Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ህወሓት “ስሜን ልታጠፋ”ነው! (ከአብርሃ ደስታ)

$
0
0

ህወሓቶች ስሜን ለማጥፋት ዝግጅት መጀመራቸው የዉስጥ ምንጮች ገልፀውልኛል። ታድያ ቀጣዩ የመንግስት ሚድያዎች አጀንዳ ለመሆን ስለበቃሁ ህወሓትን የፈጠረ … ( ማነው የፈጠረው ደሞ?) የተመሰገነ ይሁን። እንዳዉም ሳስበው ለዓቅመ ትችት ደርሻለሁ ማለት ነው። ለማጥፋት ሚድያ የሚያስፈልገው ስም አግኝቻለሁ ማለት ነው። ስሜን ለማጥፋት ከተዘጋጁ ስም አለኝ ማለት ነው። ዕድሜ ለህወሓቶች! ለነገሩ ህወሓቶች ስም ያለውና የሌለው መለየት አይችሉም። እስቲ የሓሰት ውንጀላዎቻቸውን ለመስማት ያብቃን (ለነገሩ በቂሊንጦ ማረምያቤት ጀምረውታል አሉ)።

አብርሃ ደስታ

አብርሃ ደስታ

መስከረም አከባቢ ነው (ከዓረና ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ)። አቶ አባይ ወልዱ ካቢኔያቸውን ሰብስበው “አብርሃ ደስታን መከላከል አንዱ የፖለቲካ አቅጣጫችን ነው” ማለታቸው ሰማሁ። በሚልዮን የሚቆጠር በጀትም መመደቡ ሰማሁ። ግን አላመንኩም። ምክንያቱም በጀት በመመደብ አብርሃን እንዴት መከላከል ይቻላል? ሰለማዊ ታጋይ ነኝ። ጠመንጃ የለኝም።

የሰማሁት ግን ብዙ ታማኝ የህወሓት ካድሬዎች ተመልምለው የፌስቡክ አጠቃቀም ሰልጥነው የአብርሃን ሐሳብ ማፍረስ እንዲችሉ ማብቃት ነበር። ግን የፌስቡክን አጠቃቀም መሰልጠን ሐሳብ ማመንጨት ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። እነዚህ የፌስቡክ ስልጠና የተሰጣቸው ታማኝ ካድሬዎች ሲጨንቃቸው በሓሳብ ከመከራከር ይልቅ መሳደብን መረጡ። በስድብ ሐሳብን ማሸነፍ ግን አይቻልም። እናም አልቻሉም።

እናም የተመደበው ገንዘብ ለታማኝ ካድሬዎቹ (የባለስልጣናቱ ቤተሰቦች) ተሰጠ። ሐሳብን ሊያመነጩ የሚችሉ ካድሬዎች በዝምድና ተመርጠው እንደየ አስፈላጊነታቸው በሑመራና ሌሎች ከተሞች መሬት በነፃ ተሰጣቸው (አርሶአደሮችን በማፈናቀል፣ ደግሞ አርሶአደር የት ይደርሳል? በረከተ ስምዖን ትዝ አለኝ)። ኢንቨስተሮች ሆኑ። ኢንቨስተሮች በመሆናቸው ህወሓትን አይተቹም እንጂ እኔም ለመንቀፍም ግዜና ፍላጎት አልነበራቸውም።

ከነዚህ መሬት የተሰጣቸው ካድሬ ኢንቨስተሮች አንዱ የግል ጋዜጠኛ ነኝ የሚል ሲሆን ባለፈው ሦስት ወራት በህወሓት መሬት እንዳልተሰጠው ሲምል ቆይቶ ዛሬ ግን በሑመራ መሬት እንዳለው አረጋግጦልኛል። እንዲህ ነው። ሰውየው ጋዜጠኛ ነው። በሑመራ አከባቢ የሚገኝ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን በምስጢር መሰጠቱ ፅፌ ነበረ። ዛሬ አገኘኝና “የፃፍከው ስህተት ነው” አለኝ። “ስህተት ስለመሆኑ ምን ማስረጃ አለህ?” ስለው “እኔ ራሴ በሑመራ መሬት አለኝ። የኔ መሬት አልተወሰደም”አለ። ይገርማል። አንደኛ ከወራት በፊት በህወሓት መሬት ከተሰጣቸው ወጣቶች አንዱ እንደሆነ ነግሬው “ስህተት ነው። መሬት አልተሰጠኝም” ብሎኛል። ዛሬ የተበላሸበት ረስቶት ነው። ሁለተኛ በሑመራ ያለው የሱ መሬት ስላልተወሰደ ለሱዳን የተሰጠ የኢትዮጵያ መሬት የለም ማለት አይቻልም። ምክንያቱም መላው ሑመራ ለሱዳን ተላልፏል አልተባለም።

