በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ 9 ቀበሌዎች ማለትም ሉቃ፣አይመሌ፣ሻላ፣ጎራ፣ቦላ፣ኦሎና፣ጊሽማ፣ጎኔ፣ኡፊ ቀበሌዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚስፈልጋቸውና በአካባቢው የርሃብ ምልክቶች መታየታቸውን በደቡብ ኦሞ ዞን የአንድነት አመራሮች ለፍኖተ ነፃነት ገለጹ፡፡ ሻላ ጉያዮ፣ ቦላ፣ ኡፊ፣ ቦና፣ አይመሌ፣ ጊሽማ በተባሉት ቀበሌዎች ደግሞከፍተኛ የውሃ ችግር እንዳለባቸውም ታውቋል፡፡
በነዚህ ቀበሌ ውስጥ ያሉ አርብቶ አደሮች የዳልጋ ከብቶቻቸው፣ ፍየሎቻቸውና በጎቻቸው ሣርም ቅጠልም ማግኘት ስላልቻሉ እየሞቱባቸው ነው፡፡ ከየትኛውም ወገን ምንም ዓይነት ዕርዳታ ላገኙም ሲሉ በደቡብ ኦሞ ዞን የአንድነት አመራሮች አስረድተዋል፡፡ እነዚህን ወገኖች የሚረዱ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲያቀርቡላቸው በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በፓርቲያችን ስም እንማፀናለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በአካቢው ከጥር ወር ጀምሮ መዝነብ የሚገባው ዝናብ እስካሁን ባለመዝነቡ ከዚህም በኋላ ዝናቡን በመጠበቅ ሊከሰት የሚችለውን ችግር የከፋ እንደሚሆን የገለፁት የአንድነት አመራሮች እስካሁን የደ/ኦ/ዞ አስተዳደር ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳልወሰደም በአካባቢውም የአደጋ መከላከልን ዝግጁነት መስሪያ ቤት የሌለ መሆኑንም ጭምር ገልፀዋል፡፡