ዋሽንግተን ዲሲ፤ የካቲት 17/2006 (ቢቢኤን )፦ቁጥራቸዉ በመቶዎች የሚቆጠር እትዮጵያዉያንንና ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን በዛሬው እለት ዋሽንግተን ዲስ በሚገኘዉ የሲዉዘርላንድ ኤምባሲ ፊትለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን የሲዉዘርላንድ መንግስት ረዳት ፓይለቱን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፎ እንዳይሰጥም ጠይቀዋል።
ጠለፋዉ ለከት ያጣ ጭቆና ዉጤት ነዉ ያሉት ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች ሐይለመድህን አንባገነናዉያን የፈጠሩት ስጋት ሰለባ የሆነ ሙያተኛ ቢሆን እንጂ ለማንም ለምንም ስጋት የሚሆን አይደለም ሲሉም ድምጻቸዉን አሰምተዋል።
ረዳት ፓይለት ሐይለመድህን በአንባገነናዊዉ የኢትዮጵያ መንግስት ተንገፍግፎ የዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ድምጽን ለማሰማት መስዋእትነት የከፈለ ጽኑ ኢትዮጵያዊ ነዉ፤ ከተስፋሪዎች መጉላላት በስተቀር ማንንም አደጋ ላይ አልጣለም፤ ሐይለመድህን የኛ ጀግና ነዉ! የሲዉዘርላንድ መንግስት እንደወንጀለኛ ሳይመለከተዉ በነጻ ሊለለቀዉ ይገባል ሲሉም ተማጽነዋል።
የሲዉዘርላንድን መንግስት በመወከል ከኤምባሲ የመጡት ግለሰብም ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዉ ሰላማዊ መሆኑን አድንቀዉ ካመሰገኑ በሗላ የተሰጣቸዉን ደብዳቤ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚልኩ በማስታወቅ የተቻለዉን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
ረዳት ፓይለት ሐይለመድህን አበራን በየካቲት 10/2006 ሁለት መቶ ሁለት ተሳፋሪዎችን የጫነዉን ቦይንግ 767-300 በረራ ቁጥር ET-702 በመጥለፍ ጄኔቫ አሳርፎ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቀ ሲሆን እስከ አሁን በሲዉዘርላንድ መንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛል።
የሐይለመድህን ቤተሰቦች ፓይለቱ የአእምሮ ህመም እንዳጋጠመዉ መናገራቸዉ ታዉቋል ።ብዙዎች ግን የኢትዮጵያ መንግስት ያንሰራፋዉ የመብት ረገጣ እንዳይታወቅበት ነዉ ቤተሰቦቹን በማስገደድ የአእምሮ ህመም አለበት እንዲሉ ያደረገዉ በማለት ይተቻሉ።
ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ እትዮጵያዉያንንና ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን ረዳት ፓይለቱ ጤነኛ ነዉ የአእምሮ ህመም የሚለዉ አሉባልታ በኢትዮጵያ መንግስት የተፈበረከ ነዉ ሲሉ ያጣጥላሉ።
Photo credit: Kebadu belachew