Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ከድጡ ወደማጡ በትንሣኤው ዕለት – (የግል አስተያየት)

$
0
0

ስንታየሁ በልሁ ከሚኒሶታ (የግል አስተያየት)

የዘንድሮ አባት ለልጁ ምን እንደሚያስተምረው ሳይ የዘመኑ መጨረሻ መቃረቡን ይነግረኛል። ሁላችሁም እንደሰማችሁት ባለፈው ሳምንት የሆሳዕና እለት በገለልተኛነት ከ20 ዓመት በላይ ተከብሮ የነበረው ቤተክርስቲያናችንን በዲያስፖራው ወያኔ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመከፋፈል ለሚጠቀምበት ሴራ ተባባሪ የሆንሙ አባቶች “የአቡነ ማቴዎስን ስም በቅዳሴ ላይ ካልጠራን አንቀድስም” በሚል ጥለው መሄዳቸው መዘገቡ ይታወሳል። በዕለተ ሆሳህና፤ በሰሙነ ህማማት መቀበያ አባቶች ላለፉት ዓመታት በገለልተኛነት ያገለገሉበትን ቤ/ክ ረግጠው መውጣታቸው እጅጉን የሚያሳዝን፤ እውነት እነዚህ ካህናት የቆሙት ለእግዚአብሔር ቃል ነው ወይስ?… በሚል በስተጀርባቸውን የሚያስጠረጥር ነው።

አቡነ ዘካሪያስ

አቡነ ዘካሪያስ


ይባስ ብሎም በትንሣኤ ዋዜማ የሚደረገውን ቅዳሴ አንቀድስም በሚል የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች አዳራሽ ተከራይተው ምእመናኑን ለመከፋፈል ሲሞክሩ ሳይ ወያኔ ትዝ አለኝ። ወያኔ በሃገር ቤት አንድ የሆኑትን ሁሉ በመበታተን ተለጣፊ ሲያበጅላቸው አይተናል። ዛሬ ሚኒሶታም እየሆነ ያለው ይህ መሆኑን ሳስብ አዘንኩ። በወያኔ ስር የሰደደ ፖለቲካ እንዲህ መሆናቸንም አሳዘኝና አንዳንድ ጥያቄዎችንም እንዳነሳ ተገደድኩ።

ዛሬ የደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ካህናትን አውግዣለሁ በሚል የተናገሩት አቡነ ዘካሪያስ ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን በረት ነው ሲሉ መናገራቸው ይነገራል። በረት ያሉትን ቤተክርስቲያን ጉዳይ በፍርድ ቤት ተይዞ ሳለ፤ ፍርድ ቤቱም ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ሕዝብ ሃገር ቤት ካለው ሲኖዶስ ጋር ይቀላቀል ወይም ገለልተኛነቱ ይቀጥል ብሎ ይወስን ባለበት ወቅት፣ የተከበረውን የአሜሪካ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳያከብሩ የውግዘት ደብዳቤ መጻፋቸው አንደኛው የአሜሪካንን ሕግ አለማክበር፤ ሁለተኛው ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት አለማሟላት ነው።

እኔ በሰላም አምናለሁ። የብዙሃን ድምጽ ያሸንፍ በሚለውም አምናለሁ። ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ህዝብ የሚፈልገውን እንዲወስን ማድረግ ሲችል ካህናቱ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉትን ሕዝብ በትንሣኤ ሰሞን ጥለው መሄዳቸው እና በአዳራሽ የትንሳኤ ቅዳሴ ማድረጋቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

1ኛ. ለመሆኑ ታቦቱን ከየት አምጥተው ነው የትንሣኤ ቅዳሴ በአዳራሽ የሚያደርጉት? ይህ የቤተክርስቲያን ስርዓት ነው ወይ?

