Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ያረጋገጥነው የምግብ ኢ_ዋስትናን (ዋስትና አላልኩም) ነው –ክፍል 5 [የመጨረሻው ክፍል]

$
0
0

ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ

ይህንን ክፍል ስጀምር አንባቢያንን እንዲህ በማለት ነው። በሕዝቦቿም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ሥራቸውና መልካም ተግባራቸው የተመሰገነላቸው፤ የተወደሰላቸው፤ የተጨበጨበላቸውና ውዳሴ የተቸራቸውን ድንቅዬዎቹን ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ባይሆን ጥቂቶቹን ለሰከንድ በኅሊናችን እንድናስባቸው በመጠየቅ ነው። እነርሱ ለኛ ሻማ ናቸው። እራሳቸውን በጥረታቸው አብርተው ብርሃኑን ለኛም እንዲደርሰንና እንድንገለገልበት መንገዱን መርተውናል። እኛ ግን እርኩስና ስንኩል መንገድ ይሻላል ብለን የራሳችንን ፍልስፍናና የኑሮ ዘይቤ ትተን የሌሎቹን የማናውቀውንና ለኛ ኅ/ሰብ ምቹ ይሁን አይሁን በቅጡ ሳናረጋግጥ የተበላሸና የማይሰራ መንገድ መርጠን እነሆ ስንገታገት ግማሽ ምዕት ዓመት ሊሞላን አንድ አሥር ዓመት ቀረን። አንዳንዶቻችን የአዳምና የሔዋን ልጆች መሆናችንን እረስተን በማንነት ዙሪያ ብቻ ስናወራ ጊዜው በረረ። ሐረር የኖራችሁ ታውቁታላችሁ ብዬ አስባለሁ። ይህ ሰው የ፫ተኛው ክፍለ ጦር ኦጋዴን አንበሳ የሙዚቀኛው ክፍል (የቀላድ አምባው) ድምጻዊ ነው። መስፍን ከበደ ይባላል ። ሹመቱን እረሳሁኝ። ወታደር ሲኖርም፤ ሲሞትም በማዕረግ ስሙ ነው የሚጠራው። አስቀድሞ ታይቶት ነው መሰለኝ በ1960ዎቹ አጋማሽ እንዲህ በማለት አቀንቅኖ ነበር፦ ትውልዳችን የዓዳም አንድ ነው ደማችን፤ ከቶ ለምን ይሆን ዘር መለየታችን? ለውጥ በኑሮአችንና በአስተሳሰባችን ሲያልፍም አልነካን። በጊዜ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከፋም ለማም በሆነ ነገራቸው ለውጥ መታየት ነበረበት። በምሳሌም እንደተማርነው ” ምንም ያህል ዘመን በውሃ ውስጥ ቢኖር መዋኘት የማይማረው ድንጋይ ብቻ ነው” ተብሎ በተለይ የምዕራብ አፍሪካ ሰዎች ነገር በምሳሌ እንዳላቸው አንድ ወቅት ላይ ከረፖርተር ጋዜጣ ላይ ያነበብኩኝ መሰለኝ። ለማለት የፈለኩት እኛም በቂ እንዳልተማርንና ስህተትን በሌላ ስህተት ከመተካት በስተቀር ትርፍ ያመጣና ሕይወታችንን ከጎስቋላው ኑሮ ፈቀቅ ያደረግ እርምጃና ለውጥ አለማየታችንን ለመናገር ፈልጌ ነው።
Food security ethiopia
ለዘመናትና ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ገበሬ የተለያዩ የዕጽዋት ዝርያዎችን በመስኩ ላይና በጎተራው በመንከባከብና በመጠበቅ የሰው ልጅ ህልውና ታሪክ ከምድረ ገጽ እንዳይጠፋና እንዲቀጥል የበኩሉን ድርሻ እንደ አቅሚቲ ተወጥቷል። ለዓለምም ሕዝብ እንደ ቡና፤ እንሰት፤ ኑግ፤ ኮረሪማና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን፤ ኦክራ (የሴት ጣት)፤ ጤፍ፤ የተለያዩ የገብስ ሰብል ዓይነቴዎችን፤ ባህላዊ መድሃኒት የሆኑትን የኮሶና የድንገተኛ ዕጽዋቶችንና ሌሎች ሰብሎችንና እንስሳቶችን ጠብቆና በእንክብካቤ አቆይቶ ፤ ለራሱ ሳያልፍለት ለሌሎች አቀብሎና ሰጥቶ ቆይቷል። መልሶም የእነርሱ ተረጂም ሆኗል። ለዚህ ሁሉ ተግባሩ ደግሞ የአገሬ ገበሬን ዕውቅና ቢቸረው ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም። ለምሳሌም ያህል ለመጥቀስ የአሜሪካን የገብስ ሰብል ገበሬዎች ይህንን ውለታውን ጠንቅቀው ያውቁታል። ለምን ይህ ሁሉ የሰው ሃብትና እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች ኖሮን እንዲህ ምድር ለኛ ብቻ ሲዖል የሆነችብን ብለን መጠየቅም ተገቢ ነው። ይህንንም ገጥታችንን ለመቀየር መፍትሄው እኛ ዘንድ እንጂ ሌላ ስፍራ እንደማይኖር ተገንዝበን ቀናውን መንገድ መከተል የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለን መነሳት እንዳለብን ለመጠቆምም ነው።
ግብርና የአገራችን ዋነኞ ኢኮኖሚ መሰረት ነው። ለዕድገታችንም መሰረቱ ግብርናው ነው ካልን አገራችን የገበሬ ምድር ናት ማለት ነው። አዎን! አገራችን ኢትዮጵያ፦ የአፈር ገፊው፤ የእንስሳት አርቢው፤ የዓሳ አስጋሪው፤ የደንና ዱር አራዊት ጠባቂው፤ የንብ አናቢውና የማር ቆራጩና የሌላም ልጆች አገር ነች። ለምን ቢባል በክፍል 4 መጨረሻ ላይ ጠቀሜታው ተገልጾአል። ግብርና ክቡር ሙያ ነው። ገበሬም እንደዚያው ማለፊያና ደግ ነው ። የአገራችን ኢኮኖሚ ምን ያህል ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር የተቆራኘ ለመሆኑ ተደጋገመው የሚነገሩትን አኅዛዊ መረጃዎች መመልከቱ ይበቃል። እጅግ በድህነት አረንቋ ውስጥ ለሚገኘው 80% በላይ ለሆነው የአገራችን ሕዝብ ለኑሮው መሰረቱና መደበኛ ሥራው ነው። ከጠቅላላው የአገሪቱ ምርትም ውስጥ ድርሻው 50 % ነው። የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወደ ዓለም ገበያ ከሚጓዙት ሸቀጦቻችንም እስከ 85% ድርሻ አለው። ዋነኛ የኤክስፖርት ምርታችን ብለን የምንጠራው የኮኖሚው ዋልታ ቡና ቡና 25% ድርሻ አለው። በተጨማሪም የእንስሳት ሃብታችንም ቢሆን ለብቻው ከጠቅላላው የግብርናው ምርት ውስጥ 15% ስፍራን ይይዛል።

