Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: ከሶፖት ሻምፒዮና ከአትሌቶቻችን ምን እንጠብቅ?

$
0
0

ከቦጋለ አበበ

በቀጣዩ ወር መጀመሪያ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ አስራ አንድ አትሌቶችን ወደ ፖላንድ ሶፖት እንደምትልክ ይጠበቃል። ከአስራ አንዱ አትሌቶች በተጨማሪ ሁለት ተጠባባቂ አትሌቶች ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑም ታውቋል።
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ካሠማራቻቸው አትሌቶች ጥንካሬና አቋም በመነሳት በትንሹ አራት ሜዳሊያዎች ሊመዘገቡ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

መሐመድ አማን

ሙሃመድ ድል አድርጎ ሲገባ!

ሙሃመድ ድል አድርጎ ሲገባ!

የዓለም የስምንት መቶ ሜትር ሻምፒዮኑ ወጣት አትሌት መሐመድ አማን ያለፈውን ዓመት በስኬት ያጠናቀቀ አትሌት ነው። ከዳይመንድ ሊግ እስክ ዓለም ሻምፒዮና ያሉ ውድድሮችን ጠራርጎ በማሸነፍም በርቀቱ ኮከብ መሆኑን አሳይቷል።
መሐመድ በዘንድሮ ዓመት ያካሄዳቸውን ውድድሮችም በጠቅላላ በማሸነፍ የአምናው ብቃቱ አብሮት እንደሚገኝ አሳይቷል። ኢትዮጵያ በሶፖት የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ከምትጠብቅባቸው አትሌቶች መካከል መሐመድ ግንባር ቀደሙ ነው።
መሐመድ ከሁለት ዓመት በፊት እንዲህ በርቀቱ ስሙ ገናና ሳይሆን ቱርክ ኢስታንቡል ላይ በተካሄደ ተመሳሳይ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችሏል። መሐመድ ያኔ ያስመዘገበው የወርቅ ሜዳሊያ በታላላቅ ዓለምአቀፍ መድረኮች የመጀመሪያው ነበር። በዘንድሮው ሻምፒዮናም መሐመድ ያለፈውን ክብሩን አስጠብቆ እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ለእዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየው የሚገኘው ድንቅ አቋም ምስክር ይሆናል።

ገንዘቤ ዲባባ

በለንደን ኦሊምፒክና በሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተደብቃ የነበረችው የጥሩነሽ ዲባባ ታናሽ እህት ገንዘቤ የዘንድሮው የውድድር ዓመት «የእኔ ነው» እያለች ትገኛለች። ያለፈውን ዓመት እዚህ ግባ በማይባል ውጤት ብታጠናቅቅም ዘንድሮ ለማመን የሚከብድ አቋም በማሳየት ጀምራዋለች።
ገንዘቤ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሦስት የዓለም ክብረወሰኖችን በማሻሻል የስፖርት ቤተሰቡን አስደምማለች። በቤት ውስጥ አንድ ሺ አምስት መቶ፣ ሦስት ሺ ሜትርና በሁለት ማይል ውድድሮች በእያንዳንዳቸው የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበችው ገንዘቤ አሁን አስፈሪ አትሌት ሆናለች።
ገንዘቤ የዓለም ሻምፒዮኗን አበባ አረጋዊን በማሸነፍ ጭምር ክብረወሰን ያስመዘገበች አትሌት እንደመሆኗ መጠን ሶፖት ላይ አዲስ ነገር ካልተፈጠረ የወርቅ ሜዳሊያ የማታስመዘግብበት ምክንያት አይኖርም።
ገንዘቤ ሦስቱን ክበረወሰኖች ባስመዘገበችበት ወቅት በአንድ ሺ አምስት መቶ ብቻ ሳይሆን በሦስት ሺ ሜትርም የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ እንደምትፈልግ መናገሯ ይታወሳል። ገንዘቤ ከሁለት ዓመት በፊት በኢስታንቡል በተካሄደ ተመሳሳይ ሻምፒዮና የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንደነበረች ይታወሳል።
genzebe d

