ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌይ
የኢህአዲግ ወያኔ መንግስት የስልጣን ወንበር በትሩን በሀይል ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአኖኖር ሁኔታ ከእለት ወደ እለት እያሽቆለቆለ እና እየወረደ በመምጣቱ ሕዝቡ ከምቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት ኑሮን መቋቋም በማይችልበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኑሮ ውድነት ተቋቁሞ መኖር ከባድ ፈተና እየሆነባቸው እንደሆነ የችግሩ ሰለባና ተጠቂ የሆኑት ሰዎች በየጊዜው ከሚያሰሙት ሮሮና ጩኸት መረዳት ይቻላል::ይህንንም እየተባባሰ እና እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ዞን ስራ አስፈፃሚ የተቃውሞ ሰልፍ ሊጠራ እንደሆነ ታውቋል:: የአንድነት ፓርቲ ሊጠራ ባሰበውና በታቀደው ሰላማዊ ሰልፉም ላይ በስርዓቱ እና በኑሮ ውድነቱ የተማረሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነቂስ በመውጣት በምሬት የታመቀ የብሶት ድምጻቸውን በወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ላይ እንደሚያሰሙ ይጠበቃል:: በአሁኑ ወቅት ጥቂት የስርአቱ ደጋፊዎች እና የወያኔ ካድሬዎች ካልሆኑ በስተቀር በኑሮ ውድነቱን የተነሳ ተጎጂ ያልሆነና ሕዝቡ ኑሮን መቋቋም በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ በመገኘቱ ስርዓቱን የማያማርር የህብረተሰብ ክፍል የለም ብል ማጋነን አይሆንብኝም ::
የወያኔ መንግስት የሚያራምደው ፖሊሲ የመላው ኢትዮጵያን ሕዝቡ ፍላጎት እና ጥቅም ማዕከል ያላደረገ ሲሆን የተወሰኑን የህብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል :: መላውን የኢትዮያ ህዝብ እና ክልል ተጠቃሚ ያላደረገው የመንግስት የልማት ስትራቴጂ ፖሊሲ እና በመላው ሀገሪቱ ላይ በስፋት ተንሰራፍቶ ያለው ሙሰኝነት ከእለት ወደ እለት የሕዝቡ የአኖኖር ሁኔታ እያሽቆለቆለ እና እየወረደ እንዲመጣ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ሲሆኑ ለኑሮ ውድነቱ ግንባር ቀደም ተጠያቂው መሆን ያለበት ሀገሪቱን እየመራው እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት እያሳደገ እንዳለ የሚያወራው የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ነው:: በነገራችን ላይ የኢህአዲግ መንግስት በየጊዜው ስለ ሀገሪቷ ኢኮኖሚ እድገት የለመደውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ይለፍልፍ እንጂ ይህን በፍጥነት እያደገ ነው ብሎ ወያኔ የሚያወራለትን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተ የተባለው እድገት ከወረቀት ኣልፎ መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም የሚሉ ሰዎች በብዛት የሚገኙ ሲሆን ይህም ሀሳብ እኔንም ጨምሮ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው::
ታስታውሱ እንደሆነ የወያኔ ቁንጮ የነበረው ሟቹ የቀደሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በአሥር አመት ዉስጥ «ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ትችላለች። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቀን ሶስቴ እንዲመገብ እናደርጋለን» ብለው ነበር ነገር ግን ይህ የአቶ መለስ ዜናዊ ንግግር የውሃ ላይ ሽታ ሆኖ ቀረ :: በአንጻሩ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀን ሶስቴ እንዲመገብ እናደርገዋለን ያሉለት ኢህአዲግ ኢትዮጵያን በብቸኝነት በሀይል መግዛት ከጀመረ ወደ 23 አመታት እየተጠጋ ሲሆን በእነዚህ አመታቶች ውስጥ ምንም የተለወጠ ነገር የለም:: የወያኔ መንግስት በተቆጣጠረው በመገናኛ ብዙሃን እንደሚለፈልፉት የኢትዮጵያ ኢኮነሚው ዕድገቱ በፍጥነት ሽቅብ እየገሰገሰ ሳይሆን ወደታች እያሽቆለቆለ ይገኛል:: ምናልባት የኢኮኖሚ እድገቱ በወረቀት ስሌት ላይ ኑሮ እጅግ መራራ ከመሆኑ የተነሳ የሰዉ የአኖኖር ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ዉስጥ ዉስጡን የሚያልቁት ወገኖቻችን ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነዉ።በአሁኑ ሰአት ሕዝቡን የውሃ እጦት፣ የመብራት እጦት፣ የኔት ዎርክ ችግር፣ የትራንስፖርት እንደሚፈልገው አለማግኛት በአጠቃላይ ችግሩ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል:: በይበልጥ የአዲስ አበባን ነዋሪ ክፉኛ ምሪት ውስጥ አስገብቶታል::