የአገራችን ግብርና ዋና ዋና ገጽታዎቹ ምንድር ናቸው? በዋናነት የሰብል ልማት ላይ ያተኮረው ግብርናችን የዝናብ ጥገኛ ነው። የዝናቡ ተስተካክሎ በጊዜው መምጣት፤ መጠኑና ሥርጭቱ ለምርቱ ብዛትም ሆና ጥራት ወሳኝ ናቸው። የምግብ እህሎች የሚባሉቱ የብርዕና የአገዳ (ጤፍ በቆሎ ማሽላ ስንዴ ገብስ አጃ ዳጉሳ) ፤ ጥራጥሬ (ባቄላ አተር ምስር ሽምብራ አኩሪ አተር አደንጓሬና ሌሎች)ና የቅባት (ኑግ ሰሊጥ ተልባ ለውዝ) እህሎች በዋነኛነት የለማውን ማሳ (ከ80 _90%) እጅ ሸፍነውት ይገኛሉ። እንደ ጠቅላይ ስታትስቲክስ ጽ/ቤት የ2005 የግብርና እንቅስቃሴ ናሙና ጥናት ረፖርት መሰረት ( አሃዙን ለማንበብ እንዲመች ወደ ሚቀርበው ለማጠጋጋት ተሞክሯል) በምግብ ሰብል ምርት የተሸፈነው ማሳ በጠቅላላው (በአነስተኛና በዘመኑት እርሻዎች በመኽርና በበልግ ወራት) መጠን 12 1/4 ሚሊዮን ሄክታር ሲደርስ ከእዚሁ ማሳ ላይ ብቻ ወደ 231 ¼ ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ እህል እንደተሰበሰበ ተገልጾአል ። እስቲ ስለዚህች አሃዛዊ መረጃ መሰረት አድርጉና ለጠቅላላው ሕዝብ ቁጥር ግምት አካፍሉትና የሚሰጣችሁን የነፍስ ወከፍ ዋጋ ተመልከቱት። ምን ይሰማችኋል? ይሄ የነፍስ ወከፍ ዋጋ የአትክልትና ፍራፍሬ፤ የሥራ ሥሩንና የቅመማ ቅመሙንና ሌሎችን ውጤት እኮ አይጨምርም። ታዲያ ውጤቱ ትክክል ነው ብለን የምናምን ከሆነ፤ ለምን በረሃብ ፤ በችጋርና በጠኔ እንሰቃያለን? ግብርናችን አንድ ቦታ ላይ በችግር ተውተውትቧል ማለት ነው። በተደጋጋሚ ለእርሻ አገልግሎት የዋሉት ማሳዎች የለምነት ደረጃቸው የቀነሰ ነው። አስተራረሳችን በአብዛኛው እጅ ዛሬም ጥንታዊና በዘልማድ ላይ የተመሰረት ነው። በኢትዮጵያ ምድርና ማሳዎች ላይ ብዙ ትራክተሮችና ተጎትተው የሚሽከረከሩ መሳሪያዎች አያጔሩም፤ የማጨዳ መውቂያና መፈለፈያ መኪኖች አይሽከረከሩባትም። በአገሪቱ አገልግሎት ላይ የትራክተሮች ብዛት ለሚታረሰው መሬት ወይም ደግም ለገበሬው ቁጥር ቢካፈል ድርሻው በጣም አነስተኛና ደካማ ነው። ይህም ማለት ግብርናችን በአብዛኛው በእጅ ሃይል የሚከናወን ነው ማለት ነው። የምርት ማሳደጊያዎች አጠቃቀማችን እንዲሆን ከምንፈልገው እጅግ ወደ ታች የተጎተተና የራቀ ነው ። በአትክልትና ፍራፍሬ፤ የሥራ ሥር ተክሎች የተሸፈነው ማሳም ስፋት ትልቅ ነው። የኢኮኖሚ ዋልታ ቡናችንም ለብቻው የያዘው የማሳ ስፋት ክ1/2 ሚሊዮን ሄክታር በላይነው። የጫት ተክሉም ቢሆን ቀላል ግምት የሚሰጠው አልሆነም ። ከፍተኛ የሰው ኃይል የተሰማራበት ይህ የሰብል ልማት ንኡስ ክፍል ምርትና ምርታማነቱ እጅግ በአነስተኛ ደረጃ ለይ ነው። ለምርትና ለምርታማነቱ መጨመር ተገቢው ስፍራ የተሰጣችው የግብአት ( ምርጥ ዘር፤ የመሬት ማዳበሪያ ፤ ጸረ_ተባይና ሌሎች) አጠቃቀሙ በዝቅተኛ ደረጃ ለይ ነው በተለይ በግብርናቸው ዕድገት ላይ የጎላ ለውጥ ካስመዘገቡት አገሮች ተርታ ሲነጻጸር። ዛሬም ብሐራዊ የበቆሎ ምርት አማካዪ ከ25 _30 ኩንታል/ ሄክታር በላይ አልዘለለም። በምርምር ጣቢያዎች፤ በአንዳንድ ሠፋፊ እርሻዎችና በጣት የሚቆጠሩ የገበሬዎች ማሳ ምርቱ ከፍ ያለ እንደሆን ይነገራል። የምንኮራበት የጤፍ ሰብልም በአስራዎቹ የመጀመሪያ ረድፈ እንጂ ከአስራዎች ግማሽ በላይ አልወጣም፤ ማሽላም ከ20 ኩንታል/ ሄክታር በላይ አልዘለለም፤ የባሌና አርሲ የስንዴ ሰብል ቀበቶዎች ብለን የምንጠራችው ስፍራዎችም የሚመዘገበው አማካይ ምርት ከሄክታር ከ20 ኩንታል በቅጡ አልተሻገረም። ይህ ማለት ደግሞ ከዚህ በላይ መጓዝ አይችሉም ማለት እንዳልሆነ አንባቢ ግንዛቤ እንዲያገኙ ይጠየቃሉ። ባጭሩ ሁኔታዎቹ ተሰፋ አስቆራጭ ናቸው ማለት አይደለም። በተቃራኒው መቆም የሚያስችል ችሎታ በገበሬውም በተፈጥሮም አሉ። ዋነኛ የግብርናው ተዋንያኖቹ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ከእጅ ወደ አፍ የሚያመርቱ በመጨረሻው የድህነት መስመር ላይ የተሰለፉ ግፉአን አምራቾች ናቸው። የይዞታ መጠናቸውም ከድሮው እጅግ በፍጥነት እያሽቆለቆለ መጥቶ ከ 1 ሄክታር በታች መሆኑ ከተገለጸ ሰነባበተ። ቁጥራቸው በዛ ያለ ገበሬዎችም ከኩርማንና ከበሬ ግንባር ያላነሰ መሬት መጠን ይዘው ይማስናሉ። መቼስ የአባ ወራው ሆነ የእማ ወራው ብዛት ስንት እንደሆን በቅጡ አይታወቅም። ከጠቅላዩ ስታትስቲክስ የተለቀቁት መረጃዎች እንደሚጠቁሙትና እነሱንም መሰረት በማድረግ የቤተሰቡን ቁጥር ሳይጨምር ከ14 ሚሊዮን በላይ ሳይገመት አይቀርም። ከእዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ወንድ ?ምን ያህሉ ሰቶች? እንደሆኑ የሚታወቅ አይመስልም። በእድሜ ደረጃም ቢሆን፤ በመደበኛ የትምህርት ችሎታቸው ተለይቶ የተቀመጠ መረጃ ለማግኘት ያስቸግራል። ሌላም ልጨምር በየተሰማራበት ንዑስ የሥራ ክፍልም ምን ያህል እጁ እንደሆነ የሚገልጥ ቀጥተኛ መረጃ በቀላሉ ማግኝት አይቻልም። ይሄን ጊዜና ነው የጠቅላይ ስታትስቲክስ መ/ቤት እጅግ አስፈላጊነትና መልካም መግለጫ ሰጭነት ስፍራው። ” ሃሎ ሃሎ ሃሎ ሃሎ ጠቅላይ ቢሮ “ በ1950ዎቹ የተጫወተው ባህታ ገ/ሕይወትም አይደል። መረጃ ዘርዘርና ረቀቅ ተደርጎ ሲቀርብ ለሚተነትነው አካልም ሆነ መረጃውን መሰረት አድርጎ አገልግሎቱን አዘጋጅቶ ለተጠቃሚው በበቂ ለማድረስ ደፋ ቀና ለሚሉት ተቋሞችና ድርጅቶች እጅግ ይጠቅማል፤ ያግዛልም፤ ይረዳልም። ይህ ስራው ሁሉ ከእጅ ወደ አፍ ብቻ የሆነው ገበሬ ለዕለት ተዕለት ለቤተሰቡና ለራሱ ምግብ ፍጆታ የሚውል ምግብ እንጂ የሚያመርተው እንዲህ ተርፎት የከተማውን ነዋሪ ለማጥገብ ተገቢውን ድጋፍ ከሚመለከታቸው ካልተቸረው በስተቀር የዳገትን ያህል አስቸጋሪ ነው። እንግዲህ ሰለ ግብርናው ልማትና ዕድገት ሰናወራና መግለጫ ስንሰጥ በቅድሚያ ስለሱ መሆን አለበት። ችሎታውን ሳንንቅ፤ አቅሙንና ክህሎቱን ሳንለካ ብዙ ጊዜ አላዋቂነቱን እንሰብካለን። ገበሬ አካባቢውን ጠንቅቆ ያውቀዋል። ጥሩ ተመራማሪ ነው። የተመራማሪው ሳይንቲስት ሥራ መሪውና መምህሩ ገበሬ ነው። ከእርሱ ችግሮቹን ጠይቆና ለይቶ ቅደም ተከተል አስይዞም አይደል ፤ ለችግሮቹ መፍትሄ ለማበጀት ምርምሩን በመስክና በቤተ ሙከራ የሚያደርገው። እኛ እናውቅልሃለን የምንለው የምንበልጠው ችሎታችንን በወረቀት ላይ ባማስፈርና ሰነዶችን በማዘጋጀት፤ ለስብሰባ ብቁ እንዲሆኑ በማቅረብ ነው ብል ብዙ ስህተት ላይ አልወድቅም። ታዲያ ሁላችንም ብንሆን ለሃገሪኛው ዕውቀትና ክህሎት ተገቢውን ስፍራ ብንሰጥ ማለፊያ ስራ ነው ለማለት ይቻላል። በተጨማሪም እኒሁ ገበሬዎች እንደ መንግስት ሹመኞች፤ የፖለቲካ አዋቂዎችና ሌሎች አካላቶች ሁሉ ሰዎች መሆናቸውን አንዘንጋ። በቂ ችሎታና ክህሎት ያላቸውና ሥራን እንደ አቅሚቲ በመፍጠር ኑሯቸውን ለማሸነፍና ለማሻሻል የሚፍጨረጨሩና እምቅ ሃይልና በተስፋ የሚኖሪ፤ ከዛሬ ነገ ይሻላል ብለው የሚጓዙ መሆናቸውንም ከግምት ውስጥ እናስገባ። የዚህን ሰብል አብቃይ አነስተኛ ይዞታ ለይ የሚገኙትን ገበሬዎች በመርዳትና በማገዝ በብዛትና በዓይነት ምርት አምርቶ ወደ ገበያ በማውጣትም ለኑሯቸው በቂና አስተማማኝ ገቢ አግኝተው ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ የሚረማመዱበትን መንገድ አቅጣጫ ማስያዝ አጣዳፊ ተግባር ነው። ይህንን ስንፈጽም ብቻ ሰለ ምርትና ምርታማነት ከፍ ሲልም ስለ ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የምናወራው።