ሐጎስ ገብረህይወት

«ትንሹ ቀነኒሳ በቀለ » በሚል እየተሞካሸ የሚገኘው ሐጎስ ገብረህይወት ሶፖት ላይ ከሚነግሱ አትሌቶች መካከል አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል። በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና ትልቅ ጥረት አድርጎ የብር ሜዳሊያ በአምስት ሺ ሜትር ማስመዝገብ የቻለው ሐጎስ በእዚህ ዓመት በሦስት ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ድንቅ ብቃት በማሳየት አሸንፏል።

ሐጎስ የዓለም ወጣቶች የሦስትና አምስት ሺ ሜትር ባለ ክበረወሰን ሲሆን በተለያዩ ውድድሮች የሚያሳየው ጥንካሬ የሶፖት የሦስት ሺ ሜትር ንጉስ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከእዚህ ባሻገር ያለፈው ዓመት የአምስት ሺ ሜትር የዳይመንድ ሊግ አሸናፊው የኔው አላምረውና ደጀን ገብረ መስቀል በርቀቱ ከሐጎስ ጋር ይወዳደራሉ።

ሦስቱ አትሌቶች በእዚህ ወር የቤት ውስጥ ውድድር በሦስት ሺ ሜትር ተገናኝተው ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። እነዚህ አትሌቶች ልዩ ብቃት ያላቸው ብቻም ሳይሆኑ አሁን ላይ እየበሰሉ መጥተዋል። ከእዚህ ቀደም በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች በጥቃቅን ስህተቶች የሚገባቸውን ሜዳሊያ ያጡበት አጋጣሚ ሶፖት ላይ ይደገማል ተብሎ አይታሰብም። እንዲያውም የሦስቱ አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር በመረዳዳት ላይ ያተኮረ ከሆነ አረንጓዴውን ጎርፍ ሶፖት ላይ የምናይበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ጥርጥር የለም።

የአልማዝ አያናና ህይወት አያሌው ጥምረት

በሴቶች ሦስት ሺ ሜትር በእርግጠኝነት ከአንድ በላይ ሜዳሊያ ሊመዘገብ እንደሚችል መናገር ይቻላል። የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ካሻሻለችው ገንዘቤ ዲባባ በተጨማሪ አልማዝ አያናና ህይወት አያሌው በርቀቱ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው።
አልማዝ አያና በቅርቡ መታየት የጀመረች ወጣትና ባለ ድንቅ ተሰጥኦ አትሌት ነች። በሞስኮው ሻምፒዮና መሠረት ደፋር በአምስት ሺ ሜትር ላስመዘገበችው የወርቅ ሜዳሊያ ወጣቷ አትሌት ምንያህል አስተዋፅኦ እንደነበራት ይታወሳል። አልማዝ ለመሠረት የወርቅ ሜዳሊያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማበርከቷ በተጨማሪ የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፈች አትሌትም ነች። አልማዝ ሞስኮ ላይ ከነበራት ብቃት ተነስቶ ሶፖት ላይ ሜዳሊያ ውስጥ እንደምትገባ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

በመሰናክል ውድድሮች የምናውቃት ህይወት አያሌው በዘንድሮው የውድድር ዓመት መነጋገሪያ ከነበሩ የአትሌቲክሱ ዓለም ክስተቶች አንዷ ነች። ህይወት በግል አገር አቋራጭ ውድድሮች አምስት ጊዜ በተከታታይ በማሸነፍ አስገራሚ ብቃት ያሳየች አትሌት ነች። በእዚህ ርቀት ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ትጠብቃለች። ከአትሌቶቹ ጥንካሬ አንፃር የትኛዋ አንደኛ እንደምትሆን መገመት ቢከብድም የሦስቱ አትሌቶች ውህደትና የቡድን ስራ ለሜዳሊያ ያበቃቸዋል ተብሎ ይታሰባል።

መኮንን ገብረመድህን

በኢስታንቡሉ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው መኮንን ገብረመድህን ወደ ሶፖት ይጓዛል። መኮንን በርቀቱ ካለፈው የተሻለ ሜዳሊያ ይዞ እንደሚመለስ ተስፋ ተጥሎበታል። በእዚህ ርቀት ሌላው አትሌት አማን ወጤ ከመኮንን ጋር በርቀቱ ኢትዮጵያን ይወክላል። ሁለቱ አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑም ይጠበቃል።

በሴቶች አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ከገንዘቤ ዲባባ በተጨማሪ አክሲማይት አምባዬና ጎድፋይ ፀጋዬ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>