በአዲስ አበባ ታላቁ አንዋር መስኪድን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ዋናዋና ከተሞች ‹‹ሰላታችንን በመስጂዳችን!›› በሚል መሪ ቃል ህዝበ ሙስሊሙ እያካሄደው ያለው መስጂድ ተኮር የዘመቻ እንቅስቃሴ አካል የሆነው እና የዘመቻው ማጠናቀቂያ የጁምኣ የተቃውሞ ትእይንት በደመቀ መልኩ ተካሂዷል::
ህዝቡን ከመስጂዱ ለመነጠል በመንግስት በኩል እየተሰራ ያለውን ህገ ወጥና ኢ-ህገ መንግስታዊ ስራም ለራሱ ተረድቶ ላልሰሙት ሁሉ በማሰማትና መስጂዶቹን በዒባዳ በማድመቅ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ ወቅታዊና አንገብጋቢ የመስጂድ ባለቤትነትን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ የመንግስትን እና የመጅሊስን ሴረኞች እንቅልፍ ማሳጣቱንም ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ የውስጥ መረጃዎች እያጋለጡ ነው፡፡ ‹‹ሰላታችንን በመስጂዳችን!››ዘመቻ የዛሬው ጁሙአ ድረስ ቀጥሎ የቆየ ሲሆን በአዲስ አበባና በተመረጡ የክልል መስጂዶች ላይም አስቀድሞ የነበሩንን ቋሚ ትዝታ ጥለው ያለፉ ግዙፍ ተቃውሞዎችን በሚያስታውስ መልኩ የደመቀ የተቃውሞ ስነስርአት በማድረግ በሰላማዊ ሁኔታ ዘመቻው መጠናቀቁ ታውቋል::
በዚህም መሰረት ከቀኑ ስድሰት ጀምሮ በአዲስ ወደ አዲስ አበባ አንዋር መስኪድ እና በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ የተቃውሞ ወደተመረጡ መስኪዶች የተመመው ህዝበ ሙስሊሙ የመስኪዶችን ውስጥ እና ደጅ በመሙላት መስኪዶቹ የራሱ ሃብት መሆናቸውን እና ሙስሊሙ ህዝብ ሰላም ፈላጊ መሆኑን በደመቀ ተቃውሞ ነጭ ምልክቶችን በማውለብለብ ገልጿል::
ህዝበ ሙስሊሙ ዘመቻውን በተሳካ መልኩ በማድረግ ሰላማዊ ተቃውሞውን አሰምቶ ከኮሚቴው ጎን ዛሬም ቃሉን አክብሮ እንደቆመ በማሳየት በሰላም መመለሱን ለማረጋገጥ ተችሏል::