ከእንሰሳት ሃብታችንም የምናገኘው ጥቅም በበቂ አገልግሎ ት ላይ የተመሰረተ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር ያስቸግር ይሆናል። ቢሆንም ይኽው ሃብታችንን እንዳያድግ ቀፍድዶ የያዘንን ችግሮች ለይተን አውቀን ቅደም ተከተል አስይዘን ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ለአርቢዎቻችን ካደረግን ተጠቃሚ የማንሆንበት ምክንያት የለም። ከጠቅላይ ስታትስቲክስ ቢሮ የተለቀቀ የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያመለክተው (2005 እ ኢ አ) አገራችን ወደ 50 ሚሊዮን የሚደርሰ የከብቶች፤ ከ20 ሚሊዮን በላይ የበጎች፤ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍየሎች፤ ወደ 45 ሚሊዮን የሚጠጉ ዶሮዎችና 2 ሚሊዮን ተግማሽ የሚደርስ የንብ ቀፎ የተሰማራባት በለሃብት ነች። ፈረስ፤ አህያ፤ በቅሎንና ግመልን መረጃው ስላላስፈለገኝ አልጠቀስኩትም። ይኽው ዋነኛ የአገራችን የመረጃ ምንጭም ጽ/ቤት ከላይ በተጠቀሰው ዓመት ብቻ የዘመናዊውን የእንሰሳት እርሻዎች ምርት ሳይጨምር ወደ 3 1/3 ቢሊዮ ን ሊትር ወተት፤ 176 ½ ሚሊዮን ሊትር ጥቂት ፈሪ የግመል ወተት፤ ወደ 40 ሚሊዮ ን ኪሎ ግራም የማር ምርት፤ ወደ 94 ½ ሚሊዮን በቁጥር የዕንቁላል ምርት (ትንሽ ነው፤አንድ ዕንቁላል ለአንድ ሰው እንደማለት ነው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከዕንቁላል በሚገኘው ፕሮቲን ዕጥረት ይሰቃያል ማለት ነው።) ከአነስተኛ ይዞታ ካላቸው አርቢዎች አገሪቷ እንደሰበሰበች ገልጿል። የነፍስ ወከፍ ድርሻችንን ለማወቅ ያው እንደተለመደው ማካፈል ነው ለሕዝብ ቁጥር። ትክክለኛ ቁጥር ከሆነ ይናገራል፤ ይገልጻል፤ ዓይን ይከፍታል። የውሸት ከሆነ ደግሞ አይታይም፤ ምኞት ነው። ስለሆነም ኩነቶችን በአግባቡ አይገልጥም፤ አያስረዳምም። ጉም ነው። ጥጥ ነው። ብን ብሎ ይጠፋል።

በዋናነት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በፍጥነት ለማሳደግ የሚረዳው መንገድ የገበያና የኢንዲስትሪ መሰረትን ሊያስጥል የሚያስችለን በዘመናዊ ዘዴ እርሻ የሚያርሱና የሚያበቅሉ እንዲሁም እንስሳትን የሚያረቡና ተዋጽዖዎችን በብዛትና በጥራት ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ የገበያ ዋጋ የሚያከፋፍሉ እርሻዎችን ማስፋፋትና ቁጥራቸውንም በየጊዜው እንዲጨምሩ በማድረግ ነው። እነዚህኑ ገበያ መርና የዘመኑትን እርሻዎች ማብዛትና ማስፋፋት በአነስተኛ ይዞታ ላይ የሚገኙትን ሰብል አብቃዮችን ሆነ እንስሳት አርቢዎችን እንዲሁም ንብ አናቢዎችንና ዓሳ አስጋሪዎችን ጨምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፤ በጠቃሚም ሆነ በጎጂ ጎኖች እየታየና ውጤቱም በአግባቡ እየተገመገመ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ለውጥና ግፊት እንዲያመጣ ዝግጅቱን ከወዲሁ ማጠናቀቁ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። እነዚህ ሰፋፊ እርሻዎችን ዓይነትና የይዞታ መጠናቸውን ለመግለጽ የተደራጀ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ብዙም ሰለነሱ ማውራትም ያዳግታል። ምን አልባትም ከመንግስት የመሬት መቀራመት ዝብርቅርቅ አሰራር ጋር ያስከተለውን ችግር ተመልክቶም ሊሆን ይቻላል።

ለመሆኑ ከእዚህ አስፈላጊና መሰረታዊ ብለን ከጠራነው ክፍለ ኢኮኖሚ ጀርባ የትኞቹ ተቋሞች ናቸው የሚገኙት? በእኔ ዕይታ በዋናነት ብዬ ከምጠቅሳቸው ልጀምር።

ፓርላማ (ምክር ቤት)

የአገሪቱ የምትደዳርበትን ሕግ፤ ደንብ፤ ሥርዓትን ከሚቀርጸውና ከሚያጸድቀው የሕዝብ ተወካዮችና የፌደራል ምክር ቤት ብንጀምርስ? ይህ በሕዝብ ድምጽ የበላይነት አግኝቻለሁ ብሎ በየአዳራሹ ሰብሰባ በማድረግ የሚያስተላልፈው ውሳኔ መንግስት የሚባለውን ተቋም ፍላጎት ወይስ የአርሶ አደሩን ጥቅም አስጠባቂ ነው? የሕዝብ መሰረታዊውን ፍላጎት ተመልክቶና ተከታትሎ ነውን የተጣለበትን ኅላፊነት የሚወጣውን? ለመሆኑ ስለ አገሪቱ ግብርና ይዞታ በየዓመቱ ስንት ጊዜ እንደ ዋነኛ አጀንዳ ቆጥሮ ተወያይቶበታል? ምንስ ያህል ጠቃሚ ውሳኔዎችን አሳልፏል? በመገናኛ ብዙሃን ዜና እንደምንሰማው የም/ቤቱ አባላት ጎበኙ፤ አደነቁ፤ የሚኒስቴሮችን ረፖርትአዳመጡና ማብራሪያ ሃሳብ ጠየቁ? በቃ ይሄው ነው እርምጃችሁ? አለቀ ደቀቀ! ሕዝብ ስራችሁን የሚገመግመው መንግስት ለማድረግ የፈለገውን በመደገፍ ብቻና በምታወጡት እጅ እንዳልሆነ ስንቶቻችሁ ታውቁት ይሆን? ከተከበሩት የፓርላማው ተወካዮች ተነሳሽነት አሳይተው ከላይ ለጠየቅሁት ጥያቄ ተገቢ መልስ የሚሰጥ ይኖር ይሆን ?

ግብርና ሚኒስቴርና የክልል ግብርና ቢሮዎች

እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በንጉሥ ምንይልክ አስተዳደር ዘመን በአዋጅ በ1907 ዓም የተቋቋመው የአሁኑ ግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስቴር ቀደም ሲል ጀምሮ ለበርካታ ጊዜያት ስሙንም ቀያይሯል። ለመጥቅስም ፦ የእርሻ፤ የእርሻና ሕዝብ ማስፈር፤ የእርሻና የመሬት ይዞታ፤ የእርሻ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት፤ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ስሞቹ ለአብነት ከሚጠቀሱቱ ዋነኞቹ ናቸው። ቁም ነገሩ ከስሙ ምን አለን ነው የሚባለው። ከፊታውራሪ፤ብላቴና ደጃዝማች ማዕረጎችን ጨምሮ በትምህርታቸው የዶክተር ማዕረግ ያላቸውንና በዕውቀታቸው በልምዳችው፤ በክህሎ ታቸውና በአስተዳደር ችሎታቸው የተከበሩና የተመሰገኑ ትጉህ የሆኑት ጨምሮ የወያኔ/ ኢሕአደግ የጦር አበጋዝ የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሠን በሚንስትር ማዕረግ መርተውታል። አንዳንዶቿም ለሁለተኛ ጊዜ በድጋሚ ተሹማዋል። ለመጥቀስም፦ ዶ/ር ገረመው ደበሌና አቶ ዘገዬ አስፋው ናቸው። ፎቷቸውም በካዛንቺስ በሚገኘው የሚኒስቴሪ ጽ/ ቤት መግቢያ አዳራሽ ተስቅሏል። ጠቅላላ ቁጥራቸውን ለማወቅ ከጽ/ ቤቱ ማግኘት ይቻላል። አንዳቸውም ግን የአገሪቱን ግብርና ኢኮኖሚ ከፍ አድርገው ጥግ አልያሲያዙትም ወይም አላነሱትም። ነገር ግን በቀድሞዎቹ ሚንስትሮች ጊዜ አገሪቷ እንዲህ እንዳሁኑ የችጋር፤ የረሃብን የድርቅ ምሳሌ ሆናና ለዜጎቻ ማፈሪያ የሆነችበት ጊዜ ከ1966 ዓም ድርቅ በስተቀር የከፋ ጊዜ በታሪኳ አታውቅም። አንድ የጋራ የሆነ ጠባያቸው አላቸው። ይኽውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጥረታቸው አድናቆትን አልቻራቸውም፤ አላጨበጨበላቸውም፤ ዘፈንም ሆነ ግጥም አልዘፈነምም፤ አልገጠምምም። እኔ የማስታውሰው የዶ/ር ገረመውን መንበር በ1975 ዓም የተረከቡት አቶ ተኮላ ደጀኔ ግን በወሰዱት የፈጣን የመዋቅር ማሻሻያና ማስተካከያ እርምጃ በዋናውና በየክፍለ ሃገሩ ዋና ከተሞ ች ለይ ብቻ ተኮልኩሎ የተቀመጠውን የሰው ሃይል ገበሬውን ተጠግቶ አገልግሎቱን እንዲቸረው በማሰብ በተወሰደው እርምጃ ሰለባ የሆኑቱ እንዲህ ባማለት ተቀኝተው ነበር። በተኮላ፤ ጉዴ ፈላ።

