Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ያልታሰረው ማን ነው?? (ከአንተነህ መርዕድ)

$
0
0

 

ud-bahirdar-demo

UDJ – Bahir Dar Demonstration

ሰሞኑን አንድ ኢትዮጵያዊ በቶሮንቶ የህሊና እስረኞችን ለመዘከር በግሉ አዳራሽ ተከራይቶ የአንዱዓለም አራጌን “ያልተሄደበት መንገድ” የሚለውን መጽሃፍ ለሽያጭ በአቀረበበት ቦታ ተገኝቼ ነበር። በዚህ አዳራሽ አንዱዓለምን፣ እስክንድርን፣ ርዕዮትን …ወዘተ ለመዘክር ብለው የተሰባሰቡ ሰዎች ብዛት ስመለከት “በእውነቱ እስረኞች እኛ ነን ወይስ እነ ዓንዱአለም?” የሚል ጥያቄ ጫረብኝ። አገርን ያህል ትልቅ ነገር ከራሳችን የፖለቲካና የግል ጠባብ ፍላጎት ዙርያ ቀንበበን ልንከተው ስንቸገርና አልሆንልን ሲል ደግሞ እርስ በርሳችን ስንጎነታተል አሁን አለንበት የመከራ ዘመን እንድንቆይ በራሳችን የፈረድን መሆኑ ግልጽ ይሆናል።

ትንሹን ህይወታቸውንና ጠባቡን የግል ፍላጎታቸውን በትልቁ ለሚያይዋት ኢትዮጵያ የሰውትን ወንድሞቻችንን ልናስታውስ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ብዙዎቻችን በተረባረብንና የነሱን ከባድ መስዋዕት በትንሽ በትንሹ በተጋራናቸው ነበር። እውነቱ ግን ያ አይደለም። ለብዙዎች የእንቅስቃሴያችን ማዕከል ሁሉ “እኔ” ስለሆነ ከዚያ የተለየን ማውገዝ፣ ማደናቀፍ፣ አለመተባበር…ተግባራችን የሆነ ይመስላል።

አንዱዓለም እንዳለው ከዚህ በፊት ያልተሄደበትን የመቻቻልና የመከባበር መንገድ መጀመር የጊዜው ጠቃሚ እርምጃ ነው። ይህ ሁኔታ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ የዮሃንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቁጥር3 እስከ 11 “ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘች ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርስዋን አቁመው መምህር ሆይ ይች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴ እንደነዚህ ያሉትን እንዲወገሩ በህግ አዘዘን። አንተስ ስለእሷ ምን ትላለህ? አሉት።….ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በደንጋይ ይውገራት አላቸው።…እነሱ ይህንን ሲሰሙ ህሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ” ይላል። ከኛም መካከል ህሊናው የሚወቅሰው ካለ ከተሳሳተ ድርጊቱ መቆጠብ አለበት። በዚሁ መጽሃፍ ቅዱስ የሉቃስ ወንጌል ላይም “በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፤ በራስህ ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ለምን አትመለከትም?” ሲል ይደግመዋል። እያንዳንዳችን የምንከተለው መንገድ ትክክል ሊመስለን ይችላል። የሌሎችን ሆነ የእኛን ትክክለኝነት የሚዳኘው ተግባራችንና ጊዜ ነው። እስከዚያው ግን መከባበርና መተባበርን የመሰለ ትልቅ ነገር የለም።

ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት ሰዎች ሆነ ተራው ግለሰብ የራሳቸውን ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ስህተት ላይ ብቻ ማተኮር ሲጀምሩ የውድቀታቸው መነሻ ይሆናል። ማንም ሰው ሲሠራ ሊሳሳት ይችላል። መጥፎው ነገር ከስህተት አለመማር ነው። ስህተቱን በጸጋ የሚቀበልና የሚያርም ትልቅ ነው። በእስልምና እምነትም ሃዲስ ላይ (በትክክል መጥቀስ ባልችል ይቅርታ ይደረግልኝ) እንዲህ ይላል “የማያውቅ ሆኖ የማያውቅ መሆኑን ማወቅ የማይፈልግ ቂል ስለሆነ ሽሸው። የማያውቅ ሆኖ አለማወቁን የሚያውቅ ከሆነ ልጅ ነውና አስተምረው። የሚያውቅ ሆኖ አዋቂ መሆኑን የማያውቅ ከሆነ ቀስቅሰው፤ ተኝቷልና። አዋቂ ሆኖ አዋቂነቱን የሚያውቅ ከሆነ ጥበበኛ ነውና ተከተለው” የብዙዎቻችን ባህሪ ባንዱ ሁሉ የሚካተት ነውና ቦታችንን ማወቅና እርምጃችንን ማስተካከል የተገባ ነው። ስለሆነም የታሰሩ ወንድምና እህቶቻችን የተሸከሙት እዳ ከግላችንና ከቡድናችን ፍላጎት በላይ አገራዊ ስለሆነ ከመጎነታተል፣ ከመከፋፈል ወጥተን አገራዊ ስፋት ባለው አላማ ዙርያ በጋራ መቆም ይኖርብናል።

ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስና “ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች እስር ቤት ናት” የሚለው ለትናንቶቹና ለዛሬዎቹ ጠባቦች መንደርደርያ ማዕከላዊ ሃሳብ ቢሆንም ደጋግመው እንደሚናገሩት ይህንን ብሂል በሃቅ ለብሄር ብሄረሰብ ነፃነት አልተጠቀሙበትም። ያ ቢሆን ምንኛ በታደልን። ድርጊታቸው ግን ተቃራኒ በመሆኑ ኢትዮጵያን ወደ ገሃነምነት ቀይረዋታል።

በአምደጽዮን፣ በፋሲለደስ፣ በቴዎድሮስ፣ በዮሃንስ፣በምኒልክ፣ በሃይለስላሴ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማበብ ነበረበት ብሎ የሚያስብ አእምሮ ቅንነት አለው ብለን አንጠብቅም። እነዚህ ነገስታት ግዛታቸውን ለማስፋት፣ በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት ባደረጉት እንቅስቃሴ ጭካኔ የተሞላበትን መንገድ መሄዳቸው ግልጽ ነው። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናስተዳድራለን ብለውም አያውቁምና የሚጠብቅም አልነበረም። ዳኝነታቸው ርህራሄና ፈሪሃ እግዜብሄር ያለበት እንዲሆን ሁሌ ባያከብሩትም ይናገራሉ፤ ህዝቡም ይጠብቃል።

ዛሬ በትናንት ታሪክ ታስረን፣ ለዚያ የከፋ ድርጊት ከመካከላችን ተጠያቂ ፍለጋ ስንኳትንና አጽም ለማውጣት መቃብር ስንቆፍር የሁላችን መቀበርያ አዳዲስ መቃብር እየተዘጋጀልን መሆኑን ዘንግተናል። በተለይም በዴሞክራሲ ስም እየማሉ የገዙን ሁለቱ ስርዓቶች ማለትም ደርግና ወያኔ ካለፉት ነገሥታት በባሰና በዘገነነ ሁኔታ ጨካኞች ናቸው። አገሪቱንም ወደ ሙሉ እስር ቤትነት የቀየሯት እነዚህ አምባገነኖች ያለፉትን አገዛዞች በኮነኑበት አንደበት የራሳቸውን ትልቅነት ከመስበክ ወደ ኋላ አላሉም። በነዚህ አገዛዞች “ኢትዮጵያ የዜጎች ሁሉ እስር ቤት ናት” የሚለው ከፀሃይ የደመቀ ዕውነት ነው።

