(ዘ-ሐበሻ) የአንበጣ መንጋ በሶማሊያ፣ በኦሮሚያና በድሬደዋ ባሉ 13 ወረዳዎች ስጋት ሆኗል ሲል የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር በመንግስታዊ ሚዲያዎች በኩል አስታወቀ። እንደ መግለጫው ከሆነ የአንበጣው መንጋ በቅድሚያ የታየው በሶማሊያ ክልል ቶጎ ጫሌ አካባቢ ቢሆንም ወደ ሌሎች ክልሎችም እየተዛመተ መጥቷል።
የአንበጣ መንጋው ከሶማሊላንድ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በድሬደዋ አስተዳደር ባሉ ወረዳዎች 14 የሚሆኑ የአንበሳ መንጋዎች መግባታቸውን አረጋግጫለሁ ሲል የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤትቱ “የአንበጣ መንጋውን 95 በመቶ መከላከል ችያለሁ፤ በሰብል ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰም” ቢልም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን መንግስት አፋጣኝ እርምጃ አልወሰደም በሚል ይወቅሳሉ። የአንበጣ መንጋው ወደ ሌሎች ከተሞች እንዳይዛመትም ከፍተኛ ስጋት አለ ተብሏል።