በመሠረቱ ይህ የሚኒስቴር መ/ቤት ሲዋቀር በዋናነት ኃላፊነት የተሰጠው የአገሪቱን ግብርና ልማት ለማስፋፋትና ለማሳደግ ሲሆን በተጨማሪም የተገቢ ፖሊሲ ሃሳብ በማመንጨትና ለተግባራዊነቱም አርሶ አደሩን ማዕከል በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን ደረጃ በደረጃ ለመለወጥ ነበር። ግብርና ሚኒስቴር እኔ እስከማውቅው ድረስ የሰራው መዋቅር እራሱኑ መልሶ አላሰራው እያለ ማነቆ ስለሆነበት እንዲሁ ራሱን በማዋቀር ጥሩ የሥራ ጊዜውን ያጠፋ መ/ ቤት ነው። ዋናው ግብርናን ተልዕኮ የሚያስፈጽመው ክፍል ተገፍቶ ድጋፍ ሰጪና የአስተዳደርና የፋይናንስ ክፍሉ አንበሳ የሚሆኑበት ጊዜ ይበዛል። መዋቅሩ በቀላሉ ስራን በመደገፍ የሚያቀላጥፍ ሳይሆን ትከሻቸውንና ኃያልነታቸውን ለማሳየት ብቻ በሚሞክሩ አለቃዎች ተሞልቷል። መዋቅሩም ቢሆን ግዙፍና ቦርቃቄ ፤ በእዝ ሰንሰለት የተንዛዛ ነው። ዛሬ ደግሞ ይህ መዋቅር በክልል፤ በዞንና እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ የተዋቀረ ነው። ጥያቄው ለምን ተዋቀረ ሳይሆን ተልዕኮውን የአቅሙን ያህል ድርሻውን ይወጣል ነው። አንድ የጥበብ ሰው ሠዓሊን ግብርና ሚ/ርን ሳለው ተብሎ ሥራ ቢሰጠው በብሩሹ እጅግ ግብዳ፤ ግዙፍና ቅርጽ የሌለው ሰው አድርጎ ሰርቶ ያስቃችኋል። ግብርና ሚ/ ር በተማረ የሰው ኃይልም ቢሆን ከትምህርት ሚኒስቴር ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ምሁራኖቹን በአግባቡ የተጠቀማባቸውና በችሎታቸው ያሰማራቸው አይመስልም። የግብርና ሚ/ር ካለው ነገር ሁሉ የዘመቻ ስራ ይወዳል። ደራሲ በዐሉ ግርማ በኦሮማይ መጽሃፉ እንደጠቀሰው ለቀይ ሽብር ዘመቻ፤ ለአረንጓዴው ዘመቻ፤ መሃይምነትን ለማጥፋት ዘመቻ፤ የቀይ ኮከብ ጥሪ ዘመቻና ሌሎችም ማለቂያ የሌላቸው ዘመቻዎች አይነት እኔ በማውቀው ግብርና በሽ ነበር። ዛሬም ቢሆን ይህ በሽታ ጠፍቷል ከነጭርሱ ብሎ ለመናገር አይቻልም። የዘመቻ ሥራ የአንዴ ተግባር ስትሆን ተሰተካክላ በሯሷ አትቆምም፤ አትቀጥልምም። ምንአልባት የዘመቻ ሥራ ለሃገር መካላከያ ሠራዊት በፍጥነት ጠላት ሳይደራጅበትና መሬት ሳይዝበት ሊጠቅመው ይችላል። ለሁሉ ነገር ግን ዘመቻን እንደ ዋነኛ የስራ ስልት አድርጎ መቀጠል ሥራን ያበላሻል። የሕግ አስፈጻሚነት ድርሻውን ከኤክስቴንሻ ን አገልግሎቱ መለየት መቻል አለበት። የሚያወጣቸው መረጃዎቹና የሰብል ግምገማ ረፖርቶቹ መሆን ያለባቸው በተጨባጭ በተሰበሰቡና እውነትነት ኖሯቸው በሚያሳምኑና ምክንያት ባላቸው ላይ ተመስርተው እንጂ የባለሙያውን ግምት፤ፍላጎትና ዕውቀት ብቻ መሰረት አድርገው መሆን የለባቸውም። ጥሩ ምርታማነት በተወሰኑ በጣት የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ውጤት ብቻ እያጎላን ስለ ተቀረው ገበሬ ጭምር አድርገን የምናወራና ረፖርት የምናደርግ ከሆነ እየሰራን ሳይሆን ምኞታችንን እያጋነንን ነው የምንገልጸው። በተጨማሪም ነፍሳችንን ነው ደስ ያሰኘናት እንጅ በተጨባጭ ያረገገጥነው የለም። ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ገበሬ ምርታማነት በዓለም በሚገኙት ገበሬዎች ሁሉ በአብዛኛው ምርቶቹ በዝቅተኛ ደረጃ ለይ ነው። በ1980ዎቹ መጨረሻና 1990ዎቹን ይዞ በዘመቻ መልክ የተጀመረው “ኤክስቴንሺን ፓኬጅም” በአንዳንድ ስፍራዎች ምርትና ምርታማነተን ቢያጎናጽፍም በሌሎች አስፈላጊ ተብለው በተጠቀሱ ስልቶች ስላልታገዘ የተፈለገውን ውጤት ያመጣ አይመስልም። “የኤክስቴንሺን ፓኬጁም” በአንዳንድ ክልሎች፤ ዞኖች፤ ወረዳዎችና በተለያዩ ልማት ጣቢያዎች የፉክክርና የመበላለጥ ስሜት የነገሰበት አሰራር እንዲነግስ መንገድ በመክፈቱ ስራዎቹን ለመከታተል የልማት ሰራተኞቹ በውጥረት እንዲሰሩ አስገድዷቸው እንደነበር በገሃድ የታየ ሃቅ ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ የአንድ ሰሞን የዜና ዘገባ መሰረት ክልሎችም ሆኑ ወረዳዎች ጤናማና አካባቢን ያላገናዘበ ውድድር ውስጥ የገቡ ይመስል ይሄን ያህል ገበሬዎች በዚህ ፓኬጅ ታቀፉ፤ ይሄን ያህል መሬት በዚህ ሰብል ተሸፈን፤ ይሄን ዓይነት ግብዓት በዚህ መጠን ለገበሬው ተሰራጨ፤ ይሄን ያህል ምርት ተሰብሰቦ ይሄን ያህል የሚገመት ብር ገበሬው አገኘ፤ የገበሬው ምርታማነት ጨመረ የሚል የተጋነነ ወሬ መልቀቅ ስራዬ ተብሎ ተይዞም ነበር። አንዳንዴም ታረሰ የሚሉትና ተገኘ ብለው የሚዘግቡት ደግሞ ከሰብሉ የዘር መጠን በብዙ የዘለለ አይመስልም ( አጃይባ ነው)። እነዚህ የተጋነኑና እጅግ ጥቂት ገበሬዎችን የሚገልጹ ረፖርቶች ከፕሮፓጋንዳ ከመንዛት የዘለለ ለድሃው አርሶ አደር አስገኝተውለታል ተብሎ የሚነገር የኑሮ ለውጥም፤ ሸማቹንም ህብረተሰብ ጨምሮ ካለምንም ማጋነን የለም። ይህንንም ስል ስራዎቹ አልተሰሩም፤ አልተለፋም፤ አልተደከመም፤ አልተወጣምና አልተወረደም ለማለትና ለማጣጣል ፈልጌ አይደለም። ስንቱ በየክልሉ፤ በዞን፤ በየወረዳውና በየልማት ጣቢያው የሚገኝ የልማትም ሆነ ከስራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላችው ሁሉ ባጭር ጊዜ የመስክ ስልጠና በዘመቻው ላይ ተሳትፈዋል። ይህንንም በዓይኔ በብረቱ ያየሁት ነው። ችግሩ ግን ጋዜጠኞች ተብዬዎቹ ስራውን በአፋቸው ላይ በፕሮፓጋንዳ ጨረሱት። የበረከተውና የተለቀቀው ” የዜና ምርት “ እንጂ የእህል ምርት ሆኖ አልተገኘም። በቁጥርና በአኅዝ የገበሬውን ቤት ምርት በምርት አደረጉት። ይገኛል ተብሎ ተገምቶ የተሰጣቸውን ምርት በመሰላቸው ዋጋ እያባዙ ጭቁኑን ገበሬ ብር በብር አደረጉት። አሁንም ደግሜ እናገረዋለሁ እነዚሁ ጋዜጠኞች ከሂሳብ ትምህርት ጥሩ አድርጎ የገባቸው መደመርና ማባዛት ብቻ ነው። አንድ ገበየሁ ውቤ ለአንድ ሺ የዘመኑ ጋዜጠኞች ተብዬዎች ይበቃል። ይህንንም ስናገር ታዲያ የተከበሩና በዘገባቸው የተደነቁና የሕዝብ ይሁንታ የተቸራቸውም የሉም ለማለት ግን አልደፍርምም፤ አይዳዳኝምም። ሁሉም ስራው ያውጣው!
አብረሃም ሊንከልን የተባሉት የተባባሩት አሜሪካ መንግስት የቀድሞ ፕሬዚዳንት የሳቸውን መንግስት የግብርና ዴፓርትመንት “ the people’s department,” ብለው ይጠሩት እንደነበር ከአንድ ” አሜሪካኖችና ግብርናቸው” ከሚል የቆየ መጽሔት ላይ አየሁት። እንግዲህ እንደሳቸው አባባል “ሕዝባዊ “ ማለታቸው አይደል። አዎን! ሕዝብ እየራበው፤ ጠኔ እያዳፋው፤ በምግብ እጥረት በሽታ እያንገላታው እያለ ስለ ሌላ ልማት ብንነግረው ትርጉም የለውም። በቂ ምግብ ካላገኘ የማሰብም፤ የመስራትም፤ የማምረትም፤ የመጀገንም አቅምና ታሪክ የመስራት ችሎታውም ይቀንሳል። ረሃብ ክፉ ነው። ቅስም ይሰብራል፤ ያስከፋል፤ ከሰውነት ጎዳና ያወጣል፤ ያሳፍራል፤ ያሰድዳል፤በመጨረሻም ይገድላል። ሕዝብ የመብላትም ሆነ ጤናውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው መንግስታዊ ተቋሞች ሁሉ ይህንን ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን ተገንዝበው ነው ወደ ሥራቸው መግባት የሚችሉት እንጂ እንዲሁ ግድ የለሽ ሆኖ ሥራን መጀመር ያስጠይቃል።