ይህን ዓለም ያወቀውን እውነት በመካድ የትናንቶቹ አምባገነኖች መንግስቱ ኃይለማርያምና ፍቅረስላሴ ወግደረስ የነሱ አገዛዝ ፍትህ የሰፈነበት፣ ዴሞክራሲ የሞላበት የሚያስመስል ስንክሳራቸውን አሳትመው እንደጲላጦስ እጃቸውን ሊታጠቡ ይዳዳቸዋል። ፍቅረስላሴ “እኛና አብዮቱ”ባለው መጽሃፉ ቢያንስ ለታሪክና ለህዝብ ክብር ትንሽ የቅንንነት ጥፍጣፊ እንኳ ጨምሮበት ‘ሰርተን ያለፍነው ስህተት ይህ ነበር፣መጪው ትውልድ ከእኛ ስህተት ተምሮ መልካም አገር መገንባት አለበት’ የሚል እውነት በመጠኑም ይዞ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ ለብቻቸው ያዝዟቸው በነበሩት ሠርቶ አደር ጋዜጣ፣አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ፣ ሄራልድ፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን ላይ ሲያደነቁሩን የኖሩትን ፕሮፓጋንዳ ሃያ ሶስት ዓመታት ሲያመነዥከው ቆይቶ ለህትመት ሲያበቃ የህዝቡንም የማስታወስ ችሎታ መናቁን አሳይቷል። ፍቅረስላሴ በእስር ባሳለፈው ሃያ ዓመታት ወደ ኋላ በትዝታ መለስ ብሎ የሄዱበትን መንገድ ሁሉ በመቃኘት ወደ እውነቱ ቀርቦ መገኘት ሲገባው ሲታሰር ተኝቶ ሲፈታ የነቃ ይመስል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቀድሞ ያለፈበትን የመከራ ዘመን ሆነ አሁን እየደረሰ ያለበትን ጭቆና ዳግም እንዳይመለሱ በመታገል ላይ እያለ ፍቅረስላሴ ባንኖ በመንቃት ድሮ የጻፈውም ሜሟር እንዳለ ይዘምርልናል። “በማይጨው ጊዜ የደነቆረ ስለማይጨው ሲተርክ ይኖራል” እንዲሉ ስልጣን ሲለቁ እንደደነቆረና ከዚያ ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ በምን አስተሳሰብ ላይ እንዳለ ለመገንዘብ ያልታደለ መሆኑ እንድናውቅ ያደርጋል።

ፍቅረስላሴ አሁን ድረስ የሚያመልክበትና በፍርሃት የሚያሸረግድለት መንግስቱ ኃይለማርያም ብቸኛ አላማው የሆነውን የስልጣን ጥማቱን ለማርካት የህዝቡን ለጋ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን በእድሜና በልምድ መከበር የሚኖርባቸውን አዛውንት ኢትዮጵያውያንን፣ ጓደኞቹን ሳይቀር ተራ በተራ ሲያርዳቸው ቆሞ ሲንቀጠቀጥ፣ ማረጃ ሰይፍ ሲያቀብል እንዳልነበረ የነሱን የፍጅት ዘመን ከወያኔ ጋር እያነጻጸርን እንድንናፍቀው በተዘዋዋሪ ሊነግረን ይሞክራል።

የኢትዮጵያን ጠላቶች በየፈፋው ያርበደበዱት እነጄኔራል ታሪኩ ላይኔ፣አማን አንዶም፣ አምሃ ደስታ፣ ፋንታ በላይ ….ወዘት ዛሬ ተርፈው የተንሸዋረረ ታሪክ ሊነግሩ እንዳሉት በፍርሃት አልራዱም። አምባገነኑን አምባገነን ነህ እያሉ ነው የሞቱት። ታሪካቸውን ራሳቸው ባይናገሩም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል። ሲያከብራቸውም ይኖራል። እነሱንና አገሪቱ የገደሉት የታሪክ ዝቃጮች ስለሥራቸው ምን ቀለም ቢቀባቡ ማንነታቸውን ሊደብቁ አይችሉም።

ለመሆኑ የአስራ ሰባት ዓመቱ የ“እኛና አብዮቱ” ውጤት ምን እንዳስገኘ ፍቅረስላሴ ይዘረዝረዋል? ህዝቡንና አገሪቱን ቀፍዶ አስሮ ለወያኔና ለሻዕብያ ያስረከበው ማን ነው? “ወርቅ ሲያነጥፉለት ፋንድያ የሚመርጥ” ብሎ መንግስቱ ሃይለማርያም የሰደበውን ህዝብ አንተም በተጠያቂነት ታቀርበው ይሆን?