2ኛ. ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ገለልተኛ መሆኑና በሃገር ቤቱ ሲኖዶስ ስር ያልሆነ ቤተክርስቲያን ሆኖ ሳለ አቡነ ዘካሪያስ እነ ዲያቆን ቶማስን፣ ቀሲስ አሰፋ፣ መልዓከ ኃይል ጌታሁን ለዲያቆን ሰረገላና ሌሎችም ያውም በሰሞነ ህማማት ድንጋይ ሳይቀር ወደ ጌታን በሚማጸንበት ወቅት “ፈርማችሁ ወያኔ ሁኑ” በሚል መንፈስ ባለው ደብዳቤ የማውገዝ ስልጣን ማን ሰጣቸው? ገና ባልተወሰነ ጉዳይ ይህን ማድረጋቸው በሕግ አያስጠይቃቸውም ወይ?

3ኛ. በአዳራሽ ይደረጋል በተባለው ቅዳሴ ለስርዓተ ቅዳሴ የሚያስፈልጉ እቃዎች ከደብረሰላም ቤ/ክ ከተወሰዱ ጉዳዩ የቤተክርስቲያንን ንብረት በመዝረፍ ወንጀል አያስጠይቅም ወይ?

4ኛ. ፍትሃ ነገስት ካህናት ይወገዙ የሚለው ሃይማኖታቸውን ሲቀይሩ ነው። ዛሬ አቡነ ዘካሪያስ እነዚህን ውድ የኢትዮጵያ ልጆችና ከሕዝብና ከእግዚአብሄር ጋር የቆሙትን አገልጋዮች ዲያቆን ቶማስን፣ ቀሲስ አሰፋ፣ መልዓከ ኃይል ጌታሁን ለዲያቆን ሰረገላና ሌሎችም አውግዣለሁ ሲሉ ከምን ተነስተው ነው? በየትኛው ፍትሃ ነገስት ላይ በተጻፈ ነገር የሚያወግዙት። እንደኔ መወገዝ ያለበት ቤተክርስቲያኒቱን ጥሎ፤ ልጆቹን በትንሣኤ ምድር ጥሎ የሄደው ነው።

5ኛ. ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ ስንት ጳጳሳት ህልም ያዩበት፣ የባረኩት፣ ብዙ የሃይማኖት ልጆች ያደጉበት ቤተክርስቲያን ሆኖ ሳለ አቡነ ዘካሪያስ በአባቶች ያልተባረከ በረት ነው ሲሉ ወቅሰውታል። ዛሬ ታዲያ እነ አባ ሃይለሚካኤል ባልተባረከና ታቦት በሌላው አዳራሽ ውስጥ ቅዳሴ ሲጠሩ ይፈቀዳል?

6ኛ. አንባቢው የአቡነ ማርቆስን ተለያዩ ንግግር እንዴት ይመለከተዋል። አባት ስለመለያየት ነው እንዴ የሚሰብከው?

እንደኔ ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያናችን ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ ሲሆን፤ እነ አባ ሃይለሚካኤል እስካሁን በገለልተኛነት ያገለገሉበትን ቤ/ክ ጠቅላላ ጉባኤ እስኪጠራ ድረስ ምእመናኑን አንድ አድርገው ማስተማር ሲችሉ፤ በትንሣኤ በዓል መባረክ ሲችሉ ለመበተን መሮጣቸው ቢያሳዝነኝም ጠቅላላ ጉባኤው ምላሽ ይሰጣል።

እግዚአብሔር ሰላሙን ያምጣልን! ከጎናችን የቆሙት አባቶቻችን ዲያቆን ቶማስን፣ ቀሲስ አሰፋ፣ መልዓከ ኃይል ጌታሁን ለዲያቆን ሰረገላና ሌሎችም እግዚአብሔር ረዥም የአገልግሎት ዘመን ያድርግላቸው፤ የወያኔ የፖለቲካ ሴራ ያልተገለጠላቸው ሌሎች ወንድም እና እህቶቻችንም እግዚአብሔር በዕለተ ትንሣኤው ልቦናቸውን እንዲገልጽ እጸልያለው።

መልካም ዓመት በዓል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>