ሌሎቹን ተቋሞችም እንዲሁ በጨረፍታ ወይም በወፍ በረር ቃኘት አድርጎ ማለፍም ተገቢ ነው። እነሆ! በጥቂቱ።

የግብርና ምርምር ተቌሞች

ከተመሰረተ ግማሽ ምዕተ ዓመት እያስቆጠረ ያለው የግብርና ምርምር ተቋም ዛሬ ላይ ራሱን በፈዴራልና በክልል በሚተዳደሩና በአገሪቱ የተለያዩ የግብርና ሥነ ምህዳር ቀጠና በመከፋፈል ምርምሩን እነደሚሰራ ይታወቃል። ዛሬ ቁጥሩ 55 የሚደርስ የምርምር ተቋም፤ ማዕከልና የሙከራ ጣቢያዎች እንዳሉት ይገለጻል። በመሠረቱ ምርምር ሁልጊዜ ከምርት ቀድሞ ይገኛል። ዛሬ የተገኘውን የምርምር ውጤት በአንድ ጀምበር ማሰራጨት አይቻልምም፤ አይታሰብምም። ነገር ግን የምርምሩ አካሄድ መሆን ያለበት በቅደም ተከተል የአገሪቱ ግብርና ዕድገትና ልማት ላይ ማነቆ በሆኑ ችግሮች ላይ ቅድሚያን ያስቀምጣል። መጨመር የምፈልገው ነገር ቢኖር ሌሎች አገሮች ጫፍ የደረሱበትንና የተራቀቁበትን እኛ ግን በሰለጠነ የሰው ኃይል፤ በመሳሪያዎች፤ በበጀት ዕጥረትና በአሰራር ደንብ ባልተዘጋጀንበት የምናስበውን ለጊዜው ትተን፤ ምርምሩ የአካባቢ ገበሬውን ዕውቀትና ክህሎት መሰረት አድርጎ ቢንቀሳቀስ ወደ ተግባር ለመለወጥ ያፈጥናል። ትኩረት ለሃገሪኛ ዕውቀትና ልንሰራ በምንችላቸውና ፈጣን ለውጥ ልናገኝባቸው፤ ወደ ተግባር በቀላሉ በሚመነዘሩት ላይ አትኩሮት ማድረግ ሳይሻል አይቀርም በማለት አስተያዬቴን በዚህ ተቋም ላይ ልቋጭ።

የግብርና ትራንስፎርሜሺን ኤጃንሲ

አዲስ የተቋቋመው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲም ያዘጋጀውን ሰነድ መሰረት አድሮጎ መንቀሳቀስ ተቻለ መሰረት ለመጣል ደግ እርምጃ ነው። መቼስ በወረቀት የሰፈረና ያማረ ነገር የሃሳብ ነጸነት በሌለበት አገር ወደ ተመኘው ለመጓዝ እክል አያጣውም። ነገር ግን የመንግስት ዶማዎች፤ ቡሾች፤ “ቹሽኪዎች” እየቆፈሩ በአሰራሩ ለይ ማነቆ እንዳይሆኑበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻዋል። “ቹሽኪ” በቡልጋሪኛ ቋንቋ ቃሪያ ማለት ሲሆን ቃሉንም አንዳንድ እድሜ ጠገብና ነገር በምሳሌ ዕውቀታቸው ልክ ጥግ የደረሰባቸው አዋቂዎች ብቻ ይጠቀሙበታል። እንግዲህ በኛም ቢሆን ቃሪያ አንድም ይለበልባል፤ ያቃጥላል፤ ሰው ይፈጃል። ከፍ ሲል ደግሞ እንዲህ ” የበሬ አፍንጫ “ አይነቱ ትልቁ ቃሪያ ደግሞ ውስጡ ባዶ ቦሸቃ ስለሆነ መሰለኝ እኒያ ቡልጋዎቹ ይህንን የሚናገሩቱ። ሰለ ወደፊት ዕጣው በጎ ከመመኘት በስተቀር ለወቀሳ ገና ልጅ “ሙጫ” ነው። እንደ ስሙ ያድርግለትና ለውጥ ለማምጣት ያብቃው። ኤጀንሲውም አሜን እንደሚል ተወዲሁ ይታየናል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች

የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞችም በዘርፉ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይል አምራቾችና አቅራቢዎ ች ስለሆኑም ልዩ ትኩረትን ይሻሉ።በትምህርቱ ዝግጅትም የሚያስተምሯቸውን ወጣቶች የኢትዮጵያ ግብርናን የሚገልጽ በኮርስ ደረጃ አዘጋጅተው እዚያው በትምህርት ላይ ሳሉ መተዋወቁ እጅግ አስፈላጊ ነው። ምሩቃኑ ወደ አገልግሎት መስጠት ሲሸጋገሩ በቀላሉ ችግር የመፍታት አቅማቸው ይዳብራል። አለባለዚያ እንደገና አዲስ ተማሪዎችና ሠልጣኞች ይሆናሉ። ትምህርት ቤቶቻችን የድምጻዊያንና የገጣሚያን ጥበ ብ ተሰጥኦ ያላቸውን ማሳያ መድረክ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ይህንኑ መሰረት በማድረግም ተማሪዎቻችን የሂሳብ ፤ የሳይንስ፤ የምህንድስና፤ የጤና፤ የምግብ ቴክኒዎሎጂና ሌሎች ተዛማጅ ዕውቀቶች ችሎታ ያላቸው መገኛ (መናኽሪያ ) መሆናቸውን ጭምር ማሳየት መቻል አለብን። ከበቂና ከተሟላ ዝግጅት ጋርም የተማሪውን ብዛትም ሆነ ጥራት ለማስተካከል ለአፍታ ቸል መባል የማይገባው ጉዳይ ነው። ብዛቱን ከጥራቱ ጋር ጎን ለጎን ለማስኬድ የሚያስችል አማራጭም አስቀድሞ እንዳለ መገንዘብ አለብን። በዚህ ጎዳይ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ምሁራንን ሃሳብ አለመረጃ ማጣጣል ተገቢም አይደል፤ እንዲያውም ይወገዛል። አስተምራ የልጆቻን ዕውቀት የምታባክን አገር ብትኖር እምዬ ኢትዮጵያ ነች። የሰው ሃይልም በአግባቡ ካልተገለገሉበትም እንደ ሌሎቹ ሃብቶች ይባክናል፤ መቅኖ ያጣል። የወደፊቱ ምሁራኖች ተቀርጸው የሚወጡበት ማዕከልም በመሆኑ፤ ተማሪዎች በፍርሃት ሳይሆን በነጻነት ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ መሆንም ሲችል ጭምር ነው። በአገራችን የመጀመሪያው የእርሻ ትምህርት ተቋም አምቦ ከተማ የሚገኘው የዛን ጊዜው የአምቦ እርሻና ቴክኒክ ትምህርት ቤት እንደሆነ ያውቃሉን? በ1939 ዓም እ ኢ አ የተመሰረተው ይኽው የእርሻ ትምህርት ቤት ፶ ኛውን የወርቅ ኢዬቤልዩ በወርሃ የካቲት 1989 አክብሯል። እኔም በቦታው ተገኝቼአለሁ። ፸፭ኛውን ለማክበር ደግሞ በ2014 ዓም ዕድሜ እንመኛለን። ቪቫ አምቦ እርሻ ተቋም!!! ዛሬ አምቦ ዩኒቨርስቲ።

የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅቶች

ሌላዎቹ ደግሞ የግብርና ምርት ማሳደጊያ አቅራቢዎ ች ናቸው። የመሬት ማዳበሪያና ጸረ ተባዮች ኬሚካሎችን በማቅረብ ይታወቃሉ። በተለይ የመሬት ማዳበሪያ አቅራቢዎቹ በመንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ንብረት ናቸው። በገበሬው ልፋትና ኪሳራ ንግዳቸውን በትርፍ ያጣድፋሉ። ለገበሬው በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ ፤አያቀርቡም መንግሥትስ ገበሬውን በዋጋ ይደጉማል፤ አይደጉምም መረጃው የለኝም። ቀደም ሲል የነበሩት የግል አስመጬዎች ግን ከጨዋታው ውጭ እንደሆኑ የኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ኃ/ተ/ማን ብቻ ማስታወሱ ይበቃል። በርካታ የግል ካምፓኒዎችም በጸረ ተባይ አስመዝጋቢነትና የተመዘገቡትን ጸረ ተበዮች ወደ አገር ውስጥ በፍቃድ በማስገባት ያከፋፍላሉ። ገበያ መር ላልሆኑ ገበሬዎች ግን አንዳንዶቹ ዋጋቸው ከገበሬው የመግዛትና የመጠቀም ጥቅም አንጻር ሲታይ በለው የሚያሰኝ አይዶለም ። ለኢትዮጵያ ገበሬዎች የተሻሻሉና የተመረጡ ዘሮችን በማቅረብ በዋናነት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት የሚባለው መንግሥታው ድርጅት ሲሆን በአነስተኛ መጠን ደግሞ የግልም እንዳሉ ይጠቀሳል። ቢሆንም የገበሬውን የምርጥ ዘር ፍላጎት በዓይነትም፤ በብዛትም ለማሟላት አልቻሉም። ዘርን በማምረትና በማከፋፈል እንቅስቃሴ መሳተፍ ለሚፈልጉ ባለ ሃብቶች መስኩ ብዙ ተወዳዳሪ የሌለበት መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እገልጻለሁኝ። ባልተፈታው የመሬት ጥያቄ ምን ያህል ያስኬዳል? መልስ የለኝም።

የገበያ ሥርዓት ማስፋፊያ ድርጅቶች

የግብርና ምርት የገበያ ሥርዓት ምን ይመስላል የሚለውን ለመመልከት በቂ መረጃ ባይገኝም በገበያው ሥርዓት ገበሬው ላለመጠቀሙ ግን በተዘዋዋሪ መናገር ይቻላል። የቀድሞው የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት አሰራር ግን በአምራቹ ገበሬ ላይ ተመልሶ እንዳይመጣ ለማስገንዘብ እንወዳለን። እ ሰ ገ ድ ገበሬውን እያስለቀሰና እንደ ኩዳዴ ወር (የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች የሚጾሙት ነው) ድመት (ሰሞነኛ አባባል ነች። ቃሉን ከመገናኛ ብዙሃን እሰጥ እገባ ነው ያገኘሁት) እያከሳ ፤ዓይጥና ዓይጠ መጎጥ ግን እያኮራና እያወፈረ መኖሩን በጀብራሬዎች አንደበት ሲገለጽ እንደነበረው “ ኩራ እንደ እ ሰ ገ ድ ዓይጥ” እንደተባለው ዓይነት ጨዋታ ግን መስማት አንፈልግም። ለገበሬው ምርት በጥናት ላይ የተመሰረተ ዋጋ እንዲከፈለው እንጂ በርካሽ ዋጋ ተገዝቶ መንግስት ለሸማቹ ኅ/ሰብ ዋጋ ለማረጋጋት በሚል ሽፋን ብቻ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የሚደረገው ጨዋታ መቆም አለበት።

የመስኖ ልማት ድርጅት

የመስኖ እርሻ የሚሰጠውን ጥቅም ማውራት እንደው ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆንብኝ ጥቂት ብቻ ልበል። የአሜሪካውን ካሊፎርኒያ ግብርና ያየ ደግሞ አብዛኞውን የካሊፎርኒያ ደረቅ ሸለቆዎችን እንዴት በቋሚተክሎች ፍራፍሬዎች፤ በአትክልቶች፤ በሩዝ ሰብል፤ በጥጥና በከብቶች መኖ ምርት አልምቶ የዛሬዋን ካሊፎርኒያ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የ40 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት አድርጎ በአገሪቱና በዓለም ደረጃ ቀዳሚ ስፍራ እንዳስያዛት መናገር ደግሞ አስፈላጊ ይመስላኛል። ስለኛ ግን መናገር የምፈልገው ነጥብ አለኝ። ይኽውም በመስኖ ልናለማው የሚችል በሚሊዮኖች የሚገመት መሬት እንዳለንና ይህም ስታትስቲክስ ከዘመነ ደርግ ብዙም ፈቀቅ እንዳላለ ነው የምንረዳው። የመስኖ ውሃ ለረዥም ጊዜ አገለግሎት ለይ በአግባቡ እንዲውል ካስፈለገ የመስኖ ሥራ መዋቅር በመስክ ላይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ለውሃው አስተዳደርና ፍትሃዊ አጠቃቀም ከወዲሁ እንዲታሰብበት ለማስገንዘብ ጭምር ነው። የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ወሃ አጠቃቀም ነገን ጭምር ማሰብ አለበት። መንግስት እንዲህ ዓባይን ለመገደብና የኃይል አጠቃቀማችንን ከፍ ለማድረግ የሚሰሩትን ሥራም ጎን ለጎን የተገኘውንም ዕውቀትና ክህሎት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ዋነኛው የሆኑት የውሃ ምንጫችን ወንዞቻችንን በመጥለፍ በዓመት ሁለቴና ከተቻለ ከዚያም በላይ እንድናመርት ቢያደርጉን ምንኛ በታደልን። አዋሽ፤ ባሮ፤ ጊቤና ግልገል ጊቤ፤ ሶርና ገባ፤ ዴዴሳ፤ ዳቡስ፤ ዋቢ ሸበሌ፤ ሻያ፤ ቦርከና፤ ጀማ፤ ጉደር፤ ያዩ፤ ፎገራ፤ የጨዋቃ፤ ኦሞና በዕውቀት ማነስ ምክንያት ያልጠቀስኳቸውን ሁሉ ጨምሮ በምድራችን በደጃፋችን አይደል የሚፈሱት።በእጃችንና በደጃችን ያለውን የውሃ ሃብትም ከምርጥ የአገሪቱ መሃንዲሶች ጋር መክረው መስኖ በመስኖ ቢያደርጉን ምን ገዶአቸው። ተው ስማኝ አገሬ ማለትስ ይዀው አይደለምን? በ1971ዎቹ የተጀመረው የአረንጓዴው ዘመቻ ያስከተላቸው ጥፋቶች ነገር ግን ምንም ያልተነገረላቸው የውሃ ሃብት አጠቃቀም ችግሮች ነበሩብን። እንዲህ ልግለጸው። የጨፌ መስኮችንና ረግረግ መሬቶችን በማጠንፈፍ ወደ ልማት ማምጣት በሚል አደገኛ ስልት ስንት እርጥብና ረግረግ መስኮችን አድርቀን ዛሬ ወደ ሜዳነት የለወጥናቸው ሥፍራዎች እንዳሉ አንባቢያን እንዲረዱልኝ፤ የልማት አርበኞቻችንም ግንዛቤ እንዲጨብጡልኝ ፈልጌ ነው። እርጥብ መሬቶችና ረግረግማ ሥፍራዎች ለወንዞቻችንና ለጅረቶቻችን መጋቢ አናት መሆናቸናውን እንኳን እኛ ድኩማን የግብርና ባለሙያዎቹ ግንዛቤ ሳንጨብጥ ፤ በአንድ ወቅት የኢሉባቦር ዋና አስተዳዳሪ ተብለው የተሾሙት በልማት ስራቸውና ሕዝብን በልማት ማሰማራት ዋና ሃይል እንደነበር በአመራራቸው የታወቁቱ አቶ አንሙት ክንዴ በአንድ የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ሥራ ዓመታዊ ግምገማ ላይ ነበር የኛዎቹ የግብርናው ልማት ስራ መሪዎቹ ረፖርታቸውን ሲያቀርቡ ልክ ግዳይ እንደጣለ አንበሳ ይሄንን ያህል የጨፌና ረግረግ መሬት ወደ ልማት አመጣን እያሉ ለተሰብሳቢው ሲደሰኩሩ አዳምጠው ጉዳዩ ልማት ሳይሆን ለነገው የውሃው ሃብታችን የጥፋት መጀመሪያ መሆኑን በመብለጥ የተናገሩት። የአለም ማያ፤ የአደሌና የላንጌ ሐይቆች፤ አናታቸው የጨፌ መስክ የነበሩት የሐረር ሐማሬሳ ከተማ ከበው ወደ ፈዲስ የሚፈሱት ሁለት ወንዞችና የኢሉአባቦር እርጥብና ረግረግ መሬቶች ዛሬ ደርቀውና አንዳንዶቹ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ለመገኘታቸው ለእኔ ዓይነተኛ ምሳሌዎችና አስረጅ ናቸው። እንክብካቤና ጥበቃ ለርጥብና ረግረግንም ሥፍራዎች ጠቃሚና ዓይን ከፋች ስልት ነው።