አዎ ኢህአፓዎች፣ መኢሶኖች፣ወዝሊጎች፣ ማልሬዶች፣ ሻዕብያዎች፣ ወያኔዎች፣ ኦነጎች…..በዚች አገር ውድቀት አውቀውም ሆነ ሳያውቁ አስተዋጾ ማድረጋቸውን ለማወቅ ህዝቡ የፍቅረስላሴንና የጓደኞቹን ምስክርነት የሚፈልግ አይደለም። ምንም እንኳ ይህ ነበር የኛ ድርሻ ለማለት ድፍረቱን ባያገኙትም ህዝብና ታሪክ የሁሉንም አስተዋፆ አይረሳውም።

ቀበሌዎችን፣ የጦር ካምፖችን፣ መኖርያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ሁሉ ወደ እስር ቤትነት የቀየረ፣ ወላጆች የልጆቻቸውን  አስከሬን ለመቀበል የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ ያስከፈለ፣ አልቅሰው እርም እንዳያወጡ የከለከለ፣ አዛውንቱን ኃይለስላሴን ያለፍርድ ገድሎ መቃብራቸው ላይ መፀዳጃ ቤት የሰራ…ወዘተ ይህን ሁሉ ያደረገ የደርግ ስርዓትና መሪዎቹ የሌሎችን ያነሰ ስህተት የሃጢያታቸው መጠራረጊያ ፎጣ ሊያደርጓቸው የሚያስችል የሞራል ብቃት የላቸውም።

የመሬት አዋጅን እንደትልቅ ድል ደጋግሞ ማንሳቱም የሚገርም ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን የተዋደቁለ የመሬት ጥያቄ በደርግ ሆነ በወያኔ አልተመለሰም። አዋጁ መሬትን ከመሬት ከበርቴዎች ነጥቆ ገበሬውንና መሬቱን የአምባገነኖች ንብረት ነው ያደረገው። ወያኔዎችም ካባታቸው ደርግ ደህና አድርገው ተምረዋልና  ኢትዮጵያዊ የመሬት ባለቤት የሚሆነው “በኢህአዴግ ሬሳ ላይ ነው” ሲል መለስ ዜናዊ ደምድሞታል።

ከገበሬው የወጣን ነን የሚሉት የደርግ አባላት ሆኑ ለገበሬው ቆሜያለሁ የሚሉት ወያኔዎች በካድሬዎቻቸው አማካይነት ንብረቱና ራሱን ገበሬውን የራሳቸው የግል እቃ፣ በቤቱም ውስጥ እስረኛ አድርገውታል። በህብረት እንዲያርስ የተገደደውና በችጋር የተጠበሰው የአርሲ ገበሬ “በናንተ ህብረት እርሻ ያተረፍነው በርሃብና በተባይ ማለቅን ነው” ብለው ብልቃት ሙሉ ቅማል ለደርግ ባለስልጣን ማሳየታቸውን በወቅቱ በቦታው የነበርነው ጋዜጠኞች ተመልክተናል። ይህን እውነት በአብዛኛው  አገሪቱ ለሥራ በተዘዋወርሁባቸው ወቅት ባይኔ አይቻለሁ።

