ዕድሜዬ 17 ዓመት ሲሆን በ10+3 ፕሮግራም የኮሌጅ ትምህርቴን ከጀመርኩ ወራትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ግን በትምህርቴ መግፋት የምችል አይመስለኝም፡፡ የደረሰብኝ ችግር ትምህርቴን ማስተጓጎል ብቻ ሳይሆን አጠቃላዩ ኑሮዬንም ምስቅልቅሉን እያወጣው ነው፡፡
እንደሚታወቀው ክላስ ገብቼ ትምህርት መማር የምችለው ቀን ቀን ነው፡፡ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ይመስለኛል ክፍል ውስጥ እንቅልፍ እየወሰደኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ ከአየሩ መቃትነት የተነሳ ደግሞ ታግዬ እንኳን የምቆጣጠረው አልሆነልኝም፡፡ ይህ ችግሬ በአሁኑ ጊዜ በጣም እያሳፈረኝ ነው፡፡ ችግሬን እንደ ችግር ቆጥሮ የሚያዝንልኝ ሰው እንኳን የለም፡፡ በስርዓት ተቀምጬ አስተማሪ በምከታተልበት ሳላስበው ዥው ያለ እንቅልፍ ይወስደኛል፡፡ ግንባሬን ከዴስኩ ጋር የማጋጭበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡
ይህን ችግሬን ያወቁ ልጆች ወደ ኋላ አካባቢ እንድቀመጥ መከሩኝና ያሉትን አደረግሁ፡፡ እኔ ስተኛ ግን ክላሱ እስኪያልቅ ድረስ የሚቀሰቅሰኝ ሰው የለም፡፡ ይህስ ባልከፋ፣ ሆኖም ወዲያው እንቅልፍ እንደወሰደኝ የሚያሳቅቅ ነገር ይደርስብኛል፡፡ ምን መሰላችሁ ይሄ እንደ ዱካክ ነገር ደረቴን ፈጥርቆ ይዞ እንዳልንቀሳቀስ ያሳስረኝና ሳላስበው ቀጭን ጩኸት አሰማለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው መምህሩ መተኛቴን የሚያውቁት፡፡ ተቀስቅሼ ስነቃ ደግሞ ተማሪው ሁሉ እየሳቀብኝ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት አድርጌ ነው የምማረው? ይኸው ትምህርት ካቋረጥኩ ሁለት ሳምንት ሆኖኛል፡፡
ይህ ዱካክ እና በቀን የመተኛት አባዜ መፍትሄ አለው ትላላችሁ? ማብራሪያችሁን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡
የእናንተው ጢኖ
የዶ/ር ዓብይ ዓይናለም ምላሽ፡- ውድ ጢኖ ለጥያቄህ ልባዊ ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ሳይታሰብ እና ሳፈለግ የሚመጣ የቀን እንቅልፍ በአጠቃላይ ህይወት ላይ የሚያመጣው ምስቅልቅ እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑ ቅድሚያ ሰጥተነዋል፡፡
ምናልባት ለትምህርትህ ከምትሰጠው ላቅ ያለ ግምት አንፃር ክፍል ውስጥ ተቀምጠህ የማንቀላፋቱን ነገር የበለጠ ትኩረት ሰጠኸው እንጂ ህመሙስ ከዚህ የባሰም ፈተና ሊያስከትልብህ ይችላል፡፡ ሳይፈልጉ በቀን መተኛት በጣም መጥፎ ክስተት ነው፡፡ ህመሙ በህክምናው ዓለም ‹‹Narcolepsy›› ተብሎ ይጠራል፡፡
‹‹Narcolepsy›› የእንቅልፍ መዛባት ቢሆንም ከሌሎች ተያያዥነት ካላቸው የእንቅልፍ መዛባት ችግርህ ለየት የሚያደርገው ቁጥራቸው በጣም ውስን በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ህመም በመሆኑ ሳቢያ ነው፡፡ አልጋ ላይ ተጋድመው አይናቸውን ቢጨፍኑም እስከ ውድቅት ሌሊት ወይም እስከ ንጋት ድረስ እንቅልፍ አልወስድ ብሏቸው ሲገላበጡ የሚያድሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርጋቸውም ግማሽ ሰዓት ወይም አንድ ሁለት ሰዓት ብቻ ከቆዩ በኋላ ተመልሰው የሚነቁና የቀረውን የሌሊት ክፍል ፈጠው የሚያድሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ጠዋት ከእንቅልፋቸው መንቃት ተስኗቸው ተጋድመው ያረፍዳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ‹‹Narcolepsy›› የጥቂቶች ብቻ ችግር ነው፡፡
‹‹Narcolepsy›› በጣም አደገኛ ህመም ነው፡፡ የዕለት ስራን በወጉ ለማከናወን፣ ለመብላት፣ ለመዝናናት፣ ወዲያ ወዲህ ብሎ ለመንቀሳቀስ የህሊና ንቃት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የመኪና መንገድ ለማቋረጥ፣ ማሽን ላይ ለመስራት ወይም መኪና ለማሽከርከር ብሩህ የአዕምሮ ንቃት ማስፈለጉ የግድ ይላል፡፡
በእርግጥ ይህ ህመም ያለባቸው ሰዎች ተረጋግተው ክፍል ውስጥ መማር ይከብዳቸዋል፡፡ ከዚህ ህመም ጋር በተያያዘ መልኩ የሚከሰት አንድ ሌላ ችግር አለ፤ ይህም በተለምዶ ‹‹ዱካክ›› እየተባለ የሚጠራውና በእንቅልፍ ዓለም ውስጥ ሆነው መሰቃየት ሲሆን በጣም የሚያስጨንቅ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ ሁኔታ ‹‹Sleep paralysis›› ተብሎ ይጠራል፤ ዱካክ እንደማለት ነው፡፡ በእርግጥ ከቀን እንቅልፍ ‹‹Narcolepsy›› ጋር ባልተያያዘ ሁኔታም ሊከሰት ይችላል፡፡ በተለይም ታዳጊ ህፃናት እና ጎረምሶች ናቸው በዚህ ችግር የሚጠቁት፡፡
ህመሙ ህክምና ያስፈልገዋል፡፡ አለበለዚያ ግን በሽተኛውን ለአደጋ ወይም ለሞት የሚዳርግ ክስተት ያስከትልበታል፡፡
ውድ ጠያቂያችን የስነ አዕምሮ ሐኪሞች ክትትል የግዴታ ያስፈልጋል፡፡ የሚታዘዙልህ መድሃኒቶች ጥንቃቄ ካልታከለባቸው በጣም አደገኞች በመሆናቸውም ሁኔታህ እየታየ የመድሃኒቶቹ መጠን ያስተካክልም ዘንድ መጠቆም እንወዳለን፡፡