የገጠር መሬት ሃብት አስተዳደር ተቋም

የኢትዮጵያ መሬት የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሃብት በመሆኑ አገልግሎቱም በቅድሚያ ለኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች መሆን ይገባዋል። ኢትዮጵያዊያን በመሬታቸው የበቀሉትን ምርቶች ቅድሚያ ተጠቃሚ እንጂ ተመልካች መሆን የለባቸውም። አገራቸው ያፈራውን ምግብ እነርሱ ሳይቀምሱና ሳያጣጥሙ የሌላ አገር ሰዎችን መቀለብ ከሞራል ጥያቄም ባሻገር መብታቸው መሆኑን አስረግጬ መናገር እሻለሁ። ግብርናውን ለማዘመን በሚል ፈሊጥ ለዘመናት በመሬቱ በዘልማድ መንገድ ሲንከባብና ለምነቱን ሲጠብቅ የኖረውን አገሪኛ ሰዎች እያፈናቀልን ለውጭ ኢንቨስተር መሬትን የሚያክል ንብረት እዚህ ግባ በማይባልና የነዋሪውን ጥቅም ባላገናዘበ መልኩ የሚካሄደው የመሬት መቀራመት የኋላ የኋላ የሚጎዳው አገርና ሕዝብ ነው። ጥቂት ባዕዳንን ሃብት በሃብት ላይ እንዲጨምሩ ብቻ በማሰብ፤ድሃን ከሚወዳት መሬቱ ማፈናቀል ሃጢአት ነው። የሕዝቡን ህልውናና ደህንነት ሳይሆን እያስከበርን ያለነው በላዩ ላይ አደጋና ተጨማሪ ስጋት ነው እያስቀመጥን ያለነው። በተጨማሪም በስራ ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ስም ጥቂቶች እንዲከብሩና የሃብት ደረጃቸውን ከፍ ባማድረግ የሚቀመጡበትን ልክ እንጂ ያሻሻልነው የሕዝቡን የምግብ ዋስትና አይደለም እያረጋገጥን ያምንገኘው። ሃብት ፈጣሪው ሕዝብ ይሄ ስንኩልና ጎዶሎ አሰራር ይጎዳዋል፤ በአገሩም ባይተዋርና የበይ ተመልካች ያደርገዋል። ከልቡም ልማት ተብዬው እንቅስቃሴም አያሳትፈውም። የውጭ ኢንቨስተመንት በሌሎች የስራ መስኮች ተጨማሪ ሃብት ማስገኘት ይቻል ይሆናል። በግብርናው ክፍለ እኮኖሚ ግን በተለይ ከመሬት ጋር በተገናኘ ላይሰራ ይቻላልና ጠንቀቅ ማለቱ ከፖለቲካ ዝርክርክነትና አስቸጋሪነት አንጻር ሲታይ ማለፊያና ይበል የሚያስኝ ሙያ እንዳይደለ መሬቱን እየቸረቸሩት ለሚገኙት የመንግስት ተቋም ሹመኞችና ጥቅመኞች ጉዳዩን በትኩረት እንዲመለከቱት ይሁን ስል እጠይቃለሁ። እስከዛው ግን መስራት በምንችለው አቅማችን ቅድሚያ ለኢትዮጵያዊያኑ ይሁንልን። ለውጭ ባለ ሃብት የከፈትነውን ዕድል ሳናጓድል የአገሪቱን ባለሃብቶች እንዲጠቅም አድርጎ ማሳተፉ ተገቢ ነው።

የሙያ ማኅበሮቻችን

በአገሪቱ በርካታ የሙያ ማኅበሮ ች አሉ። ለመጥቀስም፦ የሰብል ሳይንስ፤ የአዝርዕት ጥበቃ፤ የኢኮኖሚክስ፤ የየደን ልማት፤ የእርሻ መሃንዲሶች፤ የምግብ ጥናት፤የጤና፤ የገበያ ጥናት፤ የሥነ ሕይወት፤ የአፈር ሳይንስ፤ የኮንስትራክሺን፤ የሜካኒካል መሃንዲሶ ችና ሌሎችም። አንዳንዶቹ ዕድሜ ጠገብ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ገና ሙጫ ናቸው። የምግብ ዋስትናቸው ከእድሜያቸው አንጻር ገና አልተሟላም። በምግብ እጦት፤ በጠኔ፤ ችጋርና ድርቅ ምክንያት በእድሜያቸው ማስመዝገብ ያለባቸውን ቁመትም ሆነ ክብደት ገና አልደረሱበትም። ዓመታዊ ጉባኤ ያካሂዳሉ፤ የምርምርም ሆነ የልማት ጥናት ወረቀቶች ይቀርባሉ። ውይይት ይደረግባቸዋል፤ ጥያቄዎች ይቀርባል መልስ ይሰጥባቸዋል። ዕውቀት ይጨምራል፤ ልምድ ይካበትበታል፤ ማን ምን እንደሆንና ምን እንደሚሰራ ይታወቃል። ጥሩ ነው። ዕውቀት ለብቻው ከሆነና ወደ ተግባር በሰንካላ አመራርና ፖሊሲ ካልተተረጎመ እንደምን ይጠቅማል? ምሁራን ስለሙያቸው ዋጋ ትክክለኛውን ካላወሩበት፤ የተሳሳተውን ካላስተካከሉበት፤ ሁሉ ነገር ፖለቲካ ነው ብለው ካመኑበት፤ ዕውቀት ከጋን ውስጥ መብራትነት አልወጣችም ማለት ነው። ትምህርት ለምርምር ለምርትና ለችግር መፍቻነቷ ታዲያ ለመቼ ነው? ምነው ስለ ሙያችን አንደበታችን ተዘግቶ የፓርቲ ፖለቲከኞች ስለ ሙያችን ደግመው ሲያስተምሩን ለመማር ፍቃደኞች ሆንን? በሙያችን ቀድመን መታየት ሲገባን ዛሬም ተማሪዎች ነገም ተማሪዎች ሆነን መታየት ፈለግን? ዕውቀታችንን መሰረት አድርገንማ ሃሳባችንን መግለጽና ማብራራት ካቃተን አካላችንንም ሆነ ኀሊናችንንም ጭምር ምርኮኛ አድርገናል ማለት ነው። እግዚኦ ከዚህስ ይሰውረን! ካለፈ በኋላስ ቢናገሩት ማንን ሊጠቅም? ትንሽ፤ ትንሽ ካሁኑ ጀምሮ እንናገር። ትንሽ ትንሽ መስዋዕት እንሁን። እንግዲህ ሺ ዓመት አይኖር።

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች

ከዚሁ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ጀርባ ደግም መንግስታዊ ያልሆኑ የሚባሉ ምግባረ ሠናይ ድርጅቶች አሉ። በንጉሱ ጊዜ በቁጥርብዛታቸው በአስራዎቹ ሲገመቱ፤ በደርጉደግሞ በመቶዎቹ ነበሩ። ዛሬ ግን ቁጥራቸው ከ1500 በላይ እንደሆኑ በቅርቡ የኢሳ ቱ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እንግዳ አድርጎ ያቀረባቸው ባለሙያ በቃለ መጠይቅ ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል። አብዛኛዎቹ በገጠር የሚገኘውን የሕዝብ ክፍል ለመርዳትና በአኗኗሩ ላይ ለውጥ ለማምጣት የተሰለፉ አጋዥ ኃይሎች ናቸው። በሰብል ልማት፤ በውሃና አፈር አጠባበቅ፤ በአነስተኛ መስኖ አገልግሎት፤ በደን ልማት፤በሰብል ዘርና ሌሎች የተክል መራቢያ አካሎች በማቅረብ፤ በጤናውና በኑሮ ዘዴውና በሌሎችም ለተጠቃሚው አገልግሎ ቶችን በማቅረብ ይታወቃሉ። አገልግሎታቸው ምን ያህል ጠቅሟል የሚለው ውስጥ ለመግባት ሌላ ክትትልና ጥናት ስለሚያስፈልገው እዚያ ውስጥ የምገባበት ችሎታውም አቅሙም የለኝ። እዚሁ ዘንድ ላቁም። ብቻ ከገበሬው ኑሮ ጋር እንደተሰለፉ ለመግለጽና ለመረጃ ያህል ነው ያቀረብኩት።

ታዲያ ይህ ሁሉ የተቋምና የሰው ሃይል ተሰልፎና ተግባሩን ካከናወነ ለምንድነው ከዚህ አ ስከፊና ጎስቋላ ኑሮ እኛ ኢትዮጵያዊያኑ መውጣት ያቃተን? የኔም፤ የናንተም ፤ የሌሎችም የኛን ችግር መስማት የሰለቻቸው የዓለም ህብረተሰብ ክፍሎች ዋነኛ ጥያቄ ነው። አገራችንን ሁላችንም በምንፈልገው ና በወደድነው መልኩ ተርጉመናታል፤ ተረድተናታል። ቁም ነገሩ ግን ያለው መለወጥ (ቃሉን ጠበቅ ተደርጎ ይነበብ) መቻሉ ላይ መሰለኝ።