ደርግ የጀመረውን የአፈና መንገድ ወያኔዎች በረቀቀና በሰላ መልኩ ተጠቅመውበታል። የመሰረት ደንጋዩን ያስቀመጡላቸው ግን እነፍቅረስላሴ ናቸው። ወያኔ አገርን በመበተን ከደርግ የከፋ ቢሆንም የደርግን ዘመን የሚናፍቁ ካሉ የዚያ ስርዓት ተዋናዮችና ተጠቃሚዎች የነበሩ ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከሁለቱም አምባገነኖች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይገባዋል።

ወደ ተነሳሁበት የእስር ጉዳይ ልመለስና በደርግ ሆነ በወያኔ መታሰርን በተደጋጋሚ ቀምሼዋለሁ። ለምን ታሰርሁ ብዬ አልቆጭም። ከህዝቡ መከራ የተጋራሁበት እውነተኛ የህይወቴ ምዕራፍ ስለነበር ባሰብሁት ቁጥር መጠነኛ የመንፈስ እርካታ ይሰማኛል። ሁለቱም ስርዓቶች በጣም ፈሪዎች ስለሆኑ በጣም ጨካኞች ናቸው። የተማሩትንና ለስልጣን ተቀናቃኝ ይሆናሉ ያሉትን ማሰርና በግፍ መግደላቸው እንዳለ ሆኖ በሁለቱም ስርዓቶች የሰባና የሰማንያ ዓመት በጤና የደከሙ ከፊሎችም ዐይናቸው የታወሩ አዛውንቶች ያለፍርድ እስር ቤት ቀስ እያሉ በሞት ሲያሸልቡ አይቻለሁ። መደገፍያ ከዘራቸውን ማንሳት የማይችሉትን አዛውንትና ክፉና ደግ የማያውቁ ህፃናትን የስርዓታቸው ተቀናቃኝ አድርገው የሚባንኑ አምባገነኖች ናቸው ሁለቱም።

ያ ሁሉ መጨፍጨፍ፣ ያ ሁሉ እስር የደርግን ስርዓት ከመፈራረስ፣ መንግስቱን ከመፈርጠጥ፣ ጓደኞቹን እነፍቅረስላሴንና ለገሰን እንደበግ ከመጎተት አላዳናቸውም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወያኔዎች ግድያውን፣ እስሩን ካስተማራቸው ከደርግ በባሰ ሰልጥነው ውድቀቱንም እየወረሱት ነው። የተፈጥሮአቸው እድገት ጣርያ (ክላይማክስ)ላይ ደርሰው ቁልቁለቱን ጀምረዋል። የገነቡት ሁሉ እየተናደ እንዳይቀብራቸው ራስን የማዳን ጥድፊያ ላይ ተጠምደዋል። ይህ መንፈራገጥ ግን የበለጠ ሚዛናቸውን እያሳታቸው ቁልቁል ይወረውራቸዋል። ሲወድቁ በሚያደርጉት መንፈራገጥ ብዙ ጉዳት ማድረሳቸው ግን የተጠበቀ ነው። የወያኔ የአጥቂነት ጊዜ አልፎበት አሁን በመከላከል ላይ ተጠምዷል። ጅኒው ከጠርሙሱ ወጥቷልና መልሶ የመክተት አስማት የሚሠራ አልሆነም።