በአዲስ አበባ ሕዝቡ ታክሲ ለመያዝ በወረፋ ላይ
በመላው አገሪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የውሃ፣የመብራትና የቴሌኮም አገልግሎት ጥራት መጓደልና የአገልግሎት መቋረጥ እንዲሁም በአገሪቷ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዉጭ ምንዛሪ እጥረት እየታየ ሲሆን በሀገሪቱ ላይ በደረሰው በኢኮኖሚ ችግር የተነሳ ሕዝቡ ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ በመገኘቱ ነገሮች እየከረሩ በማንኛውም ጊዜና ሰሀት ግባታዊ ሕዝባዊ አመጽ ሊነሳና ትልቅ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል የሚሰጉ ብዙዎች ናቸዉ።
በአሁኑ ሰአት እንደሚታየው እና መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥን ይፈልጋል ህዝቡ ሀገሪቱን እየመራ ባለው የወያኔ መንግስት ለመመራት ፍቃደኛ አይደለም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሮሮ በማሰማት ላይ ይገኛል:: በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ ከየቦታው የሚሰማው እና የሚታያው የሰበዓዊ መብት ረገጣው አፈናና ግድያው ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ በየቀኑ እያሸቀበ የመጣው የኑሮው ውድነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ጋር ሆድ እና ጀርባ ሆነው እንዲቀጥሉ እያደረጋቸው ሲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የሕዝቡ ንዴትና ቁጣ በከፍተኛ ሁኔታ በመፋፋም ላይ ይገኛል::
ከዚህም የተነሳ መንግስት በየቀበሌው፣በየመስሪያ ቤቱ በሚጠራቸው ማንኛውም ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ለመገኛት ሕዝቡ ፍቃደኛ እና ደስተኛ አይደለም:: ስለዚህም የሕዝቡ ከመንግስት ጋር ሆድና ጀርባ መሆን የወያኔን መንግስት ክፉኛ ጭንቀት ውስጥ የከተተው ጉዳይ ሲሆን በመሆኑም ለመጪው 2007 ለሚደረገው ምርጫ የሕዝቡ በመንግስት ላይ ያለው ጥላቻ እየጨመረ መምጣት እራሱን የቻለ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ይገመታል::
በአዲስ አበበ የውሃ ወረፋ
የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ባለስልጣኖች በሚቀጥለው አመት ምርጫ የሕዝቡን ድምጽ እንደማያገኙ በሚገባ ቢረዱትም ነገር ግን የለመዱትን የማጭበርበር እና የሌብነት ልምዳቸውን በመጠቀም ለቀጠይም አመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የበላይ በመሆን ሕዝብን እየጨቆኑና እየረገጡ ለመኖር የሚያስችላቸውን ስትራቲጂ በመንደፍ እነሱ እንደሚሉት የጀመሩትን የልማት ዕቅድ ለመተግበር ሳይሆን ኢትዮጵያን የማፈራረስና ኢትዮጵያውነትን የመጥፋት ዘመቻቸውን ለማስቀጠል የሚያረዳቸውን ማንኛውንም እርምጃ ሁሉ ከመውሰድ ወደ ኋላ አንደማይሉ የተረጋገጠ ነው::
እንደ እኔ አስተሳሰብ የወያኔ ኢሕአዲግ መንግስት በምንም ታአምር በምርጫ ተሸንፉ ስልጣኑን በቀላሉ ይለቃል ወይም ስልጣኑን ለተቃዋሚዎች ያጋራል የሚል እምነቱም የለኝም::በአሁኑ ሰአት እንደምናየው እንዲሁ በቀላሉ የኢሕአዲግ መንግስት ስልጣኑን ይለቃል ወይም ለተቃዋሚዎች ያጋራል ብሎ ማሰብ የዋህነትና የማይታሰብ ጉዳይ ቢሆንም ነገር ግን ወያኔና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆድና ጀርባ እንደሆኑ ለብዙ ጊዜ እንደማይቀጥል በምሪት እና በህልእ የተሞላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣ ገንፍሎ ወያኔ ዳግም እንዳያንሰራራ ወደ መቃብር ይወስደዋል ብዬ አምናለው:: ስለዚህ የወያኔ መሰሪ አካሂድ ተስፋ ሳያስቆርጠን የወያኔን መንግስት በተገኛው መንገድ ሁሉ በመታገል እና በመቃወም የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻነት ለማረጋገጥ ትግላችንን ማቀጣጣል ይጠበቅብናል::ኢትዮጵያ በቆራጥ ታጋይ ልጆቿ ከወያኔ አገዛዝ ነጻ ትወጣለች::
ድል ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ !!!
gezapower@gmail.com
Image
gezahegn abebe.jpg