Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ስለመሬት መሸጥ መለወጥ -ተጨማሪ ማብራሪያ (ፋሲል የኔዓለም)

$
0
0

 

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም

ውድ ስርጉትና ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች የጽሁፌን ይዘት በደንብ ባለመረዳት ይመስል “ የምን ጠጋ ጠጋ” ብለውኛል። እኔና ኢህአዴግ ከምንጠጋጋ ጸሃይና መሬት ቢጠጋጉ ይቀላል። ወያኔን የምደግፍበት አንድ ነገር አገኘሁ ማለቴ ስላቅ ነው። ወያኔ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ይላል። ይህን ያለው ከ20 በፊት ነው። ዛሬ ግን በሙሉ ልቡ ደፍሮ እንደዛ አይልም። ለምን? ያን ጊዜ የህወሃት ሰዎች ገንዘብ አልነበራቸውም። ዛሬ ግን የአገሪቱን መሬት ጠቅልለው የሚገዙበት ገንዘብ አላቸው። ዛሬ መሬትን በግል አዙር ብንለው መሬቱን እነማን እንደሚገዙት እናውቃለን። በ20 አመት ፖለቲካ ማሰብ የለብንም። ብዙ ህዝብ አገራችን ያለችበትን ሁኔታም የተረዳ አይመስለኝም። ዛሬ ገንዘቡ ኢፈርት በተባለው በህወሃት ድርጅትና በአላሙዲ ስር ነው ያለው። መሬት ወደ ግል ቢዞር እኮ የሚገዙት ሁለቱ ናቸው። እና 90 ሚሊዮኑን ህዝብ ባሪያ እናድርገው። ወያኔን ታግሎ መጣልና አዲስ መንግስት ማቋቋም ተገቢ ነው። አሁን መሬትን ወደ ግል አዙር እያልን ከጨቀጨቅነው ግን በደስታ ያዞርና ሌላው ህዝብ የዝምባብዌ ወይም የደቡብ አፍሪካ እጣ ይገጥመዋል።

 

አንዳንድ ሰው ስለ አዲሱቹ ካፒታሊስቶች የገባው አልመሰለኝም። ኢትዮጵያ እኮ የደቡብ አፍሪካ አይነት የኢኮኖሚ ስርአት እየገነባች ነው። በዘር ላይ የተመሰረተ ስርአት።

ለማንኛውም ለሌሎች አስተያየት ሰጪዎች የሰጠሁትን መልስ እዚህ ላይ እንዳለ አትሜዋለሁ። የአቋም ለውጥ ያደረኩ የሚመስላችሁ ካላችሁ ጽሁፌን እንደገና እንድታነቡት እመክራለሁ።

 

“ዳዊት ሰለሞን የተባለው ሰው በመሬት ዙሪያ ለጻፍኩት መልስ ሰጥቷል። አመሰግናለሁ። እኔ ከ20 አመት የኢህአዴግ የስልጣን ጊዜ በሁዋላ የተገለጠልኝ ሃሳብ እንደሆነ፣ ቀደም ሲል መሬት እንዲሸጥ እንዲለወጥ ስፈልግ እንደነበር የሚያስመሰል ሃሳብ አቅርቧል። ያነሳቸው ሃሳቦች ብዙም ጠናካራ ሆነው ባላገኘኛቸውም፣ ለትምህርት ይሆነን ዘንድ ትንሽ ለማለት ፈለኩ።

 

ቀደም ብየ እንደገለጽኩት መሬት ወደ ግል እንዲዞር ከሚፈልጉት መካከል ነኝ። ነገር ግን በዚህ መንግስት መሪነት የሚደረግን ክፍፍል አልደግፍም። ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኢህአዴግ መሬት ወደ ግል መዞሩ ኢህአዴግን ቢጠቅመው ኖሮ እስካሁን ያደርገው ነበር በማለት መሬትን ወደ ግል ማዞር ለፖለቲካው እንደሚጠቅም ገልጿል። የዳዊትም ሃሳብ ተመሳሳይ ይመስላል። የእኔ ሃሳብ ደግሞ መንግስት መሬትን ወደ ግል እንዲያዞር ከመጠየቅ ፣ ስርአቱን ቶሎ አስወግዶ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚቋቋመው መንግስት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያከፋልፍ የሚል ነው።

 

ኢህአዴግ  መሬት ለማከፋፈል ለምን አልፈለገም? ብዙ ሰዎች ህዝቡን ለመቆጣጠር ስለሚመቸው ነው ብለው ምክንያት ይሰጣሉ። ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መሬት ወደ ግል ቢዞርም ኢህአዴግ ሌላ የመቆጣጠሪያ ዘዴ መፍጠሩ  እንደማይቀር ማወቅ አለብን።   ለእኔ ዋናው ምክንያት ኢህአዴግ የራሱን ካፒታሊስቶች እስኪፈጥር ጊዜ ለመውሰድ ስለፈለገ ነው። ባለፉት 22 አመታት ወያኔ በአንድ ዘር ላይ የተማከለ ካፒታሊስቶችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በስልጣን ላይ እስካለ ድረስም ይህንን ስራውን ይቀጥልበታል። ካፒታሊስቶች በቂ ሀብት አጠራቅመው አገሪቱን ሙሉ በሙሉ  የሚቆጣጠሩበት ደረጃ መድረሱን ወያኔ ሲረዳ ፣  ማከፋፈሉ አይቀርም። ምክንያቱም መሬት  ወደ ግል ቢዞር መሬቱን የሚገዙት እነዚህ ካፒታሊስቶች ይሆናሉና። ይህ አካሄድ ደግሞ የአገሪቱ መሬት በጥቂት ካፒታሊስቶች እጅ እንዲወድቅ ያደርጋል። እነዚህ ካፒታሊስቶች ደግሞ በአብዛኛው የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው። ወደድንም ጠላንም አብዛኛው መሬት በእነሱ እጅ መውደቁ አይቀርም። መሬት በመንግስት ስር ከቆየ ግን አዲሱ መንግስት  ሲመጣ በቀላሉ ይነጥቃቸዋል። አዲስ መንግስት ከመምጣቱ በፊት መሬት ወደ ግል ቢዘር  ፣ የሚመጣው መንግስት ጦርነት የሚገጥመው ከእነዚህ ካፒታሊስቶች ጋር ይሆናል።

 

መለስ በአንድ ወቅት  “መሬትን ወደ ግል ብናዞር መሬቱን የሚገዙት እነማን እንደሆኑ እናውቃለን፣ ሌላው ህዝብ መሬት የሚገዛበት ገንዘብ የለውም ፣ ስለዚህ መሬት ወደ ግል ቢዞር በአንድ ብሄር እጅ ተመልሶ እንዲገባ ማድረግ ነው።” ብሎ ነበር። መለስ አንድ ብሄር የሚለው የፈረደበትን አማራ ነው። መለስ ባለፉት 23 አመታት ሲሰራ የነበረውም ካፒታሊስቶች በአብዛኛው ከራሱ ወገኖች ብቻ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። በአሁኑ ሰአት መሬትን ወደ ግል ማዞር የአገሪቱ ሰፋፊ መሬቶች በእነዚህ ካፒታሊስቶች እጅ እንዲወድቅ ማድረግ ነው። ወያኔ ዘረኛ መንግስት ባይሆን ኖሮ ችግር አይኖርብኝም ነበር። ዘረኛ መንግስት ደግሞ ፍታሃዊ በሆነ መንገድ መሬት ወደ ግል ያዞራል ብሎ ማለት ራስን ማሞኘት ነው።”

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>