ታላቁ ሩስያዊ ደራሲ፣ የታሪክ ምሁርና የሶብየትን አምባገነንነት አጥብቆ ይተች የነበረው አሌክሳንደር ኢሳየቪች ሶልዝሄንጺን የሩሲያውያንን መከራ ለዓለም በሚገባ ካሳወቀባቸው በርካታ ሥራዎቹ ዘ ጉላግ አርፒላጎ የዘረዘራቸውን ስናነብ ደርግና ወያኔዎች ያንን እያነበቡ የፈጸሙ ይመስለናል። በአንደኛው ጽሁፉ  “እኛ በሚሊዪን የንምቆጠር ሩስያውያን ሴቶችና ወንዶች ከቀን ቀን፣ ከዓመት ዓመት ራሳችንን ደፍተን ወደ እስር የምንጎተትበት ምክንያት ይህ ነው። የማስጠንቀቂያ ደወል አናጮህም። በጎዳናዎች ተቃውሟችንን አናሰማም። እንዲያውም በተቃራኒው በጎዳና ላይ በጓደኞቻችን ፊት ስንነዳ እኛ ግዞተኞች ምንም እንዳልተፈጸመብን ፊታችንን ቅጭም አድርገን አንገታችንን ደፍተን፤ እነሱ የነገ ግዞተኞችም እኛን እንዳያዩ ዐይናቸውን መሬት ላይ ተክለው እንተላለፋለን። ህዝባችን ይህንን ድርጊት ሂደቱን ሳያዛባ ተግባራዊ ማድረጉን ተክኖበታል። በብዙ ማሰቃየት የታጀበው ምርመራ ሲጠናቀቅ እኛ ትንንሾቹ አሳዎች መረባቸው ውስጥ ዋኝተን እንገባላቸዋለን። …ባህሩን የሞላን ጥሩ አሳዎች፤ የአጥማጆቻችንን መንጠቆ ጉሮሮአችን ውስጥ ለማስገባት የምንሽቀዳደም፤ እኛን በመጎተት እንዳይደክሙ  ወደ ላይ ቀዝፈን የምንቀርብላቸው…..” እያለ ለአምባገነኖች የመከራ ማገዶነት ምንም ሳይንፈራገጡ ወደ ማረጃው፣ ወደ እስሩ የሚሽቀዳደሙ ሩሲያውያንን የሸነቆጠበት አነጋገር እኔንም እንዳለንጋ መንፈሴን ይተለትለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በመደበኛ እስር ቤቶች፣ በጦር ካምፖችና በድብቅ እስር ቤቶች የሚማቅቀውን ኢትዮጵያዊ ቁጥር ማወቅ ይከብዳል። በደፈናው እኛና ዓለም የሚያውቃቸው ደፋርና ለዴሞክራሲ ስርዓት ማበብ ከፍተኛ መስዋዕት በመክፈል ላይ ያሉትን አንዱዓለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ፣  አቡበከርና ጓደኞቹ ……እያልን ብንዘረዝር ቁጥራቸው የትየለሌ ነው።

እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው በአካል የተገደቡ እስረኞች ናቸው ብንልም በመንፈስ ልዕልና ያላቸው ንፁሃን ናቸው። በእኔ አስተያየት እነሱ ሳይሆኑ እኛ ቀሪው ኢትዮጵያውያን ነን እስረኞች እላለሁ። እስክንድር፣ አቡበከር፣ ውብሸት፣ ርዕዮትና አንዱዓለም በአካል ከታሰሩበት ወህኒ ዘልቀው በመንፈስ ነጻ መሆናቸውን አሳውቀውናል። ያሉበትን መከራ እንደ ኢምንት በመቁጠር የምንከፍለው ቀላል ነው እያሉ ምንም ለመክፈል ያልተዘጋጀነውን፣ ከዳር ቆመን በፍርሃት የምንርደውን ህሊናችን እንዲሞግተን በመተው ባለ እዳ አድርገውናል።

ርዕዮት፡ “በኢትዮጵያ ፍትህ ማጣትና ጭቆና የተንሰራፋ በመሆኑ ለህይወቴ አዳጋ ይኑረውም አይኑረው ለእውነት እቆማለሁ” ብላለች። ይብላኝ ለእኔና ለእናንተ ዳር ለቆምነው።

አንዱዓለም፡ “ያልተሄደበት መንገድ” በሚል ርዕስ ከእስር ቤት ጠባብ ክፍል በጻፈው መጽሃፉ “እስር የስቃይ ብቻ ቢሆንም ከነፃነትና ከዴሞክራሲ እጦት አይከብድምና በጸጋ መቀመል ነበረብኝ”  ሲል የአካል ስቃይን ፈርተን ህሊናችንን ለአሰርነው አማራጩን ይነግረናል። ከዚያም አልፎ “ይህ ሁሉ የመከራ ሸክም የማን ነው? የታሳሪ ፖለቲከኞች ብቻ ወይስ የነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ሁሉ?”  በማለት የፍትህና የነፃነት ናፍቆታችን አፋዊ በመሆኑ ህሊናችን እንዲወቅሰን ጥያቄውን ወረወረልን።

