሮ በእግር ኳሱ ኢንዱስትሪ ውስጥ የነበሩት የዩዲኔዜ ባለቤት ጂያንፓውሎ ፓዞ የኢኮኖሚው ቀውስ እንዳለ ሆኖ ትርፍ የሚያገኙበትን መንገድ አግኝተውታል፡፡ ክለባቸው ታዳጊ ተጨዋቾችን ከውጪ በማምጣት አጎልብቶ በከፍተኛ ትርፍ አሳልፎ ይሸጣቸዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ፓዞ የስፔኑን ግራናዳ እና የእንግሊዙን ዋትፎርድ እግርኳስ ክለብንም የግላቸው አድርገዋል፡፡ የፋይናንሱ ሁኔታ ጥሩ ባልሆነበት በዚህን ወቅት ትርፍ ማስመዝገብ የቻለው ሌላኛው ክለብ ጁቬንቱስ ነው፡፡ ለዚህም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የራሱ ስታዲየም ባለቤት መሆኑ ነው፡፡ በመላው ሀገሪቱ በአቅራቢያው ባለ የመንግስት መስተዳድር ያልተያዘ ብቸኛው ስታዲየም ነው፡፡ የዋና ከተማዋ ክለብ ሮማም ተመሳሳይ የሆነ ገድል ለመፈፀም ተነሳስቷል፡፡ በዚህ ዓመት የአዲሱን ስታዲየም ግንባታ ይጀምራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በ2016/17 የውድድር ዘመን አገልግሎት መስጠት ይጀምራል የሚል ግምት አለ፡፡ በጣልያን የሚገኙ የክለብ ባለቤቶች ወዴት ማምራት እንደሚፈልጉ ሀሳቡ ያላቸው ይመስላል፡፡ በሚሊዮኖች የሚከፈላቸው ከዋክብት ዘመን አልፏል፡፡ በመጪው ዘመን የዜና ርዕስ የሚሆኑት የእግርኳሱን ዓለም ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው በክለቦቻቸው ያደጉ ወጣቶች ናቸው፡፡