የህወሓት ፖለቲካ ስም የማጥፋት ፕሮፓጋንዳ ነው። ህወሓቶች የሰው ስም ብቻ አይደለም የሚያጠፉ፤ የሰው ህይወትም ያጠፋሉ። ይህን ሁሉ ተግባራቸው እናውቀዋለን። እናም በስም ማጥፋት ዘመቻ የሚሸበር የለም። ህወሓትን የምቃወመው መጥፎ ስለሆነ ነው። እናም በስም ማጥፋት ዘመቻ ተሰማርቶ መጥፎነቱን ቢያጋልጥ ህወሓትን የምቃወምበት ምክንያት ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ አይደንቀኝም።

አንድ አምባገነናዊ ስርዓት የሚፈፅማቸው ተግባራት ስም ማጥፋት፣ ማሰቃየት፣ ማሳሰር፣ መግደል ናቸው። ከዚህ ዉጭ ምንም ማድረግ አይችልም። ፍቅርን የማስፈን፣ ፍትሕን የማንገስ፣ እኩልነትን የማረጋገጥ፣ ስልጣንን ለህዝብ የማስረከብ፣ ነፃነትን የመስጠት ብቃት የለውም። ነፃነት ለመስጠት ብቃት ይጠይቃል። ሰው ለመግደል ግን ጠመንጃ መያዝ ብቻ በቂ ነው። ስለዚህ አምባገነናዊ ስርዓት የሚችለው ነገር መጥፎነት ነው። መጥፎ ስለሆነም ነው የምንቃወመው። ምክንያቱም የምንፈልገው መጥፎነንት ሳይሆን መልካምነት ነው። መጥፎ ተግባር በሌላ መጥፎ ተግባር ስለማይሸነፍ የህወሓት መጥፎነት በመልካምነት ለማሸነፍ እንሞክራለን። ምክንያቱም የምንታገለው ህወሓትን ለመተካት (ህወሓት የሚሰራውን መጥፎ ተግባር ለመድገም) ሳይሆን የህወሓትን የመጥፎነት ስርዓት በመልካም ህዝባዊ ስርዓት ለመቀየር ነው። የምንቃወመው ስርዓቱን ነው።

ምክር አለኝ! አሁን የታሰበው ስም የማጥፋት ዘመቻ በ2007 ምርጫ ወቅት ቢሆንላቹ ይሻላል። ምክንያቱም ዓላማቹና ሀይማኖታቹ ስልጣን ነው። ስለዚህ በምርጫ ወቅት ቢሆን መልካም ነው። ለማንኛውም ህወሓቶች መልካም ዕድል ብያለሁ (ለዘመቻው)። እንደ አኬልዳማና ሐረካት ለትዝብት የሚዳርጋቹና የሚያከስራቹ መሆን የለበትም።

ስሜ አይጠፋም። ምክንያቱም ስም የሌለው ስሙ አይጠፋም። ስም ለማጥፋት መጀመርያ ስሙ መኖር አለበት። አሁን ግን ስሙ የለም። ስም ለሌለው ሰው ስም ለማጥፋት የሚደረግ ዘመቻ ስም መፍጠር ነው የሚሆነው። ስለዚህ ስም ለማጥፋት ሲሉ ስም ይፈጥሩልኛል። እናም ይተውታል የሚል ግምት አለኝ። አጀንዳው የተነሳው እኔን ለማደናገጥ ታስቦ ሊሆን ይችላል።

It is so!!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>