እስክንድር፡ ሰሞኑል ለልጁ (ርዕሱ ለልጁ ይሁን እንጂ መልዕክቱ ለእኛ ነው) ከእስር ቤት በፃፈው ደብዳቤ “በጣም ናፍቄሃለሁ። እናትህንም ጭምር። ስቃዩ አካላዊ ስቃይ ብቻ ነው የሚሆነው። የቤተሰባችን ስቃይ ለረጂም ጊዜ መከራ ከተሸከመው ህዝባችን ተስፋ ጋር የተቆራኘ ነው።ከዚህ የበለጠ ክብርም የለም።ስቃዩን ሁሉ በመቋቋም፣ የሚቻለውን ሁሉ ርቀት በመሄድ፣ማንኛውንም አቀበት በመውጣት፣የትኛውንም ባህር በማቋረጥ ነፃነት ላይ በመድረስ ጉዞአችንን ማጠናቀቅ አለብን። ከዚህ ያነሰ ትግል ህሊናን ማደህየት (ባዶ ማስቀረት)ነው” ሲል ጽናቱንና የምንሄድበትን እርቀት አመልክቶን “አምባገነንነት ፍርሃት የነገሠበት በመሆኑ መንግስታዊ ሽብር፣ እስራትና ማሰቃየት ዋነኛ ተግባሩ ነው። በዚህ መንገድ ግን ሁሉንም ህዝብ ማንበርከክ አይቻልም። ነገር ግን የተወሰኑ ሰዎችን የጥቃት ኢላማ በማድረግ ብዙውን ሰው በፍርሃት ማደንዘዝ ይችላሉ። በጥቁር ዓለም ጥንታዊ የመሆናችን የጋራ ኩራት ይህንን አስማት ለመጨረሻ ጊዜ እንድንሰብረው ያስገድደናል” ሲል በነሱ መታሰርና መሰቃየት ሩቅ ሆነን በፍርሃት ተሸብበን የታሰርነውን ሊፈታን ይታገላል።

ሌሎችም እስረኞች ደጋግመው በተለያዬ መልክ ያስተላለፉልን መልዕክት ይሄው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህዝብ በአጠቃላይ እስረኛ መሆኑ ቢታወቅም ውጭ ያለነው እንኳ በፍርሃት፣ በራስ ወዳድነት፣ በክፍፍል፣ በመከነና የትም ባላደረሰን የትናንት አስተሳሰብና ከዚያም አልፎ በስሜታዊነት እስረኛ ነን። አንዱዓለም፣ እስክንድርና ሌሎችም የሚሉን ‘አሳሪ ሳይኖራችሁ ራሳችሁን ያሰራችሁ ራሳችሁን ነፃ አውጡና ትልቅ አገራዊ ዓላማ ይዘን አገር ነፃ እናውጣ’ ነው የሚሉን።

የጽሁፌ ማጠቃለያው ሁላችንም እስረኞች ነን።በመጀመርያ ራሳችንን ነፃ እናውጣ። ከዚያ የታሰሩ ወንድሞቻችንን፣ እህቶቻችንንና አገራችንን ነፃ ማውጣት እንችላለን።

ግለሰብ ሆኖ በህሊናው፣ ድርጅት ሆኖ በአሰራሩ ነፃነት ከሌለው ለነፃነት ቆሜያለሁ ማለት ከአፋዊነት አይዘልም። እስከ አሁንም የሆነውና ያየነው ይህንኑ ነው። ራሳችን ለራሳችን የነፈግነውን ነፃነት ከአምባገነኖች በልመና አናገኝም።

ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ!

ጸሃፊውን በamerid2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>