ዜጠኛ ሓገዞም መኮነን (ወይን ጋዜጣ)
======================
የቀድሞ የወይን ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሓገዞም መኮነን ለሁለት ሳምንታት ያህል ደብዛው ካጠፋ በኋላ (ትናንት ደብዛው ስለመጥፋቱ ፅፌ ነበረ) ዛሬ በህይወት እንዳለ ደውሎ ገልፆልኛል። ጋዜጠኛ ሓገዞም ለሁለት ሳምንታት የጠፋበት ምክንያትና መንገድ ከመግለፅ ቢቆጠብም የህወሓትን የዓፈና ተግባራት ማጋለጥ ከጀመረና ከወይን ጋዜጣ አዘጋጅነት ከለቀቀ በኋላ በጠላትነት እንደተፈረጀ፣ ሚስጥር እንዳያወጣ እየተባለ በደህንነት ሰዎች ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግበት፣ በሌሊት ሁለቴ የግድያ ሙከራ እንደተደረገበት፣ አሁንም ቢሆን የዉስጥ አዋቂ ከመሆኑ የተነሳ የቁም እስረኛ በመሆኑ ስራ ሰርቶ መብላት እንዳቃተው በስልክ ገልፆልኛል። የህወሓቶች የዓፈና ተግባራት የሚያጋልጥ መፅሓፉ በቅርቡ እንደሚታተም ተናግሯል።
ስለዚህ የጋዜጠኛ ሐገዞም መኮነን ቤተሰቦችና ወዳጆች ሐገዞም በህወሓቶች ክትትልና ዛቻ በአግባቡ መስራት ባይችልም በህይወት አለ።
ህወሓቶች እስካገለገልካቸው ድረስ ይጠቅሙሃል፤ የነሱ ባርያ ሁነህ እነሱን እስካገለገልክ ድረስ ቁሳዊ ጥቅም ይሰጡሃል። ነፃነትህ የጠየቅክ ግዜ ግን ወዮልህ! በህወሓት ቁሳዊ ጥቅም እንጂ ነፃነት መጠየቅ አይቻልም። ቁሳዊ ጥቅምማ ማንም የሰው አገልጋይ (ባርያ) ያገኘዋል። የሚፈለገው ነፃነት ነው። ነፃነት ከተነፈጋቸው ዜጎች ዋነኞቹ የህወሓት አባላት ናቸው። መቃወም አይፈቀድላቸውም፤ ይሄው እኛ ግን ችግር እየደረሰብን ቢሆንም በነፃነት መተቸት እንችላለን። የሚደርስብን ችግር እናውቀዋለን፤ እናም በሚደርስብን በደል አንምበረከክም። ነፃነት ይሻለናልና።
(ወይን ጋዜጣ የህወሓት ልሳን ነው)።