ለማጠቃለል ሙከራ እናድርግ። ላለፉት 6ትና 7 ዓመቶች መሰረታዊ የሚባሉት የምግብ እህሎችና ውጤቶች ዋጋቸው በፍጥነት ዕለት በዕለት እየናረ አይቀመሴ ደረጃ ለይ ደርሷል። በውጤቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች በልቶ ማደር ምኞት ሆኖባቸዋል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሰማይ ያህል እርቋቸዋል። ትናትን ማመስገን ከተጀመረ ሰነባብቷል። ኑሮ ተወደደ፤ መብላት አልቻልንም የየዕለት የሕዝብ እሮሮ ነው። ጋሽዬዎችና አባቶች ኪሳቸው ባዶ ነው፤ እትዬና እናቶችም የእጅ ቦርሳቸው ለስሙ ነው ያለው። ደፍሮ የመግዛት አቅማቸው ተሟጧል። ጥያቄው ከገዢዎችችን መልስ ጋር አልተጣጣመም። የጥያቄው መልስ በተጓዳኝ መስመሮች መንገድ ላይ ነው እየተጓዘ የሚሄደው። ተጓዳኝ መስመሮች አይነካክም፤ አይገነኙም። ጉዟቸው አይደረሰበትም፤ የትዬሌሌ ነው። ምግብን በገበያ ላይ ማየት እንጂ ገዝቶ መጠቀም አቅም ቀን በቀን እየተሸረሸረና እየጠፋ ነው።

ምግብ መብት ነው ተብሎ አገሮች ሁሉ መሰረተ ሃሳቡን ከተቀበሉትና ያንንም ለመተግበር በየዓመቱ መሃላና የድርጊት ፕሮግራም ከተነደፈለትም ሰነባብቷል። በርግጥም ሰናስበው ደግሞ መራብና በችጋር ጠኔ ስቃይ ማየትም መብት ነው ብሎ የሚከራከር ጤናማ አእምሮም ያለው ሰው ያለም አይመስለኝም። ያለመራብ መብት እንጂ የመራብ ግዴታ የለብንም። ባጭር አገላለጽ መራብን የሰው ልጆች ሁሉ ሊጠሉትና ልንጠየፈው የሚገባ ውጉዝ ሁነት ነው። ዱሮ እንደምናስበው የ 40 ቀን ዕድልና ዕጣም አይደለም፤ የእግዜርም ቁጣም ሊሆን አይችልም። እንደ ዜጋ ሁሉም ሰዎች ለኑሯቸው የሚበቃ አስፈላጊውን አልሚ ምግቦ ች የያዘ ምግብ ማግኘት አለባቸው። ምግብ መብት ነው ሲባል ደግሞ መንግስት የሚባለው ተቋም በየቤቱ እየዞረ ምግብ ያድል ማለትም አይደለም። ነገር ግን በዋናነት ሰው በፈጠረውም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ችግር ምክንያት በጊዜያው፤ በአጣዳፊና ሥር በሰደደ የምግብ እጦት ችግር ሰለባ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች አለምንም አድልዎ ሰው በመሆናቸው ብቻ መታደግ እንዳለበት ለመግለጽ ነው። የመንግስት አንዱ ተግበር በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩትን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደህንነትና ጤናቸውን መጠበቅ ነው። ይህም በመሆኑ መንግስት ለአሰራር ያመቸው ዘንድና ተጠያቂነቱንና ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የምግብ ዋስትና ሕግና ደንብ አውጥቶ ካለምንም አድልዎ መተግበር አለበት። ለዜጎቹ መራብና መጎሳቆል ሃላፊነቱ የመንግስት እንጂ የሌሎች እንዳልሆነ ጠንቅቆ ማወቅ ያሻዋል። የኢትዮጵያ ምድር አንዱ በልቶና ጠግቦ የሚያደርገውን ያጣበት ሌላኛው ደግሞ ረሃብን እያሰበና እየተጨነቀ የሚኖርባት ምድር መሆኗ ማቆም አለበት። ምግብ አንዱን ወገን ጠቅሞ ሌላውን መጉጃ መሳሪያ መሆን የለበትም። ክቡሩን የሰው ልጅ ማስራብና በጠኔ ማንገላታት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ስለሆነ ” ውጉዝ ከመአርዮስ” መባል ያስፈልገዋል። ወንጃልም ስለሆነ እንደየደረጃው ያስጠይቃል፤ ብያኔም ያሰጣል ፤ ያሳስራል፤ ምህረትም አያሰጥም፤ ከፍም ካለ በሞት ያስቀጣል። ድሃን መርዳት እንጂ በረሃብ መቅጣትም በሃይማኖቱም አስተሳሰብ ቢሆንም ኩነኔ ና ሃጢአት ነው። ከአካል ሞት በኋላም ላለው መንፈሳችን በመንግስተ ሰማያትም አያስገባምም ፤ እንዲያውም በጀሃነም ያስቀጣል። በአንድ አገር፤ ክልልና ቀዬ የሚኖሩ ሕዝቦች እንዲህ ቅጥ ያጣ የተመሰቃቀለ ኑሮ የሚገፉበት ዐብይ ምክንያት የፖለቲካው ምስቅልቅልና በጥቅም የተሳሰረ የኢኮኖሚ መዋቅር በመሆኑ፤ ይህ ችግር ሳይቃለለ የምግብ ዋስትናን ከቃላት ባሻገር ልናገኘው እንደማንችል መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ጠቅለል ባለ አነጋገር የምግብ ዋስትና ችግር ምርት በመጨመር በሚደረገው ሩጫ ብቻ የሚፈታ ሳይሆን ፖለቲካዊም ችግር ጭምር ነው። ፖለቲካ ደግሞ ሰው ሰራሽ ነው። ስለሆነም ፖለቲካዊ መፍትሄ በሰዎቻችን መልካም ፍቃድ ያስፈልገዋል ማለት ነው። የተዝረከረከና የተጨማለቀ፤ የተወሰኑ ቡድኖችን ጥቅም ብቻ ለመጠበቅ የቆመ ፖለቲካ ደግሞ ችግሩን ሊፈታ የሚያስችል ተቋማዊም ሆነ ሰዋዊ አቅምና ችሎታ የለውም፤ አይጠበቅምም።

ሌላው ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው ነጥብ ደግሞ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄን ጉዳይ ነው። ለገበሬው ያለችው አንድ ትልቁ ሃብት መሬት ብቻ ናት። ገበሬው የመሬቱ ባለቤት ከሆነ ንብረቱን ጥሎ ከተማም አይሰደድም። ማነው ሃብቱን ንብረቱን ጥሎ ንብረት አልባ ለመሆን የሚመኘው። እንደውም ብዙ እንዲያመርት እንደ ማትጊያ ዘዴ ይሆነዋል። የኪራይ ንብረት ሲሆን ግን ያልተሟላ ዕለት ሲመጣ ጥሎት ወደ ከተማ ይሰደዳል። ገበሬም እንደኛው ሰው ነው፤ነገን ከኛ በተሻለ ያስባል ፤ ስኬታማ ኑሮን ለመኖር ይታገላል፤ ይጥራል። በዚህ ጉዳይ ላይ የገበሬው ድምጽና ፍላጎት ይጠና ፤ ይጠየቅ። ገበሬውም ድምጹን የሚያሰማበት የራሱ ብቻ የሆነ ማኅበርም ከቀድሞዎቹ የገበሬ ማኅበር በተለየ ሁኔታ በራሱ አነሻሽነትና ጥያቄ መመስረት አለበት። ከመንግስት ሰዎች የሚጠበቀው ደግሞ የመሬት ይዞታውን ማሻሻል እንጂ ማጃጃል መሆን የለበትም። የበለጠ የገጠሩን ኑሮ ምቹ ካደረግንለት ወደ ከተማ ስደት አይጠበቅም። የከተማ ከንቲባዎቻችን ከተሞቻቸውን ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ እንፈልጋለን የሚሉትን ዲስኩር በገጠሩ ማስፋፋት ይጠበቅብናል። ገበሬን በሽታ እንዳይነካው ጤንነቱን በቅርብ እንጠብቅለት። ገበሬ ሲታመም፤ አገርም ይታመማል። መሬት ጦም ማደር ትጀምራለች። ጦም ያደረ መሬት የሚያበቅለው አረሞችን ነው። ገበሬም አይሙት፤ የሞተ እንደሆን ዕውቀቱንና ክህሎቱንም ጭምር ይዞ ነው የሚሞተው። የዕውቀትና የክህሎት ድርቅ ደግሞ ውጤቱ አስከፊ ነው። ምች ይመታናል፤ አጠውልጎም ያጠፋናል። እግዚዎ! መሃረነ ክርስቶስ! ጸሎቱን ጨርሱ። እኔስ አበቃሁኝ ያሰብኩትን ቢሆንም ባይሆንም፤ ቢያስከፋም ቢያስደስትም ተነፈስኩኝ። አሜን!!!!!
በሌሎች መጣጥፍ ዐርዕስት እስከምንገናኝ ጤና ይስጥልኝ!!!
ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>